Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow ልመና ይከልከል!
ልመና ይከልከል! Print E-mail
Wednesday, 30 July 2008
Imageድሆች ነን? አዎን! ድሆችን መርዳት ይገባል? አዎን! የተቸገረ የተራበ ይለምናል? አዎን! የሚለምኑት ወደው ነው? አይደለም! ተቸግረው ነው፡፡ ሕብረተሰቡ ችግረኞችን የመርዳት ኃላፊነት አለበት? አዎን! መንግሥትም? አዎን! የተቸገሩትን በበቂ ደረጃ እየረዳን ነው? አይደለም!

ልመና ይቅር ስንል ችግር የለም፣ ረሃብ የለም፣ ደሃ የለም ለማለት ፈልገን አይደለም፡፡ ችግረኞችና ድሆች ብንሆንም ድህነትን እንደብቅ፣ እንሸፋፍን ማለታችንም አይደለም፡፡ ድሆች የምንረዳበትን መንገድ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እናድርገው ለማለት ፈልገን ነው፡፡ በየመንገዱና በየትራፊክ መብራቱ በሚደረግ ምፅዋት ድህነት አይፈታም፤ ችግር አይቃለልም፡፡ ይልቁንም ጉዳቱ እጅግ ከፍተኛ እየሆነ ነው፡፡

በየመንገዱና በየትራፊክ መብራት ልመና፣ በየሆቴልና በየታሪካዊ ቦታዎች ያለ ልመና፣ ቱሪስቶች የሚፈሩትና በእጅጉ የሚተቹት ሆኗል፡፡

በአሁኑ ጊዜ፣ በዓለም ያለው የቱሪስቶች እንቅስቃሴ በተለይም በወጣቶች አካባቢ በማኅበር ተደራጅተው የመንቀሳቀስ መልክ እየያዘ መጥቷል፡፡ በጋራ ቦታ (አገር) ይመርጣሉ፣ ስብሰባ እያካሄዱ የት አገር መሄድ ጥሩ እንደሆነ ልምድ ይለዋወጣሉ፣ በኢንተርኔት ይወያያሉ ወዘተ.

ልምድ ሲለዋወጡ ስለኢትዮጵያ የሚያነቡት ነገር አለ፡፡ ውብ አገር፣ ውብ ሕዝብ፣ ውብ ታሪክ፣ ውብ የአየር ጠባይ፣ ግሩም ሰላምና መረጋጋት ያለባት አገር ናት፡፡ ነገር ግን ልመና እጅግ ዘግናኝ ነው ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ በኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ አጅበውህ የሚሄዱ ለማኞች አሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያለው ታሪካዊ ቦታ ግሩም ነው፡፡ ነገር ግን እዚያ ያለው ልመናና የአካል ጉዳተኝነት ሲታይ ታሪካዊ ቦታ ለመጎብኘት ሳይሆን የአካል ጉዳትና ልመና ለማየት የሄድክ ነው የሚያስመስለው ይላሉ፡፡ በዚህም ብዙዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚፈልጉትን አያበረታቱም፡፡ ምክር አይሰጡም፡፡

ቱሪዝም በልመና እየተጎዳ ነው፡፡ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ አንዱ መፍትሔም በየመንገዱና ታሪካዊ ቦታ ያለውን ልመና ማስቆም ነው፡፡

ቱሪስት ወይም ፈረንጅ ስለሚጠላው አይደለም ይከልከል የምንለው፡፡ ድሆች የሚረዱበት መንገድ መለወጥ አለበት ለማለት ነው፡፡ በልመና የተሰማሩት፣ ከአዲስ አበባ ውጭ ይኖሩ የነበሩ ስለሆኑ፣ ቅድሚያ ከቂያቸው ሳይወጡ፣ እዚያው ለመርዳት መሞከር ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ እየታዩ ያሉ አንዳንድ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎችም ሊበረታቱና ሊጠናከሩ ይገባል፡፡ ለልመና ሕዝብ ከአካባቢው መነሳት የለበትም፡፡ ክልሎች እዛው እርዳታ የሚያስተካክሉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው፡፡

በአዲስ አበባ የሚኖሩ ወላጅ አልባ ሕፃናት መረዳት አለባቸው፡፡ በየመንገዱ ሲለምኑ ፍራንክ መስጠት ሳይሆን በአንድ ማዕከል ወይም ድርጅት የሚረዱበትን መንገድ በማቀናበር ሊሆን ይገባል፡፡

በልመና ላይ ለተሰማሩት በየመንገዱ የምንሰጠው ገንዘብ ወይ ከቦታቸው ሳይወጡ ወይም በጋራ በሚጠቀሙበት ማዕከል በኩል ሊሆን ይገባል፡፡

ልመና ይቅር ሲባል በፈቃደኝነት ይሁን ወይስ በክልከላ? በክልከላ ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ በፈቃደኝነት ሊሳካ አይችልም፡፡ ክልከላውንም ቢሆን ብቻውን ሳይሆን ትምህርት መስጠትና በቄያቸው በአማካይ ቦታ እርዳታና እገዛ ማድረጉ በመጠናከር ጭምር መሆን አለበት፡፡ ልመና ተከልክሏል ብሎ ዝም ማለቱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ከነመፍትሔው ማድረግ የግድ ነው፡፡

ልመና የመከልከል ጉዳይ በአንድ ጊዜ ይሳካል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ቀስ በቀስ ሥራ ላይ መዋል አለበት፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች በአስቸኳይ መጀመር አለበት፡፡ በተለይም በየመኪና መንገዱና በየትራፊክ መብራቱ ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡

እንደዚህ ዓይነት እርምጃ ይወሰድ ሲባል ድህነትን የመደበቅ ሙከራ አድርገው የሚወስዱ ይኖራሉ፡፡ ፣መለመን መብታቸው ነው፤ ካልፈለገ ሰጪ እምቢ ይበል እንጂ፣ የሚሉ አስተያየቶች ሊመጡ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ከድጋፍና ከእገዛ ጋር ከሆነ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

ይህ ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ አስተዳደሩ ብቻ ይወጣው የሚባል ጉዳይም አይደለም፡፡ ሲቪል ማሕበረሰቡ፣ የግል ኢንቨስትመንት ዘርፉ፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎችም ሊረባረቡበት ይገባል፡፡ በተለይ፣ በተለይ የሃይማኖት ድርጅቶች ልዩ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

ይህም ቢሆን ለዘለቄታው መፍትሄ አይሆንም፡፡ ዘለቄታዊ መፍትሔው ድህነትን ማስወገድ ነው፡፡ ድህነት እስኪወገድ ድረስ ግን የእርዳታ አሰጣጣችንን መንገድ እንቀይር፡፡ በየመንገዱ የትራፊክ መብራት ላይ ልመና ይከልከል!
 
< Prev   Next >