| የናሳ ሥራዎች በቀጥታ ድረገፅ ተቀመጡ |
|
|
| Wednesday, 30 July 2008 | |
በናሳ (የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም) የተነሱ የተለያዩ ምስሎች እንዲሁም በቪዲዮና በድምፅ የተቀረፁ የተለያዩ የሳይንሳዊ ግኝት ስብስቦች በቀጥታ (online) ድረገፅ መቀመጣቸውን ናሳ አሳውቋል፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በቀጥታ ድረገፅ የተለቀቁት የናሳ ስብስቦች በጠፈር ምርምሩና አትራፊ ባልሆነው ኦንላይን ላይብረሪ (Internet Archive) ጋር በተደረገ የአምስት ዓመት የትብብር ስምምነት ነው፡፡ በመረጃ መረቡ ናሳ በ50 ዓመት የሥራ ታሪኩ ያነሳቸው የተለያዩ ፎቶዎች፣ የአፖሎ ኘሮግራም፣ የሃብል ስፔስ ቴሌስኮኘ እንዲሁም ስለ ዓለም አቀፉ የስፔስ ማዕከል የተለያዩ መረጃዎች ተጭነዋል፡፡ የኦባማ ባዮ ፊዩል ፖሊሲ ፈተና ገጥሞታልለመጪው የአሜሪካ ኘሬዚዳንታዊ ምርጫ በእጩነት የቀረቡት ባራክ ኦባማ በባዮፊውል ላይ ያላቸውን ፖሊሲ ሊያስቀይር የሚችል ጫና እየመጣባቸው ነው፡፡ ሴናተር ኦባማ ለበቆሎ ገበሬዎች የሚደረገውን ድጐማ አጥብቀው ይደግፋሉ፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው ደግሞ ኦባማ ለገበሬዎች የሚሰጠውን ድጐማ የሚደግፉት የኢታኖል ምርትን ለማስፋፋት ነው፡፡ ሆኖም ከኦባማ አማካሪ የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየው ባዮፊውል ከውስብስብ ችግሮች ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የአማካሪው ዳኔል ካመን ሪፖርት እንደሚያሳየው ከበቆሎ በተሰራ ኢታኖል የሚንቀሳቀሱ መኪናዎች መደበኛውን ነዳጅ ከሚጠቀሙት በባሰ መልኩ የግሪን ሃውስ ትነት አላቸው፡፡ በበርክሌይ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ኘሮፌሰር እንደተናገሩት በበቆሎ ምርት ላይ የሚደረግ ድጐማ የእንስሳት ምግቦች እንዲወደዱ ከማድረጉም በተጨማሪ የአኩሪ አተር ምርት በሰፊው እንዲመረት ያስገድዳል፡፡ የአኩሪ አተር ምርት በድንግል መሬት ላይ ከተዘራ ደግሞ ብዙ የግሪን ሃውስ ጋዝ ትነት ይኖረዋል፡፡ ባራክ ኦባማ የኘሬዚዳንት ቡሽን መርህ በመከተል ለበቆሎ አምራች ገበሬዎች የሚሰጠውን ድጐማ ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ በአሜሪካ በበቆሎ አምራችነታቸው በሁለተኛ ደረጃ የሚታወቁት የኢሎኒስ ገበሬዎች ደግሞ የኦባማ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ የኦባማ አማካሪ እንደሚሉት ኦባማ ባዮፊውልን በተመለከተ ጥልቅ ፖሊሲ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለኦባማ የገጠማቸው ፈተና ለኘሬዚዳንታዊ ዕጩነት ያበቋቸውን ገበሬዎች የበቆሎ ድጐማ መቀጠል ወይም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ "የአየር ንብረት ለውጥ እንገታለን፤ ድሃዎችን እንረዳለን" በማለት የገቡትን ቃል ማክበር የሚለው ላይ ውሳኔ መስጠት ነው፡፡ የስፔስ ቱሪዝም ጀት ለእይታ በቃ በእንግሊዝ በንግዱ ዓለም ታዋቂ ከሆኑት የሚመደቡት ሚ/ር ሪቻርድ ብራንሰን በስፔስ ላይ ጉብኝትን አስመልክቶ ለሚሠሩት ኘሮጀክት ጥቅም ላይ የሚውል ጀት በአሜሪካ ማሳየታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ሁለት የጀት ሠራተኞችና ስድስት ተሳፋሪዎችን በሚይዘው ጀት በስፔስ ላይ ጉብኝት ለማድረግ ከ25ዐ ሰዎች በላይ ተመዝግበዋል፡፡ እያንዳንዳቸውም 200"000 ዶላር ከፍለዋል፡፡ ዋይት ናይት ቱ ወይም ኢቭ የሚል ስያሜ የተሰጠው ጀት ሰዎችን ይዞ ለስፔስ ጉብኝት ከመሰማራቱ በፊት ከመጪው በልግ ጀምሮ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የዘረመል ምህንድስና በምስጢር ይካሄዳል በዘረመል ምህንድስና (ጂ.አም.ኦ) ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉ ሳይንቲስቶች ሙከራ የሚያደርጉበት አካባቢ በሚስጥር መጠበቅ አለበት እያሉ ነው፡፡ ዘረመል ምህንድስና የሚካሄድባቸው ስፍራዎች ለህዝብ ግልፅ ይሁኑ በሚል የአውሮፓ ህብረት ያወጣውን ሕግ በሚፃረር መልኩ የዘርፉ ባለሙያዎች በድብቅ ጥናታቸውን ማካሄዳቸው አግባብ አይደለም ሲል የምግብና የገጠር ጉዳዮች ኢንቫይሮመንት ክፍል (ዴፍራ) ተቃውሟል፡፡ አያይዞም "የአውሮፓ ህብረት ፍርድ ቤት ውሳኔን እንጠብቃለን" ብሏል፡፡ ሆኖም በዘረመል ምህንድስና ጥናታቸውን የሚያካሂዱ ሳይንቲስቶች "ጥረታችንን ግልፅ ብናደርግ የዘረመል ምህንድስና ተቃዋሚዎች ግኝቶቻችንን ያጠፉብናል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ በዘረመል ምህንድስና ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉት ኘሮፌሰር ሃዋርድ አቲክሰን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ማጥናት የጀመሩት የድንች ዝርያ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ድንቹ በሽታ የመቋቋም አቅም ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ በተተከለ በሦስተኛው ሳምንት ውስጥም ያድጋል፡፡ ቻይና ኢንተርኔትን በመጠቀም ትልቁን ስፍራ ያዘች ቻይናውያን ኢንተርኔትን በመጠቀም በዓለም ትልቁን የህዝብ ቁጥር እንደሚሸፍኑ መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡ "በቻይና በአሁኗ ሰዓት ከ253 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ኢንተርኔት እየተጠቀሙ ነው" ሲል ቢቢሲ የቻይናን ኢንተርኔት ኔትወርክ መረጃ ማዕከል ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ አብዛኛዎቹ ቻይናውያን ኢንተርኔት የሚጠቀሙትም በብሮድባንድ ነው፡፡ አሜሪካ በሰኔ 2008 ካስመዘገበችው 223 ሚሊዮን የኢንተርኔር ተጠቃሚ የቻይናው በልጦ ተገኝቷል፡፡ አሜሪካውያን ኢንተርኔትን በመጠቀም ዓለምን ሲመሩ የነበረ ቢሆንም ቻይናውያን ያሳዩት ፈጣን ለውጥና እድገት በዓለም ኢንተርኔትን በመጠቀም ትልቁን ስፍራ እንዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡ አጫሽ የትዳር አጋር ያላቸው ለምት (stroke) የተጋለጡ ናቸው የትዳር ጓደኛዎ የሚያጨስ/የምታጨስ ከሆነ እርስዎ ባያጨሱም በስትሮክ የመጠቃት እድልዎ ከፍተኛ ነው የሚለን የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ነው፡፡ የአሜሪካ ጆርናል ኦፍ ኘሪቬንታቲቭ ሜድሲን ስተዲ እንዳመለከተው ከአጫሾች ጋር የሚኖሩ አጫሽ ያልሆኑ ሰዎች በስትሮክ የመያዝ እድላቸው 72 በመቶ ደርሷል፡፡ አጫሾች በስትሮክ የመጠቃት እድላቸው ቀድሞውንም ከፍተኛ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ለሁለተኛ አጫሾች የነበረው ጥናት የሚያሳየው ግን እድሉ አናሳ እንደነበረ ነው፡፡ በየጐዳናው ማጨስ በተከለከለባቸው እንደ እንግሊዝ ባሉ አገራት ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ስለሚያጨሱ ቤተሰቦቻቸው ለጭሱ ተጋላጭ እየሆኑ ነው፡፡ የጥናቱ ተካፋይ የነበሩት ዶ/ር ማሪያ ግላይመር እንደተናገሩት በትዳር ጓደኛሞች መሃል የሚኖር የአንደኛው ወገን አጫሽነት ሌላኛውን በእጅጉ የሚጐዳው መሆኑን የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |