Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Sep 07th
Home arrow Sections arrow እናትነት ማየት ለተሳናቸው
እናትነት ማየት ለተሳናቸው Print E-mail
Sunday, 03 August 2008

Image
ወ/ሮ ወይንሸት በዙ
Image
ወ/ሮ ገነት ከተማ
በምሕረት አስቻለው

"ነፍሠ ጡር ሆኜ በመንገድ፣ አወቶብስ ላይ እንዲሁም ሆስፒታል ውስጥ የሚመለከቱኝ ሰዎች ምን አለበት ቢቀርባት፣ ምን ያደርግላታል የሚሉ አስተያየቶችን ይሰነዝሩ ነበር፡፡ በትዳር ያለሁ ሁሉ አይመስላቸውም፡፡ ተደፍራ ወይም ቀብጣ ነው የሚል እሳቤአቸው በንግግራቸው ይንፀባረቃል፡፡ አስተያየታቸውን ልስማ አልስማ እንኳ አያስተውሉም፡፡ ይህ ደግሞ ሞራልን የሚጐዳ ነገር ነው" ይላሉ ወ/ሮ ወይንሸት በዙ የተባሉ ማየት የተሳናቸው እናት፡፡

 

አንደኛው አይናቸው የአራት ዓመት ህፃን ሳሉ በአደጋ፣ ሌላኛው ደግሞ የስምንት ዓመት ልጅ ሆነው በኩፍኝ እንደጠፋ የሚናገሩት ወ/ሮ ወይንሸት የእርግዝና ጊዜአቸው ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ሕብረተሰቡ አንዲት አካል ጉዳተኛ ሴት አርግዛ ሲመለከት እንደሚከብደው ይህ ደግሞ በእንቅስቃሴ ወቅት መጋጨት ወይም መውደቅ ይኖራል፣ ከሚል ሥጋት በመነሳት ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ አካል ጉዳተኛ ነፍሰጡር እናቶች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ጉዳት ደረሰባቸው ማለት ሌላ አካል ጉዳተኛ መፍጠር በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ወይንሸት በአሁኑ ወቅት የአስራ ሰባትና የዘጠኝ ዓመት ሴት ልጆች አሏቸው፡፡ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በዲኘሎማ ተመርቀዋል፡፡ የፍኖተ ተሀድሶ ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ ባለቤታቸው ደግሞ በከሚሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ደግሞ በአዲስ አበባ ጤና ኮሌጅ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ነች፡፡

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሰበታ መርሀ እውራን አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሆነ፤ ትዳር በመሰረቱበት ወቅትም ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

"ነፍሰ ጡር በነበርኩበት ወቅት ሰውነቴ የዳበረ እልነበረም፡፡ ኑሮዬም ዝቅተኛ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የተገላገልኩት በቀላሉ አልነበረም፡፡ የእኔም ሆነ የወለድኳት ህፃን ኪሎ በጣም አነስተኛ ነበር፡፡ ሀኪሞቹ በሁኔታው መቸገራቸውን ከንግግራቸው ድምፀት እረዳ ነበር፡፡ የህፃኗ ኪሎ ከሚጠበቀው በታች በመሆኑ በልዩ ክፍል ውስጥ እንድትተኛ ተደርጐ ነበር፡፡ ያለምንም ድካም በተደጋጋሚ ልጄ ወዳለችበት ክፍል እየሄድኩ አጠባት ነበር"፡፡

የልጃቸው ኪሎ እስኪስተካከል ማንኛዋም እናት ማድረግ የሚገባትን እንክብካቤና የሀኪም ክትትል አድርገዋል፡፡ ከሦስት ወር በኋላ የባለቤታቸው እናት ህፃኗን ወስደው ማሳደግ በመፈለጋቸው ስምንት ዓመት እስከሚሞላት ከሳቸው ጋር ቆየች፡፡ ይህ የሆነው የኑሯቸው ሁኔተ የተስተካከለ ባለመሆኑ ነበር፡፡

ቅድመ ወሊድ ክትትል ያደርጉ በነበሩበት ወቅት በህክምና ባለሙያዎች ይደረግላቸው የነበረው ክትትልና እንክብካቤ መልካም ነበር፡፡ አብረዋቸው ወደ ሆስፒታል ይሄዱ የነበሩ ሰዎች እሳቸው ሀኪማቸውን ለማናገር ወደ ህክምና ክፍል ሲገቡ አብረዋቸው ይገቡ እንደነበር በማስታወስ፤ ይህ ቅር ያሰኛቸው እንደነበር አመልክተዋል፡፡ "አጋጣሚም ሊሆን ይችላል በሕክምና በኩል የተዛባ አመለካከት አልገጠመኝም፡፡ የሚስጥር አለመጠበቅ ግን ተከስቶብኛል፡፡ ለሀኪም የምነግረው ግላዊ ምስጢር ሊኖረኝ ይችላል፡፡ አብረውኝ የሄዱ ሰዎች አብረውኝ ይገቡ ነበር፡፡ ረዳቴን ውጭ ቅሪ ብቻዬን ነው መግባት የምፈልገው አለማለቴ ምን አልባትም በራስ አለመተማመን ይሆናል፡፡ አሁን ቢሆን ግን ዶክተሬን ብቻዬን ማነጋገር እንደምፈልግ እገልፅ ነበር፡፡ ይህ የሆነው የመጀመሪያ ልጄን ነፍሰ ጡር በነበርኩበት ወቅት ነበር" ብለዋል፡፡

የመጀመሪያ ልጃቸውን እንደተገላገሉ ሀኪሞች ህፃኗን እንዲያቅፏት ሲያደርጉዎት የተሠማዎትን ስሜት ይግለፁልን? ስንል ጠየቅናቸው፡፡ በዚያ ቅፅበት የነበራቸውን ስሜት ፈፅሞ መግለፅ እንደማይችሉ፤ የመጀመሪያ ልጃቸው በመሆኗ፣ እናትነትና የልጅ ፍቅር ፍፁም ደስተኛ አድርጓቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ልጄ ማንን መሠለች የሚለው ነገር ብዙም አያስጨንቃቸውም ነበር፡፡ የሕፃኗን ድምፅ በተደጋጋሚ ለመስማት ግን ይጓጉ ነበር፡፡ የፀጉሯንና የሠውነቷን ልስላሴ ለማወቅ የራሳቸውን መንገድ ይጠቀሙ ነበር፡፡ በቦታው የነበሩ ሰዎች (ሐኪሞች) ግን ህፃኗ ምን እንደምትመስል ይነግሯቸው ነበር፡፡ እነዚያ ሰዎች ስለህፃኗ የሚሰጡትን አስተያየት በአእምሯቸው ቢይዙትም ዘወትር ልጃቸውን ሰያቅፉ የሚታያቸው እሳቸው ስለህፃኗ በሀሳባቸው የሳሉት ስዕል ነበር፡፡

ወ/ሮ ወይንሸት እንዳሉት፣ ህፃን ልጅን ከማቀፍ ጀምሮ ማጠብ፣ ማልበስ፣ ፀሀይ ማሞቅና መቀባባት ካለማየት አንፃር ማየት ለተሳናት እናት ከባድ ሊመስል ቢችልም ለልጃቸው ተገቢውን እንክብካቤ አድርገዋል፡፡ እንዴት ማቀፍ እንዳለባቸው ሀኪሞች አሳይተዋቸው ነበር፡፡ ለማጠብ ደግሞ ለመጀመሪያ ቀን ጐረቤቶቻቸው ረድተዋቸዋል፡፡ እሳቸውም ሆኑ ሌሎች ማየት የተሳናቸው እናቶች በሌሎች የስሜት ሕዋሳቶቻቸው በመታገዝ ለልጆቻቸው ልዩ እንክብካቤ ያደርጋሉ፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ሦስት ወር ከሆናት በኋላ ስምንት ዓመት እስኪሞላት ያሳደጓት አያቷ በመሆናቸው ልጅ ማሳደግ ምን እንደሚመስል ሙሉ በሙሉ የተመለከቱት በሁለተኛ ልጃቸው ነው፡፡ ከመመገብና ከማልበስ ባሻገር ባህሪው ጥሩ እንዲሆን፣ በተለይም የአካል ጉዳተኛ ልጅ በመሆኑ የበታችነት ስሜት እንዳያድርበት አድርጐ ማሳደግ የአካል ጉዳተኛ ወላጆች  የተለየ ኃላፊነት ነው፡፡ ልጆቻቸው በአመለካከትም ሆነ በትምህርት የተሻሉ እንዲሆኑ የተለየ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

በእግራቸው መሄድ ሲጀምሩ የተለያዩ ነገሮችን በመነካካት ሲያጠፉ ያን መቆጣጠር ከባድ እንደሆነ፤ መውደቅ መነሳታቸው ሀሳብን እንደሚከፋፍልና እንደሚረብሽ ይናገራሉ፡፡ ከቤት መውጣትና አካባቢያቸውን ማስተዋል ሲጀምሩ እንቅስቃሴአቸው ይጨምራል፡፡ ይህ ደግሞ የበለጠ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የህፃናትን እንቅስቃሴ (የአካል ጉዳተኛ ልጆችን ብቻ ሳይሆን) የማንኛውንም ህፃን ሁኔታ በመከታተል ሕብረተሰቡ ኃላፊነት ይወስዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ልጆች ተገቢ ያልሆነ ተግባር ሲፈፅሙ ወይም የማይገባቸው ቦታ ላይ ሲገኙ ህብረተሰቡ በዝምታ አለማፉና በሌሎችም ተመሳሳይ ሁኔታዎች በልጆች እድገት ላይ የህብረተሰቡ ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ተረድተዋል፡፡

"አሁን ልጆቼ አድገው በተለያዩ ቦታዎች ሰዎች ሲመለከቱኝ የሚሰጡት አስተያየት ደስ የሚል ነው፡፡ ቢሆንም ልጆች ያፈራሁት ለመጠቀም ስል እንደሆነ የሚያስቡ በርካቶች ናቸው፡፡ አንድ ሰው ልጅ የሚወልደው ለመጠቀም ብቻም አይደለም፡፡ በርግጥ ቢጠቅሙኝ ብንጠቃቀም ደስ ይለኛል፡፡ ሕይወት በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተች ናትና፡፡ ግን ልጆች ያፈራሁት ሊጠቅሙኝ ብቻ ሳይሆን ዘሬን ለመተካትና በመልካም ሥነ ምግባር የታነፁና ጥሩ ራእይ ያላቸው ልጆች ለማበርከት ነው" በማለት በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው አካል ጉዳተኛ ልጅ የሚወልደው በልጆቹ ለመጠቀምና ለመገልገል ነው የሚል አመለካከት ሊቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከመጀመሪያ ልጃቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የጓደኝነት እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ ወይንሸት ወደ ገበያ የሚሄዱት ከልጃቸው ጋር ነው፡፡ ወደ መሥሪያ ቤታቸው ሲሔዱም ታክሲ ታሲዛቸዋለች፡፡

የአካል ጉዳተኛ ልጆች በማንኛውም አካባቢ ጫና (ስነ ልቦናዊ) ስለሚገጥማቸው ያን እንዲቋቋሙ ለማድረግ ልጆቹ በአመለካከት፣ በትምህርት ብቃት፣ በስነ ምግባር እንዲሁም በአለባበስ ከለሎች ልጆች የተሻሉ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል እንደ ወ/ሮ ወይንሸት እምነት፡፡ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ፣ ጥሩ የትምህርት ቁሳቁሶች ከያዙ ተማሪዎች ያከብሯቸዋል፣ የተሻለ ቦታ ይሰጧቸዋል፡፡ በማንኛውም ረገድ የተሻሉ ከሆኑ የአካል ጉዳተኛ ልጅ በመሆናቸው የዝቅተኝነት ስሜት እንደማይሰማቸው ጠቁመዋል፡፡ ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ወላጅ ሁኔታውን በጥልቀት ስሚያውቅ (ከአካል ጉዳተኝነት ጋር በተያያዘ የሚደርሱ ጫናዎች) የበለጠ ጥረት እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል ያልሆኑ አመለካከቶች እንዲቀየሩ ያደርጋል፡፡

ምንም እንኳ ባለቤታቸው በሥራ ምክንያት ቢርቁም የልጆቻቸውን፣ የአጠቃላይ ቤተሰቡን ሁኔታ ዘወትር በስልክ ይከታተላሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜአትም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ይጠይቋቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ደግሞ የቤተሰባቸውን አጠቃላይ ሁኔታ እንደምትከታተል በዚህም ሙሉ በሙሉ ኃላፊነታቸውን እንደተጋራች ከንግግራቸው ለመረዳት ችለናል፡፡

በእርግዝናም ይሁን በማንኛውም ሁኔታ ከአካል ጉዳተኝነት ጋር በተያያዘ የሕብረተሰቡ ግንዛቤ መሻሻሉን ይህም ከቃላት አመራረጥ ጀምሮ አካል ጉዳተኞችን ከማግለል ይልቅ የማክበርና የመንከባከብ ነገር እየታየ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ያነጋገርናቸው ሌላዋ ማየት የተሳናቸው እናት ወ/ሮ ገነት ከተማ ይባላሉ፡፡ ማየት የተሳናቸው በተወለዱ በሀያኛው ቀን ጨረር አይናቸው ላይ ባደረሰባቸው ጉዳት ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን ያረገዙት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ ገነት በአሁሉ ወቅት የሦስት ሴትና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው፡፡ "የመጀመሪያ ልጄ ሀያ ሁለት ዓመቷ ነው፡፡ በዚያ ወቅት ተማሪ ነበርኩ፡፡ እርግዝናዬ አያስታውቅም ነበር፡፡ ስለዚህም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የተለየ የተሰጠኝ አስተያየት አልነበረም፡፡ እኔ ግን ተማሪ  ስለነበርኩም ይሁን አላውቅም ልጅ የመውለድም ይሁን የማሳደግ ፍላጐት አልነበረኝም፡፡ በዚህም ለአንድ መሀን አክስቴ እንደተገላገልኩ እንደምሰጣት ቃል ገብቼላት ነበር" በማለት ከተገላገሉ በኋላ ግን ሀሳባቸውን በመሰረዝ ልጃቸውን ሳይሰጡ መቅረታቸውን ገልፀውልናል፡፡ "የልጄን የመጀመሪያ ድምፅ ስሰማ ሁሉም ነገር ተቀየረ፡፡ የማላውቀው ስሜት ውስጤን ተሰማው" ብለዋል፡፡

ልጆቻቸው ህፃናት ሳሉ ያደርጉላቸው የነበረውን እንክብካቤ በማስመልከት፣ የመጀመሪያዎቹን ሁለቱ ልጆቻቸውን ገላ ያጥቡላቸው የነበሩት የቅርብ ዘመዶቻቸው እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን ማየት የተሳናቸው በመሆኑ ሳይሆን ህፃናቱን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ካለማወቅና ይቀጩብኛል ከሚል ፍራቻ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ልጅ ስለመውለድና ስለማሳደግ ያላቸው ስሜት በመጀመሪያ ልጃቸው ቢቀየርም ከእርግዝና ጀምሮ ሁሉን ነገር ማስተዋልና ማጤን የጀመሩት ከሁለተኛው ልጃቸው በኋላ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ የመጨረሻው ልጃቸው አራት ዓመቱ ሲሆን እርሱን ባረገዙበት ወቅት ከብዙ ሰዎች ይበቃሽ ነበር የሚል አስተያየት ይሰጣቸው እንደነበር አልደበቁም፡፡

በአሁኑ ወቅት ባለቤታቸውም ሆኑ እሳቸው በአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ራሷን ችላ የወጣች ሲሆን ከመጨረሻው በስተቀር ሌሎቹ ተማሪዎች ናቸው፡፡

"ብዙ ሰዎች ካለማየት ጋር በተያያዘ ልጅ ማሳደግ የሚያስቸግረን ወይም የማንችል ይመስላቸዋል፡፡ የልጆቻችን በትምህርትም ሆነ በስብዕና በሚማሩበት ክፍልም ሆነ በምንኖርበት አካባቢ ላሉ ልጆች ምሳሌ መሆን የሕብረተሰቡን የተሳሳተ አመለካከት ይቀይራል፡፡ በምንኖርበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ልጆቼ ልጆቻቸውን እንዲያስጠኑአቸው ሲጠይቁኝ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል" ብለዋል፡፡
 
< Prev   Next >