Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ኧረ ባቲ ባቲ
ኧረ ባቲ ባቲ Print E-mail
Sunday, 03 August 2008

ከሔለን ይታየው

"ኧረ ባቲ ባቲ ገንደሪዩ
ሐድራ የሚገባው ደራርበው ሲተኙ"

የሚለውን ዜማ ወደ ባቲ የሚሄዱ አውቶብሶች ሁሉ ያለማቋረጥ አለመጠቀማቸውን አወግዛለሁ፡፡ ባቲን ለሚያውቃትና ለትንሽ ጊዜ የተለያት ኧረ ባቲ ባቲ በሚለው "ዘፈን ልቡ በናፍቆት መቃጠሉ አይቀርም፡፡ እንደኔ ላለው "የባቲ ፍቅረኛ" ባቲን በቅኝት ስያሜዋ ብቻ ከሚያውቃት በተለየ መልኩ በልቡ ውስጥ ተሰንቅራ ትቀራለች፡፡ እናም ትዝታዬን አንግቼ ወደ ባቲ ሄድሁ፡፡

 

ተወልጄ ያደግኩበት ቀበሌዬን ለማየት፣ ደቡብ ወሎ በምትገኘው ጥንታዊቷ ባቲ ከተማ በመጓዝ ላይ እያለሁ በጣም ብዙ የምናፍቃቸው ነገሮች ተደቀኑብኝ፡፡ ያሳደገችኝ ባቲ እንዴት ሆና ይሆን? ትርንጎዋና ሎሚዋ ቆንጆዎቹ ጭምር እንዴት ከርመው ይሆን? ጓደኞቼስ? እያልኩ ባቲ እስክደርስ በሀሳብ ናወዝሁ፡፡

የውቦች ከተማ፣ የቆንጆዎች መፍለቂያ የተባለላት ባቲ ገና ወደ ከተማዋ ሲገቡ መግቢያው ላይ በትልቁ "ባቲ የቆንጆዎች አገር ነች" የሚል ፅሑፍ አየሁ ያንን ፅሑፍ የሰቀለውን መረቅሁት፡፡ እኔ ለመመረቅ ባሰብሁ ቁጥር የባቲ የልጅነት መራቂዎቹ ታሰቡኝና እንደገና በትዝታ ሰመጥሁ፡፡

ባቲ ከተማ ስደርስ ከምሽቱ 2፡30 ገደማ ይሆን ነበር፡፡ አውቶብስ ተራ ይጠብቁኝ የነበሩት ዘመዶቼን ሳገኝ ደስታ ሰውነቴን አዝናናው፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ቀበሌየን ማየት ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥር የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ በጣም ተደስቼ ባለሁበት ወቅት ተወልጄ ያደኩበት ቤታችንን ሳየው እንባ ተናነቀኝ፡፡

ባቲ በአራት ዓመት ውስጥ ካየኋት ብዙ ለውጥ አላሳየችም፡፡ በእርግጥ መንገድ ተሰርቷል፡፡ ውስጥ ለውስጥ በየሰፈሩ የነበሩ የጠጠር መንገዶች የአሸዋ ንጣፍ ተሰርቶላቸዋል፡፡

ስልክ በጣም ጥቂት ቤቶች እንጂ በቅርብ አልነበረም፡፡ አሁን ግን በየቤቱ፣ በየሱቁ፣ በየቢሮው ሁሉም ቦታ በቅርብ ይገኛል፡፡ በተወሰነ እርቀት ላይም ቴሌ ሴንተሮች ይገኛሉ፡፡ የሞባይል አገልግሎትም ጀምሯል፡፡ በዚህ ደስ ሲለኝ ነገር ግን የንግድ እንቅስቃሴዋ መድከሙና መሰረተ ልማቱ አድጎ ባለማየቴ ቆጨኝ፡፡ የውሃ ችግር ባቲን ክፉኛ ጎድቷታል፡፡ አንድ ጀሪካን ውሃ በብር፣ ለተሸካሚው ደግሞ ሁለት ሦስት ብር እየከፈሉ ያስቀዳሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ውሃው እንደልብ ከተገኘ ነው፡፡

በሚቀጥለው ቀን ጎረቤቶቼን እየተዘዋወርኩ ሰላም አልኩኝ፡፡ ግን ትመጣለች፤ ብሎ የጠበቀ ባለመኖሩ ሁሉም ሊያውቁኝ አልቻሉም ነበር፡፡ ለካ እኔም ለእነሱ ተለውጫለሁ፤ ክብደት ጨምሬያለሁ፤ አድጌያለሁ፡፡ ለእኔም ብዙዎቹ ተለውጠውብኛል ትልልቅ የነበሩት አርጅተው ልጆች የነበሩት አድገው፣ ሳይ በተራዬ ተገረምሁ፡፡

ባቲ ትንሽና ደማቅ ከተማ ናት፡፡ ከኮምቦልቻ አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝና ባቲ ለመድረስ በኮምቦልቻና በባቲ መካከል ደጋንና ገርባ የሚባሉ ከተሞች ማለፍ ያስፈልጋል፡፡

ባቲ ለአፋር ክልል ቅርብ በመሆኗ አፋሮችና ኦሮሞዎች ይኖሩባታል፡፡ ከአፋር ክልል፣ ቡርቃ፣ ዱብቲ፣ አሳይታ፣ ሚሌ፣ ዳሊፋጌ ጭፍራ ወዘተ. በቅርብ ያዋስኗታል፡፡
 
የተቆረቆረችው ከአዲስ አበባ በ10 ዓመት ቀድማ ነው፤ ቢባልም ያላት እድገት ግን እንደ እድሜዋ አይደለም፡፡

በኦሮሚያ ክልል የምትገኘው ባቲ የገጠሩ ነዋሪዋ፣ በአብዛኛው የሚጠቀመው ቋንቋ ኦሮምኛን ነው፡፡ በገጠሩ የሚኖሩት ወንዶች፣ ሽርጥ አገልድመው ከላይ ሸሚዝ ለብሰው ደግሞ ኮንጐ ጫማ ይጫማሉ፡፡ ከእጃቸው ላይ ዱላ አይጠፋም፡፡ ሴቶቹ ቅቤ የተነከረ አቡጀዲ ጉርድ ቀሚስና እንደ ቲሸርት ተሰፍቶ ወይንም ደግሞ ብትኑን አሰፍተው ሙሉ ቀሚስ ከላይ ደግሞ ጉፍታ በመልበስ ይታወቃሉ፡፡

ከተማዋ ብዙም ሰፊ ባትሆንም ደማቅና የማትከብድ ከተማ ነች፡፡ ካሏት ነገሮች በነዋሪዎቹ ዘንድ ናፍቆቱ ከዓይን የማይጠፋው የሰኞ ገበያ ነው፡፡ ሰኞ ዕለት ገና ከጠዋቱ ጀምሮ ሕዝብ ወደ ገበያ ይጎርፋል፡፡ በዚያው አካባቢ በገጠሩ ክፍል የሚኖሩት ከጨፌ፣ ከጋዱላ፣ ከጫጫቶ ወዘተ. ከአካባቢው ከተሞች ደግሞ ከገርባ፣ ከደጋን፣ ከኮምቦልቻና ከደሴ በሚመጡ ነጋዴዎች ትሞላለች፡፡ ገበያው ይጦፋል፡፡ ገበያተኛውም ይጐርፋል፡፡ ባቲ ትፍለቀለቃለች፡፡

ሰኞን የባቲ ተወላጆች በናፍቆት ይጠብቋታል፡፡ ተማሪዎችም ሳይቀሩ ሰኞን ይናፍቃሉ፡፡ የጧት ፈረቃ ተማሪዎች ከሰዓት በኋላ፣ የከሰዓት በኋላ ተማሪዎች ደግሞ ጧት ገበያውን ሳይሳለሙ አያድሩም፡፡

በሰኞ ገበያ ወጣቶች ሊተጫጩና የከንፈር ወዳጅ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የገጠሩ ህብረተሰብ ወጣት ወንድና ሴቶች የከንፈር ወዳጅ መሆን የሚችሉ ሲሆን ከመሳሳም የዘለለ ምንም ዓይነት ነገር ማድረግ አይፈቀድም፡፡ ተሳስተው እንኳን ወሲብ ከፈፀሙ ወንዱ እንዲያገባት ይገደዳል፡፡

ብዙ ጊዜ መተጫጨትና መጋባት የሚኖረው በሙስሊሞች ኢድ አልፈጥር በዓል ወቅት ነው፡፡ ከሁሉም የገጠሪቱ ክፍል ብዙ ሴቶች እና ጐረምሶች ባቲ በመሰባሰብ ኳስ ሜዳ በሚባለው ቦታ ላይ "እሌሄ ወሊሌሄ" እያሉ ሴቶቹና ወንዶቹ ወገብና ወገባቸውን በእጅ በመያያዝ የሚጫወቱት ዜማ አለ፡፡ በዚያን ቀን ብዙ ወንዶች እጮኛ ለመምረጥ ይመጣሉ፡፡ ወንዱ የፈለጋትን ሴት አብራው እንድትጨፍር ይጠይቃታል፡፡ እሷም ከተስማማች አብራው ትጨፍራለች፡፡

በዚያ ቀን በየቤቱ የሚበላው ነገር ይበረክታል፡፡ ቁርቁራው (ጋባ"፣ ቴምሩ፣ እንኳዩ፣ ሸንኮራው፣ ማንጐው ፍራፍሬው ሁሉ በዚያ ቀን በየቤቱ አይጠፋም፡፡

የከብት ተራው፣ የዶሮውና እንቁላሉ፣ የቅቤ፣ የሸንኮራ አገዳው ወዘተ. የሌለ ተራ የለም፡፡ እስከ ማታ 12 ሰዓት ገበያው ይቆማል፡፡ ሁሉም ሰው ለሳምንት የሚሆነውን ገበያይቶ ወደየቤቱ ይገባል፡፡ ነጋዴዎቹም የያዙትን ሸጠው በሸጡት ደግሞ ሸምተው ወደየቀበሌያቸው ይገባሉ፡፡ ትርምሱ ግርግሩ ሁሉም ነገር ግን የሚናፈቅ ነው፡፡ ስለዚህ ባቲን ጥለው ቢሄዱ የሰኞ ገበያ ናፍቆት ተሰንቅሮ ይቀራል፡፡

አሁን ያለው የኑሮ ውድነት በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት እኔ የማውቃቸው ነገሮች በሙሉ በአምስትና ስድስት እጥፍ ጨምረዋል፡፡ ለምሳሌ ድሮ ሃምሳና ሰባአምስት ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ሸንኮራ አገዳ፣ አሁን አራት ብር ከሃምሳ ሳንቲም፣ ድሮ አንድ ብር ይሸጥ የነበረው ማንጐ፣ አሁን ሦስት ብር፣ አራት ብር ይሸጥ የነበረው ትርንጐ፣ አስራ ሁለት ብር፣ አንድ ወልዲያ (ከአንድ ኪሎ በላይ የሚይዝ ጣሳ) ጤፍ፣ ሁለት ብርና ሦስት ብር፣ ይሸጥ የነበረው፣ አሁን አስራ አራት ብር፣ የፀጉር ቅቤ በሲኒ ሁለት ብር ይሸጥ የነበረው አስር ብርና በጐማ ደግሞ አስር ብር ይሸጥ የነበረው ሃያ ሰባት ብር፣ ዶሮ አምስትና ስድስት ብር የምትሸጠዋ ሴት ዶሮ ሃያ ስድስት ብር ሆኗል፡፡ ባቲዎች ኑሮ በጣም ከብዷቸዋል፡፡ በዚህ የኑሮ ክብደት ባቲ ቆዝማለች፡፡  

በባቲ ከተማ መሀል ገበያ ውስጥ የሚገኘው በቁመቱም ሆነ በስፋቱ በጣም ትልቅ የሆነ የሚገርም ብረት ይታያል፡፡ በፊት እዚያ አገር ስኖር ብዙም ትኩረት ሰጥቸው አላውቅም ነበር፡፡ አሁን ግን ስለዚህ ብረት ምንነት ስጠይቅ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ የተፈረደበት ወንጀለኛን በስቅላት የሚቀጣበት እንደነበርና አሁን ግን እንደዚያ ዓይነት ቅጣት እንደሌለ ተነገረኝ፡፡ ምንም ዓይነት ወንጀል የሰራ ሰው እዚያ ብረት ላይ ይሰቀል እንደነበር ይነገራል፡፡

ምንም እንኳ የኑሮ ውድነት ቢያንገላታውም የሰው ፍቅር አኗኗሩ በጣም የሚገርምና የሚያስደንቅ ነው፡፡ ከተማዋ ላይ ሙስሊሞችም ክርስቲያኖችም ሁሉም በፍቅርና በመተሳሰብ ይኖራሉ፡፡ የሃይማኖት ልዩነት የለም፡፡ በአንድ ዕድር ውስጥ የሁለቱም ሃይማኖት አማኞች በአንድነት ይካፈላሉ፡፡ በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ አይለያዩም፡፡ ባቲ እንዲህ ያለች የፍቅር ከተማ ናት፡፡ ባቲ የኢትዮጵያ የመቻቻል ተምሳሌት ናት ቢባልም ይቻላል፡፡

በባቲ ለሴት ልጆች ያለዕድሜያቸው እንዲያገቡ ይገደዳሉ፡፡ ገና የ12 እና የ13 ዓመት ልጆች እያሉ ለእጮኛ ይሰጣሉ፡፡ እንዲማሩ አይበረታቱም፡፡ ተምሬ የት ልደርስ? በሚል ተስፋ መቁረጥ ትምህርታቸውን እያቋረጡ የሚያገቡ አልጠፉም፡፡ ከተማ ውስጥ ከሙዋዕለ ሕፃናት እስከ ፕሪፓራቶሪ ትምህርት ቤት ቢኖርም የሙያም ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች አቅም ያላቸው ከሚሴ፣ ደሴ ወይም ኮምቦልቻ ቤት ተከራይተው ወይም ዘመድ ጋር ሆነው ይማራሉ፡፡ አቅም የሌላቸው ተማሪዎች ግን ሳይማሩ ያችኑ ባቲን የሙጥኝ ብለው ይቀራሉ፡፡ ሴት ልጆች ትምህርታቸውን እንደ ጨረሱ ያላቸው አማራጭ ወደ ትዳር መግባት ብቻ ነው፡፡ ገና ካለ ዕድሜያቸው የልጅ እናት ሆነው ማየት ቅር ያሰኛል፡፡

ከአለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ተበራክቶ ያየሁት ጫት ነው፡፡ ጫት በሰፊው ይቃማል፡፡ ጫት የሚቃመው "ለመደበሪያነት" መሆኑ ቀርቶ አሁን በየቀኑ ከምሳ ሰዓት በኋላ መደበኛ ተግባር ወደመሆን ተቃርቧል፡፡ አብዛኛው የከተማ ነዋሪ ሁሉም በእጁ ጫት ይዞ ይታያል፡፡ እቤታቸውም እንግዳ ሲጋብዙ ከምሳ በኋላ ጫት ተዘጋጅቶ "ተፈርሾ" መጠበቅ ልማድ ሆኗል፡፡ የማይቅም ሰው ምንም እንደማያውቅ ተደርጎ የሚታሰብበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በጫት ተማሪ ነው፤ ሠራተኛ ነው፤ ተብሎ የሚለይበት ሁኔታ የለም፡፡ ሁሉም ተመሳስለዋል፡፡ ጫት ለመቃም ተማሪ ነው ወይም ልጅ ነው ተብሎ መከልከል ቀርቷል፡፡ ወላጅ ከልጁ ጋር ቁጭ ብሎ ጫት የሚቅምበት ሁኔታ በመኖሩ በጣም አዝኛለሁ፡፡ ይኸ ለውጥ በዝቶ ያየሁት በሌለሁባቸው ጥቂት ዓመታት በመሆኑም ገርሞኛል፡፡

በተወሰነ ደረጃ ከብድርና ቁጠባ ገንዘብ ወስደው እንዲሰሩ በተሰጠው ፈቃድ መሠረት እራሳቸውንም የቀየሩ ሰዎች አይቻለሁ፡፡ ሁሉም የሥራ ተነሳሽነት ኖሮት የተለወጡትን በማየት መቀየር ቢችል በጣም ጥሩ ነው እላለሁ፡፡

በባቲ ቆይታዬ ያቺን "ሚጢጢ" ከተማ እንደ ቀድሞዬ ስዞራት ከረምኩ፡፡ አንዳንድ ጓደኞቼን አግኝቼያለሁ፡፡ ሥራ ባይኖራቸውም ተስፋ የማይቆርጡ ጓደኞቼ ባላቸው ነገር ይደሰታሉ፡፡ እኔም እዚያ በመገኘቴ ተደስቻለሁ፡፡ ግን ከተማዋ ባለማደጓ ልቤ አዝኗል፡፡ ቀድሞ ከአሰብ ጋር ባላት መገናኛ ሞቆ የሚታየው የንግዱ እንቅስቃሴዋ እንኳ የተዳከመ ስለመሰለኝ ተቆጨሁ፡፡ በባቲ ከጥበብ መነሻዋ አድጋ እንድትታይም ተመኘሁ፡፡ "እስከ መቼ ኧረ ባቲ ባቲ" በመዝፈን ብቻ እንድትቆም ትደረጋለች??
 
< Prev   Next >