Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow ወርቅ ቅብ ብረት በማቅረብ ብሔራዊ...
ወርቅ ቅብ ብረት በማቅረብ ብሔራዊ... Print E-mail
Sunday, 03 August 2008
ወርቅ ቅብ ብረት በማቅረብ ብሔራዊ ባንክን ያጭበረበረው ግለሰብ ምስክር ሆኖ ቀረበ

በስድስት ዙር 13 ሳጥን ወርቅ ቅብ ብረት አቅርቧል

በታምሩ ጽጌ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ በሚያዚያ ወር 2000 ዓ.ም በተፃፈ የክስ ማመልከቻ ክስ በመሰረተባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሰራተኞችና ነጋዴዎች ላይ ወርቅ ቅብ ብረታ ብረት በማቅረብ ብሔራዊ ባንክን ያጭበረበረውን ግለሰብ በከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት በማቅረብ ሐምሌ 24 ቀን 2000 ዓ.ም የምስክርነቱን ቃል አሰማ፡፡ ግለሰቡ በስድስት ዙር 13 ሳጥን ወርቅ ቅብ ብረታ ብረት ለባንኩ ማቅረቡን ተናግሯል፡፡
የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ሊያስመሰክር ካቀረባቸው 19 የሰው ምስክሮች መካከል ሙከሚል ሸሪፍ የተባለውን ግለሰብ የመጀመሪያ ምስክር በማድረግ አስመስክሯል፡፡

ምስክሩ የአቶ ሙደሲር መሀመድ ሶፋም ተቀጣሪ ሰራተኛ መሆኑንና በኦሮሚያ ክልል አላጌ የእርሻ ጣቢያ እንደሚሰራና በአሰሪው በአቶ ሙደሲር ትዕዛዝ አራት ፎቶ ግራፍ ተነስቶ ይዞ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ተናግሯል፡፡

ስሙን በመለዋወጥ የተለያዩ የንግድ ፈቃድና መታወቂያዎች ከተሰራለት በኋላ ለብሔራዊ ባንክና ለሚመለከታቸው አካላት ተሰራጭቶ (ዶክመንቱ) ከአቶ ሙደሲር በሚደርሰው ትዕዛዝና የሚሰጠውን ዕቃ ወደ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤትና ወደ ብሔራዊ ባንክ ሲያመላልስ መቆየቱን ገልጿል፡፡

ከአለቃው በከረጢት ተደርጎ የሚሰጠውን ወርቅ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት ወስዶ ካስመረመረ በኋላ፣ በሳጥን አሽገው “ታሽጓል” የሚል ማህተም ባለበት ወረቀት አራት ቦታ ተለጥፎበት ይዞ ሲወጣ፣ ለአለቃው በመደወል አንድ ሱቅ ላይ እንደሚገናኙም ተናግሯል፡፡

አቶ ሙደሲር መሐመድ የታሸገውን ሳጥን ተቀብሎት ለሃያ ደቂቃ ያህል እንዲጠብቀው ካደረገ በኋላ “ማህተም አድርጌበት ላምጣልህ” በሚል ወደ ቤት ይዞ እንደሚገባና ሳጥኑን አምጥቶ እንደሚሰጠው የገለፀው ምስክሩ ሳጥኑን በቀጥታ ወስዶ ለብሔራዊ ባንክ እንደሚያስረክብ ገልጿል፡፡

ይዞ የሄደውን ሳጥን ለብሔራዊ ባንክ ሲያስረክብ በአንድ ፎርም ላይ እንደሚያስፈርሙት የተናገረው ምስክሩ በስድስት ዙር 13 እሽግ ሳጥኖችን ለባንኩ ማስረከቡን ገልጿል፡፡

ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ አስር ሳጥኖችን ተረክቦ ሲያበቃ አለቃው ማህተም አድርጌ ላምጣልህ ብሎ ወደቤት ይዞ ከገባ በኋላ 13 ሳጥኖችን እንደሰጠውና እንዳስረከበ፣ የባንኩ ኃላፊዎችም ሳይጠይቁ እንደተቀበሉት ተናግሯል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቁን ሽያጭ ብር በአንድ ጊዜ እንደማይረከብና፣ አምስት አምስት ሚሊዮን በማድረግ በየቀኑ እንደሚወስድ ምስክሩ ተናግሯል፡፡

ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ አወል መሐመድ በሚል ስም ህብረት ባንክ እንደሚያስገባ የገለፀው ምስክሩ የባንኩ ኃላፊዎች አንቀበልም በማለት ሲያሰቸግሩት ከሱ (መደሲር) ጋር በስልክ ሲያገናኛቸው እንደሚስማሙና አስግብቶ እንደሚሄድ አስረድቷል፡፡

13 ሳጥኖችን ወደ ብሔራዊ ባንክ ካስገባ በኋላ ወደ መደበኛ ሥራው (አላጌ እርሻ ቦታ) እንዲመለስ መደረጉን የገለፀው ምስክሩ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተደውሎለት “ትሰሩት በነበረው ሥራ ምክንያት ሙደሲር ስለታሰረ ወደ አዋሽ ናና ደውልልኝ” የሚል ትዕዛዝ ከአብዱልሽኩር መሐመድ ሲደርሰው ወደ አዋሽ መምጣቱን ገልጿል፡፡

አዋሽ ድረስ ሾፌር ተልኮለት ወደ ሐረር መወሰዱን፣ ከሀረር በሞያሌ አድርጎ ወደ ኬንያ እንዲሄድ መደረጉን፣ ከኬንያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ሚኪ የሚባል ሰው (አብዱልሽኩር መሀመድን ነው) መጥቶ ፓስፖርት ወጥቶልሃልና ትሄዳለህ እንዳለውና በመጨረሻም የትም ሳይሄድ በቁጥጥር ስር መዋሉን ለፍርድ ቤቱ ምስክሩ አስረድቷል፡፡

ምስክሩ በስም እየጠራ የምስክርነት ቃሉን ያሰማባቸው ተከሳሾች፣ በጠበቆቻቸው አማካኝነት የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠይቀውት፣ ምንም ሳይደናገጥና ሳይፈራ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በማጣሪያ ጥያቄ ለምስክሩ በርካታ ጥያቄዎች ያነሳ ሲሆን፣ በተረጋጋና ሁኔታ ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ምስክሩ ከኬንያ ተይዞ እንደመጣ ለአንድ ወር ከታሰረ በኋላ መለቀቁን ከመግለጹም በተጨማሪ “በሥራ አማካኝነት ነው የማውቃቸው” ያላቸውን ከብሔራዊ ባንክ ሦስት፣ ከጆኦሎጂካል ሰርቬይ ሁለትና ከነጋዴዎቹ ሁለት፣ ተከሳሾችን ተነስቶ ለፍርድ ቤቱ አሳይቷል፡፡

የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ሊያሰማቸው ካዘጋጃቸው 19 ምስክሮች መካከል፣ አንደኛው ምስክርና እሱን በሾፌርነት ያጓጓዘውን ሐምሌ 24 ቀን 2000 ዓ.ም ጠዋት፣ ከሰዓት ደግሞ የተለያዩ ፎርጅድ ሰነድ ባዘጋጁ ተከሳሾች ላይ ሁለት ምስክሮች እንዲሁም ሐምሌ 25 ቀን 2000 ዓ.ም ጠዋትና ከሰዓት የኦዲት ሰራተኛ (ሴት) በወርቅ አያያዝና እንዴት መጓጓዝ እንደነበረበት የሚያስረዱ በምስክርነት ቀርበው መስክረዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸው ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለጥቅምት 20 ቀን 2001 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ መሰል ወርቅ ቅብ ብረታ ብረት በመቀበል ከ156 ሚሊዮን ብር በላይ መጭበርበሩን፣ ስድስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች (ከባንኩ”፣ ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ አራት የሥራ ኃላፊዎች፣ 16 ነጋዴዎችና አንድ ድርጅት በቁጥጥር ሥር ውለው በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደተመሰረተባቸው፣ በተደጋጋሚ የሰነድ ልውውጥ ተደርጎ፣ ፍርድ ቤቱ በብይኑ የተከሳሾችን ማስረጃ እንዳልተቀበለውና ወደ መደበኛ ክርክር ገብተው እንዲከራከሩ ብይን መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
 
< Prev   Next >