| የኦሳማ ቢንላደን ወንድም... |
|
|
| Sunday, 03 August 2008 | |
![]() ዶክተር ሼህ ጣሪቅ መሐመድ ![]() - 50 ኩባንያዎች የመሰረቱት ህብረት ኢትዮጵያን የንግድ ማዕከል ያደርጋል
በአሰግድ ተፈራ በሽብርተኝነት የተፈረጁት የኦሳማ ቢንላደን ወንድም ዶክተር ሼህ ጣሪቅ መሐመድ ቢንላደን ኢትዮጵያን እንደሚጐበኙ የኢትዮጵያ ወኪላቸው አቶ መስፍን አስፋው ከበደ በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ ከቢላደን ቤተሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት ሼህ ጣሪቅ ቢላደን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ሃምሳ የዓለም ታዋቂ የንግድ ተቋሞች ኢትዮጵያን የንግድ ማዕከል ለማድረግ መወሰናቸውን ተከትሎ መሆኑን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቱ የቢንላደን ቤተሰብ አባል ኢትዮጵያን እንዲጐበኙ በኢትዮጵያ የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር በኩል የተጀመረው ጥረት ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀርቦ ይሁንታን አግኝቷል፡፡ ጣሪቅ ቢንላደን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት በመጪው ጥቅምት ወር 2ዐዐ1 ዓ.ም. ይሆናል፡፡ የጣሪቅ ቢንላደን የኢትዮጵያ ጉብኝት ስኬታማ እንዲሆን ከስድስት ወር በፊት የተለያዩ ኘሮጀክቶች ተነድፈው የወረቀት ስራ በመስራት ላይ እንደሆነ ወኪላቸው አስረድተዋል፡፡ በቱሪዝም፣ በእርሻ በተለይም የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪና በማዕድን ፍለጋ ሥራ ባለሀብቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ከወኪላቸው ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ባለሀብቱ ከወንድማቸው ኦሳማ ቢንላደን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ያስታወቁት አቶ መስፍን ጅቡቲንና የመንን በቀይ ባህር በድልድይ ለማገናኘት ከሁለቱም መንግሥታት ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው ..የአልኑር ሲቲዳ.. ኘሮጀክት ከ5ዐ የዓለም ታዋቂ ኩባንያዎች ህብረት (Al Noor Alliance) በመፍጠር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ መስፍን ገለፃ 2ዐዐ ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀውን ድልድይ ለመገንባት የተፈጠረው የአል-ኖር ህብረት ከአሜሪካ፣ ከካናዳ፣ ከእንግሊዝ፣ ከዴንማርክ፣ ከቱርክ፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከአረብ ኢምሬትስ አገራት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ አቶ መስፍን አያይዘውም ..ህብረቱ የሀይማኖትና የድንበር ልዩነትን ወደ ጐን በመተው በዓለም አዲሱን የገበያ ትኩረት የሳቡትን መካከለኛው ምስራቅንና አፍሪካን በባህር በማገናኘት ንግድን ማስፋፋት ነው.. ህብረቱ ከጅቡቲና ከየመን መንግሥታት ጋር ጁላይ 28/2008 ጅቡቲ ፓላስ ኬምኘኒክይ ሆቴል ባደረገው ስምምነት መሰረት ሁለቱን ከተሞች ለማገናኘት በባህር ላይ የሚዘረጋው ሰስፔንሽን ድልድይ ስድስት መኪኖችንና አራት ባቡሮችን በአንድ ጊዜ ሲያስተናግድ የነዳጅና የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎችም እንደሚኖሩት ኘላኑ ያሳያል፡፡ 28.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ድልድይ በሁለት ጫፎቹ ማለትም በጅቡቲ 1 ሺህ፣ በየመን 1 ሺህ 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያላቸው አዳዲስ ከተሞች ይኖሩታል፡፡ በመጪው ዓመት የሚጀመረው ድልድዩ ስራ የመካከለኛውን ምስራቅና የአፍሪካን ሕዝባች በንግድ የሚያስተሳስር መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሉ ከፍተኛ ባለሀብቶችንም እንዲጋብዝ ታስቦ መሆኑን አቶ መስፍን ያስረዳሉ፡፡ በዓለም ላይ በአሁኑ ሰዓት በንግድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወደ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገሮች በስፋት የገቡት ቻይና፣ ህንድ፣ ሩሰያና ብራዚል የአጋጣሚውን ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያመለከቱት አቶ መስፍን ..የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ከነዳጅ ሽያጭ የሚያገኙት ከፍተኛ ክምችት ያለው ገንዘብ በሌሎች ንግዶች ላይ ለማዋል እንዳሰቡ በኑር ሲቲ ስለታመነበት ለኘሮጀክቱ 2ዐዐ ቢሊዮን ዶላር ተመድቧል.. በ2008 ግብፅን ጨምሮ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች አንድ ትሪሊዮን የሚጠጋ ገቢ ማግኘታቸውን የጠቆሙት የሼህ ጣሪቅ የኢትዮጵያ ወኪል ..የአረብ አገሮች ከነዳጅ ንግድ ውጪ ገንዘባቸውን በሌሎች የንግድ መስክ ማዋል አለባቸው፡፡ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገችው አፍሪካ ደግሞ የንግዱ ማዕከል ናት፡፡ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች.. በማለት ዶ/ር ሼህ ጣሪቅ መሐመድ ቢላደን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እቅድ መያዙንም አስረድተዋል፡፡ ከባለሀብቱ ጋር ህብረት የፈጠሩትን ጨምሮ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም አስታውቀዋል፡፡ ዱባይ ወርልድ የተባለ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍ የመጀመሪያ ደረጃ ንግግር መደረጉን ገልፀን በቅርቡ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |