Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ኢትዮጵያና ኤርትራ -10 ዓመታት...
ኢትዮጵያና ኤርትራ -10 ዓመታት... Print E-mail
Sunday, 03 August 2008

Imageኢትዮጵያና ኤርትራ -10 ዓመታት ወደ ኋላ
በጌታቸው ንጋቱ

የኢትዮ ኤርትራ ነገር እንዳልሆነለት የገለፀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለስምንት ዓመታት ያህል የአገሪቱን ድንበር ሰላም ማስከበር ሥራ ሲያከናውን የከረመውን አንሚ ከሐምሌ 23 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ ማንሳቱን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦር ያለ ማንም ጣልቃ ገብ ፊት ለፊት በተፋጠጡበት በአሁኑ ሰዓት ቀጣዩን ነገር መገመት አዳጋች ሆኗል፡፡

 

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪሙን የአንሚ ቆይታ ጊዜ በዚህ መልኩ መጠናቀቁ እጅግ እንዳሳዘናቸው የገለጹት ባን ኪሙን ኢትዮጵያና ኤርትራ የቀረበላቸውን የመፍትሄ ሃሳብ በሙሉ አለመቀበላቸውና ከእንግዲህ በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር አካባቢ መቆየት የማይታሰብ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ "አሁንም ኢትዮጵያና ኤርትራ ችግራቸውን በውይይት መፍታት ከፈለጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መልካም ትብብር ያደርገላቸዋል" ያሉት ባን ኪሙን ሁለቱ አገራት በወሰዱት እርምጃ ማዘናቸውን ገልፀዋል፡፡ "አሁን ያለውን ሁኔታ አገራቱ በራሳቸው ለመፍታት ይችላሉ" የሚል እምነት እንዳላቸው የገለፁት ባን ኪሙን የአልጀርሱን ስምምነት አገራቱ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የተቻላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

የሁለቱ አገራት ድንበር ውጥረት የነገሰበት ቢሆንም የሁለቱም አገራት መንግሥታት ጦርነት እንደማይፈልጉ መግለጫ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደገለፁት "የሠላም አስከባሪው ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሚናቸው የሚተካ አይደለም አንልም፡፡ አሁንም በድንበሩ አካባቢ አንፃራዊ ሠላም አለ" ሲሉ እንደምንጊዜውም ሁሉ ኢትዮጵያ በማንኛውም መልኩ ወደ ጦርነት እንደማታመራና ጦርነት እንደማትፈልግ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንደወትሮው ሁሉ ለሠላም ዝግጁ መሆኗን እና የድንበሩን ጉዳይ በሠላም ለመፍታት እንደምትፈልግ ገልፃለች፡፡ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጦር ካልሰበቀ በስተቀር ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት እንደማታመራ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲገልጽ የሚኖረው እርምጃም ከኤርትራ ወገን ጥቃት ከተቃጣ ራስን የመከላከል እርምጃ ብቻ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ሃሳቡንና አቋሙን አስቀምጧል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረ መስቀል በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "አንሚ መውጣቱ ጦርነት አያስከትልም፡፡ አንሚ ላለፉት ስምንት ዓመታት ያህል የነበረው ሚና ለስም ብቻ የተቀመጠ ነው፡፡ አንሚ መኖሩም ጦርነት እንዳናካሂድ አልከለከለንም፡፡ አሁንም ወደ ጦርነት የማንገባው ጦርነት ስለማንፈልግ ነው" ብለዋል፡፡ "ኢትዮጵያ ልዑላዊ ግዛታችንን ወርራ ተቀምጣለች፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድንበራችንን ኢትዮጵያ ለቅቃ እንድትወጣ ግፊት ሊያደርግ ይገባል" ሲሉም አቶ የማነ አክለው ገልፀዋል፡፡

ኤርትራ ባድመ በድንበር ኮሚሽኑ ውሣኔ የተፈረደላት በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያስረክባት ስትጠይቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ለኤርትራ የተሰጠውንም ሆነ ለኢትዮጵያ የተሰጠውን መሬት ከመረካከብ በፊት መደራደር አለብን ይላል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እንደማታደርግ ስትገልጽ ከመቆየቷም በላይ ሉዓላዊ ግዛቷን ለማስመለስ የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን ጦርነት ልትጠቀም እንደምትችል ስትዝት ከርማለች፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ለ10 ዓመታት ያህል ሲለፋበት የነበረውን የሠላም ሂደትና ዓለም አቀፋዊ ጥረት ወደ ኋላ የመለሰ ከመሆኑም በላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት "ከደሙ ንጹህ ነኝ" ብሎ መውጣቱ ተጨማሪ ውጥረት ያሰፍናል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ ኤርትራ ጦርነትን እንደ አማራጭ ብትጠቀምስ ለሚለው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዚሁ ጉዳይ ለፓርላማ ምላሽ ከዚህ ቀደም ሲሰጡ የኤርትራ መንግሥት ወደ ጦርነት ቢገባ ራሱን በራሱ እንዳጠፋ እንደሚቆጥርና ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ቢገባ እንደማያዋጣው ጠንቅቆ እንደሚያውቅ አስረድተዋል፡፡

የሆነው ሆኖ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ በተለያየ አቅጣጫ ጥቃት እየሰነዘረ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ይገልጻል፡፡ የኤርትራ መንግስት በሶማሊያ ጉዳይ ያለው ጣልቃ ገብነት፣ የኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎች (ኦነግና ኦብነግ"ን በማስታጠቅና ከሶማሊያ አክራሪዎች ጋር በመስራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር ወቀሳ ይቀርብበታል፡፡ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ የቀጥታ ጦርነት ብትከፍት በጦር ሃይልና ብዛት ስለማይመጣጠኑ የኢትዮጵያን ትኩረት የሚስቡ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ለመቆየት እንደምትሻ ብዙ ተንታኞች ሲያስረዱ በቅርቡ ጅቡቲ ላይ ኤርትራ የቃጣችው ጥቃት ኢትዮጵያን ስጋት ውስጥ ለመጣል የታቀደ እንደሆነ ሲገለጽ የኢትዮጵያ መንግሥትም በጅቡቲ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዟል፡፡ ኤርትራ ጅቡቲን በመውረር የኢትዮጵያን የወደብ ጥቅም ላይ አደጋ ለመጣል ያሰበ እርምጃ ለመውሰድ ብታስብም የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ የኤርትራ ሃሳብ የማይሳካና ኢትዮጵያን የሚያሳስብ እንዳልሆነ ሲገልጽ ኤርትራም እንደዚህ የከፋ አደጋ በወደብ ጥቅሟ እንደማታደርስባት ኢትዮጵያ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

የኤርትራን ጉዳይ ከአገር ውስጥ ሠላም ጋርም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያያይዘው ሲሆን በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ የሚደርሱ የተለያዩ የቦምብ ፍንዳታዎች በኤርትራ መንግሥት አቀነባባሪነት የሚፈፀሙ እንደሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ይገለፃል፡፡

ከዚህ አልፎ በሁለቱ አገራት መካከል ከባድ ጦርነት ይካሄዳል የሚል ፍራቻ ያላቸው ብዙ ወገኖች ሲኖሩ ከእነዚህም መካከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገኝበታል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት በድንበር አካባቢ ያለው የጦር ሃይል አሰፋፈር በሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል በማንኛውም ሰዓት ሊፈነዳ የሚችል ጦርነት ያዘለ መሆኑኑና አሁን ባለው ስሜት ጦርነት የማይቀር መሆኑን የሚያሳይ ሁኔታ እንዳለ ይገልፃል፡፡ ጦርነት የማይቀረው ሁለቱም አገራት ከስምንት ዓመታት በፊት ከያዙት አቋም ያልተነቃነቁና በአቋማቸው የፀኑ በመሆናቸው እና የተባበሩት መንግስታት የሠላም ማስከበርም ሆነ፣ ዲፕሎማቲክ ጥረት ውጤት አልባ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለቱም መንግስታት ጦርነት እንደማይናፍቁ እየገለጹ ቢሆንም አሁን ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ የሚችልና በማንኛውም ወቅት ወደ ሙሉ ጦርነት (full scale war) ሊቀየር እንደሚችል ተመድ ስጋቱን ይገልፃል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በኤርትራ ያላቸው ተቀባይነት እያደር እየቀነሰ መምጣቱ፣ አገሪቱ ከምዕራባውያን አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ መበላሸቱና የአገሪቱ ድህነት ደረጃ እየከፋ መምጣቱ ከፍተኛ ግፊት እንዳሳደረባቸው የሚገልጽ ሲሆን፣ ኢሳይያስ ይህንን ሁሉ ለማስታገስ ሲሉ የአገር ውስጡን ችግር ወደ ውጭ ማሻገር እንደሚፈልጉ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ በአገር ውስጥ ያለው አለመግባባት ብዙ ተቃዋሚዎችን እየፈጠረ እና ከውጭ በኤርትራ መንግሥት ላይ እየተሰነዘረ ያለው ጫናም እየተበራከተ መጥቷል፡፡

የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች ራሳቸውን በማጠናከር የስደት መንግሥት እያቋቋሙ እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን በኤርትራ የፖለቲካ ክፍተት (Political Vaccume) ሳይፈጠር፣ ስልጣን የመያዝ ዕቅድ አላቸው፡፡ እነዚሀ የኤርትራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የሚገለጽም ሲሆን፣ ስልጣን እንዴት ልይዙ ይችላሉ የሚለውን ጥያቄ በተለያየ መልኩ ምላሽ እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ቢገቡ ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል ሃሳብ ሲኖር ተቃዋሚዎቹ በኤርትራና ኢትዮጵያ ጦርነት ማብቂያ የኢሳይያስን መንግሥት አስተዳደር ለመረከብ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው የተለያዩ ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡ ተቃዋሚዎቹ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኘነት መልካም በመሆኑና ኢሳይያስ አፈወርቂ ከአፍሪካ ቀንድ ካልተነሱ ሠላም አይገኝም፤ የሚለው አመለካከት በብዙዎች እየታመነበት መምጣቱ ይህንኑ ሃሳብ በመጫን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጦርነት እንዲደረግ ይፈልጋሉ የሚል ነው፡፡

የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት መበላሸት በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ አደጋ ያለው በመሆኑም ጉዳዩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ማግኘት አለበት ሲሉ የሚሰጡ አስተያየቶች የኤርትራና ኢትዮጵያ ጉዳይ የሶማሊያን ጉዳይ ውስብስብ እንዳደረገው፣ የተለያዩ የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋቶች በሁለቱ አገራት ግጭት እየተከሰተ እንደሆነ፣ ኤርትራም ለአሸባሪዎች የአፍሪካ ቀንድን እያመቻቸች መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያስረዳል፡፡ አሜሪካም የኢሳይያስ አስተዳደር እንዲወገድ የምትፈልግ ሌላ አካል ነች፡፡ የአሜሪካን አቋም የተረዱት ኢሳይያስ አፈወርቂም በአሜሪካ ላይ በተደጋጋሚ የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ለድንበር ግጭቱ አለመፈታት የአሜሪካ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በምዕራባውያን አገራት በተለይም በአሜሪካ ተስፋ የቆረጡት ኢሳይያስ ወደ አክራሪዎችና አሸባሪዎች እየሄዱና ለእነሱም የጦር መሳሪያና የስልጣን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት በ1990 ዓ.ም ግንቦት ወር የተጀመረው ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት በመግባት ወረራ በመፈፀሟ ነበር፡፡ ኤርትራ ጦርነት ከኢትዮጵያ ጋር ያካሄደችው ከኢትዮጵያ በተገነጠለች አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ጤናማ ያልሆነው ግንኙነት አስር ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል ባደረጉት ጦርት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን አሁን ጦርነት የሚቀሰቀስ ከሆነ ከዚህ የከፋ አደጋና ጥፋት ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው ተመድ ይገልፃል፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግጭት የድንበር ብቻ እንዳልሆነ የሚጠቁሙ መረጃዎች ግጭቱ ኢኮኖሚያዊ አንድምታም እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

ከሁለቱ ዓመት ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን በድል እንዳጠናቀቀ ሲገልጽ የሁለቱ አገራትን ግንኙነት ወደ ጤናማነት ለመመለስ የተለያዩ ወገኖች ጥረት አድርገዋል፡፡ ጥረታቸው የሰመረላቸው የአልጄሪያው ፕሬዚዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ሁለቱ አገራት የአልጀርስ ስምምነትን እንዲፈራረሙ አስቻሉ፡፡ በአልጀርሱ ስምምነትም መሠረት ኢትዮጵያና ኤርትራ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሠላም አስከባሪ ኃይል በኢትዮ ኤርትራ ድንበር እንዲሰፍር፣ አንድ ገለልተኛ የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ የሁለቱን አገራት የድንበር ይገባኛል ጥያቄ እንዲፈታና የኮሚሽኑ ውሳኔም የመጨረሻና ተፈፃሚነት ያለው እንዲሆን ይጠይቃል፡፡ ሁለቱም አገራት ለአልጀርሱ ስምምነት እየተገዙ ተኩስ አቁሙ ቢቀርም የድንበር ችግራቸው ግን አስር ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

አሁን ደግሞ ያለው ሁኔታ ከ10 ዓመት በፊት ወዳለበት እየተመለሰ መሆኑ ያሰጋው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሠላም አስከባሪ ኃይል ጓዙን ጠቅሎ ከሐምሌ 23 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ እንዲወጣ ወስኗል፡፡ ከኤርትራ ቀድሞ የወጣው የሰላም አስከባሪ በኢትዮጵያም ያለው ቆይታ በዚህ ውሳኔ መሠረት ተጠናቋል፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ ያልሆነና የማይሆንበት ደረጃ ላይ መገኘቱም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ ጦርነት እንደሚያመራና በአሁኑ ወቅት ያለው ሠላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታ (No peace, No war situation) የአገራቱን ልማት እንደገታውም የተባበሩት መንግስታት ሲያመለክት በሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ላለፉት 10 ዓመታት ተጋልጠው መክረማቸውን ይገልፃሉ፡፡

አሁንም መፍትሄው የት እንዳለ አይታወቅም፡፡ "ኤርትራ ድርድር አልፈልግም፤ የተፈረደልኝ መሬት ይሰጠኝ" ትላለች፡፡ ኢትዮጵያ "የድንበር ማካለል ከማድረጋችን በፊት ድርድር ይቅደም" ትላለች፡፡ የተባበሩት መንግስታት ይህንን ሁኔታ ከዚህ በላይ ማስታመም አቅቶታል፡፡
 
የኢትዮ ኤርትራ ግጭት ካሌንደር
ግንቦት 4፣ 1990  -  ኤርትራ ኢትዮጵያን ወረረች
ሰኔ 9፣ 1992     -  ኢትዮጵያ ጦርነቱን ማሸነፏን አወጀች
ታህሳስ 4፣ 1993  -  የአልጀርሱን ስምምነት ኢትዮጵያና ኤርትራ ፈረሙ
ሚያዚያ 5፣ 1994 -  የድንበር ኮሚሽኑ ውሣኔ አሳለፈ
ሚያዚያ 5፣ 1994 -  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በክርክሩ መርታቷን
                   አስታወቀ
ኅዳር 15፣ 1997   - ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በመርህ ደረጃ
                   መቀበሏን  ገለፀች
ታህሳስ፣ 2000     - ኤርትራ አንሚን አባረረች
ታህሳስ 25፣ 2000  - የድንበር ኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ አብቅቶ ተበተነ
ሐምሌ 23፣ 2000  - የአንሚ ሠላም አስከባሪ ኃይል ሙሉ በሙሉ ተነሳ
                    የቀን አቆጣጠር  - እንደ ኢትዮጵያ
 
< Prev   Next >