| ጎጆ የወጡት 5ቱ ጥንዶች |
|
|
| Sunday, 03 August 2008 | |
|
በእለቱ ማሕሙድ ጀማል ከዘቢባ አብደላ፣ መሐመድ ከዲር ከአሚና አደም፣ ዩሱፍ ሽፈራው ከንጁማ ኢብራሂም፣ ሀሰን አብዱልገፋር ከአሊያ አብዱል ላጢፍ፣ ሸረፈዲን ኢብራሂም ከአኒሳ ቃሲም ጋር ጋብቻቸውን ፈፅመዋል፡፡ የሆቴል ዝግጅቱንና የባለትዳሮቹን መቋቋሚያ ወጪ የሸፈነው ወፋ ዴቨሎኘመንት ኤንድ ኢስላሚክ ሪሊፍ አሶስዬሽን የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን በማኅበራዊ መናጋት ላይ ከሚሰራ የኩዌት ድርጅት ድጋፍ እንደተደረገለትም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች በእለቱ 5ቱን ጥንዶች ሲዳሩ አጀንዳ ያደረጉት፣ ወጣቶች በቅርብ ዓመታት ለጋብቻ የቀዘቀዘ ስሜት የማሳደራቸውን ነው፡፡ ጋብቻን ወጣቶች በጊዜ ሲፈፅሙት ከነሙሉ ኃላፊነቱ ስለሚሸከሙት በዋዛ ፈዛዛ የሚያጠፉት ጊዜን ጠቃሚ በሆነ ሥራ ላይ እንዲያውሉት ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለማህበረሰቡ ብሎም ለሀገሪቱ መረጋጋትና መበልፀግ የራሱ የሆነ በጎ ተፅእኖ ማሳረፍ ያስችላል ብለውም እንደሚያምኑ በተለያየ መንገድ አሳይተዋል፡፡ ወንድ ሙሽሮች በታዳሚ አባቶቻቸው፣ ሴት ሙሽሮችም በታዳሚ እናቶቻቸው ሰብሰብ ተደርገው የልምድ ተሞክሮ እንዲቀስሙ ተደርጓል፡፡ ለእለቱ ሥነ ሥርዓት አርአያ ተደርገው እንደተመረጡ ሁሉ ትዳራቸው ሌሎች ወጣቶችን እንዲያነሳሳና አርአያነታቸው እንዲቀጥል ለማድረግ እንዲችሉ ምክር የተቀበሉት የተሳካ የረጅም ዘመን የትዳርና የእውቀት ልምድ ካላቸው አባቶችና እናቶች ነው፡፡ የወፋ ዳይሬክተር ሼክ መሐመድ ሐሰን እንዲሁም የኘሮጀክት አስተባባሪው አቶ አደም ተሾመ፣ የመርከዚል ኢንሱዋር ዳይሬክተር ዶ/ር ጄላኒ ከድር፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የእርዳታና ልማት ማኅበር ዳይሬክተር ሀጂ አዳነ ማሙዬ እና አቶ አደም ካሚልን ጨምሮ በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ እንግዶች፣ ወጣቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለትዳር ያለው ስሜት የቀዘቀዘ በመሆኑ የህብረተሰቡን መናጋት እያባባሰ እንደመጣ ስምምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ አደም ካሚል የተለያዩ ጥናቶችን በመጥቀስ ትዳር አልባ ወጣቶች መበራከታቸው የሴተኛ አዳሪዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርንና ሌሎች ችግሮችን ማስከተሉን አብራርተዋል፡፡ ሼክ መሐመድ ሐሰን 5ቱ ጥንዶች በምን መስፈርት እንደተመረጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ "በአቅመ ደካማነት፣ ለማግባት ያላቸው ፍላጎትና ለጋብቻ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ መስፈርቶችን ከሌሎች በአንፃራዊነት በተሻለ ሁኔታ አሟልተው በመገኘታቸው ነው" ብለዋል፡፡ አቶ አደም ተሾመ በማህበራዊ ችግሮች፣ በሰብአዊ አገልግሎቶችና ልማት ላይ ባለፉት ዓመታት ይሰራ የነበረው ወፋ ከማህበራዊ ችግሮች አንዱ በሆነው በኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ በሽታ ላይ በርካታ ስራዎች መሥራቱን አስታውዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለጋብቻ ወይም ለትዳር ያለው ትኩረትና ክብር በተለይ በወጣቶች ዘንድ እየቀነሰ በመምጣቱ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታን ለመከላከል የጋብቻ ባህልን ማዳበርና ማስፋፋት አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኙት ጠቁመዋል፡፡ ሼክ መሐመድ ሐሰን ቀደም ብሎ የአወሊያ ትምህርት ቤት ርዕስ መምህርና የኢትዮጵያ የእስልምና ጉባዔ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በህብረት ጥንዶችን በመዳር ተግባርም ሲሳተፉ ይህ ሦስተኛ ጊዜያቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ 30 ጥንዶችን በመዳር የአስተባባሪነት ሚና ተወጥተዋል፡፡ የአምስቱ ጥንዶች ተወካይ ሆኖ በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረገው ወጣት ማሕሙድ ጀማል፣ የሥርዓቱ ታዳሚዎች ማግባት እየፈለጉ ያልቻሉትን ሌሎች ወጣቶች እንዲድሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከስብሰባው መልስ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎችም ይህን ተግባር በትብብር ሊሠሩት እንደሚገባ ገአሳስበዋል፡፡ ሀጂ አዳነ ማሙዬ በመዳርና በማቋቋም ላይ የሚሰራ ድርጅት ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የወፋ ዳይሬክተር ሼክ መሐመድ ሐሰን ጋብቻ በአብዛኛው ሀይማኖት የተከበረ ሲሆን፣ በእስልምና ለጋብቻ የደረሱ ወጣቶችን መዳር ኃይማኖታዊ ትዕዛዝ በመሆኑ ለጋብቻ ደርሰው በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ፍላጎታቸውን ማሳካት ላልቻሉት ወጣቶች ድጋፍ መስጠትና ማቋቋም ማኅበራዊ ችግሮችን ከማቃለልም የዘለለ ዓላማ ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ አደም ተሾመ ድርጅታቸው በተናጠልም ይሁን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር የመዳርና የማቋቋም ተግባር ወደፊት ይቀጥልበታል ወይ ተብለው ሲጠየቁ "አምስቱን ጥንዶች ስንድርና ለመቋቋሚያ ለእያንዳንዳቸው አራት አራት ሺህ ብር ስንሰጥ የወፋን ራዕይና አላማ እያስፈፀምን ነው፡፡ ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ ያገኘነው ምላሽ አበረታች በመሆኑ ከሌሎች ድጋፎች ጋር ተጣምረን የምንመለስበት ይመስለኛል፡፡ በመላው ሀገሪቱ በርካታ ሰብአዊ ድጋፎችንና የልማት እንቅስቃሴዎችን ከመንግሥት ጋር ተባብረን እየሰራን በመሆኑ እሱን በማይጎዳ መልኩ እርዳታ ካገኘን እንቀጥልበታለን፡፡ የአሁኑ ሥነ ሥርዓት ወጪ ካገኘነው እርዳታ የበለጠ ነው" ሲሉ መልሰዋል፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች እስላማዊ ማኅበሮች ወቅፍ (እርዳታ የሚለግሱትና ስጦታ የሚበረከትላቸው) የሚባሉትን ጨምሮ በጋብቻ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ መሰል ድርጅቶችን ለማቋቋም አመቺ ሁኔታዎች እንዳሉ የኡማ ሆቴል ታዳሚዎች ይቀበላሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |