Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ፌዴሬሽኑ "የአትሌቲክስ" ቢሆን...
ፌዴሬሽኑ "የአትሌቲክስ" ቢሆን... Print E-mail
Wednesday, 06 August 2008

ፌዴሬሽኑ "የአትሌቲክስ" ቢሆን ምን ይውጠን ነበር?
ታሪኩ ነገራ

አርብ ነሐሴ 2 ቀን 2000 ዓ.ም የሚከፈተውና የሚጀምረው ቻይና የምታስተናግደው የዘንድሮው 29ኛ ኦሊምፒያድ የአገራችንንም ጨምሮ የእያንዳንዱ አገር የውስጥ ዜና እና የመላው ዓለም ኢንተርናሽናል ዜናና አጀንዳ ሆኗል፡፡ ሆኖም ይቀጥላል፡፡ ከእያንዳንዱ አገር የኦሊምፒክ ቡድን ምልመላና ምርጫ እንጀምር፡፡

 

ለእያንዳንዱ የኦሊምፒክ ጨዋታ የሚዘጋጀው የልዑካን ቡድን ልክና መጠን በየጊዜው እያደገና እየጨመረ በመምጣቱ ዓለማቀፋዊው የኦሊምፒክ ኮሚቴ በኦሊምፒክ ጨዋታው የሚሳተፈውን የልዑካን ቡድን አባላት ቁጥር ጣሪያ መወሰን ተገድዷል፡፡ ጣሪያው ከመወሰኑ ጋር መከበር እና መጠበቅ ያለበት የተሳትፎ የብቁነት ወግና ደንብ (ኮድ) በኦሊምፒክ ቻርተር ተወስኗል፡፡ የአንድን አገር የኦሊምፒክ የልዑካን ቡድን አባላት መርጦና መልምሎ የመላክ ኃላፊነት የእያንዳንዱ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው፡፡ ብሔራዊው የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚመርጠውና የሚመለምለው እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የኦሊምፒኩን ቻርተር እንዲሁም እያንዳንዱ ጉዳይና ዘርፉ የሚመለከተው ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን ያወጣቸውን ኢንተርናሽናል የኦሊምፒክ ኮሚቴ ያፀደቃቸውን ደንቦች የሚያሟላ መሆን አለበት፡፡

በዚህም መሠረት እያንዳንዱ ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን በስልጣኑ ዙሪያ ያለውን ስፖርት የብቁነት መመዘኛና ቅድመ ሁኔታ በኦሊምፒክ ቻርተር መሠረት ያወጣል፡፡ ይህም መመዘኛና ቅድመ ሁኔታ ለኢንተርናሽናል የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ቀርቦ ይፀድቃል፡፡ ይህን የመሰለው የብቁነት መመዘኛ አፈጻጸምም የሚመለከተው እያንዳንዱን ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን የእነሱንም የዘርፍ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና የብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴውን ነው፡፡ እንዲያውም በኦሊምፒክ ቻርተሩ ደንብ አንቀጽ 49/3 እንደተወሰነው አንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽን የአገሩ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በሰጠው የምርጫ ውሳኔ ላይ ያለውን ቅሬታ በይግባኝ ለኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ማቅረብ የሚችለው ዘርፉ በሚመለከተው ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን አማካኝነት ነው፡፡

የማንኛውም አገር የስፖርት መዋቅርና አደረጃጀት መሠረታዊ አሀድ ክለቦች ናቸው፡፡ አትሌቶች የስፖርቱን ዓለም የሚያውቁት የሚተዋወቁት በዚሁ አሀድ አማካኝነት ብቻ ነው፡፡ አትሌቶች የክለቦች ናቸው፡፡ ክለቦች የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አባላት ናቸው፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ደግሞ የብሔራዊ የአሊምፒክ ኮሚቴዎችና የኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኖች አባላት ናቸው፡፡ የእያንዳንዱ አገር ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደግሞ በኦሊምፒክ ቻርተርና ደንቦች አማካኝነት ከኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የአንድ አገር ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚቋቋመው የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴን እውቅና አግኝቶ ነው፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ ብሔራዊ ኮሚቴ ከኦሌምፒክ ቻርተር፣ ሕግና ደንቦች ጋር የተጣጣመ የገዛ ራሱ ሕገደንብ ይኖረዋል፡፡ በዚህ መልክ የተቋቋመ የአንድ አገር ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዚያ አገር የግዛት ክልል ውስጥ የኦሊምፒክ እንቅስቃሴን ወይም ንቅናቄን ለመምራት ብቸኛው ሥልጣንና ተግባር ያለው እሱ ነው፡፡ ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች (ጌምስ) የልዑካን ቡድን የመምረጥና የመላክ ሥልጣንም የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ነው፡፡ በአገሪቷ ዳር ድንበር ውስጥ የኦሊምፒክ ቀለበቶችን፣ ዓርማዎችንና ምልክቶችን የመጠቀም ብቸኛ የባለቤትነት መብት ያለውም እሱ ነው፡፡

የአንድ አገር ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የዚያው አገር ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴን እውቅና ማግኘት ብሎም የብሔራዊ ኮሚቴው አባል ለመሆን ለኦሊምፒክ ቻርተሩ ደንብ መሠረት ከሌሎች መካከል ስፖርቱ የሚመለከተውና የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ እውቅና የሰጠው የኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን አባል መሆን አለበት፡፡   

የ29ኛው የቤጂንግ ኦሊምፒያድ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ የልዑካን ቡድን ሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2000 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተመንግሥት የኦፊሻል አሸናኘት የተደረገለት መሆኑን ሰምተናል፡፡ አርብ ነሐሴ 2 ቀን በሚደረገው የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ በአገሮች (የእንግሊዝኛ) የስም ፊደል ተራ ቅደም ተከተል መሠረት (በኤርትራ) እና በኤስዩንያ መካከል የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ ከ200 የማያንሱ ተካፋይ አገሮች/ግዛቶች አካል ሆኖ ሲተም እናየዋለን፡፡

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የምናየው በዚህ የሁሉም ሰንደቅ ዓላማ በሚታይበት በመክፈቻው ሥነ ስርዓት ላይ ብቻ ስላለ መሆኑ ግን በእጅጉ ተስፋ አለን፡፡ ከላይ ፈጣሪን ከታች አትሌቶችን ይዘን ይህ እንደሚሆን ደግሞ እርግጠኞች ነን፡፡ ከአሁኑ በእርግጠኛነት መናገር የምንችለው አንድ መላው ዓለም የሚያውቀው እውነት አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር ውስጥ የሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን አንድም ታሪክ ስምና ዝና ያላቸው አለዚያም ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ብቻ ካሜራው የሚያተኩርባቸው ኮሜንታተር ጋዜጠኞች ስማቸውን ተረካቸውን እያነሱ የተመልካች ዓይን ልብ እንዳላቸው ደጋግመው በስም የሚጠሯቸው መሆናቸው ነው፡፡ እንደተለመደው አትሌቶቹ የሚሮጡበት የውድድር አደባባይ ሁሉ ኢትዮጵያውያን የሌለበት ቦታ ስለሌለና በጭራሽ ጠፍተው ስለማያውቁ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዚህም ምክንያት ሲውለበለብ ማየታችን የማይቀር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መልካም ፈቃድ ከሆነ እንዲያም ሆኖ ስፖንሰር ነን ተብየዎችና ቴሌቪዥኑ ራሱ በመካከል እየገቡ ዋነኛና ወሳኝ ጊዜ ጥልቅ እያሉ ካላስቸገሩንና ካልረበሹን በስተቀር ከዚህ ሁሉ በላይ ተስፋ የምናደርገውና እርግጠኛ ሆነን የምንጠብቀው ከፍ ያለው ብዙ አገር ይኖራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ብሔራዊ መዝሙሩም እንዲዘመር ከፍ ያለ ተስፋ አለን፡፡ እርግጠኛም ነን፤ አንጠራጠርምም፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በአትሌቶቹ ጥረትና አሸናፊነት ነው፡፡ አትሌቶች ራሳቸው እንደማንኛውም ዜጋ ባንዲራቸው ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ማየት ይወዳሉ፡፡ ደስ ይላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ የተውለበለበበት ብሔራዊ መዝሙሩ ጮህ ብሎ የተዘመረበት አገር ወርቅ በወርቅ በሆነችበት ምክንያት ደግሞ ከእነሱ መካከል በአንዳቸው ወይም በመላው ወይም በሁሉም ምክንያት መሆኑም ከማናችንም በላይ ይበልጥ ያስደስታቸዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ከሩጫና ከሯጭ በላይ በርካታ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡

ኢትዮጵያ የሩጫና የሯጭ አገር ናት፣ ይህንንም ከሮምና ከቶኪዮ ጀምሮ በመላው ዓለም ፊት አስመስክራለች፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በባዶ እግር ጭምር ሮጠው ብቁ ተወዳዳሪነታቸውን ብቻ ሳይሆን የማይበገር አሸናፊነታቸውን አረጋግጠው ያንንም ጠብቀው የዘለቁት፣ በዓለም አደባባይ ከዓለም ምርጥ ሯጮች ጋር ሮጠው ኢንተርናሽናል ሚኒማ አስቀድመው አሟልተው ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ለዓለም የስፖርት ሕግና መዋቅራዊ አደረጃጀት ተገዝተው፣ አክብረውና አስከብረው ነው፡፡ አትሌቶች በክለብ ታቅፈው ክለቦች ፌዴሬሽን መስርተው እያንዳንዱ ፌዴሬሽን በአገር ውስጥ የኦሊምፒክ (ብሔራዊ) ኮሚቴው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የየዘርፉ ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን አባል መሆን ስለቻሉና ሲችሉ ነው፡፡

ወደ ቤጂንግ 29ኛው ኦሊምፒያድ በሚወሰደው መንገድ እና በሂደቱ ውስጥ አንዳንድ "ትንታ"ዎች መከሰታቸው አልቀረም ነበር፡፡ እነዚህ አሁን የመዘንጋታቸውንና የመታለፋቸውን ያህል እውነትም ትንታዎች ብቻ የነበሩ ስለመሆናቸው በእርግጠኛነት መናገር አይቻልም፡፡ አንደኛው "ትንታ" የሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን የቤጂንግ ኦሊምፒክ ተሳትፎ በተመለከተ የተወራው ራሱም በተናገረው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ግልጹንና እርግጠኛውን ጉዳይ አፍረጥርጦ ያወጣው ባይሆንም ኢንተርናሽናል ሚዲያው ከድርሻው በላይ ብዙ አስተጋብቷል፡፡ ከቤጂንግ አዲስ አበባ፣ ከስታዲየም አራት ኪሎ አደራ አስነስቷል፡፡

ከአበበ ቢቄላ ጀምሮ ያሉት አትሌቶች በተሻለ መብት መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ አፍሪካ አትሌቶች ያሰሙትን ድንቅ ንግግር አድምጠናል፡፡ "አፍሪካ ወድቃ ውዳቂ ሆኖ ክንዷን ተንተርሳ በነበረበት በዚያ ወቅት ብቻችሁን ያለማንም እርዳታ ባንዲራዎቹን ያውለበለባችሁ እናንተ ናችሁ" ያሏቸው አትሌቶችን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በጭራሽ ብቻችሁን አይደላችሁም ብለው ካደነቋቸውና ካበረቷቸው አትሌቶች መካከል አንዱ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው፡፡ በዚያው መድረክ ይሁን በሌላ ለጊዜው እርግጠኛ አልሆንኩም እንጂ አቶ መለስ በተለይም ለኃይሌ ለራሱ ያሉት አንድ ሌላ ተጨማሪ ነገር ነበር፡፡ ይህንን የነገረን ራሱ ኃይሌ ለአንድ ሳምንታዊ የአገራችን ጋዜጣ በሰጠው ቃለምልልስ አማካኝነት ነው፡፡ መደበኛ ባልሆነ እግረ መንገዳዊ አነጋገር፣ "እንግዲህ ልጆችህን ይዘህ ቤጂንግ ትሄዳለህ"?" ብለውታል፡፡ በዚህ ምክንያት ይሁን ወይም በሌላ ኃይልም የኦሊምፒክ የልዑካን ቡድናችን አባል ሆኖ ወደ ቤጂንግ ተጓዥ ነው፡፡ አለዚያም ይህ ሁሉ መላምት ነው፡፡ ውሸት ነው፡፡ የኃይሌ የቤጂንግ ጉዞ በራሱ በጥንት በጥዋቱ እቅድ መሠረት የተከናወነ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ አንድ የ"ትንታ" ችግር ፈጥሮ የነበረ ነገር ነው፡፡

ሌላም በጉምጉምታ የተሰማ፣ በጽሑፍም ያየሁት ጋዜጦች ዜና አድርገው አውጥተውት ያነበብኩት "ትንታ" ቢጤ ነገር ነበር፡፡ ይህም ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ ምክንያት ተነሳ የተባለው ግጭት ነው፡፡ እውነትም ሆነ ውሸት አንድ ከፍተኛ ፋይዳ፣ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ዋነኛና ዓይነተኛ ጉዳይ ከበስተጀርባው አለ፡፡ የአትሌቶች መብት የአትሌቶችን መብት በሚመለከት የሚከተሉት ጥያቄዎች የማያወላውልና እርግጠኛ ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ የምልመላ መመዘኛ ቅድመ ሁኔታዎች አግባብ ባለውና ባለመብት ባለሥልጣን የተቋቋሙ ናቸው? እነዚህስ መመዘኛዎች የምልመላው አሠራር ከመጀመሩ በፊት አስቀድመው በጽሑፍ ያሰፈሩት የታወቁ ናቸው? አትሌቶችን በሚመርጠው በብሔራዊው የኦሊምፒክ ኮሚቴና በሚያስተዳድረው የስፖርት ዓይነት ዙሪያ የመመዘኛ ቅድመ ሁኔታዎችን በሚያወጣው ብሔራዊ ፌዴሬሽን መካከል የተደረገ በጽሑፍ የሰፈረ ስምምነትስ አለ? አሰልጣኞች (በተለይም የቲም ባልሆነ ስፖርት ያሉ አሰልጣኞች) በምልመላው/ምርጫው ሥርዓተ ሂደት ውስጥ ሚና አላቸው? የአትሌቶች ቅሬታ የማቅረብ መድን ወይም መፍትሔ ምንድነው? እነዚህ ሁሉ መልስ ማግኘት ያለባቸው መሆኑን የሚሰጣቸውም መዋስ ከኦሊምፒክ ቻርተሩና ሕጐች የሚጣጣም መሆን እንዳለበት የሚወሰነው የበላይም ሆኖ የሚገዛው ራሱ የኦሊምፒኩ ንቅናቄ መርህ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን "ትንታ"ዎች አልፈን አሁን የደረሰንበት የእድገት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እነዚህን "መሰናክሎች" ያለፍነው ራሱ "የሩጫ"ው ህግ በሚፈቅደው መሠረት በማያዳግም ሁኔታ ስለመሆኑ አላውቅም፡፡ እሩጫውን እንደሚያስተዳድረው፣ እሱኑ ራሱንም እንደሚዳኘው ለምሳሌ እንደ "ፍልስ ስታርት" ያለ ግልጽ አሰራር አስተዳደር 2ኛ ስለመኖሩ በእርግጠኛነት መናገር የሚችል አይመስለኝም፡፡

ከእነዚህ የበለጠ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያስከትም ከሚችል የማይወጡበት የአረንቋ ውስጥ አደጋ የተረፍነው ግን ለ"ጥቂት" እና በአጋጣሚ እንዲሁም በ"ኪነጥበቡ" ነው፡፡ የሰይጣን ጆሮ አይስማውና በእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን ላይ የደረሰው ችግር የተጣለው እገዳ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽናችን ቢሆን ኖሮስ? ይህንን ጥያቄ የማቀርበው በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ምትክ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቢሆን ኖሮስ? የምለው በፌዴሬሽኖች መካከል ወይም ተፈጻሚ በሚሆነው የእገዳ ህግ መካከል እጣ ፋንታችን ስላልሆነ ነው፡፡ ያለ እግር ኳስ "የረሳንን ዓለም ረስተን" መኖር ስለምንችል ነው፡፡ የደረሰ ወይም ሊደርስ የሚችል የቅርብ ጊዜ ያንዣበበ አደጋም በዚህ ረገድ አይታየንም፡፡ አትሌቲክስ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በአገራችን የእግር ኳስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል የሚታየው ከአደጋ የሰወረን "አንጻራዊ" ልዩነት ምክንያትም ይኸው ራሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የህጋዊነትና ወይም የህግ የበላይነት "ህዋስ" ከሌላው ፌዴሬሽን የበለጠ ሆኖ ሳይሆን አደጋው አስፈሪ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡

የኦሊምፒክ ቻርተር አንድ ድንጋጌ (ቁጥር 33) እንደሚለው፡፡
To be recognized by NOC and accepted as a member of such NOC, a national federation must exercise a specific and real sports activity be affiliated to an if recognized by the loc and conduct its activities incompliance with both the Olympic Charter and the rules its IF.

በሌላ አነጋገር በኦሊምፒክ ቻርተር ህግ መሠረት የእያንዳንዱ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባላት በአብዛኛው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ማለት ዞሮ ዞሮና ከሁሉ አስቀድሞ የብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ነው ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ (የቀድሞው) የስፖርት (ኮሚሽን) ህግ መሠረት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማለት "በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደንብ መሠረት በስፖርት ፌዴሬሽኖች የተቋቋመ ኮሚቴ ነው" እርግጥ ነው የየትኛውም አገር ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እጅግ በጣም የተለየ/ልዩ የሥልጣን ድርሻ አለው፡፡ ይህም በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ብሔራዊ የልዑካን ቡድን ማቅረብ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአገራችንን ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴን ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሚያቀርባቸው የልዑካን ቡድኑ አባላት አኳያ የተለየ የሚያደርገው የምንካፈልበት የውድድር ዓይነት በሩጫ ላይ የተወሰነ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ሳይሆን ከመላ ጐደል የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ፉት ቦል ፌዴሬሽንን አያቅፍም፡፡ የዚህ ምክንያት በፉት ቦል ከመታገዳችን በፊት ከዚያ ቀደም ብሎ ስላልተሳካልን ስለተሰናከልን ነው፡፡  

መልካም አስተዳዳር ጐድሎናል፣ የኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኑን ህግና ደንብ ውሳኔና ትዕዛዝ አላከበርንም ተብለን የታገድነው አንጸባራቂ ድል በምናስመዘግብበት የስፖርት ዘርፍ ቢሆን ኖሮስ? ወይስ በጭራሽ ሊሆን አይችልም? ሊሆን የማይችለው አንድ ፌዴሬሽን ከሌላው የተለየ የተሻለ ሆኖ? የሕግ የበላይነት ህዋሱ በመዳበሩ? ወይስ "የምቾት ፖለቲካ" ጉዳይ?

እንዲህ ስል የአትሌቲክሱን የስፖርት ዘርፍ የሚመራውና የሚያስተዳድረው ፌዴሬሽን ብፁዕ፣ ብቁ፣ የአሰራርና የተቋም ነጻነት አለው ብሎ ለመመስከር አይደለም፡፡ በጭራሽ፡፡ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና በፌዴሬሽኑ እና በዘርፉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መካከል ያለው ልዩነት በምን ላይ የተመሰረተ ነው? ችግር ውስጥ ከገባው ከሌላው ፌዴሬሽን በምን ይለያል? ለሚሉ ጥያቄዎች መስጠት ያለበት ምላሽ ራሱ አሉ የሚባሉ ችግሮች መቋጫ ምንጮች መካከል አንዱ ነው፡፡

በአገራችን በስፖርት (ኮሚሽን) ህግ መሠረት (1987) የስፖርት ማህበር ማለት የስፖርት ክበብ የኢትዮጵያ አሊምፒክ ኮሚቴ የስፖርት ፌዴሬሽን ማለት ስለሆነ በኢትዮጵያ በስፖርት ማህበራትና በመንግሥት መካከል ያለው ልዩነትና አንድነት ምንድነው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡
 
< Prev   Next >