Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Monday
Sep 08th
Home arrow Sections arrow የቴዲ አፍሮ ጠበቃ ታሠሩ
የቴዲ አፍሮ ጠበቃ ታሠሩ Print E-mail
Wednesday, 06 August 2008
- ፍርድ ቤቱ ዛሬ ውሳኔ ይሰጣል

በታምሩ ጽጌ

የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሠፋ፣ ሐምሌ 19 ቀን 2000 ዓ.ም በወጣው በአዲስ ነገር ጋዜጣ አንደኛ ዓመት ቁጥር 040 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "የፍርድ ቤትን ሥራ አካሄድ በመንቀፍና በመዳፈር" በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ታሰሩ፡፡ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አቶ መስፍን ነጋሽም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእሥር ላይ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከከፍተኛው ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት በተፃፈ ደብዳቤ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋን ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 28 ቀን 2000 ዓ.ም አስሮ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ይታዘዛል፡፡

ኮሚሽኑ በወቅቱ የጋዜጣውን ዋና አዘጋጅ አቶ መስፍን ነጋሽን አግኝቶ አቶ ሚሊዮንን ሳያገኝ በመቅረቱ ያገኘውን ብቻ በመያዝ በዕለቱ ከቀኑ አስር ሰዓት ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ለምን እንደተፈለጉ ካስረዳና ቃላቸውን እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ፣ ፖሊስ ሁለቱንም ተከሳሾች (ሚሊዮንና መስፍንን) ለትናንት ሐምሌ 29 ቀን 2000 ዓ.ም እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ የዕለቱ ችሎት አብቅቷል፡፡

ፖሊስ አቶ መስፍን ነጋሽን ይዞ ወደ ፖሊስ ኮሚሽን ሲመለስ ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋን እዚያው ፖሊስ ጣቢያ እንዳገኛቸውና ሁለቱም ፖሊስ ጣቢያ ማደራቸውን ከፍተኛው ፍርድ ቤት አግኝተን ያነጋገርናቸው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ገልፀውልናል፡፡

ትናንት ሐምሌ 29 ቀን 2000 ዓ.ም ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ጀምሮ በከፍተኛው ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት የሁለቱን (የጠበቃ ሚሊዮንና መስፍንን) የክስ ሂደት ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት ያመሩት የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ ጠበቆች፣ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦችና ባልደረቦች ሲሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ከጠዋቱ 5፡30 ሰዓት ተሰይሟል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ዳኛ አቶ ልዑል ገ/ማርያም 5፡30 ሰዓት ተሰይመው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሐምሌ 28 ቀን 2000 ዓ.ም ቀርበው ቃላቸውን መስጠታቸውን ካስታወሱ በኋላ፣ መዝገቡ የተቀጠረው አቶ ሚሊዮን አሰፋ በጋዜጣው ላይ የሰጡት መግለጫ ላይ ቃላቸውን እንዲሰጡ ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብ መታዘዙን ተናግረው ፖሊስ ማቅረብ አለማቅረቡን ጠይቀዋል፡፡

ፖሊስ ጠበቃ ሚሊዮን አስሮ ማቅረቡን ካረጋገጠ በኋላ ቃላቸውን እንዲያቀርቡ ተጠይቀው በጠበቆቻቸው አማካኝነት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ጠበቃ በመሆን ጠበቃ አበበ አስማረና ጠበቃ ወንድአወክ አየለ የቀረቡ ሲሆን፣ ጠበቃ አበበ በሰጡት ምላሽ፤ "ደንበኛዬ በጋዜጣው ላይ ሁለት ነገር አንስተዋል፡፡ አንደኛው፣ ፍርድ ቤቱ ቴዲ በተከሰሰበት ወንጀል ይከላከል በማለት በሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ እጠይቃለሁ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው፣ ዳኛ ልዑል ገብረማርያምን ለዳኞች አስተዳደር በዲሲፕሊን እከሳለሁ የሚል ነው" ብለዋል፡፡

ጠበቃው ቀጥለው እንደገለፁት፣ "አንድ ተከራካሪ ጠበቃም ሆነ ሌላ አካል ይግባኝ ማለት መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ተከራካሪው ወገን ሳይጠይቀው ፍርድ ቤቱ እራሱ ይግባኝ ማለት ትችላላችሁ ማለት አለበት" በማለት ይግባኝ እላለሁ ማለታቸው "ሊያስከስሳቸው አይገባም" ብለዋል፡፡

"በዳኛው ላይ ያለኝን ቅሬታ ለዳኞች አስተዳደር ዲሲፕሊን ጉባኤ አቀርባለሁ" ማለት፣ ከመብት አንፃር የዲሲፕሊን ቅሬታ ማቅረብ እንደሚቻል የገለፁት የአቶ ሚሊዮን ጠበቃ መግለጫው ማስፈራሪያ፣ ዛቻ ወይም የፍርድ ቤትን የሥራ ሂደት የሚያውክ አለመሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

ደንበኛቸው መግለጫውን የሠጡት ከችሎት ውጪ መሆኑን የገለፁት ጠበቃ አበበ፣ "በዳኛ ላይ ዛቻ አቅርበሃል" እንደማያስብል አስረድተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች እንደተረጋገጠውና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም እንዳረጋገጠው "አንድ ሰው ሃሳቡን የመግለጽ መብት ተሰጥቶታል" ያሉት ጠበቃ አበበ፣ ደንበኛቸው የሰጡት መግለጫ የተፈቀደ መብት መሆኑንና ከችሎት ውጪ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በቀናነት ተመልክቶት በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡

"ዳኛው የዐቃቤ ሕግን ሥራ ተክቶ ነው የሰራው ይላል፤ በጋዜጣው ላይ የተሰጠው መግለጫ፡፡ ይህ ከአንድ የህግ ሰው የሚጠበቅ ነው?" ሲሉ ዳኛ ልዑል ጠይቀዋል፡፡

ጠበቃ አበበ በሰጡት ምላሽ፣ ደንበኛቸው የመናገር መሠረታዊ መብታቸውን ተጠቅመው የራሳቸውን አስተያየት እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡

ዳኛው ቀጥለው ባነሱት ነጥብ "ዐቃቤ ሕግ በተሳሳተ ማስረጃ እየተከራከረ ነው" ብለዋል፡፡ ይህ አባባል ለተከሳሹ የሚጠቅም ነው? ተገቢ አባባልስ ነው?" በማለት በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሹ ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ለፍርድ ቤቱ እንደገለፁት፣ "የሰጠሁት መግለጫ የይግባኝ ነጥቦቼ ናቸው፡፡ ምናልባት ፍርድ ቤቱ ሲመለከታቸው ደካማ ነጥቦች ሆነውበት ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ጠንካራ ነጥቦቼ ናቸው፡፡ በወንጀለኛ ህግ ቁጥር 141 መሠረት ሊቀበለው ወይም ላይቀበለው ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ መስፍን ነጋሽ ሐምሌ 28 ቀን 2000 ዓ.ም ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት መታመማቸውን መግለፃቸውን ተናግረው፣ "አሁንም ስላመመኝ የዋስትና መብቴ ይጠበቅልኝ" በማለት ቢያመለክትም ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ መዝገቡን መርምሮ ዛሬ ውሳኔ እንደሚሰጥ ከገለፀ በኋላ፣ ፖሊሲ ሁለቱንም ታሣሪዎች ጣቢያ አሳድሮ ከጠዋቱ አራት ሰዓት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
 
< Prev   Next >