| የዚምባቡዌ መንግሥትና ተቃዋሚ... |
|
|
| Wednesday, 06 August 2008 | |
|
የዚምባቡዌ መንግሥትና ተቃዋሚ ፓርቲ የጥምር መንግሥት ለመመስረት እየተወያዩ ነው
በዘገባው መሠረት የኘሬዚዳንት ሙጋቤ መንግሥትና የተቃዋሚው ፓርቲ መሪዎች በዚምባቡዌ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የመጨረሻ ዙር ውይይት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ እያካሄዱ ነው፡፡ በዚህም በዚምባቡዌ የተቃዋሚ ፓርቲና በመንግሥት መካከል የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ አዲስ የመንግሥት መዋቅር የሚመሰረትበትን ሁኔታ እያመቻቹ መሆኑ ታውቋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ኘሪቶሪያ ከተማ የገዢው የዛኑ ፒኤፍ ፓርቲና የተቃዋሚው ሙቭመንት ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ ፓርቲ ተወካዮች የስልጣን ክፍፍል በማድረግ አዲስ የመንግሥት መዋቅር ለመመስረት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካው ኘሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውይይት የተሳካ እንዲሆን ጥረት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡ ኘሬዚዳንት ምቤኪ የሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችን በተናጠል አነጋግረዋል፡፡ ኘሬዚዳንቱ ከዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሞርጋን ቻንጋራይ ጋር ባደረጉት ውይይት በዚምባቡዌ የጥምር መንግሥት የሚፈጠርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚጥሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲው አንጃ መሪ አርዙር ሙታምባራ ያለፈው ሳምንት ከኘሬዚዳንት ምቤኪ ጋር ባደረጉት የተናጠል ውይይት ጥምር መንግሥት በመመስረት የዚምባቡዌን የምርጫ ቀውስ ለመፍታት ቃል ገብተዋል፡፡ ኘሬዚዳንት ምቤኪ ከዚምባቡዌው አቻቸው ከኘሬዚዳንት ሙጋቤ ጋር ባደረጉት ተመሳሳይ ውይይት የስልጣን ክፍፍል በማድረግ የምርጫ ግጭቱን ለመፍታት ተስማምተዋል፡፡ ኘሬዚዳንት ምቤኪ ከተቃዋሚ እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ጋር ባደረጉት ውይይት እንዳለው በገዢው ፓርቲና በተቀናቃኝ ፓርቲ ጥምር የተመሰረተውን የፈረንሳይ መንግሥት ዓይነት ለመመስረት አቅደዋል፡፡ በስምምነቱ የጥምር መንግሥቱ የኘሬዚዳንቱንና የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን የመንግሥት ስልጣን በአዲስ መልክ የሚመሰርት መሆኑ ታውቋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ኘሬዚዳንት በዙምባቡዌ የሚፈጠረውን የጥምር መንግሥት ምስረታን በተመለከተ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኘሬዚዳንቱ ምዕራባዊያን በዙምባቡዌ የውስጥ ጉዳይ በመግባት የጥምር መንግሥት ምስረታውን እንዳያፈርሱ አስጠንቅቀዋል፡፡ የፈረንሳዩ ኘሬዚዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ የኘሬዚዳንት ምቤኪን አደራዳሪነት አድንቀዋል፡፡ ኘሬዚዳንት ሳርኮዚ "የአውሮፓ ህብረት ኘሬዚዳንት ምቤኪ በዚምባቡዌ የጥምር መንግሥት ለመመስረት የጀመሩትን ጥረት ይደግፋል" ብለዋል፡፡ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን በኘሬዚዳንት ምቤኪ አደራዳሪነት የተጀመረው የጥምር መንግሥት ምስረታ ለዚምባቡዌ ግጭት ብቸኛ አማራጭ መፍትሔ መሆኑን ዘግበዋል፡፡ በጥምር መንግሥቱ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን የስልጣን ማዕረግ ቻንጋራይ እንደሚይዙት ተገምቷል፡፡ በጥምር መንግሥቱ የኘሬዚዳንትና የጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም ሶስት የምክትል ኘሬዚዳንት የስልጣን ማዕረግ እንሚኖር ታውቋል፡፡ በዚህም የተቃዋሚው ፓርቲ አንጃ መሪ ሙታምባራ የምክትል ኘሬዚዳንትነት ቦታ ሊይዙ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡ የፈረንሳይ መንግሥት አወቃቀር ቅጂ እንደሆነ በሚነገርለት የዚምባቡዌ የመንግሥት መዋቅር ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡ በዚህም የዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ቶኮዛኒ ኩፔና የገዢው ፓርቲ አባልና የሙጋቤ ታማኝ ኢመርሰን ማንጋዋ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ተገምቷል፡፡ በድርድሩ ሞርጋን ቻንጋራይ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለመያዝ ፍላጐት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ቻንጋራይ ኘሬዚዳንት ሙጋቤ የሀገሪቱ የክብር ኘሬዚዳንት እንዲሆኑና በሀገሪቱ የፓርላማ የመንግሥት መዋቅር እንዲዘረጋ አሳስበዋል፡፡ የገዢው ፓርቲ ተወካዮች በበኩላቸው በኘሬዚዳንት ሙጋቤ የስልጣን ወሰን ላይ የማይደራደሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ከተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ነገር ግን ውዝግቡ መብረዱን የደቡብ አፍሪካ የመረጃ ምንጮችን በመጥቀስ ዘገባው አትቷል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው ድርድር ከተጠናቀቀ ኘሬዚዳንት ሙጋቤ የሚኒስትሮች ካቤኔና ጠቅላይ ሚኒስትሮችን እንደሚሰይሙ ይጠበቃል፡፡ በዚህም የመንግሥት ስልጣን ድርሻ ከገዢው ፓርቲ ይልቅ ተቃዋሚዎች በይበልጥ የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ እንደሚኖር ታውቋል፡፡ ድርድሩ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በዚምባቡዌ አዲስ የጥምር መንግሥት በተሳካ ሁኔታ እንደሚመሰረት አስታውቀዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1998 እስከ 2000 ድረስ በዚምባቡዌ የጥምር መንግሥት ተመስርቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተያያዘ ዜና የደቡብ አፍሪካ ሀገራት የልማት ማህበረተሰብ አባል ሀገራት የዚምባቡዌ ፓርቲዎች የስልጣን ክፍፍል ስምምነት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ አባል ሀገራቱ በጋራ ባስተላለፉት መልዕክት በደቡብ አፍሪካ አደራዳሪነት የተጀመረው የስልጣን ክፍፍል ውይይት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል፡፡ በሌላ በኩል የቦትስዋና መንግሥት በበኩሉ ኘሬዚዳንት ሙጋቤ በአባል ሀገራቱ ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ አሳስቧል፡፡ የሀገሪቱ ኘሬዚዳንት "ኘሬዚዳንት ሙጋቤ በመጪው የአባል ሀገራቱ ስብሰባ ላይ የሚገኙ ከሆነ ቦትስዋና በስብሰባው ላይ አትገኝም" በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |