| መፍትሄው - "ድርድር" አለዚያም "ጦርነት" |
|
|
| Wednesday, 06 August 2008 | |
በጌታቸው ንጋቱየኢትዮ-ኤርትራ ድንበር የሠላም አስከባሪ ኃይል (አንሚ) መነሳቱን ተከትሎ የተለያዩና የተደባለቁ አስተያየቶች እየተሠነዘሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመውሰዱ ወቅሶታል፡፡ ሁሉም ወገኖች ድርድር፣ ንግግርና ውይይት ያስፈልጋል ሲሉ ኤርትራ የማይታሰብ እያለች ነው፡፡ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ከፈፀመችበት ግንቦት 199ዐ ዓ.ም. እስካለፈው ሳምንት ድረስ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል፣ ሲያደራድርና የሠላም ማስከበር ሥራ ሲሰራ የከረመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጉዳዩ መውጣቱን ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች የተለያየ አስተያየት እየሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ጉዳይ ወደ ጦርነት ያመራል ከሚሉ እስከ ምንም ዓይነት ለውጥ አይፈጠርም፤ ጦርነት አይኖርም እስከሚለው ድረስ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታው ምክር ቤት አንሚን አላሰራ በማለት አዋርዳ ያስወጣችው ኤርትራን ባለመቅጣቱ እየወቀሰ ኤርትራም የአልጀርሱን የሠላም ስምምነት መጣሷን ይገልፃል፡፡ የሆነው ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነት እንደማይፈልግና የኤርትራ መንግሥት ወደ ሰላማዊ ውይይት ድርድር መምጣት እንደሚኖርበት ያስረዳል፡፡ ድርድርና ውይይት በሌለበት ሰላምና ልማት እንደማይኖር የገለፀው የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ያለውን የድንበር ችግር ለመፍታት ያለው ብቸኛ አማራጭ መደራደርና መነጋገር ብቻ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ ውይይትና ድርድር በሌለበት ጦርነትና አለመረጋጋት ሁልጊዜ እንደሚከሰት የገለፀው የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላትም ኤርትራ የያዘችው አካሄድ ለአገሪቱም ሆነ፣ ለአካባቢው ሰላምና ልማት አስቸጋሪ ሁኔታ በመፍጠሩ ወደ ድርድር እንድትመጣ እንዲያደርጉ እየጠየቀ ይገኛል፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሠላም ማስከበር ሥራ ትቶ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ያለውን የድንበር ችግር ለመፍታት የሁለቱ አገራት መንግሥታት መነጋገርና መስማማት አለባቸው ይላል፡፡ "ተነጋግሮና ተደራድሮ ለመግባባትና ችግራቸውን ለመፍታት ሁለቱ አገራት አያንሱም" የሚሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባንኪሙን የመንግሥታቱ ድርጅት አገራቱ ችግራቸውን ለመፍታት ዝግጁ በሆኑበት በማንኛውም ወቅት አብሯቸው ሊሰራ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አገሪቱ የአልጀርሱን ስምምነት እንዲያከብሩና ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ጥሪ አቅርበው መፍትሄው ድርድርና ውይይት ብቻ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩኘ በተደጋጋሚ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ እንደሚያሳስበው መግለጫ ሲያወጣ የከረመ ሲሆን የፀጥታው ምክር ቤት የሰላም አስከባሪ ኃይሉን ከኢትዮ-ኤርትራ ለማስወጣት መወሰኑን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ አሁን ያለው ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ሌላ ጦርነት ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ አገራቱ ወደ ጦርነት ሊወስዳቸው ከሚችሉ እርምጃዎች እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡ ሁለቱም አገሮች እ.ኤ.አ በ2000 የፈረሙት የአልጀርሱን ስምምነት እንዲያከብሩ ጥሪ ያቀረበው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩኘ ስምምነቱ ካልተከበረ በአፍሪካ ቀንድ ሊደርስ ስለሚችለው አስከፊ ጦርነትና ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ያለውን ስጋት ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታትም በመሃከላቸው ያለውን ግጭትና የድንበር ችግር ለመፍታት ቀርበው መነጋገርና መደራደር እነደሚኖርባቸው ድርጅቱ አክሎ ገልጿል፡፡ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ያለበት ሁኔታ ጦርነት ሊሸከም የሚችል እንዳልሆነም ተገልጿል፡፡ ሁለቱም አገራት ወደ ጦርነት መሄድ እንደማይፈልጉ ፍላጐታቸውን እያሳወቁ የሚገኙ ከሆነ ጦርነትን ማስቀረት የሚቻለው በድርድርና በንግግር መሆኑን ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩኘ ገልጿል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ኘሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አሁን ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም አስከባሪ ኃይል ከድንበር አካባቢ ለቆ ቢወጣም የግድ ጦርነት ይነሳል የሚል ስጋት እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡ "አንሚ በአካባቢው መኖሩ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ለመረዳት ያስችላል እንጂ በራሱ ጦርነት አይከላከልም፡፡ ሁለቱ አገራት ያለባቸውን ችግር ሊፈቱ የሚችሉት ሁለቱ መንግሥታት ብቻ ናቸው" ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ሁለቱም መንግሥታት አልጀርስ ላይ የፈረሙትን ስምምነት ማክበርና ማስፈፀም እንደሚኖርባቸው ገልፀዋል፡፡ "የአንሚ ቆይታ በዚህ ዓይነት መንገድ ማለቁ ጥሩ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ የሰላም አስከባሪ የለም ብሎ ወደ ጦርነት መግባት እብደት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ጦርነትና ውጊያ ባይኖርም ሰላምም የለም፡፡ ይህ ደግሞ የአገራቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየጐዳ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት መበላሽትም በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አለመረጋጋቶች እንዲባባሱና እንዳይፈቱ እያደረገ ነው" የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ አሁን ያለው ችግር ሊፈታ የሚችለው በድርድር ብቻ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ "የተባበሩት መንግሥታት አሁንም አገራቱ ለድርድር ዝግጁ ከሆኑ እንደሚያደራድር ገልጿል፡፡ አሁን የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት አደራድሩን፤ ችግራችንን በውይይት እንፈታለን ማለት አለባቸው" ያሉት ዶ/ር ነጋሶ እስካሁን ለአሥር ዓመታት ያህል የድንበር ችግሩ ሳይፈታ የቆየው ሁለቱ መንግሥታት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ "መንግሥታቱ ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ አገራቱ ጦርነት ለማስተናገድ የሚሆን አቅም የላቸውም፡፡ በመሆኑም ችግሩን በድርድርና በውይይት ለመፍታት መሞከር እንጂ ከዚህ ውጭ አማራጭ የለም፡፡ ጦርነትም የሚታሰብ መሆን የለበትም" በማለት ዶ/ር ነጋሶ አሁን ያለው ውጥረት ተለውጦ ሠላም ስለሚሰፍንበት ሁኔታ ያስረዳሉ፡፡ የኢዴአፓ መድህን ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "አገራቱ ወደ ድርድርና ንግግር መምጣት አለባቸው፡፡ ጦርነት በማናቸውም መንገድ ተመራጭ አይደለም" ሲሉ የሠላም አስከባሪው በመውጣቱ ግጭት እንደማይቀሰቅስና አገራቱ ጦርነት የሚፈልጉ ቢሆን እስካሁን ድረስ ሊዋጉ ይቻሉ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ "የአንሚ መነሳት መልቀቅ በአካባቢው ያለውን ውጥረት ያሳስሰው ይሆናል፡፡ አንሚ ቢኖር አገራቱ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ሪፖርት ሊያደርግ ይችላል" የሚሉት አቶ ልደቱ ጦርነት በማምጣትና በማስቀረት በኩል ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደማይኖረው ይገልፃሉ፡፡ አንሚ በስምንት ዓመታት የሠላም ማስከበር ሥራው ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፈንጂዎች ያመከነ ሲሆን በድንበር አካባቢ ላሉ የሁለቱ አገር ዜጐች የመጠጥ ውሃ ሲያቀርብና የጤና እንክብካቤም ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይህንን በጐ የአንሚ አገልግሎት አሁን የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ ነዋሪዎች አጥተውታል፡፡ "እኛ ከአልጀርሱ ስምምነት ጀምሮ ተቃውሞ ነበረን፡፡ ተቃውሟችንንም በወቅቱ ገልፀናል፡፡ የአልጀርስ ስምምነት ላይ የተፈፀመው ስህተት ነው አሁን ያለንበት ደረጃ ያደረሰን" የሚሉት አቶ ልደቱ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታትና ለአስር ዓመታት የዘለቀው አለመግባባት ወደ ጦርነት እንዳያመራ ውይይትና ድርድር እንደሚያስፈልግ፣ ከድርድርና ከንግግር ውጭ ምንም ዓይነት መፍትሄ እንደሌለና የሁለቱ አገራት መንግሥታትም ወደ ሠላማዊ ንግግርና ድርድር መምጣት አለባቸው ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን አቶ ልደቱ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት ኘሬዚዳንት ኘሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው የአንሚ መውጣት የተለየ ነገር እንደማይፈጥርና ጦርነት እንደማይከሰት ያላቸው ተስፋ ያስቀምጣሉ፡፡ ጦርነት አይኖርም ተብሎ መዘናጋት እንደማይገባ የገለፁት ኘ/ር በየነ መንግሥት የአገሪቱን የድንበር አጠባበቅ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለውና ለዓመታት የዘለቀው የሁለቱ አገራት ያለመግባባት ሊፈታና ሊቋጭ የሚችለው በውይይትና በድርድር ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ የተለያዩ ወገኖች እየመከሩና እየጐተጐቱ ቢሆንም ኤርትራ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከጅቡቲ ጋር የጀመረችው አተካሮ በአካባቢው ጦርነት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የማይቀር መሆኑን የሚያመላክት ነው እየተባለ ይገኛል፡፡ ኤርትራ ከጅቡቲ ጋር የጀመረችው ግጭት ፈረንሳይንና በጅቡቲ የጦር ኃይል ያላትን አሜሪካን እንዲሁም የጅቡቲ ወደብን የምትጠቀመውን ኢትዮጵያን ጭምር አስቆጥቷል፡፡ የኢሳያስ አስተዳደር ከውጭም ሆነ ከውስጥ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ወደ ጦርነት ለመግባት እንደማይፈራም የሚያስረዱ አሉ፡፡ አንድ የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ እንደሚናገሩት ግን አሁን ያሉ ሁኔታዎች ለድርድር እና ለንግግር አመቺ እና ተስፋ ሰጪ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ከምትደራደር የኤርትራን አስተዳደር ተዋግታ እንድታስወግድላቸው የሚፈልጉ ኃይሎች በመኖራቸው በአፍሪካ ቀንድ በቅርቡ አንድ ጦርነት እንደሚኖርና ይህም የኢሳያስ አስተዳደር ማብቂያ እንደሚሆን ያመለክታሉ፡፡ "ለእኔ የኤርትራ መንግሥት የመጨረሻ ሠዓቱ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ የአንሚ መውጣት፣ የኤርትራ ተቃዋሚዎች መጠናከርና ኢሳያስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተቀባይንት ማነስ የመደራደር አቅማቸውን የጐዳው ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከመደራደርና ጉዳዩን ክፍት አድርጐ ከማቆየት አጭርና ውጤታማ ጦርነት ማድረግ ይመርጥ ይሆናል" የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ኢሳያስም ይህንን ነገር ስለሚገነዘቡት የሞት ሽረት ጦርነት ውስጥ ሲገቡ እንደሚችሉ የሚያስቡት እኝሁ ግለሰብ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ ጦርነት ቢካሄድ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት በሕዝብ ላይና በገራቱ ላይ የማይቀር መሆኑን ሲገልፁ ጦርነት አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ሰይጣን (necessary evil) ነው ተብሎ ስለሚታሰብ አገራቱ ወደዚህ እርምጃ ያመራሉ ብለው እንደሚጠብቁ ይገልፃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረው ግንኙነት መጨረሻው ሳይለይለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ የድንበሩን ግጭት ለመፍታት ድርድር የግድ ነው ስትል፤ ኤርትራ በፍፁም ድርድር አይኖርም ትላለች፡፡ ጦርነት እንደማትፈልግና ድርድርም እንደማትቀመጥ የምትገልፀው ኤርትራ የኢትዮጵያን መንግሥት ሉዓላዊ ግዛቷን ለቅቆ እንዲወጣላት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እየጠየቀች ትገኛለች፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ ባድመን ለኤርትራ እንደሰጠ የሚገልፀው የኤርትራ መንግሥት ምዕራባዊያን አገራት የዓለም አቀፍ ሕግ እንዳይከበር ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ይገልፃሉ፡፡ ሁለቱ አገራት ወደ ውይይት፣ ንግግርና ድርድር ይመጣሉ ወይስ ወደ ጦርነት ይሄዳሉ? ጦርነት ይኖራል፤ አይኖርም የሚለው ጉዳይ ግን ቀን የሚፈታው የአፍሪካ ቀንድ አገሪቱና የሕዝባቸው ጥያቄ ሆኖ ይቆያል፡፡ የሁለቱ አገራት የድንበር አለመስማማትና ግጭት የሁለቱ አገራት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሌሎች የአካባቢው አገራት እንዲሁም ዓለም አቀፍ አንደምታ ያለው መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአፍሪካ ቀንድ ባለሙያ ሲገልፁ "ከሁለቱ መንግሥታት አንዳቸው መነሳት አለባቸው፡፡ ችግሩን በድርድርና በውይይት መፍታት መልካም ቢሆንም ሁለቱ መንግሥታት የሚደራደሩና የሚነጋገሩ እንዳልሆኑ ይገባኛል፡፡ ጦርነቱ በእርግጥ የኤርትራን መንግሥት የሚያዋጣ አይደለም፡፡ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ግን የዓለም አቀፍ ድጋፍም ሆነ የኃይል ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ ስለሚያመዝን የኤርትራ መንግሥት ብዙም ተስፋ አይኖረውም" በማለት ያስረዳሉ፡፡ ኢሳይያስ አፈወርቂም በከፍተኛ የውስጥ ፖለቲካ መፈራረስ ወስጥ ስላሉ ወደ ወረራ (frustration-aggression) በመግባት የመንግሥታቸውን ፍፃሜ እንደሚያቀርቡ የሚገልፁት ባለሙያው ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ጥቅሟ የሚያስፈልጉትን የድንበርና የወደብ ጥያቄዎች ለመመለስ ጦርነትን እንደመጨረሻም አማራጭ ቢሆን ልታየው እንደምትችል እና በኤርትራ አዲስ መንግሥት ተቋቁሞ ኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ እንዲመለስ እንዲያደርግ ትፈልጋለች የሚል ግምት እንዳላቸው አስተያየት ሰጪው ጨምረው ይናገራሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |