Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow የግጭት አፈታት በቦረናና በገብራ
የግጭት አፈታት በቦረናና በገብራ Print E-mail
Wednesday, 06 August 2008

Imageበሔኖክ ያሬድ

ኢትዮጵያ በርካታ ብሔረሰቦች የሚኖሩባትና የየራሳቸው መለያ የያዙ ባህላዊ ሥርዓቶች፣ ታሪክና ቋንቋ አላቸው፡፡ ከአነዚህ ሥርዓቶች መካከል አንዱ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው፡፡

 

የአገሪቱን ረቂቅ ወይም ግዙፍ ያልሆኑ (ኢንታንጀብል) ቅርሶችና ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶች ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ በመሥራት ላይ የሚገኘው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በቅርቡ ካጠናቸው መካከል አንዱ በገብራና በቦረና መካከል ያለው ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ስንሻው የባህላዊ አንትሮፖሎጂ መምሪያ ኃላፊ መግለጫ የቦረና ኦሮሞ በደቡብ ኢትዮጵያና በሰሜን ምዕራብ ኬንያ ይኖራል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖሩት ቦረናዎች በኦሮሚያ ክልል ባሉት የቦረናና ጉጅ ዞኖች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የቦረና ሽማግሌዎች እንደገለፁት፣ አካባቢው የኦሮሞ ታሪክና ባህል መፍለቂያ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ የእስልምናና ክርስትና እምነት ተከታዮች ቢኖሩም ብዙኃኑ ቦረና በራሱ የእምነት ሥርዓት በአንድ ዋቃ የሚያምን ነው፡፡ የቦረና ሕዝብ ለበርካታ ምዕት ዓመታት ሥራ ላይ የዋለ የገዳ አስተዳደር ሥርዓት ያለው ሲሆን፣ የሥርዓቱ መሪ አባ ገዳ በየስምንት ዓመቱ ይመረጣሉ፡፡

ገብራዎች በደቡብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ይኖራሉ፡፡ በቦረና ዞንና በሶማሌ ክልል በሊበን ዞን ስር የሚኖሩት ገብራዎች  በተበታተነ ሁኔታ የሰፈሩ ናቸው፡፡
ምጣኔ ሀብታቸው በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ የግመል እርባታ ዋናው የኢኮኖሚ መሠረት ነው፡፡ አቶ ጌታቸው እንደገለፁት በገብራ አራት ዓይነት ግመሎች አሉ፡፡ እነርሱም የግርዛት ግመል፣ የጥሎሽ ግመል፣ ከሌሎች የተዘረፈ ግመልና የተገዛ ግመል ናቸው፡፡ ግመልና ከብት በገብራዎች ሕዝብ ዘንድ ከኢኮኖሚ በተጨማሪ ማኅበራዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ለግጭት ካሳ፣ ለሠርግ ጥሎሽና ለማኅበራዊ ግንኙነት ማጠናከሪያነት ያገለግላሉ፡፡

በሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙት ገበሬዎች እንደሚያስረዱት የገብራ ሕዝብ የራሱ ባህላዊ አስተዳደር እንዳለውና በመሃሉ በቦረና ተጽዕኖ ከገዳ ሥርዓት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት መተዳደሩን ይገልፃሉ፡፡ በራሱ ባህላዊ አስተዳደር የሚተዳደር ሲሆን፣ መሪውም ከኢትዮጵያና ከኬንያ በተውጣጡ ወደ 10"000 በሚጠጋ ሕዝብ የተመረጡ ናቸው፡፡ መሪው ታሊያ የሚባል ማዕርግ ያላቸው ሲሆን፣ 13ቱ የገብራ ጎሳዎች እያንዳንዳቸው 3 በድምሩ 39 ምክትል ታሊያዎችና አማካሪዎች አሏቸው፡፡

ቦረናና ገብራዎች ለበርካታ ዓመታት አብረው በመኖራቸው አንድ ቋንቋ ቢናገሩም የእምነት፣ የአኗኗርም ሆነ የዘር ግንኙነት የላቸውም፡፡ ሁለቱም ማንነታቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ናቸው፡፡

የቦረና ኦሮሞዎች በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳያቸውን በባህላዊ አስተዳደራቸው ይወያያሉ፡፡ ለችግሮቻቸው በባህላዊ መንገድ መፍትሔ ይሰጣሉ፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች እንዲሁም የውሃና የግጦሽ መሬት አጠቃቀምን በተመለከቱ ሕጎች አሏቸው፡፡ ሕጎቹ ያልተፃፉና በቃል የሚተላለፉ ሲሆኑ አንድ ገዳ ስልጣን ከተረከበ በአራተኛው ዓመት ጎሜጋዮ (ስብሰባ) ተደርጎ የሚሻሻሉና የሚጨመሩ ሕጎች ተስተካክለው በቃል እንደሚተላለፉ አቶ ጌታቸው ያብራራሉ፡፡

ለምሳሌ የሚሸሽን ሰው የገደለና ወገኑ የሆነውን ቦረና የደበደበ ይቀጣል፡፡ ሚስቱን ደብድቦ የገደለ እንዲሁም ቦረና ቦረናን አይገልም የሚለውን ሕግ ጥሶ ሆን ብሎ የገደለ በሞት ይቀጣል፡፡ ነገር ግን ገዳዩ ሟችን በስህተት የገደለው ከሆነ መጀመሪያ በአገር ሽማግሌዎች ይጣራል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ግድያው በስህተት መሆኑን ካረጋገጡ የገዳይ ወገን ለሟች ወገን 30 ከብት ካሳ እንዲከፍል በማድረግ በሁለቱ ወገኖች መካከል ቅራኔ እንዳይኖር ያደርጋሉ፡፡ የገዳይ ወገን ካሳውን የመክፈል አቅም እንደሌለው ሽማግሌዎች ከተገነዘቡ ሌሎች ጥቃቅን ነገሮችን አብረው በመቁጠር 30 እንዲሞላ አድርገው በሟችና በገዳይ ወገን መካከል እርቅ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ባህላዊ ስርዓትም ቅራኔ እንዳይስፋፋ በማድረግ በብሔረሰቡ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡  

ይህ ስርዓት ቦረና ውስጥ ብቻ ሳይሆን ቦረና ከጉጅ፣ ቦረና ከአርሲ እንዲሁም ቦረና ከገብራ ወዘተ. ሲገዳደል ጭምር የሚፈጸም ስርዓት ነው፡፡ በመሆኑም በግለሰብ መካከል የተፈጠረ መገዳደል ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግጭት እንዳያመራ የሚያደርግ ስርዓት ነው፡፡

የቦረና ኦሮሞ ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር በተለይም ከጉጅና ከአርሲ ኦሮሞዎች ጋር ሲጋጭ በባሕላዊ የእርቅ ስርዓት ችግሩን ሲፈታ ኖሯል፡፡ ለምሳሌ በቦረናና በአርሲ ወይም በቦረናና በጉጅ መካከል ግጭት ከተፈጠረ ግጭቱ እንዲቆም አስቀድሞ የፈለገው አካል አንድ ባህላዊ ልብስ የለበሰና ሊቾ (አለንጋ"ና በግ የያዘ ሽማግሌ ወደ ተቃራኒው ወገን ይልካል፡፡ የተቃራኒው ወገንም ሽማግሌውንና የሰላም ጥሪውን በመቀበል ለሽማግሌው ክብር ይታረዳል፡፡ እንዲሁም ቡና ይፈላል፡፡ የሰላም መልዕክተኛውም ጉዳዩን ለተቃራኒው ወገን በተብራራና ግልጽ በሆነ መንገድ ያስረዳል፡፡ የተቃራኒው ወገን ሽማግሌዎችም በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ ለመልዕክተኛው ቀጠሮ በመስጠት ይሸፍታል፡፡

በቀጠሮው ቀንና ቦታ ሁለቱም ወገኖች ተገናኝተው የግጭቱን መንስኤ በሰከነ መንፈስ ይወያያሉ፡፡ ጥፋተኛው ጥፋቱን ካመነ በኋላ የጋራ ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ ከዚህ በመቀጠል አካላቸው ያልጎደለ የእርቅ ከብቶች ይቀርባሉ፡፡ የአገር ሽማግሌዎችም ከብቶቹን እየዳሰሱና ሊቾ (አለንጋ) በከብቶች ጀርባ ላይ በማድረግ "ለዚህ ከብት መታረድ ምክንያት የሆነውን ሰላም አምጣልን" በማለት ይመርቃሉ፡፡ ከምርቃቱ በኋላ ከብቶች ታርደው ሁለቱም ወገኖች አብረው ይበላሉ፡፡ የከብቶቹ ቆዳም በቀጭኑ ተልትለው (መደቻ) እጃቸው ላይ ያስራሉ፡፡ መደቻ የእርቅ ተምሳሌት ሲሆን፣ እንደ ግለሰቦች ፍላጎት ለተወሰኑ ቀናት እጃቸው ላይ ያስሩታል፡፡ ይህ ስርዓት በቦረና፣ በጉጅና በአርሲ መካከል የሚደረግ ሲሆን፣ በሕዝቦች መካከል ያለው ግጭትና ቅራኔ እንዳይሰፋ በማድረግ በመካከላቸው ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

እንደ ቦረና ኦሮሞ ሁሉ የገብራዎች ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት እንዳለው ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፣ በሶማሌ ክልል የሚገኙ ገብራዎች እንዳስረዷቸው በታሊያ የሚመራ ባህላዊ አስተዳደር አላቸው፡፡ በገብራ ውስጥ የሚከሰትም ሆነ በገብራና በሌላው ብሔረሰብ መካከል ያለ ችግር በአመዛኙ በባህላዊ መንገድ እንደሚፈታ ያስረዳሉ፡፡

ለምሳሌ አንድ ገብራ ሌላውን ገብራ በድብደባ ቢጎዳው መጀመሪያ ማቀዝቀዣ ተብሎ 10 ብር ወይም ቱስባ (መቁጠሪያ) ለተበዳይ ወገን ይሰጣል፡፡ በመቀጠልም ሽማግሌዎች ተወያይተው እንደ ጥፋቱ መጠን ጥፋተኛው እስከ 15 ግመል ቅጣት እንዲከፍል ያደርጋሉ፡፡ አንድ ገብራ ሌላውን ገብራ አይገልም፡፡ አንድ ገብራ ሌላውን ገብራ ከገደለ ጉዳዩ በሽማግሌዎች ከተመረመረ በኋላ ግድያው ሆን ተብሎ የተፈፀመ ከሆነ ገዳይ በሞት ይቀጣል፡፡ ነገር ግን ግድያው በስህተት የተፈጸመ ከሆነ ገዳይ ለሟች ወገን እስከ 30 ግመል እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ የሁለቱ ወገን ጎሳዎች ካሳ የማይቀባበሉ (የማይበላሉ) ከሆነ ጉዳዩ በድርድር እልባት ይሰጡታል፡፡ በገብራና በገሪ መካከልም ግድያና ድብደባ ከተፈፀመ በተመሳሳይ ሁኔታ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ያቤሎ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ገብራዎች እንደሚያስረዱት፣ አንድ ገብራ ሌላውን ገብራ በስህተት ቢገል መጀመሪያ የገዳይ ወገን ሟች ቀብር ላይ የሚያስፈልገውን ያርዳል፡፡ በመቀጠል የአገር ሽማግሌዎች ተሰባስበው በጉዳዩ ከመከሩ በኋላ ግድያው በስህተት የተፈፀመ ከሆነ የገዳይ ወገን ለሟች ወገን 30 ከብት እንዲሰጥ ይወስናሉ፡፡ ይሁንና የሚከፈለውን ከብት የገዳይ ጎሳ ስለሚያዋጣ ከጎሳው ተብሎ የተወሰነ እንዲሁም ለሽማግሌዎች ተብሎ የተወሰነ ከብት ከተቀነሰ በኋላ ቀሪው ለሟች ወገን ይሰጣል፡፡ ይህ ስርዓት በተመሳሳይ ሁኔታ በአንድ ቦረናና ገብራ ወይም በገብራ ጉጅ መካከል ግድያ ከተካሄደ ተፈፃሚ እንደሚሆን ሱርፃ አካባቢ የሚኖሩ የገብራ ሽማግሌዎች እንዳስረዷቸው አጥኚው ገልፀዋል፡፡

ገብራና ቦረና ኦሮምኛ ተናጋሪ ሲሆኑ ለበርካታ ምዕት ዓመታት በሰላም የኖሩ ናቸው፡፡ ከዚህም በመነሳት ገብራ ቦረና እየተባሉ ለረጅም ዓመታት ሲጠሩ ኖረዋል፡፡ ገብራዎች የገዳ ሥርዓትን በተጽዕኖ ለተወሰነ ጊዜ የተቀበልነው ሥርዓት ነው ቢሉም ቦረናዎች በበኩላቸው ገብራዎች በገዳ ሥርዓት ይተዳደሩ በነበረበት ወቅት ሁለቱ ሕዝቦች በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ መኖር እንደቻሉና ችግሮቻቸውን በገዳ ሥርዓት የመፍታት እድሉ ሰፊ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ሕዝቦች በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን አንድ ቡሳ ጎንፎ (እርስ በእርስ የመረዳዳት) ሥርዓት ውስጥ ስለነበሩ ቦረና ሲቸገር ገብራ ይረዳል፤ ገብራ ሲቸገር ቦረና ይረዳ እንደነበረ መረጃ ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡

የሁለቱም ምጣኔ ሀብት የተመሰረተው በእንስሳት እርባታ ቢሆንም ቦረናዎች በከብት እርባታ ላይ እንዲሁም ገብራዎች በግመል እርባታ ላይ በማተኮራቸው የግመሎች የውሃ ፍላጎት ዝቅተኛ በመሆኑ ሁለቱም በአንድ ኤላ ከብቶቻቸውን ሲያጠጡ ኖረዋል፡፡
የቦረና ኦሮሞ አንፃራዊ በሆነ መንገድ ከአርሲና ከጉጅ ጋር በግጦሽ፣ በውሃና በግለሰቦች ምክንያት በርካታ ግጭቶች ደርሰዋል፡፡ በእነዚህ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭቶች ጦርነት አስፈላጊ አለመሆኑን የተገነዘበው ወገን ሊቾ (አለንጋ"ና በግ ለሽማግሌ በመላክ እርቅ ይጠይቃል፡፡ በጉዳዩ የሁለቱ ወገን ሽማግሌዎችና መሪዎች በበቂ ከተወያዩበትና ከተስማሙ በኋላ እርቅ ይወርዳል፡፡ ሰላም እንዲሆን በአንጋፋዎች ተመርቆ ከብቶች ይታረዳሉ፡፡ ሁለቱም ወገኖች አብረው ከበሉ በኋላ ቆዳው ተተልትሎ መዲቻ (የሰላም ምልክት) ይደረጋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ገብራዎች በባህል፣ በዘርና በሃይማኖት ከሚዛመዷቸው ገሪዎች ጋር በከብት መዘራረፍና በተለያዩ ምክንያቶች ይጋጩ እንደነበርና ግጭቱን በባህላዊ የእርቅ ስርዓታቸው እንደሚፈቱት መረጃ ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡

  በአቶ ጌታቸው ጥናታዊ ማጠቃለያ ሐሳብ መሠረት ሁለቱ በግለሰብ ደረጃ የሚነሱ ቅራኔዎችን በባህላዊ መንገድ በመፍታትና ወደ ማኅበረሰብ ግጭት እንዳያመሩ በማድረግ ለበርካታ ዓመታት በሰላም ኖረዋል፡፡

የገብራ የአገር ሽማግሌዎች የገዳ ሥርዓትን በተጽዕኖ እንደተቀበሉት ቢገልጹም ሁለቱም በራሳቸው የገዳ ሥርዓት መተዳደራቸው በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉን የቦረና የአገር ሽማግሌዎች ያስረዳሉ፡፡

በገብራና በቦረና መካከል ተቃርኖና ግጭት የተጀመረው በሕዝቦቹ ፍላጎት ሳይሆን በውጭ ኃይላት ግፊት ነው፡፡ በጥቅም ምክንያት የተነሳው ተቃርኖ በአግባቡ ባለመያዙና ባለመፈታቱ ወደ ውጥረት ከፍ ሲልም ወደ ግጭት በማምራት ለሰውና ንብረት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ግጭቶች በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የቆሙና ከሁለቱም ወገን የተውጣጡ አካላት የተወያዩበት ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር በመሆኗ በፌዴራል መንግሥት በኩል የግጭት አፈታት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አቶ ጌታቸው አስምረውበታል፡፡

የባህላዊ እሴቶች እየላሉ መምጣት ለችግሮቹ መባባስ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው የአገር ሽማግሌዎች ለወጣቱ ትውልድ ባህላዊ የእርቅ ሥርዓቶችንና እሴቶችን እንዲጠብቅ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡
 
< Prev   Next >