| ኢትዮጵያና ግብፅ፤ ሆድና ጀርባ |
|
|
| Wednesday, 06 August 2008 | |
በጌታቸው ንጋቱሠሞኑን 16ኛው የአባይ ተፋሰስ አገራት የጋራ ስብሰባ በዴሞክራቲክ ኮንጐ፣ ኪንሻሳ ተካሂዷል፡፡ ግብፅ አሁንም በአባይ አጠቃቀም ዙሪያ ከሌሎች አገራት በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመግባባት አልቻለችም፡፡ ከብሩንዲ ከዴሞክራቲክ ኮንጐ፣ ከግብፅ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከሩዋንዳ፣ ከሱዳን፣ ከታንዛኒያ የተወከሉ ሚኒስትሮች በዚህ ስብሰባ ሲካፈሉ ኤርትራ በታዛቢነት ብቻ ተገኝታለች፡፡ ኬንያም በናይል ቴክኒካል ኮሚቴ አባልነቷ ተሳትፋለች፡፡ የላይኛው የአባይ ተፋሰስ አገራትና የታችኛው አባይ ተፋሰስ አገራት የሆኑት 1ዐ የመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ አገራት በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የጋራ መግባባት እንዲኖር ተከታታይ ውይይቶችና ድርድሮች የሚያደርጉ ሲሆን ሁሉም አገራት የተለያዩ ፍላጐታቸውን የሚያንፀባርቁበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ናይል ቤዝን ኢንሼኤቲቭ (NBI) ይህንን የአገራት ልዩነት ለማስታመም የተቋቋመ የጋራ ድርጅት ሲሆን በተለይ በአሁኑ ወቅት ውሃ ቀጣዩ የዓለም ጦርነት ምንጭ ይሆናል የሚለውን ስጋት ለማስቀረት የአገራቱ ድርድርና ውይይት ስኬታማ መሆኑ ለዓለም ሠላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ይነገራል፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገራት (lower riparian) ማለትም ሱዳንና ግብፅ ከሌሎቹ የላይኛው ተፋሰስ አገራት (upper riparian) በተለያዩ ጊዜያት ሳይስማሙ የሚቀሩበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በተለይም መቶ በመቶ የሕዝቧ ሕይወት በአባይ ወንዝ ላይ የተመሠረተው ግብፅ ወደ ድርድር ላለመቅረብና ስምምነት ላለመፈፀም ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን የልማት ፍላጐት ለማሟላት የአባይን ወንዝና ገባሮቹን ለተለያዩ ልማቶች ለማዋል የምትፈልግ ሲሆን ግብፅ ደግሞ ይህንን የመከላከል ስራ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ግብፅ አልፎ ተርፎም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያለ ግብፅ ፈቃድ የልማት ስራ የምታከናውን ከሆነ ጦርነት የማይቀር መሆኑን ደጋግማ ስትገልፅ ከርማለች፡፡ ሰሞኑን በተካሄደውም የናይል ተፋሰስ አገራት ስብሰባ ላይ የናይል ወንዝ ትብብር ፍሬም ወርክ (Nile River Basin Cooperative Frame Work) አንቀፅ 146 የአባይን ወንዝ በእኩል መጠቀም የሚዘረዝረውን ክፍል ሁሉም አባል አገራት ሲቀበሉት ግብፅ ይህንን ሳትቀበል ቀርታለች፡፡ የናይል 90 በመቶ ውሃ ከኢትዮጵያ የሚሄድ ቢሆንም ለወንዙ ምንም የሚያዋጡት ግብፅና ሱዳን ግን የወንዙ አጠቃቀም ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ኖረዋል፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ አርሣኖ የውሃ ፖለቲካ ኤክስፐርት ሲሆኑ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ያለው ኢፍትሃዊ አሰራር እንደሚያንገበግባቸው በተደጋጋሚ ይገልፃሉ፡፡ "ግብፅ ኢትዮጵያ ውሃዋን እንዳትጠቀም ስትከላከል ኖራለች፡፡ ይሁን እንጂ በግብፅ በረሃ ውስጥ ከፍተኛ ግምት ያለው ውሃ በትነት ይባክናል፡፡ ኢትዮጵያ አቅሟን አሳድጋ በውሃ ሃብቷ ለመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት አላት" ይላሉ፡፡ የተለያዩ የልማት ኘሮጀክቶች በአባይ ወንዝ ዙሪያ ለመሥራት ከአፄው ዘመን ጀምሮ ተነድፈው የነበረ ቢሆንም ተግባራዊነታችን ግን ከፍተኛ ችግር ይገጥመዋል፡፡ ኘሮጀክቶቹ የፈንድ ችግር የሚገጥማቸው ሲሆን በተለይ ዓለም አቀፍ አበዳሪ አገራትና ድርጅቶች ከግብፅ ጋር ካልተስማማችሁ ገንዘብ አንለቅም ማለታቸው ኘሮጀክቱ ሳይሰሩ እንዳስቀራቸው ይናገራል፡፡ ግብፅ በአባይ ወንዝ ዙሪያ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ይነሳል በሚል በተለያዩ ባለሥልጣናት እና በተለይም በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ማስፈራሪያዎች ስትሰነዝር ከርማለች፡፡ ይህ ግን ለዶ/ር ያዕቆብ የማስፈራሪያ (detterent) አካሄድ ነው፡፡ ግብፅ ጦርነት ይቀሰቀሳል፤ አባይን የነካ ከግብፅ ጋር ይዋጋል በማለት የውሃ አጠቃቀሟ ሳይስተጓጐል እንዲቀጥል የተቻላትን የማስፈራራት ዲኘሎማሲ እንደምትጠቀም ያስረዳሉ፡፡ በናይል ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የግብፅ መንግሥት ለዓመታት አንድ ዓይነት አቋም ያለው ሲሆን የአገሪቱን ጥቅም ከፍ ለማድረግ ሲልም የአገሪቱን ሚዲያ፣ ምሁራንና ዜጐች በሠፊው የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው እና ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥታት ግን ዓለም አቀፍ ስምምነት በአባይ ጉዳይ ሲፈራረሙ እንኳን ባለሙያዎችን ሳያወያዩና ሳያማክሩ እንደሚሰሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ቅሬታቸውን ያቀርባሉ፡፡ የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶች እንዳይሰምሩና አገሪቱ አባይ ወንዝ ላይ ያላት የመጠቀም ኃይል እንዳይዳብር የተለያዩ መንገዶችን እንደሚጠቀም የሚገለፅ ሲሆን የመጀመሪያው የኢትዮጵያን ሠላም ሊያናጉ የሚችሉ ኃይሎችን በእጅ አዙር በመደገፍ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዳይመጣ ማድረግ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ የግብፅ ሕዝብ በአባይ ወንዝ ላይ አንድ ዓይነት አገራዊ መግባባት ላይ እንደደረሰና ያለ አባይ መኖር እንደማይችል እንዲያምን መደረጉን ይገልፃሉ፡፡ ይህም የሆነው አገሪቱ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ የውሃ ትምህርት እንደሚሰጥና ሁሉም ግብፃዊ አባይ ደሙ እንደሆነ አምኖ እንዲያድግ እንደሚደረግ ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን የውሃ ትምህርት የማይሰጥ ሲሆን ኅብረተሰቡም ስለውሃ ጥቅምና አያያዝ ያለው ግንዛቤ እጅግ አናሳ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ መንግሥትም በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ የውሃ ሃብት ጥናት ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ ማድረግ እንዳለበት ይገልፃሉ፡፡ የናይል ቤዚን ኢንሼኤቲቭ በአባይ ተፋሰስ አገራት ሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ሥራ እንዲሰራ የሚጠበቅ መሆኑን በኪንሻሳው ስብሰባ ላይ የገለፁት የውሃ ሃብት ሚኒስትር አቶ አስፋው ዴንጋሞ በተፋሰሱ አገራት ያሉ ሕዝቦችን ድህነት መዋጋት፣ የተፈጥሮ ሃብትን መንከባከብም የኢንሼኤቲቩ ሥራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ኢንቬኤቲቩ የአባይን ወንዝ አጠቃቀም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማስፈፀምም መሥራት እንዳለበት የገለፁት አቶ አስፋው፣ "የተፋሰሱ አባል አገራት ሊሰራ ከሚችለው በላይ ለሕዝባቸው ቃል መግባት የለባቸውም" ብለዋል፡፡ የናይል ቤዝን ኢንቪኤቲቭ አባል አገራት መሪዎች በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በግብፅ ካይሮ ተገናኝተው የአባይን ወንዝ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ይነጋገራሉ፡፡ የወቅቱ የኢንቬኤቲቩ ሊቀመንበር ኮንጐ ኪንሻሳ የኢንቬኤቲቩን ሥራ እንድትመራ በዚሁ ጉባዔ ላይ ተመርጣለች፡፡ ይሁን እንጂ ናይል ቤዝን ኢንቪኤቲቭ በተፋሰሱ አገራት መካከል ዋና ስራ የሆነውን ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ተግባራዊ ለማድረግ የማይችል፣ ደካማ የማስፈፀም አቅም ያለው በመሆኑና የአባል አገራቱ በተለይ ሱዳንና ግብፅ ያላቸው ቅን ያልሆነ አቀራረብ ኢንቪኤቲቩን የይስሙላ ያደርገዋል ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ የናይልን ውሃ በማዋጣቱ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ የምትወስድ ቢሆንም ምንም ውሃ ከሚያዋጡት አገራት እንዲሁም ኩልል ያለ ንፁህ ውሃ በጥቂቱ ከሚለቁት አገራት የተለየ ድምፅና መብት የላትም፡፡ የአባይን ውሃ በፍትሃዊ መንገድ መጠቀም የሚለው የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጥያቄ ሲሆን ሌሎቹ አገራት በዚህ አጀንዳ ላይ እምብዛም መግፋትና በሱዳንና ግብፅ ላይ ጫና መፍጠር አይፈልጉም፡፡ ግብፅ የአባይን ውሃ በፍትሃዊነት ለመጠቀም ምንም ዓይነት ፍላጐት የሌላት የአገሪቱ መቶ ፐርሰንት ሕይወት በአባይ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ወደ ሊቢያና ሌሎች አገራት የአባይን ወንድ በመሸጥ (export) የምታገኘውን ገቢ በማሰብ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ግብፅ በረሃ ውስጥ አባይን በመጠቀም የተለያዩ ከተሞች እየተመሠረቱ ሲሆን ውሃውንም ከተፈጥሮ መፍሰሻው ውጭ በማውጣት እያተነኑ እንደሆነ ዶ/ር ያዕቆብ በተደጋጋሚ ይገልፃሉ፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያ ጥቅሟ እንደሚነካ በተደጋጋሚ የምትገለፅ ሲሆን ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ እያደረሰች ያለችውን ጥብቅ ተቃውሞ ያቆመ አገር አለመኖሩ ያለው ሁኔታ አጠያያቂ እንደሚያደርገው ይገለፃል፡፡ የአባይ ውሃና ከውሃው ጋር የሚጓዘው አፈርና ሃብት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ለዓመታት ራሷን በምግብ የማትችል፣ ሕዝቧ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚማቅቅና የዕለት ጉርስ የሌለው በመሆኑ በሌሎች አገራት የምግብ እህል እርጥባን የምትኖር ሲሆን ግብፅ ሙሉ በሙሉ አባይ ውሃ እየተጠቀመች ከአፍሪካ አገራትና ከአረብ አገራት ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት አገር ሆና ትገኛለች፡፡ ይህ ሁኔታ ፍትሃዊ ባለመሆኑ ኢትዮጵያም ባላት የተፈጥሮ ሃብት እንድትጠቀም ሙሉ መብት ሊኖራት ይገባል የሚሉት የኢትዮጵያ የውሃ ሃብት ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማትም ከግብፅ ጐን በመቆም የኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ የመጠቀም መብት ማደናቀፋቸውን ይቃወማሉ፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ለመጠቀም የሚከለክላት የፋይናንስ ችግር እንጂ የግብፅ መንግሥት ማስፈራራት እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡ ሁል ጊዜ የውጭ አገር የእርዳታ ድርጅቶችን ድጋፍ ከመጠበቅ ይልቅ መንግሥት የአገር ውስጥ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስልቶችን መንደፍ እንደሚያያስፈልግ በየጊዜው የሚጠቆም ቢሆንም ለውሃ ልማት የሚል የውስጥ አቅም ማጠናከር ሥራ እየተሰራ እንዳልሆነ ይገልፃል፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ እንደሚሉት፣ "ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የረሃብና ድርቅ አደጋ ሲደርስ ዝም ብሎ አያይም፡፡ የየአቅማችንን እናዋጣለን፡፡ ለረሃብና ለድርቅ ከምናዋጣ ለልማት ኘሮጀክቶች ብናዋጣና የታቀዱ የውሃ ልማት ኘሮጀክቶች ቢሰሩ ሁሉም ሰው ይመርጣል"፡፡ ኢትዮጵያ አንዳንድ የልማት ኘሮጀክቶቿ ተፈፃሚነት እንዲኖራቸው በናይል ቤዚን ኢንሺኤቲቭ አባል አገራት የምታስገመግም ሲሆን የውሃ ሃብቱ ዋነኛ ባለሃብት ሆና እያደረገች ያለው ተሳትፎና ትብብር አበረታች መሆኑን ሌሎች አባል አገር ድርጅቶች ይገልፃሉ፡፡ በኪንሻሳው ስብሰባም ኢትዮጵያ በባኮ-ኢኮቦ ወንዝ ላይ ልታደርገው ላሰበችው ልማት የሚረዳ ጥናት ኢንሺኤቲቩ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርባ ተቀባይነት አግኝታለች፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተውም አገራት በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚያደርጉትን ስምምነት ወደ ተግባር የማይለውጡ ከሆነ አስቸጋሪ የፀጥታ ችግሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ሲያመለክት፣ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ያለው ጉዳይ አሳሳቢነቱን ያሳያል፡፡ ውሃ የአገራት የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደሚችል በተደጋጋሚ የተለያዩ አካላት የሚያመለክቱ ሲሆን በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የሚደረጉ ስምምነቶች በተለይ የግብፅን ጥቅም ብቻ ማዕከል ማድረጋቸው ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት እንደሆነ ይገለፃል፡፡ ምንም እንኳን የአባይ ተፋሰስ አገራት ቁጥር አስር ቢሆንም ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት በአባይ ዙሪያ የሚያጠነጥነው የአባይ ውሃ ዋነኛ አቅራቢ በሆነችው ኢትዮጵያና የአባይ ውሃ ዋነኛ ተጠቃሚ በሆኑት ሱዳንና ግብፅ መሃከል ነው፡፡ የግብፅ መንግሥት የሱዳንን የውሃ አጠቃቀም የሚገድብ ሲሆን ኢትዮጵያ የምታመነጨውን ውሃ በፍፁም እንዳትነካ ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ ከጥንት ጀምሮ በአባይ ጉዳይ ሆድና ጀርባ እንደሆኑ የሚገኙ ሲሆን በተለይ ግብፅ ከኢትዮጵያ በኩል አባይን የማቆምና የመጠቀም ፍላጐትን ለማጥፋት በሚል የተለያዩ የጦርነት ሙከራዎች ያደረገችበት ሁኔታ አለ፡፡ የአባይን ወንዝ ከምንጩ ለመቆጣጠር በሚል ግብፅ በእንግሊዞች እርዳታ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጋ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ በ1975 እ.ኤ.አ በጉንደት (በጉንዳ ጉንዲ) እንዲሁም በ1976 እ.ኤ.አ በጉራዕ ላይ ግብፅን ድል በመምታት ሉዓላዊ ግዛቷን አስከብራለች፡፡ በአሁኑ ዘመን ደግሞ የቀጥታ ጦርነት የማታደርግ ቢሆንም ኢትዮጵያን ሠላም የሚነሳ ከተገኘ ከመርዳት ወደ ኋላ እንደማትል ይገለፃል፡፡ አልፎ ተርፎም ለአባይ ሲባል ወደቀጥታ ጦርነት ልትገባ እንደምትችል አልፎ አልፎ ዛቻ መሰንዘሯን ተያይዛዋለች፡፡ ሁለቱ አገራት በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ተመጣጣኝ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ የሕዝብ ብዛት ያላት ሲሆን ቀድሞ ሁለተኛ የነበረችው ግብፅ በሦስተኛነት ትገኛለች፡፡ አገራቱ በቆዳ ስፋትም ተመጣጣኝ ሲሆኑ በጦር ኃይሏ የአረብ አገራት ኃያል የሆነችው ግብፅ፣ ከኢትዮጵያ የተሻለ የምዕራባዊያን ድጋፍ እንዳላት ይነገራል፡፡ የሆነ ሆኖ እነዚህ በአባይ ወንዝ ዙሪያ የተለያየ አቋምና የጥቅም ጥያቄ ያላቸውና ሆድና ጀርባ ሆነው የኖሩት አገራት፣ በአባይ አጠቃቀም ዙሪያ ይስማማሉ ወይስ ይጋጫሉ ለሚለው ከመላምት ያለፈ መናገር አልተቻለም፡፡ ኢትዮጵያ ያለባትን የዕድገትና ዜጐቿን የመመገብ ጥያቄ ለመመለስ የግድ የሚላት ዘመን ላይ ትገኛለች፡፡ ግብፅ ደግሞ ኢትዮጵያ አባይን ከነካች አገር ጠፋ ትላለች፡፡ ሱዳን ከኢትዮጵያም፤ ከግብፅም ጋር እየተሞዳሞደች መኖር ትመርጣለች፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |