| “ወፍ ክንፏና እግሯ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም” |
|
| Sunday, 20 January 2008 | |
|
ዶክተሩ በላቦራቶሪው ውስጥ ሆኖ በወፍ ላይ ጥናትና ምርምር ያካሂዳል፡፡ አንዳንድ የምርምሩን ውጤት ደግሞ መዝግቦ ይይዛል፡፡ ምርምሩና የመዘገበው የምርምር ውጤት እንደሚከተለው ነበር፡፡ መጀመሪያ የወፏን አንድ እግር ቆረጠና ወፏን “ብረሪ” አላት፡፡ ወፏ አንድ እግሯ ተቆርጦ በረረች፡፡ “ወፍ አንድ እግሯ ቢቆረጥም ትበራለች” ብሎ መዘገበ፡፡ ሁለተኛውን እግሯን ቆረጠው፡፡ “ብረሪ” አላት፡፡ በረረች፡፡ “ወፍ ሁለት እግሯ ቢቆረጥም ትበራለች” ብሎ በምርምር መዝገቡ አሰፈረ፡፡ ምርምሩን “በጥልቀት” ቀጠለ፡፡ አንድ ክንፏን ቆረጠው፡፡ “ብረሪ” አላት፤ ተንገዳግዳ በረረች፡፡ “ወፍ ሁለት እግሯና አንድ ክንፏ ቢቆረጥም ትበራለች” ብሎ መዘገበ፡፡ ቀጠለ፡፡ ሁለተኛውን ክንፏን ቆረጠው፤ “ብረሪ” አላት መብረር አልቻለችም፡፡ እንደገና “ብረሪ” አላት መብረር አልቻለችም፡፡ ጮክ ብሎ “ብረሪ” አላት አልበረረችም፡፡ በምርምር ማኅደሩ እንደሚከተለው አሰፈረ፡፡ “ወፍ ክንፏና እግሯ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም፡፡” በዶክተሩ እምነት ወፏ ሁለት እግሯና ሁለት ክንፏ ከተቆረጠ በኋላ መብረር ያልቻለችው ለመብረር የሚያስችላት አካላት ተቆራርጠው ስለተጣሉ አይደለም፡፡ ያልበረረችው ብረሪ የሚለውን ቃል ስላልሰማች ነው፡፡ ክንፎቿ ሲቆረጡ የመብረር አካልና አቅም አጥታ ሳይሆን ክንፎቿና እግሮቿ ስለተቆረጡ ለጆሮዋ መደፈን ምክንያት ሆኖ ነው፡፡ ዶክተሩ የችግሩን ትክክለኛ ምክንያት ማወቅ አልቻለም፡፡ ምርምሩ የተሳሳተ ነው፡፡ መፍትሄ ስጥ ቢባልም ትክክለኛውን መፍትሄ መስጠት አይችልም፤ ትክክለኛውን ችግር አላወቀውምና፡፡ የችግሮች ትክክለኛ መንስዔና ምንነት ማወቅ የሚጠይቁ አንገብጋቢ ጉዳዮች በአገራችን አሉ፡፡ ከችግሮቹ አንዱም ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ መፍጠር ለምን አልተቻለም የሚል ነው፡፡ በተለይም በቅንጅት ዙሪያ ያለውን ችግር ካየን ለረዥም ወራት ዋናው ችግራችን ኢሕአዴግ ነው ሲሉ ቆዩ፡፡ ከዚያ ቆይቶም ዋናው ችግራችን ኢዴአፓ - መድኅን በተለይም አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው ተባለ፡፡ በቅርቡም ደግሞ በቅንጅት ለደረሰው ችግር ተጠያቂው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው፤ የሚል መግለጫ ሰምተናል፡፡ እንደገና ሰሞኑን ደግሞ ቅንጅት ላጋጠመው ችግር ተጠያቂው ኢሕአዴግ ነው የሚል አሜሪካ ከሚገኙ “ተንቀሳቃሽ ፖለቲከኞች” ወይም “መንገደኛው ፖለቲከኛ” እየሰማን ነው፡፡ ሁሉም ተጨምቆ ሲታይ “ወፍ ሁለት ክንፏንና ሁለት እግሯ ከተቆረጠ ጆሮዋ አይሰማም” የሚል ይሆናል፡፡ አሁንም ትክክለኛውን ችግር ለይቶ ለማወቅ ፍላጎትም፣ አቅምም እየጠፋ ነው፡፡ በርግጥ አንዳንድ የቅንጅት አባላትና መሪዎች የት የት ጉድለት እንደነበር የማየትና የማወቅ ፍላጎት እንዳላቸውና እንዳወቁም ምልክት እያሳዩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በተለይም ውጭ ሆነው “አትራፊ ፖለቲካ” ማካሄድ የሚፈልጉ ግን የወፍ አለመብረር ተጠያቂነት ጆሮ ነው እያሉ ናቸው፡፡ ለምንድን ነው ትኩረት ሰጥተን ስለ ጉዳዩ መወያየት የፈለግነው? መልሱ ግልፅና አጭር ነው፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ስለምንፈልግ፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ለአገር፣ ለሕዝብ፣ ለመንግሥት ለገዢው ፓርቲም ጭምር ያስፈልጋል፡፡ የ”ጭር ሲል አልወድም” ጉዳይ ሆኖ ሳይሆን የዴሞክራሲና የፍትሕ፣ የልማት፣ የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ ስለሆነብን ነው፡፡ ክንፏ ስለተቆረጠ ለመብረር ተቸገረች ብሎ እንዲነግረን የምንጠብቀው “ዶክተር”፣ “ብረሪ” የሚለውን ቃል ስላልሰማች ነው፤ የሚል መልስ ተስፋ አስቆራጭ ስለሆነ ነው፡፡ ሌላ ይመጣ እንደሆነ እንጂ እነዚህ ዋጋ የላቸውም፤ ብሎ መደምደም መጨከን ስለመሰለን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደጋፊ የማጣት ችግር ያልነበረው ቅንጅት፣ መሪ የማጣት ከፍተኛ ችግር አጋጥሞት ወደ ሁለት፣ ሦስት፣ አራት፣ አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት ቡድን እየተከፋፈለና እየተከፈለ ይገኛል፡፡ ዋናው ችግሩ ግን መከፋፈሉ ላይ አይደለም፡፡ አብረው መሄድ የማይችሉ ሊከፋፈሉ የግድ ነውና፡፡ ሲፈጠር የነበረው መደመርና መባዛት ይገርም እንደሆነ እንጂ አሁን ያለው ማካፈልና መቀነስ ብዙ አይገርምም፡፡ የሚገርመው በአሁኑ ጊዜ አንድ ዓይነት አመለካከት ሊይዙ የቻሉት ስህተታችን እዚህ እዚህ ነበር፤ ብለው ራሳቸውን ገምግመው ግለሂስ አድርገው ለሕዝብ ለመቅረብ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው፡፡ እስቲ አንድ ጥያቄ እናንሳ፡፡ እስከ ጥቂት ወራት በፊት ድረስ የቅንጅት አመራር አባላት ፓርላማ አለመግባታችን ትክክል ነው፤ የሚል መግለጫ ይሰጡን ነበር፡፡ ፓርላማ የገቡት ከሃዲዎች ናቸው ይባል ነበር፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ ፓርላማ መግባት ክህደት ነው ይል የነበረው ቡድን ፓርላማ ከገቡት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል፤ ብለው መግለጫ አወጡ፡፡ እዚህ ጋር ሁለት ምርጫ አለ፡፡ ወይ ፓርላማ የገቡት ተሳስተናል፤ ብለው ከፓርላማ መውጣት አለባቸው፣ ወይ ደግሞ ፓርላማ መግባት ክህደት ነው፤ ሲሉ የነበሩ ክህደት አይደለም፤ ተሳስተን ነበር፤ ብለው ግለ ሂስ ማድረግ አለባቸው፡፡ ስህተትን አምኖ ደፍሮ መናገር ስንል ይህን ማለታችን ነው፡፡ ቅንጅት ለደረሰበት ችግር ተጠያቂው ራሱ ቅንጅት ነው፡፡ ጨርቄን ቅሌን ማለት አያስፈልግም፡፡ ችግሩ የደረሰው የራሱን ችግር ማየት ስላቃተውና ማየት ስላልፈለገ እንጂ ጆሯችን ስላልሰማ አይደለም፡፡ ስለዚህ ደፈር ብሎ ውስጥን ማየት፣ ደፈር ብሎ ግለ ሂስ ማድረግ፣ ደፈር ብሎ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ብቸኛው ዕድሜ ቀጥል መድኃኒት ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |