| ሬዲዮ ሞርስ |
|
|
| Thursday, 07 August 2008 | |
|
ቶማስ አልቫ ኤዲሰን ብራይል የተባለው የእውራን ጽሑፍ ጠቢብ ነው፡፡ ኤዲሰን ዓይኑ አጥርቶ ቢያይም ጆሮው ምንም ድምጽ አይሰማም ነበር፡፡
ከሚስቱ ጋር ለመግባባት እንዲያመቸው የሬዲዮ ሞርስ አስተማራት፡፡ ሚስቱም በጥቂት ወራት የሞርስ መልዕክትን በሰውነት ላይ በመጠብጠብ መቀበልና ማስተላለፍ ጠንቅቃ አወቀች፡፡ ኤዲሰን የሚፈልገውን ነገር በእጅዋ ላይ በጣቱ እየጠበጠበ ያስተላልፍላታል፡፡ እሷም በተመሳሳይ መንገድ እጁ ላይ እየጠበጠበች መልስ ትሰጠዋለች፡፡ ቲያትር ቤት አብረው ከገቡም ተዋንያኑ የሚናገሩትን በዚሁ ዘዴ እጁ ላይ እየጠበጠበች ትነግረዋለች፡፡ ኤዲሰንም የትያትሩን መልዕክት በሙሉ በእጁ ሰምቶ ከትያትር ቤቱ ይወጣል፡፡ (አባይነህ አበራ፣ ጭላሃ ወግ፣ 1981) ብልሁ ማናቸው ናቸው? ጋብሮቮያዊው ርካሽ አልቤርጎ ተከራይቶ ተኝቷል፡፡ እኩለ ሌሊት ገደማ የቱሃኖቹ ምጥመጣ አላስተኛ ይለዋል፡፡ ይኸኔ አጅሬ መብራቱን ያበራና በሩን ከፍቶ ሲያበቃ ክፉኛ ወርውሮ ከዘጋው በኋላ ተመልሶ ይተኛል፡፡ ደባሉ እጅግ ተረብሾ "ምነው ጃል በጤናህ ነው?" ሲል ጠየቀው፡፡ "ደህና ነኝ ብቻ ቱሃኖቹ ስላስቸገሩኝ የሄድኩ እንዲመስላቸው ብዬ ነው" አለው፡፡ (ዐረፈ ዓይኔ ሐጎስ፣ ቀልዶች ከጋብሮቭ ምድር፣ 1979) ረዣዥም ጥፍሮች ረዣዥም ጥፍሮች የሰፊውንና የአጭሩን ያህል የሰውነትን ኃይል አይገልጹም፡፡ ረዥም ጥፍር በአብዛኛው የተወረሰ ደካማ የሆነና ለበሽታ የተጋለጠን ሳንባ የሚያመለክት ነው፡፡ በጣም ረዥምና አመድማ የሆነ ቀለም ያለው ጥፍር የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ስሜት ወይም ምልክት ነው፡፡ ይህ የበለጠ የሚያረጋግጠው የጥፍሩ ቀለም ሰማያዊ ወደመምሰል ያዘነበለ ከሆነና እንደጎን አጥንት የመሳሰሉ መሥመሮች ከታች ወደ ላይ ተደርድረው የታዩ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የተገለፀው የጥፍር አይነት ሆኖ ነገር ግን በመጠኑ አጠር ያለ ከሆነ የቀሳቢት (ብሮንክያል) ህመም ስሜት ነው፡፡ በጣም ጠበው ረዣዥም የሆኑ ጥፍሮች የሰረሰር (የጀርባ አጥንት) መዳከምን ያሳያሉ፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሥርዓተ አካል የድካም ስሜት እንዳለበት ያመለክታል፡፡ (ኃይለሚካኤል ለቴራ፣ መዳፍ እንደ መጽሐፍ (ትርጉም"፣ 1984) አለ ገና ዱባይ አለ ገና ቡርጅ ዱባይ የአለማችን ረጅሙ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ የተባለው በሰኔ ወር ውስጥ ቢሆንም ዱባዮች ወደ ሰማይ ተመንጥቀው አንጀታቸው ስላልራሰ ግስጋሴያቸው ጋብ አላለም፡፡ በቅርብ ደግሞ የተሰማው ሌላኛው የአለማችን ግዙፉ የገበያ ማዕከል በ46 ቢሊዮን ፓውንድ የሚንቀሳቀሰው የዱባይ ላንድ ፕሮጀክት አካል ሲሆን፣ 3.7 ሚሊዮን ሜትር ስኩዌር ይሸፍናል፡፡ እስካሁን ያልተጠናቀቀውን የዱባይ የገበያ ማዕከል በአራት እጥፍ አስከንድቶታል፡፡ ሌሎችም ከዚሁ ጋር የተያያዙ በርካታ እቅዶች አሉ፡፡ ከ183 ሺህ ሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት ያለው ሚርዲፍ የገበያ ማዕከል (ሲቲ ሴንተር) 100 ሺህ ሜትር ስኩዌር የላጎን እና የዱባይ ታወር የገበያ ማዕከል ስፋት ያለው ዳይራ የዱባይ ወደብ ማሻሻያ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም የዱባይ ሪል ስቴት ገበያ በ2015 በሁለት እጥፍ በማደግ (10"000"000 ሜ.ስኩዌር) ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (ከተሞቻችን መጽሔት፣ 2000) ምኒልክና ቴሌ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከጅቡቲ፣ ከሐረር እንጦጦ፣ ከፋና ነጭ አባይ ድረስ በሦስት ክፍል መድበው የባቡር መገናኛ እንዲገባ ምኞታቸውም ፈቃዳቸውም ሆኖ ለወቅቱ የቴክኒክ አማካሪያቸው ለሙሴ አልፍሬድ ኤልግ የመጀመሪያውን ክፍል ኩባንያ አቋቁመው እንዲሰሩ መጋቢት 1 ቀን 1886 ዓ.ም ውል ሰጡ፡፡ ኢልግም ይህንኑ ሥራ ለማስተባበር ከሙሴ ሊዮን ሽፍኔ ጋር ፓሪስ ላይ ቢሮ ከፈቱ፡፡ የአዲስ አበባ የስልክ ታሪፍ ማለትም የወር ቴሌፎን ኪራይ 5 ብር እና በአንድ ጥሪ 6 ሳንቲም እንዲሆን መጋቢት 1 ቀን 1947 ዓ.ም ተወሰነ፡፡ በመጋት ወር 1952 ዓ.ም ጅማ በር በሚገኘው የሬዲዮ መገናኛ ጣቢያ ሁለት ባለ 10 ኪሎ ዋት ማሰራጫ መሣሪያዎች ተተክለው ሥራ ጀመሩ፡፡ የስልክ መስመሮችን ጥገና በተመለከተ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መጋቢት 4 ቀን 1900 ዓ.ም አዋጅ ነገሩ፡፡ እንደ አዋጁ የመሥመሩ ጥገና ኃላፊነትም መሥመሩ የሚያልፍበት መሬት ባለቤት ነበር፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎት በሚገባ ለማደራጀት አስበው ዓለም አቀፍ የፖስታ ድርጅት (ዩኒየን ፖስታል) ለሚገኝበት ለስዊስ አገር መንግሥት ፕሬዚዳንት መጋቢት 10 ቀን 1887 ዓ.ም በድጋሜ ደብዳቤ ላኩ፡፡ የኮርፖሬሽኑ ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት አራት ትላልቅ ግምጃ ቤቶች በመጋቢት ወር 1947 ዓ.ም በዛሬው ሥፍራ (ራስ ከበደ ሠፈር) ተሰርቶ አስመረቀ፡፡ የተቀሩት ግምጃ ቤቶችም በየጊዜው በ1948፣ በ1952፣ በ1953 እና በ1954 ዓ.ም ተስፋፍተው ተደራጁ፡፡ (ቴሌ ነጋሪት፣ መስከረም 2000) እነዚህ ወጣቶች ብርግድግድ አድርጎ ድንኳኑን ገለጠ ኩፍ አለበትና ገላው አባበጠ እሷ ከሱ ጋራ፣ እነሱ አንድ ሆነው ቀዘፉት ሰማዩን፣ ወጡ ምድር ለቀው ስትጎትተው እሷ፣ ሲጎትታት እሱ የፍቅርን ሸማ ደርበው ሲለብሱ ወጥሮ ካቆማት ድንኳኗ ደረሱ፣ ተመልሰው መጡ ካበሰሉት ፍቅር፣ ሊበሉ ሊጠጡ ላይወጡ ሊሰምጡ እኒህን ወጣቶች ተዉ አትረብሿቸው የድሜ ደራሽ ውሃ፣ ጠርጎ ሳይወስዳቸው ይዋኙ ተዉዋቸው፣ ተዉ አትንኳቸው ስደቱን ይርሱበት፣ ባይንም አትዩዋቸው ፍቅር ከጽዋዋ፣ ፀበል ታጠጣቸው ይሳሙ መስቀሏን፣ ቡራኬ ትስጣቸው ተዉዋቸው፣ ተዉዋቸው ይልቅ "አሹ" አሹ"" እንትፍትፍ በሏቸው "ሆዴ የኔ መላ የኔ ውብ ሸበላ የኔ ማር ወተቴ የስደት ውጤቴ" ይበሉ ራሳቸው በፍቅር እርካታቸው፡፡ (መስፍን አሸብር፣ ጠብታ ፍቅር፣ 1999) * * * የባልና ሚስቱ ጠበቆች በአንድ ወቅት ባልና ሚስት ይጣሉና ይካሰሳሉ፡፡ ባልየው ጠንቀኜ የሚባሉትን አረጋዊ ጠበቃ ያቆማል፡፡ ሚስቲቱ በበኩሏ አንድ ወጣት ጠበቃ ይዛ ትቀርባለች፡፡ በሁለቱ ባለጉዳዮችና በጠበቆቻቸው መካከል ሙግቱ ቀጥሎ ከቆየ በኋላ በ፣በላ ልበልሃ"፣ የመፋለሚያው ጊዜ ሲደርስ በቅድሚያ ወጣቱ ጠበቃ የጠንቀኜን መሸምገል አስመልክቶ እንዲህ ሲል ውርድ ይነዛል፡፡ በላ ልበልሃ" . . . ሙግትን ላፍለኛ አብቹን ለጌኛ ጠንቀኜ አረጀህ አፈጀህ ተው ልቀቅ ለእኛ" ጠንቀኜም ቀበል በማድረግ ሲመልሱ፣ በላ ልበልሃ" . . . ተልጅ ጋር መምከር ብሳና ቅጠል ማጠር ድመት አይመስል አነር አንተን ወንድሜን ልምከር ፍየሎች ጠብቅ ጠንክር" በማለት ማሳቅ ብቻ ሳይሆን ሽማግሌን በመድፈሩና በማንኳሰሱ ትዝብትን አስወሰዱበት ይባላል፡፡ (ሺበሺ ለማ፣ ተጠየቅ፣ 1985) ገራገር ሰማንያዎቹ የደላቸው ላሞች ኔዘርላንድ ውስጥ ሰማንያ ላሞች ጥሩ ምርት ማስገኘት ይችላሉ በሚል ተስፋ ከፍተኛና ያልተለመደ እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ዘሰን ዘገበ፡፡ የምግብ ጥራትን ጨምሮ ላሞቹ በውሃ የሚሞሉ ፍራሾች ያሏቸው አልጋዎች ላይ እንዲተኙ እንደሚደረግ የላሞቹ ባለቤት ናንሲ ቨርመር ተናግረዋል፡፡ "ላሞቹ ደስተኞች መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ከፍተኛ ወተት የመስጠት አቅም አይኖራቸውም፡፡ ቀደም ሲል የሚተኙት ኮንክሪት ላይ ነበር፡፡ አሁን ግን ምንጣፍና የውሃ አልጋዎች ላይ ነው እንዲተኙ የሚደረገው" ብለዋል፡፡ ደስተኛ የሆኑ ላሞች የሚሰጡት ወተት ደስተኛ ያልሆኑት ከሚሰጡት የተለየ እንደሆነ ናንሲ አስረድተዋል፡፡ በመፀዳጃ ቤቶች አደናጋሪ ምልክቶች ተሰቀሉ በቻይና ዜንጉዙ ከተማ የሚገኝ ፒዛ ሬስቶራንት የወንዶችና የሴቶች መጸዳጃ ክፍሎችን ለመለየት በወንዶች መፀዳጃ ክፍል በር ላይ የሙዝ፣ በሴቶቹ ደግሞ የኮክ ምልክት በማስቀመጥ ደንበኞቹን ማደናገሩ ተሰማ፡፡ ሁኔታው ሊደረስበት የተቻለው የከተማዋ አስተዳደር በከተማው ውስጥ የሚገኙ የሕዝብ መገልገያ ምልክቶች ላይ ጥናት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡ በጥናቱም በከተማዋ ካሉ የሕዝብ መገልገያ ምልክቶች ስልሳ በመቶ የሚሆኑት ግልጽ አለመሆናቸው ሊታወቅ ችሏል፡፡ ጥናቱን ካደረገው ቡድን ተወክለው ወደ ሬስቶራንቱ የሄዱ ሁለት ባለሙያዎች በሬስቶራንቱ በነበራቸው የአስር ደቂቃ ቆይታ አስራ ሁለት ደንበኞች መፀዳጃ ቤት ለመጠቀም በምልክቶቹ ምክንያት ሲወዛገቡ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ የመፀዳጃ ቤቶቻቸውን ለመለየት የወራጅ ውሃንና የዝናብ ምልክትን የተጠቀሙ ንግድ ቤቶች መኖራቸውን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ የጥናቱ ዳይሬክተር ዣንግ ሊያንግ የሕዝብ መገልገያ ምልክቶችን በሚመለከት የከተማዋ አስተዳደር ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ የጠፋው ቡችላ በጀልባ ወደ ቤቱ ተመለሰ ይኖር ከነበረበት ፕለይማውዝ አካባቢ የጠፋው ቡችላ ከሁለት ሰዓታት በኋላ በጀልባ ወደ ቤቱ መመለሱን ዘሰን አስታወቀ፡፡ ጃክራስል የተባለው ቡችላ ሊጠፋ የቻለው አሳዳሪው ከሆኑት ቬቪን አክሰለይ ጋር የእግር ጉዞ እያደረጉ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ የውሻው አሳዳሪም ውሻው መጥፋቱን እንደተረዱ ወዲያው ፍለጋ የጀመሩ ሲሆን በበጎ አገልግሎት ሰጪ ቡድን እርዳታ በአቅራቢያው የሚገኘውንና 865 አክር ርዝመት ያለውን የኤጅግከምብ ተራራን አስሰዋል፡፡ ፍለጋቸው ባለመሳካቱ ተስፋ ቆርጠው በነበሩበት ወቅት ወደ ከተማዋ እየገባ በነበረ ጀልባ ላይ ውሻው መታየቱ ስልክ ተደውሎ እንደተነገራቸው አልደበቁም፡፡ ጥይት የማይበሳው ጡት ማስያዣ የጀርመን ሴት ፖሊሶች ጥይት የማይበሳቸው ጡት ማስያዣዎች ሊሰራላቸው ነው፡፡ መደበኞቹ የጡት ማስያዣዎች በሥራ ላይ ጉዳትን ለመቋቋም ባለመቻላቸው የተነሳ የአዲሶቹ ጥይት የማይበሳቸው ጡት ማስያዣዎች መሠራት አስፈልጓል ሲል ዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ እነዚህ ጡት መያዣዎች በፖሊስ አባላቱ ላይ ጥይት በሚተኮስበት ወቅት በፕላስቲክና በብረት ሽፋናቸው አማካኝነት ጥይቶች ወደ ውስጥ እንዳይገቡ ይከላከላሉ፡፡ ስርመን ኪባት የተባለች የሀምቡርግ ከተማ ፖሊስ አባል የጡት መያዣዎቹን በተግባር ከሞከረች በኋላ "የሰዎችን ህይወት መታደግ የሚችሉ" በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ በዚህም ሳትገደብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴት የጀርመን ፖሊሶችን በማስተባበር በሥራ ወቅት እንዲጠቀሙባቸው በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ቁጥራቸው ሶስት ሺህ የሚጠጋ ሴት የግንባር ፖሊስ ባልደረባዎች የአዲሱ ጥይት የማይበሳው ጡት መያዣ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ለእያንዳንዷ እንስት ባልደረባ ሦስት ሦስት ጡት ማስያዣዎችን በራሽን እንደሚከፋፈሉ ይፋ ተደርጓል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |