| አድዋ የኢትዮጵያ ቅርስ |
|
|
| Sunday, 20 January 2008 | |
|
ባለፈው ረቡዕ ጋዜጣችሁ ወጣት አምድ እንደተዘገበው በአድዋ ተራራ ላይ ፅሁፍ ለማስቀመጥ የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ አድዋ የኢትዮጵያ ህዝብ የታሪክ ቅርስ እንደመሆኑ መጠን የፅሁፍ መታሰቢያና ማመልከቻ በተራራው ላይ መፃፍ ጠቀሜታው የጐላ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር የክልሉም ሆነ የብሔራዊ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ተራራው ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ የሚተላለፍበትን ሁበኔታ አጠናክረው ቢቀጥሉ መልካም ነው፡፡ (ሩባቤል፣ ከሳሪስ) fየባህል ውዝዋዜ እንዲጠናከር በረቡዕ እትም ባወጣችሁት የኪንና ባህል አምድ ከአንጋፋው የውዝዋዜ አሠልጣኝ ታደለ ታምራት ጋር ያደረጋችሁትን ቆይታ እንዳነበብኩ ተገረሜያለሁ፡፡ እስካሁን በነበረኝ ግንዛቤ የባህል ውዝዋዜያችን በየሙዚቃ ክሊፖች ማጀቢያ መሆኑ የማደጉ ምልክት ይመስለኝ ነበር፡፡ ከአንጋፋው አርቲስት ገለፃ ግን በዚህ ድርጊት እየተቀየጠና ፈር እየለቀቀ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጣት ተወዛዋጮች ተጠያቂና ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ የባህል ውዝዋዜው እንዲጠናከር አንጋፋ ባለሙያዎችን ማነጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እናንተም ልምድ እንዲያካፍሉ መድረክ ብታመቻቹ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ (ምስራቅ፣ ከ22 ማዞሪያ) ኢንተር አፍሪካ ግሩኘ ሊመሰገን ይገባል ስለሀገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ዲሞክራሲን ለማበልፀግ ህዝቡ ሊኖረው ስለሚገባው ንቁ ተሳትፎ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በኢንተር አፍሪካ ግሩኘ የተዘጋጀው የምሁራን ውይይት የሚበረታታ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ እወቅናን በጥናትና ምርምራቸው ያገኙት ለማንም መዳመጥ የሚችል ሀሳብ የሚያፈልቁት እና ኘሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፣ ኘሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ ኘሮፌሰር አሉላ ፓንክረስት፣ ኘሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና ኘሮፌሰር አፍሬም ይስሀቅ ያደረጉት ውይይት ለብዙዎች ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ የሀሳብ ልዩነት ቢኖር እንኳን በምክንያት በመከራከር ማብራሪያ በመጠየቅና በመስጠት እንዲሁም ለማሳመን በመጣር እንጂ "ከእኔ ወዲያ ላሳር" በማለት የተለየ ሀሳብ ያለውን ሁሉ በመጥላትና በማራቅ መሆን እንደሌለበት አሳይተዋል፡፡ ምክንያታዊ ማህበረሰብ ደግሞ በቁጥር አነስተኛ ከሆኑት የዲሞክራሲ ኃይሎች ማለት መንግሥትና ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በላይ የራሱን እሴቶች በመያዝ የእርስ በርስ መስማማት ባህልን ካዳበረ የተሻለ ተዕእኖ መፍጠር ይቻላል፡፡ ምሁራኑን በማሰባሰብ ለውይይት የጋበዛቸው ኢንተር አፍሪካ ግሩኘ አላማ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጉላት እንደመሆኑ ይህ ዓይነቱ ውይይት ሊዳብርና ሊስፋፋ ይገባል፡፡ እናንተም በዝርዝር ሀሳቦቹን በማንሸራሸር ዜጎችም እንዲወያዩበት ብታደርጉ ጥሩ ነው፡፡ (ሙከመር፣ ከወሎ ሰፈር) የዲሽ ያለህ" ባለፈው ሣምንት ዕሁድ በወጣው ርዕስ አንቀፃችሁ "ዲሽ የሌላችሁ እንደምን አመሻችሁ . . . " ስትሉ የፃፋችሁትን በስሜት ተውጬ አንብቤዋለሁ፡፡ እንደዚህ የህዝብን ስሜት የሚዳስሱ ርዕሰ አንቀፆች መፃፋችሁን ቀጥሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካቹ የልብ ካውያ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ እንደ በቀቀን ከሚያስተጋባው እንጉርጉሮ በዘለለ አልፎ አልፎ የተሻሉ ኘሮግራሞች ያሳይ የነበረ ቢሆንም አሁን ከነአካቴው ፊቱን በጨው የታጠበ መስሏል፡፡ እንደእኔ ዲሽ ገዝቶ የውጭ ቻናሎችን የማየት ዕድል የሌለው ተመልካች "ኡ . . ኡ የዲሽ ያለህ"" እያለ መጮህ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም እንደ አሮጌ ወፍጮ ሲንደቀደቅ እኛም ጥሩ ይሆን ይሆናል ብለን ስንጠብቅ ሚሌኒየሙ ባተ፡፡ ምናለበት የማመለከተው የመንግሥት አካል የተማሩና ዕውቀቱ ያላቸውን ጋዜጠኞች ቢቀጥር? ይህ ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ግን ተስፋ አለኝ፡፡ (ዳግማዊ፣ ከራት ኪሎ) ህዝቡን አታደናግሩ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ባለፈው እሁድ ሪፖርተር ጋዜጣ ቆይታ ገፅ ኤርትራ ስትገነጠል ለተፈፀመው ጥፋት እኛም ተጠያቂ ነን ማለታቸውን አንብቤያለሁ፡፡ ወ/ሮ አረጋሽ ለኤርትራ መገንጠል እርስዎም አቶ ስዬ፣ አቶ ገብሩና ጠቅላላ የህወኀት አባሎች ጠቅላላ ተጠያቂ ናችሁ፡፡ እናንተ ከህውኀት አባልነት ባትባረሩ ኖሮ ኤርትራ እንዳትገነጠል መታገላችሁን በሰፊው ትቀጥሉበት ነበር፡፡ አሁን ስለተባረራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማደናገር ኤርትራ ስትገነጠል ለተፈፀሙት ጥፋቶች እኛም ተጠያቂ ነን ማለት ጀምራችኋል፡፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንደመቀለድ ይቆጠራል፡፡ አሁንም ቢሆን እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ኤርትራን እንደ ክፍለ ሀገራችን አድርገን ነው የምናያት ኤርትራውያኑ ወገኖቻችን ናቸውና፡፡ (ገናናው መንግስቱ፣ ከደብረዘይት) በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ዕድሮችና ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ጥር 7 ቀን 2ዐዐዐ እትም ዜና ገፅ ላይ "በየክፍለ ከተማው ተቀምጠው አንሺ ያጡ የቆሻሻ ገንዳዎች ለህብረተሰቡ ጤንነት ጠንቅ እየሆኑ ነው" በሚል ርዕስ የቀረበው ፅሁፍ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ በአንድ መንግሥታዊ ድርጅት እንቅስቃሴ ብቻ ሊቀረፍ እንደማይቻል ያስረዳል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ህብረተሰቡ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ላይ መያዝና ማስወገድን ባህል አድርጎ መያዝ አለበት፡፡ በዚህም ላይ ዕድሮች ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ መረሳት የለበትም፡፡ በወርሃዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ የደረቅ ቆሻሻን ጉዳይ እንደ አንድ አብይ አጀንዳ ይዘው መወያየትና መነጋገር ይገባቸዋል፡፡ በስራቸውም የታቀፉትን ህብረተሰብ በማስተባበር በደረቅ ቆሻሻ ላይ ማዝመት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመንግሥት እንቅስቃሴ ብቻ ከተጠበቀ የትም ሊደርስ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አቅሙ ውስን በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ውስን አቅም ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከታከለበት የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ችግር ይቃለል፡፡ (ከበደ ጌታቸው፣ ከልደታ) ሌሎችም ባለሃብቶች እንዳይከተሉት የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት ያሰሩትን ቤት በሚመለከት ጥር 7 ቀን 2ዐዐዐ የወጣው ዜና የተለያዩ ስሜቶችን እንደሚፈጥር ግልፅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ቤት ለምን ተሠራ ብሎ መውቀስ አይቻል ይሆናል፡፡ የባለቤቱ ፍላጎትና መልካም ፈቃድ ነውና በመሥራቱ ላይ ተቃውሞ ማሰማት መብት አይደለም፡፡ በክስተቱ የኑሮው ክፍተት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል የጎዳና ተዳዳሪው ቁጥር እየበዛ ሲሄድ፣ በሌላ በኩል የባለሃብቱ የገንዘብ አቅም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ የአገሪቱ ድህነት፣ የህዝቡ ሰቆቃ ለአቶ ሣሙኤል ታፈሰ ይሳናቸዋል አይባልም፡፡ ምርጫና ፍላጎት ስለሆነ በዚህ ላይ አስተያየት ማብዛትም የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ቅሬታ ያስነሳው የርችቱ ጉዳይ ነው፡፡ ርችት ባይተኮስስ? ነዋሪውን የሚረብሽ ድምፅ በከተማ ወስጥ ይፈቀዳል? ይኼ ትክክል አይደለም፡፡ የአቶ ሣሙኤል የልደት ቀንና የልጃቸው ጋብቻ የህዝብ በዓላት አይደሉም፡፡ ዛሬ እሳቸው የጀመሩትን ርችት ሌሎች ባለሃብቶች እንዳይከተሉት ምን ዋስትና አለን፡፡ ገንዘብ ሲኖር በሰማይ መንገድ ቢኖርም እየተስተዋለ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ (ገብሩ መንግሥቱ፣ ከአዲስ አበባ) ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለምን? በሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው ረቡዕ ዕትም በፖለቲካ አምድ ላይ "ወታደሩ መንግሥትን በመፈንቅለ መንግሥት ያስወግደው እንደሆነ እንጂ . . . " በሚል ርዕስ የወጣው ቃለ መጠይቅ አንብቤዋለሁኝ፡፡ በፅሁፉ አጠቃላይ ይዘት ላይ ምንም ተቃውሞ የለኝም፡፡ ርዕሱ ግን አስደንጋጭ ነው፡፡ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ያስከተለው ችግር ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ መናገር "ለቀባሪ ማርዳት" ነው፡፡ በአቋራጭ ሥልጣን የተቆጣጠረው ደርግ አገራችንን በደም አጨቅይቷል፡፡ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም እንደዚሁ፡፡ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በትር ሥልጣን የሚቆጣጠር አካል በምንም ተአምር የዲሞክራሲ ምንጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ዲሞክራሲ ሂደት ነው፤ ዲሞክራሲያውያን ተቃዋሚዎች መፈጠር ይጠይቃል፡፡ ይህንን ጊዜው ሩቅ አይሆንም፡፡ መንግሥት በመለወጡ ራሱ ዲሞክራሲ ነው ካላልነው በስተቀር ለውጡ ራሱም ዲሞክራሲያዊ ሂደት የተከተለና በሰላማዊ ትግል ብቻ መሆን አለበት፡፡ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ስሙም መነሳት የለበትም፡፡ አሁን የተጀመረው የዲሞክራሲ አቅጣጫ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ለምን? (ተስፍሽ፣ ከመሿለኪያ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |