Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያን ውህደት እንዴት?
የኢትዮጵያን ውህደት እንዴት? Print E-mail
Sunday, 20 January 2008

እኛ ኢትዮጵያውያን በርግጥ መዋሃድ አቅቶናል፡፡ ሁላችንም ግን መዋሃድ አልጠላንም፡፡ “አብረን መብላት እንጂ አብረን መሥራት አልለመድንም” እንጂ “በሁሉም ዙሪያዎች” በሥራ፣ በዴሞክራሲና  በጀግንነትና” ለራሳችን ሁነን ለሌሎች እንተርፋለን፡፡ ለራሳችን ሁነን ሌሎች ተምሳሌት፣ አርአያ እንሆናለን፡፡ ምን መሆን ነው ያቃተን? አንድ ያቃተን ትልቁ ነገር የመወሃድና የማዋሃድ ፈተና ተደቅኖብናል፡፡ መዋሃድ ምንድን ነው? የምንዋሃደውስ እንዴት ነው? የምናዋህዳቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎች አንባቢ እንደሚያነሳቸው እገምታለሁ፡፡ ተገቢም ነው፡፡

ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ነገዶች ሙዝየም ነች ሲባል አብሮ የሚነሳ አንድ ትልቅ ነገር አለ፡፡ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸው ልዩ የሆነ የአስተዳደር፣ የፍርድ አሰጣጥ፣ የፀብ ማስቀረት፣ የአኗኗር ዘዴዎች የመሳሰሉ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዕሴቶች ባለቤቶች ናቸው፡፡ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና የፕሬስ ነፃነት የመሳሰሉ መርሆዎች ቋንቋዎቹ አዲስ ይሆኑብን እንደሆነ እንጂ በእያንዳንዳችን ጓዳ በየራሳችን ቋንቋ፣ በየራሳችን መንገድና ፍላጎት ስንሰራባቸው፣ ስንጠቀምባቸው፣ ስንተገብራቸው ከራሳችን ጋር አዋህደን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የመጡ የአባቶቻችን ዕሴቶች እንዳሉን የታሪክና የስነ ማህበረሰብ ምሁራን ጥናቶች ያሳዩናል፡፡

ይህንን ለመፃፍ ያነሳሳኝ አንድ አጋጣሚ ነው፡፡ ባሳለፍነው ሣምንት ማክሰኞ ዕለት በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስብሰባ አዳራሽ አንድ ኮንፍረንስ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የኮንፈረንሱ አጀንዳ፣ Fostering Shared Core National Values Expanding Common Political Space in the New Ethiopia Millenium ወይም “ትልልቅ አገራዊ የውል ዕሴቶችን ማበልፀግ፤ በአዲሱ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የጋራ የፖለቲካ መድረክ መፍጠር” የሚል ነበር፡፡

በኮንፈረንሱ በርካታ የጥናት ፅሑፎች ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቨን “The Promise of Ethiopia public Action, Civic Forgiveness, Creative Power” በሚል ርእስ ያቀረቡት የጥናት ፅሑፍ አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ዶናል ሌቪን በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡ ሕይወታቸውን ሙሉ ማለት ይቻላል ያሰለፉት በኢትዮጵያ የስነ ማህበረሰብ ጥናት በማድረግ ላይ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በኢትዮጵያ ጥናት ማካሄድ የጀመሩበት 50ኛ ዓመት ማክበራቸው የሚታወስ ነው፡፡

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በዚሁ ፅሑፋቸው ካነሱዋቸው በርካታ ነጥቦች አንዱ በኢትዮጵያ “ሕዝባዊነት” “Public” ተፈጥሯል ወይ የሚል ነው፡፡ ምሁሩ በማእከልና በአገር ቤት አካባቢ ያሉት ሕዝቦች በዘመናዊ ዘዴዎች እንደ ሚድያ፣ ከተማነትና የገበያ መስፋፋት፣ የፖለቲካ ቁጥጥር መዘርጋት፣ የመገናኛና የመንገድ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት የመሳሰሉ መንገዶች እንደሚያስተሳስሩዋቸውና በሁለቱም “ጫፎች” መካከል የነበረውን ክፍተት እንደሚዘጋ በመሆኑም “አገራዊ” አመለካከትና “ሕዝባዊነት” መመሥረት እንደሚቻል ያስቀምጣሉ፡፡

እንደ ድህነት፣ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋና አስከፊው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት የመሳሰሉ ስር የሰደዱ ችግሮች ለማስቆም፣ እንዲሁም በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን ግንኙነት፣ የዕርዳታ “ሱስነት”ን በመሳሰሉ ትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ዜጎች የጋራ አቋምና አመለካከት ስለመያዛቸው ይጠይቃሉ፡፡ እነዚህ ትላልቅ የአገሪቱ ችግሮች ለመዋጋትና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉም ዜጎች ስምምነት ላይ ደርሰው የጋራ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመፍጠር የሚያስችል መንገድ መቀየስ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን በማመላከት፣ በተለይ ሚድያዎች ዜጎችን፣ ልሂቃንና፣ ባለሞያዎችን ለማቀራረብና ለማወያየት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ችግሩን በየማስቀረት ኃላፊነቱ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎች፣ የምሁራን (የልሂቃንና) የጋዜጠኞች መሆኑን በማስቀመጥ “ሁሉንም መጥፎ ወይም መልካም ነገሮች ለአንድ ትልቅ መሪ ብቻ መተው የለብንም” ብለዋል፡፡

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለውን ምሳሌ የሚያመለክተው የሰዎች መሰባሰብ ብቻ ሳይሆን መተባበር፣ መወያየት የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ መሆኑን አጥብቀው ይመክራሉ፡፡

በታሪክ የኢትዮጵያ መንግሥታት ራቅ ያሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አግልለዋቸው እንደቆዩ፣ ደርግም ከእነዚህ ሕዝቦች መገናኛ ዘዴ ቢፈጥርም ለማዘዝና ለመጠቀም እንጂ ችግራቸውን ለማዳመጥና ለመፍታት፣ በአገራዊ ጉዳዮች ለማሳተፍ እንዳልነበረ በማስረዳት፣ በአሁኑ ወቅት ያለው መንግሥት ፍፁም ባይባልም ነፃ ፕሬስና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የመፍጠር ሂደት እስከ 1997 ምርጫ ድረስ ከፍተኛ ሥራ ሰርቷል ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሂደት በድህረ ምርጫው መቀልበሱ ፕሮፌሰር ሌቪንን አሳዝኗል፡፡

ፕሮፌሰር ሌቪን ከ97 ምርጫ ተነስተው የሰጡት ትችት መሠረታዊና ለወደፊቱም ሁሉንም ወገኖች አስተማሪ ነው፡፡ “ምርጫው ከዚህ በፊት ያልታየ አዲስ ምዕራፍ ነው” በማለት ለዚህም ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ያስቀምጣሉ፡፡ በመጀመሪያ በአገሪቱ ግልፅ የመከራከር፣ ሃሳብ የማንሸራሸር በር መክፈቱ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ በርካታ የአገሪቱ ሕዝቦች ወደ በርካታ የአገሪቱ ፖለቲካ እንዲገቡ መፍቀዱን ያደንቃሉ፡፡

ይሁን እንጂ እንደእሳቸው አባባል በወቅቱ ከሁሉም ወገኖች የተፈጠሩ ስህተቶች “ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ አልተዘጋጀችም” የሚያስብል ነው፡፡ ብዙ ተመልካቾች በየፊናቸው በወቅቱ ለተፈጠሩ ችግሮች በኢህአዴግ ላይ ወይ በቅንጅት ላይ ያተኩራሉ፡፡ ፕሮፌሰር ዶናልድ ችግሩን ከዚህ በተለየና በሰፊ አድማስ ይመለከቱታል፡፡

በመጀመሪያ የአሜሪካ ጨምሮ የሁሉም ዴሞክራሲያዊ የሚባሉ አገሮች የዴሞክራሲያቸው አፈጣጠር ሂደት ላይ የፃፉት የፖለቲካ ሳይንቲስት ምሁራን ሥራዎች ይመረምራሉ፡፡ ዳዊ የተባለው ፀሐፊ The Republic and Its problems በሚለው መፃፉ እንዳስቀመጠው በየአካባቢው ያሉት ማህበረሰቦች የአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግባቶች መሰረቶች እንደሆኑ በማስረዳት የ”ኒው እንግላንድ” የከተሞች ተከታታይ ስብሰባዎች ለአሜሪካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፈጠር የማዕዘን ድንጋይ ጥሎ ማለፉን ያስረዳል፡፡

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ በምርጫ 97 ያጣችው ትልቁ ነገር መንስኤው ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ በኢትዮጵያ መሠረት የሌለውና በተለያዩ የአገራቱ ክፍሎች ያሉት ዴሞክራሲያዊ ባህል ግብዓት የሌለው የባዕድ ባህል በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ባህልን ማድረግ አንድ ነገር ሆኖ ምሁሩ ግን ሌላ አማራጭ አይተዋል፡፡ እሳቸው በሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች (ብሔረሰቦች) ባህልና ማህበራዊ ዙሪያ ባካሄዱት ጥናት በእያንዳንዱ ብሔረሰብ ያለው ማህበረሰባዊ ስርዓት የእርስ በርስ መከባበር፣ ውጤታማ የሆነ የፀብ/ግጭት አፈታት ዘዴና ማህበረሰባዊ ችግር ተቀባይነት ያለው መፍትሄ እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡

ምሁሩ በጥናታቸው መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ15 እስከ 20 በመቶ ከአንድ በላይ ብሔሮች የዘር ግንድ ያለው መሆኑን አስቀምጠዋል፡፡ ይህ የመወሃድ አንድ አቅጣጫ ነው፡፡ ታዲያ በአሁኑ ወቅት እንዲህ ዓይነት የብሔሮች መቀላቀልና መወሃድ ባለበት ሁኔታ የአንድ ሰው “ብሔር” መጠየቅና ማስያዝ ይቃወማሉ፡፡ ምክንያታቸው ለብዙ ዘመናት የቆየው የመዋሃድ ሂደት ፀር እንደሆነ ነው፡፡ ምሁር በብሔር የተመሰረተ የፌዴራሊዝም ስርዓት በሚያስከትለው ጉዳት ላይ ስጋት ሳያድርባቸው አልቀረም፡፡

በወቅቱ ተወያይ ሆነው የእሳቸው ፅሑፍ የገመገሙ ፕሮፌሰር እንድሪስ እሸቴ በአጠቃላይ በፕሮፌሰር ሌቪን ላይ የቀረበው ጥናት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት እነዚህ ፍትሃዊ አገር በቀል ስርዓቶችና ዕሴቶች በማዋሃድ “ሕዝባዊነትን” በማስያዝ ጥቅም ላይ ማዋል እንዲበረታታ የሚፈለጉ ቢሆንም በብሔር የተመሠረተ ስርዓት ይህንን እንደማይፃረርና እያንዳንዱ ማህበረሰብ ባህልና ዕሴት እንዲያሳድግ፣ ከራሱ በተመረጠ መሪዎች እንዲተዳደር፣ በራሱ ባህላዊ ዕሴቶች የተመሰረተ ስርዓት መተዳደሩ ሂደቱን አበረታች እንጂ ከዚህ የሚፋለስና የሚበታትን ሆኖ አላገኙትም፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ያሉት ሕዝቦች ስልጡን የአስተሳሰብ ደረጃ በአገር ውስጥ ያሉት ሆነ በውጭ አገር የሚገኙት “ሰለጠንን” የሚሉት “ስልጡን” ኢትዮጵያውያንን ያሳፍራል ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ እውነትም በተለይ ከመሃል አገር ወጥተን የማናቅ ሰለጥንን የምንል ኢትየጵያውያን አንድ ቀን ወጣ ብለን “ባልሰለጠነው” የኢትዮጵያ ክፍል ያለው የእርስ በርስ መቻቻል፣ መተሳሰብ፣ የእንግዳ አክባሪነት፣ መወያየትና የዕውቅ ባህሎች ስናይ እራሳችን ውስጥ ያለው ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ትምክህት፣ ፉክክር፣ አንዱ በሌላው ተወላጅ ላይ ያለን አመለካከት፣ ጥላቻ ወዘተ. ያሳፍረናል፡፡ እውነትም ገና የኢትዮጵያ “ሕዝባዊነት” አልመሰረትንም ያስብላል፡፡

ከአገራችን የተለያዩ የአገር አባቶች ስርዓቶች ለአብነት የሚጠቀሱ አሉ፡፡ ለምሳሌ በቅማንት (ጎንደር) የሽማግሌዎች ቡድን በየዓመቱ አንድ ሊቀመንበር ይመርጣሉ፡፡ ይህ የሽማግሌዎች ቡድን በፍትህና በአመራር ችግሮች ዙሪያ ይወያያል፣ ይመክራል፡፡ በውስጡም ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ አባላት ይኖሩታል፡፡

ሌላው በሲዳማ የሚስተዋለው ሲሆን “ጉዳመሌና” (የፍትህ ቦታ) የጉርብትና ሽምግልና የሚካሄድባቸው ሁለት ሥርዓቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ሥርዓቶች ግጭቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሲነሱ ለምሳሌ በእርሻ ማሳ፣ ድንበር፣ በግጦሽ መሬት፣ በከብቶች ሰብል ማጥፋትና በመሳሰሉት ሲከሰቱ መፍትሄ ይፈልጋሉ፡፡

ከተለያዩ ጐሳዎች የተውጣጡ የጉዳመሌ አባላት በጐሳዎች መካከል የሚከሰተውን ችግር በመወያየት ይፈታል፡፡ ገዳመሌ ማለት የጐሳ መሪዎች የሚቀመጡበት ቦታ ሲሆን ይህ ሥርዓት የሚካሄደው እንደ ስማ በለው ሁሉም በዛፍ ጥላ ስር ሆኖ ክርክሩ ሴቶችን ሳይጨምር ማንኛውንም አላፊ አግዳሚ ያካትታል፡፡ ተከራካሪዎች የሚያደርጉትን የሃሳብ ልውውጥ ሽማግሌዎች ካዳመጡ በኋላ ተሰብስበው አባል ሁሉ በተስማማበት ሁኔታ ውሣኔ ፍርድ ይሰጣል፡፡

በትግራይ አካባቢ ደግሞ “ባይቶ” ተጠቃሹ ሲሆን የአካባቢው ሽማግሌዎች ተመርጠው በአካባቢያዊ ችግሮች ዙሪያ በደብተር የተፃፉ መተዳደሪያ ደንብ በማውጣት ህብረተሰቡ ከተስማማበት በኋላ በተግባር ያውሉትና ይተዳደሩበታል፡፡

በኮንሶ “ሂዮዳ” የተሰኘ ፍርድ ቤት መሰል ሥርዓት አለ፡፡ ይህ አካል የአካባቢውን ገዥዎች በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርጉት የአስተዳደር በደል ካለ ጠርቶ ያወያያል ጥፋተኞችንም ይቀጣል፡፡ በዚህ ሥርዓት ማንኛውም ኮንሶ በመምረጥ ይሳተፋል፡፡
 
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ብሔር የገዳ ስርዓት በዴሞክራሲያዊነቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ የገዳ ስርዓት የዕድሜ እርከን ያለው፣ አሳታፊ፣ ዴሞከራሲያዊ የሆነ የፖለቲካዊ፣ የማህበራዊና ባህላዊ መዋቅር ነው፡፡

ጥያቄው እነዚህ የተለያዩ የሚመስሉ ግን አንድ የሚያደርጋቸው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና አሳታፊ ባህላዊና አገር በቀል ስርዓቶች እንዴት ማዋሃድ ይቻላል? ነው፡፡ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን እንዲህ ይቀጥላሉ፡፡ “ኢትዮጵያ ከዜሮ አትጀምርም”፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ለብዙ ዘመናት በተለያዩ መንገዶች ለምሳሌ በገበያ፣ በሃይማኖት፣በአገልግሎት ልውውጥና በጋብቻ ትስስር ፈጥረዋል ይላሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ የማህበረሰብ አንድነት አመሰራረት በትግራይና በአማራ ባህል አገራዊ ህብረ ብሔር ስርዓት ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመቶች እየተስፋፋ መምጣቱ ለአገሪቱ መፈጠር ትልቅ አወንታዊ ጎን እንዳለው ይገልፃሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ይህ ኢትዮጵያን እንደ አገር የፈጠረ ባህል ሙሉ ለሙሉ የሌሎች ማህበረሰቦች ባህልና ስርዓት ያካተተ ነው ማለት ባይቻልም ሁሉንም ማህበረሰቦች የሚጠቅም አራት መሰረታዊ ዕሴቶች መበርከቱን ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚህም ችሎት፣ ማህበር (ዕድር”፣ ሕዝባዊ ዓመፅና ዘመቻ ናቸው፡፡ የእነዚህን ባህላዊ እሴቶች ድክመት የሚሉት እቤት ውስጥ “የወንድነት” የበላይነት የጠበቁ መሆናቸው ነው፡፡

ሕዝባዊ አመፅ ያሉዋቸው ትላልቅ የአገር መሪዎች ወይም የሃይማኖት አባቶች ንጉሱ (መሪ) ከተለመደው ውጪ የአገር ባህልንና ስርዓት የሚፃረር ሥራ ሲፈፀም ሕዝቡን እንዲያምፅ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪን ይህ በምሳሌነት ሲያስረዱ በ15ኛው ክፍለ ዘመን አፄ ይስሃቅ የተባሉት ንጉስ በቤተ እስራኤል ላይ በፈፀሙት ጭካኔ የተሞላው ሥራ ከ24 ዳኞች በላይ ድርጊቱን መቃወማቸውና መባረራቸው ከሥራ፣ በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን (1434 - 68) ንጉሡ ወታደሮቻቸው በንፁሃን ዜጎች ይፈፅሙት የነበረው ጭካኔ የተሞላው ድርጊት ላይ አቡነተክለሃይማኖት ሕዝባዊ ተቃውሞ መጥራታቸውና በዚሁ ለሞት መዳረጋቸው እንዲሁም አፄ ሱሴንዬስ ሃይማኖታቸውን ወደ ካቶሊክ በመቀየራቸው የተፈጠረው ሕዝባዊ ዓመፅ የመሳሰሉ ሕዝባዊ ዓመፆች በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡

ሕዝባዊነት ለመፍጠር የሚያስችሉ ያሉዋቸው አገር በቀል ባህላዊ ዕሴቶች ወኔነት፣ የጋራ ዓላማ፣ የተለያዩ አመለካካቶችና አድማሶች፣ ይቅርታ፣ ቃል የመሳሰሉ ይገኙባቸዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ሌቪን አባባል ከሆነ “ሕዝባዊነትን” ለመፍጠር ሁሉም ኢትዮጵያውያን መከተል ያሉባቸው እርምጃዎች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ቅርበት ማግኘት፣ በትልቅ አገራዊ ውይይቶች መገኘት መሳተፍ፣ የሕዝብን ፍላጎት ለይተው ቅድሚያ መስጠት በመጨረሻም በዚሁ መልኩ በህግ አውጪና በአስፈፃሚው አካል ላይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተፅዕኖ መፍጠር ይጠቅሳሉ፡፡ ይህን ለማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከባህላዊ ዕሴቶች አጣምሮ መሥራትና ለዚህም ነፃና ኃላፊነት የሚሰማው ፕሬስ መኖር ከፍተኛ ቦታ ሰጥተውታል፡፡

ፕሮፌሰሩ የኢትየጵያ የወደፊት ዕድል በይቅር መባባል ላይ የተመሰረተ ነው ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ በብሔረሰቦች መካከል ሆነ በቡድኖችና በፖለቲከኞች መካከል ያለው ክፍተትና ልዩነት ሊዘጋ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ የይቅርታ መንፈስ ብቻ ነው፡፡ ሰዎች ስህተት መፍጠራቸው ወንጀል አይደለም፡፡ የራስ መንፈስም የአገርም ወንጀል ወይም ክፍት የሚሆነው ስህተት አለመቀበልና ይቅርታ አለመጠየቅ፣ ተበዳይም ይቅር አለማለቱ ብቻ ነው፡፡

“ኢትዮጵያውያን እንዲህ ከአገር ቤት ሰዎች እየጠራ በአገር ጉዳይ ፊት ለፊት የሚያወያይ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት መሆናቸው ዕድለኞች ናቸው” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍለች ተቀራርበው መወያየታቸውን በተመለከተ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡

በየማነ ናግሽ

 
< Prev   Next >