| ለኢግዚቢሽን ማዕከል ይሰጥ የነበረው... |
|
|
| Sunday, 20 January 2008 | |
|
ለኢግዚቢሽን ማዕከል ይሰጥ የነበረው የጨረታ ዋጋ ቀነሰ ለተሳታፊ ኩባንያዎች የ30 በመቶ ቅናሽ ሊደረግ ነው በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሥር እየተዳደረ በሚገኘው የአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማዕከል በዓላትን ተንተርሰው ለሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶች ማዕከሉን ለመጠቀም ይሰጠው የነበረው የጨረታ ዋጋ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ወደ አንድ ሚሊዮን ብር ዝቅ አለ፡፡ ለፋሲካ የንግድና ባዛር ዝግጅት ጨረታ አንድ ድርጅት ብቻ ቀርቦ አሸናፊ ሆነ፡፡ ከአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማዕከል የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከ7 እስከ10 ቀናት ለሚዘጋጁ የንግድ ትርዒትና ባዛር በዋናነት በጨረታ የሚሰጡት የዘመን መለወጫ፣ የገናና የፋሲካ በዓላት የንግድና ባዛር ዝግጅቶች ናቸው፡፡ ለ2000 ዘመን መለወጫ በተካሄደው ጨረታ አሸናፊ ሆኖ የነበረው ሴንቸሪ ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግ.ማ ማዕከሉን ለአስር ቀን ለመጠቀም 2.5 ሚሊዮን ብር ሰጥቶ እንደነበር ይገልፃል፡፡ ይህም በማዕከሉ የጨረታ ሂደት ትልቁ ዋጋ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጎት እንደነበርም ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ም/ፀሐፊና የአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት አድማሱ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት በፋሲካ የንግድ ትርዒት ባዛር ዝግጅት በወጣው ጨረታ ግን አንድ ተጫራች ብቻ የቀረበና የተሰጠውም ዋጋ አንድ ሚሊዮን 55 ሺህ ብር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ይህም የጨረታ ዋጋ በዘመን መለወጫና በገና በዓላት ለተካሄዱት የንግድ ትርዒትና ባዛር ከተሰጠው ዋጋ ያነሰ ሊሆን መቻሉን አመልክተዋል፡፡ በገና የንግድና ባዛር ዝግጅት ማዕከሉን ለመጠቀም የተለያዩ ኩባንያዎች ተሳትፈው ሴንቸሪ ትሬዲንግ 1.7 ሚሊዮን ብር ዋጋ በመስጠት አሸናፊ ቢሆንም ድርጅቱ ከሁለቱ በዓላት ከሰጠው ዋጋ ያነሰ በመስጠቱና ሌላ ተወዳዳሪ ባለመቅረቡ ባቀረበው ዋጋ መሠረት አሸናፊ እንዲሆን መደረጉንም የአቶ ታምራት ገለፃ ያስረዳል፡፡ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ በቀረበበት የዘንድሮ የፋሲካ በዓል የንግድ ትርዒትና ባዛር ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበው የሴንቸሪ ፕሮሞሽን ባቀረበው ዋጋ ብቻ አሸናፊ እንዲሆን መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ዓመት በተከታታይ የተደረጉትንና የፋሲካን ባዛር ዝግጅት ጨረታ ያሸነፈው የሴንቸሪ ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውገ ጀማነህ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት ደግሞ በማዕከሉ በሚደረጉት ጨረታዎች ላይ ተወዳዳሪ ሆነን የምንቀርብ ኩባንያዎች ዋጋውን ሰቅለነው ቆይተን እንዲወርድ ማድረጉ ለሁሉም ወገን ጠቃሚ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡ የጨረታ ዋጋው ዝቅ እንዲል በመደረጉ ለተወዳዳሪዎችም ሆነ የንግድና የባዛሩ ዝግጅት ተሳታፊዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከማድረጉም በላይ በተለይ ሸማቾች እንዲህ ባሉ ባዛሮች የሚፈልጓቸውን ዕቃዎች በቅናሽ ዋጋ እንዲያገኙ እንደሚያደርጋቸው አመልክተዋል፡፡ እንደ አቶ ዘውገ ገለፃ የጨረታ ዋጋው ዝቅ በማለቱ ለተሳታፊ ኩባንያዎች ቀድሞ ለቦታ ይከፍሉ ከነበረው ክፍያ እስከ 30 በመቶ ዝቅ እንዲልላቸው የሚደረግ መሆኑንና የተሳታፊዎችንም ቁጥር እንዲበራከት ያደርጋል ብለዋል፡፡፡ ቀደም ብሎ በተካሄዱ የንግድ ትርዒቶች በካሬ ሜትር እስከ አንድ መቶ ብር ይከፈል የነበረ ሲሆን የመጫረቻ ዋጋው ዝቅ በማለቱ ግን የአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ዋጋ ተጨማሪ እሴት ታክስን አጠቃሎ ከ55 እስከ 70 ብር ሊደርስ እንደሚችልም አቶ ዘውገ ገልጸዋል፡፡ የፋሲካን የንግድና ባዛር ዝግጅት ለየት ለማድረግ በኢግዚቢሽን ማዕከሉ ውስጥ በቅናሽ ዋጋ የሚሸጡ ለበዓሉ የሚሆኑ እንደ በግ፣ በሬ፣ ቅቤ፣ ዶሮና የመሳሰሉት የሚሸጡበትን ቦታ እያመቻቹ ሲሆን ይህም ለማዕከሉ የንግድና ባዛር ዝግጅት ያልተለመደ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ላሉ አምራቾች በተለይ ለበዓሉ አስፈላጊ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸውን ግብዓቶች ለማቅረብ የሚችሉ አነስተኛ አምራቾች ማኅበራትና ለመሳሰሉት ቦታ በነፃ ለመስጠት ጭምር መታቀዱን የገለጹት አቶ ዘውገ ይህም በበዓላት ወቅት ኅብረተሰቡ በቅናሽ ምርቶቹን እንዲገባ ለማመቻቸት ታስቦ የተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዳዊት ታዬታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |