| ጠቅሞ ለመጠቀም |
|
|
| Sunday, 20 January 2008 | |
|
በተለያዩ ብሔራዊ በአላት፣ ልዩ የኤግዘቢሽንና የባዛር ዝግጅት፣ የደንበኞች ቀንና የመሳሰሉትን አጋጣሚዎች ተጠቅመው አምራቾች አስመጪዎችና ሌሎች ተቋማት ምርቶቻቸውና አገልግሎታቸውን በቅናሽ ዋጋ በማቅረብ ሸማቾቻቸውን የማገልገል ልምድ አላቸው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ያሉ አገሮችም እንዲህ ዓይነቱን አሠራር እያዳበሩት ነው፡፡ በአገራችን ግን በትክክል ሸማቹን ሊያግዙ የሚችሉ እንዲህ ዓይነት ዝግጅቶች አዘውትረው አይዘጋጁም፡፡ ቢዘጋጁም ከአንዳንዶቹ በስተቀር ትክክለኛ ቅናሽ ተደርጐባቸው አይቀርቡም፡፡ ለእንዲህ ዓይነት አገልግሎት ብቻ ተብለው የተዘጋጁ ቋሚ ሥራዎች አለመኖራቸው ደግሞ ለጉዳዩ ትኩረት አለመሰጠቱን ያሳያል፡፡ በሌሎች አገሮች አንድ ምርት ዓመቱን በሙሉ ተመሣሣይ በሆነ ዋጋ አይሸጥም፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዋጋው ቀንሶ ደንበኛው እንደልብ እንዲያገኘው ይደረጋል፡፡ ምርቱ ተፈላጊ ሣይሆን ቀርቶ ሣይሆን እያንዳንዱ ምርት ለደንበኞች ክብር ሲባል የደንበኞች ቀን በማለት ወይም ልዩ የቅናሽ መገበያያ ቀናትን አዘጋጅተው ደንበኞችን የእድሉ ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት እንዲሰርፅ ደግሞ ከፍተኛው ድርሻ የሚወስዱትና ሁኔታዎችን የሚያመቻቹት እንደ ሸማቾች ማህበራት ያሉ ተቋማት ናቸው፡፡ ኩባንያዎቹ በቅናሽ ዋጋ ለሸማቹ እንዲደርስ ሲያደርጉ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን ትርፍ በመቀነስ ወይም (ፕሮፊት ማርጅንን በማጥበብ) እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ዕቃ 100 ብር ሲሸጡ ቆይተው ለደንበኞች ብለው በከለሉት ቀን አንዱን ወር ወይም አስራ አምስቱን ቀን የሚሸጡትን ዕቃ ከ25 እስከ 50 በመቶ በማውረድ ይሸጣሉ፡፡ ይህም ከ365 ቀናት ውስጥ 30 ወይም 15 ቀን ብቻ ለደንበኞቻቸው በመስጠት ብዙዎችን ያረካሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሂደት ብዙዎቹ ኩባንያዎች ተመሣሣይ የሆነ አሠራር ቢከተሉ ለሸማቹ ምን ያህል ጥቅም እንደሚሠጥ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በአገራችንም እንዲህ ዓይነቱን ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ሻጭና ገዥው ጤናማ ግንኙነት እንዲኖራቸው በማድረጉ ረገድም የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ አቅም የሌለው ሸማች በእንዲህ ዓይነት ዝግጅቶች የበለጠ ተጠቃሚ ስለሚያደርገው ጉዳዩ ሊመለከታቸው የሚችሉ ተቋማት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ያሉ ተቋማት ወይም የሸማቾች ማህበራት አንድ ልዩ ቦታ በማሰናዳት በተወሰነ ጊዜ ልዩነት በቅናሽ ዋጋ ምርቶች የሚሸጡበትን ማዕከላትን በመገንባት እገዛ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ኃላፊነት እንዳለባቸውም መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በአንድ ወይም በተለያዩ ማዕከላዊ ቦታዎች የሚቋቋሙ የቅናሽ ማዕከላትን በመገንባት ምርቶቻቸውን በቅናሽ ዋጋ ለመሸጥ ፍላጐት ያላቸው ኩባንያዎች በማሰባሰብ ሥራውን መጀመር ይቻላል፡፡ አለመታደል ሆነና በአንድ ወቅት በአንድ አጋጣሚ ዋጋው የተሰቀለ ዕቃ ለዋጋው መወደድ ምክንያት የሆኑ አጋጣሚዎች ቢስተካከሉ እንኳን ዋጋውን ቀንሶ የመሸጥ ባህል በብዙ ነጋዴዎች የተለመደ ባይሆንም እንዲህ ዓይነት አሠራሮችን ለመቅረፍም ይረዳል፡፡ በአገራችን የተለምዶ የግብይት ስርዓት ደንበኛን እንደ ደንበኝነቱ የመንከባከብ ባህል በተፈለገው መጠን ሊያድግ አልቻለም፡፡ እንደውም የለም ወደሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሸማቹ የግድ መግዛቱ አይቀርም በሚል አመለካከት ብዙዎቹ ነጋዴዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ድክመት ይታይባቸዋል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች ራሳቸውን ከፍ በማድረግ ለደንበኞች የሚሰጡት አገልግሎት አርኪ አይደለም፡፡ ይህም በሸማቹና በነጋዴው መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ አንድ ነጋዴ ወይም አገልግሎት ሰጭ አዘውትሮ ለሚጐበኘው ደንበኛ ክብር መስጠት ይኖርበታል፡፡ ክብር ብቻ ሣይሆን በተወሰኑ ጊዜያት ልዩነት ለደንበኛው ወይም ሸማቹ እውነተኛ በሆነ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ሊያገለግለው ይገባል፡፡ ይህ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት በተስፋፋባቸው አገሮች ወይም የደንበኛ ትርጉም በገባቸው የውጭ ኩባንያዎች (አገልግሎት ሰጭዎች) የተለመደ ነው፡፡ ለደንበኞቻቸው ምስጋና የሚያደርሱበትንና ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸው በቅናሽ የሚያቀርቡበት ጊዜያትን ያመቻቻሉ፡፡ ምርቶቻውን ተረክበው በትክክለኛ መንገድ ለሸማቹ በችርቻሮ ያቀረቡ አከፋፋዮችንና ወኪሎቻቸውን ያበረታታሉ፡፡ ይሸልማሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ የማያቋርጥ የግብይትና የደንበኞች አያያዝ ስርዓት ሸማቹን ብቻ ሣይሆን ራሳቸውንም ይጠቅማሉ፡፡ ብዙ ደንበኞችን ያፈራሉ፡፡ በአገራችንም እንዲህ ዓይነቱ ዘመናዊ የሻጭና ገዥ ግንኙነት ሊጠናከር የሚችልበት አገልግሎት በሁሉም መስክ ሊስፋፋ ይገባል፡፡ በሌላ መልኩ ለደንበኞች ተብለው የሚዘጋጁ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የደንበኞችን ፍላጎት ከማርካት በተጨማሪ በኩባንያዎች መካከል ውድድር እንዲፈጠርና ሸማቹ በዚህ ውድድር የተሻለውን እንዲመርጥ እድል ይፈጥርለታል፡፡ በናታን ዳዊት |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |