| “ዛሬ የምንፈርመው ስምምነት የመጪውን... |
|
|
| Sunday, 20 January 2008 | |
|
“ዛሬ የምንፈርመው ስምምነት የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ህልውና የሚጐዳ እንዳይሆን እንጠነቀቃለን” አቶ ተስፋዬ ወልደምህረት አቶ ተስፋዬ ወልደ ምህረት በናይል ተፋሰስ አገራት ትብብር የመተማመን ግንባታና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የጋራ ራዕይ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አስተባባሪ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሸለቆዎች ልማት ጥናት ባለስልጣን በሚባል መሥሪያ ቤት ከኤክስፐርት እስከ ተጠባባቂ ፕላኒንግ ዲፓርትመንት ኃላፊ፣ በውሀ ሀብት ሚኒስቴር የሴክተር ስትራቴጅና በውሀ ሀብት የልማት ፕሮግራምና የፖሊሲ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡ የፖሊሲ ትንተና ዝግጅት ቡድን መሪም ነበሩ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙትን አቶ ተስፋዬን በናይል ተፋሰስ አገራት ትብብር ዙሪያ ሪፖርተራችን ሀይሌ ሙሉ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ትብብር/ናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ከተመሰረተ ቆይቷል፡፡ እየሰራቸው ያሉት ሥራዎች ምንድን ናቸው? አቶ ተስፋዬ፡- የናይል ወንዝ ብዙ አገሮች የሚጋሩት ወንዝ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህን ውሀ አጠቃቀምና አያያዙን አገሮች በሙሉ የሚሳተፉበት ካልሆነ በስተቀር በአንድ ወይም በሌላው አገር ጥረት ወይም ፍላጐት ዘላቂ የሆነ መንገድ መቀየስ አይቻልም፡፡ የትብብሩ ዋና አላማ በአስሩ ተፋሰሱ አገራት የሚታየውን ስር የሰደደ ድህነት ለማስወገድ፣ ይህንን ውሀ በጋራ በመጠቀምና በማስተዳደር በልማቱ አካሄድም በጋራ በመስራት ችግርን ለመቅረፍ ነው፡፡ ሁለተኛ የተፋሰሱን አካባቢ ብንመለከት እጅግ የተሸረሸረና የተራቆተ ነው፡፡ ይህንን የተራቆተ አካባቢ ወደ ነበረበት በመመለስ ጥቅም እንዲሰጥ ወደሚቻልበት ደረጃ ለመመለስ ካስፈለገ የግድ የእነዚህ አገራትን በጋራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ይህ ሌላው አላማ ነው፡፡ በሁሉም አገሮች ከልማት ጋር የማይጣጣም የሕዝብ እድገት አለ፡፡ ይህ የሕዝብ እድገት ደግሞ በተፋሰሱ ያለው ሀብት አጠቃቀም ላይ ከባድ ተፅዕኖ እያሳደረ መጥቷል፡፡ ስለዚህ ከሕዝቡ ብዛት ጋር ሊመጥን በሚችል መንገድ ልማትን ማካሄድ እንዲቻልና በዚህ ዙሪያም ለመሥራት ነው፡፡ ሌላው አላማ ተብሎ የሚታሰበው የናይል ተፋሰስ ክልል በፖለቲካ አለመረጋጋት የሚታወቅ ነው፡፡ አለመረጋጋቱን ምን ፈጠረው? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ብዙ የሚያከራክር ነው፡፡ በምንም ይሁን በምን ያለመረጋጋት አለ፡፡ ይህንን አለመረጋጋት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ከዚህ ተፋሰስ ካለው ሀብት አጠቃቀም የሚጠቀስ ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ ኢትዮጵያን ብንወስድ ለበርካታ ዘመናት በጦርነት ስትታመስ የቆየችና በርካታ ጦርነቶችን ያሳለፈች ሀገር ነች፡፡ ከጐረቤት ሀገር ጭምር ወረራ የሚካሄድባት አገር መሆኗን የሚጠቅሱ አንዳንድ ምሁራን አገራቱ ወረራ የሚፈጽሙት አባይን መነሻ ለመቆጣጠር ካላቸው ፍላጐት ነው ይላሉ፡፡ በሌሎች አገሮች መካከል ያለው ያለመግባባትም ቢሆን የተፈጥሮ ሀብት ለመቆጣጠር የሚመነጭ ችግር ነው ብለውም ይገልፃሉ፡፡ እነዚህን አለመግባባቶች ለማስተካከል ወይም ደግሞ ተገቢ ቦታቸውን አስይዞ አገራቱ በጋራ ጥረት እንዲሰሩ እየታሰበ ነው፡፡ የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ትብብር የተመሰረተው እ.ኤ.አ በ1999 ነው፡፡ አገራቱ ከዚያ በፊት በተለያየ መንገድ ግንኙነት ያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት የነበሩት ማንኛውም ዓይነት ትብብርች ለአሁኑ የራሱ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም ይህ ነው የሚባል ውጤት አልነበራቸውም፡፡ ፕሮጀክቶቹ ተፋሰስ አቀፍ የሆኑ በየአገራቱ ተግባራዊ የሚሆኑ፣ ለተፋሰሱ ጥቅም የሚውሉ በተለይ አቅም ግንባታ ላይ የሚያተኩሩ፣ ትብብሩ እንዲሰምር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ የጋራ ራዕይ ፕሮጀክቶች የሚባሉ ናቸው፡፡ ወደ ሰባትና ስምንት የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በሙሉ የፕሮጀክት ማስተባበሪያ ክፍል አላቸው በዘጠኙም አገራት ተግባር ላይ እየዋሉ ናቸው፡፡ የፕሮጀክቶቹ ዓላማ የየሀገራቱን አቅም መገንባት ነው፡፡ አቅም ስንል የሰው፣ የተቋም፣ የአደረጃጀት ወይም የቴክኒክ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ የተፈጥሮ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል አቅም መፍጠር ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የአባይ ተፋሰስ አካባቢ የተሸረሸረና የተራቆተ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢ እጅግ የተጐዳ ነው፡፡ ይህ አካባቢ ተጐዳ ማለት ደግሞ ግብጽም ሱዳንም ቀላል የማይባል ጉዳት እንዲደርስባቸው ያደርጋል፡፡ የአባይ መነሻ የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢ በመሆኑ እዚህ አካባቢ መራቆት ተከሰተ ማለት ውሀውን ማጣት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአካባቢ ዙሪያም እንደዚሁ ራሱን የቻለ ፕሮጀክት አለን፡፡ በኢትዮጵያና በሌሎች የተፋሰስ አገራት እየተሰራበት ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡ የሀይል ምንጭ ንግድም አንዱ ነው፡፡ የሀይል ምንጭ አቅርቦትን በተመለከተ አገሮች በሙሉ እኩል እምቅ አቅም የላቸውም፡፡ በሀይል ምንጭ ረገድ ኢትዮጵያ ጥሩ እምቅ አቅም አላት የምትባል አገር ናት፡፡ የሀይል ፍላጐት ያላቸው አገራት ከውሀ በሚገኝ ሀይል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን ሀይል አፍልቆና አጐልብቶ ለሁሉም ሊጠቅም በሚችል መንገድ ለማዋል ራሱ ፕሮጀክቱ ተቀርፆ እየተሰራ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህ በአጠቃላይ የጋራ ራዕይ ፕሮጀክት የምንላቸውና ቅድም እንዳልኩት አቅም ለመገንባት፣ የልማት ሁኔታን ለመፍጠር፣ አገሮችን በማቀራረብ ረገድ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በተለየ ናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ የቀረፃቸው ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በሁለት ተከፍለው ነው ተግባራዊ እየሆኑ ያሉት፡፡ ተፋሰሱ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ አንደኛው ምሥራቅ ናይል ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ሱዳንን ግብጽን የሚያካትት ሆና ዋና ጽ/ቤቱ አዲስ አበባ ይገኛል፡፡ (ኢንትሮ) ኢስተርን ናይል ቴክኒካል ሪጅናል ኦፈስ የሚባል ቢሮ አለው፡፡ ይህ ቢሮ በሶስቱ አገራት ውስጥ የሚካሄድ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን የሚያከናውን ነው፡፡ መስኖ ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች፣ የጐርፍ መከላከል ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ የውሀ አስተዳደር ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡ ሪፖርተር፡- በአገሮች መካከል እየተካሄደ ያለው ድርድር ምን ደረጃ ላይ ደርሷል? አቶ ተስፋዬ፡- ድርድሩ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1997 ነው፡፡ ድርድሩን በአንፃራዊነት ስናየው ብዙ ዓመታት የፈጀ ይመስለናል፡፡ የአባይ ተፋሰስ አገሮች ትብብር ከመፈጠሩ በፊት ድርድሩ ነበር፡፡ ላለፉት አስር ዓመታት ድርድሩ በሁለት ደረጃዎች ሲካሄድ ቆይቷል፣ ሚኒስቴር ደረጃና በቴክኒክ ደረጃ፡፡ የአባይ ተፋሰስ ትብብር የሚኒስትሮች ምክር ቤት አለው፡፡ ይህ ምክር ቤት የየሀገራቱ የውሀ ሀብት ሚኒስትሮች አባል የሚሆኑበት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ፖሊሲ የሚቀርጽ አካል ነው፡፡ ለዚህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቴክኒክ ድጋፍ ወይም ምክር የሚሰጥ የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ በስሩ አለ፡፡ ስለዚህ ድርድሩ መንግሥት በወከላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ይካሄዳል፡፡ ከኤርትራ ውጭ ያሉት ዘጠኙ አገራት በዚህ ድርድር ይሳተፋሉ፡፡ ሪፖርተር፡- ኤርትራ በድርድሩ ያልተሳተፈችው ለምንድነው? አቶ ተስፋዬ፡- በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም አገር በድርድሩ ውስጥ መግባት ይችላል፡፡ ታዛቢ ልሁን ያለችው ራሷ ኤርትራ ነች፡፡ ኤርትራ አባል ለመሆን አልጠየቀችም፡፡ ትመጣለች ብለን ግን እንጠብቃለን፡፡ ድርድሩ በዘጠኙ አገራት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ለአስር ዓመታት ያህል ሲካሄድ የቆየው ድርድር አብቅቷል፡፡ በሚኒስትሮቹና በቴክኒካል ሰዎቹ አማካይነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ጁን 2007 ላይ አብቅቷል፡፡ ሰነዱ 39 አንቀጾች አሉት፡፡ ከእነዚህ ሰላሳ ዘጠኝ አንቀጾች ውስጥ በአንድ ንዑስ አንቀጽ ላይ ብቻ መግባባት ላይ አልተደረሰም፡፡ ሚኒስትሮች ያልተግባቡበት ይህ አንድ ነጥብ ለመሪዎች ስብሰባ ተላልፏል፡፡ ስለዚህ የአገራቱ መሪዎች ተገናኝተው ውሣኔ ባላገኘው ጉዳይ ላይ ተነጋግረው መፍትሄ ይሰጡታል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ሪፖርተር፡- ሚኒስትሮቹ ስምምነት ላይ ያልደረሱበት ነጥብ ምንድነው? አቶ ተስፋዬ፡- ሚኒስትሮች ስምምነት ያልደረሱበት ጉዳይ የውሀ ደህንነትን የሚመለከት ነው፡፡ ግብጽና ሱዳን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያነሱት ነገር አለ፡፡ የውሀውን አጠቃቀም በተመለከተ ወደኋላ ብንሄድ ከቅኝ አገዛዝ ጊዜ ጀምሮ ከዚህ በፊት የተፈረሙ ውሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የ1959 ውል የሚባል አለ፡፡ እኛን አይመለከትም፤ የውሉ አካል አይደለንም፡፡ ይህ ውል ሱዳንና ግብጽ የውሀውን አጠቃቀም በሚመለከት የተፈራረሙት ነው፡፡ ውሀውን የተከፋፈሉበት ውል ነው፡፡ ሌላው 1929 የሚባል በሌሎች አገሮች የሚጠቀስ ውል አለ፡፡ እንግሊዝ ከቀኝ ገዥዎቹ በኩል፣ ግብጽ ደግሞ ከሌላ ወገን ሆነው የተዋዋሉት ውል አለ፡፡ ከግብጽና ሱዳን ውጭ ያሉት ሰባቱ የተፋሰስ አገራት እነዚህ ውሎች አይመለከቱንም ባዮች ናቸው፡፡ ውሎቹ በአሁኑ የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ ቦታ የላቸውም ብለው ያምናሉ፡፡ በጋራ ራዕያቸው ውስጥ አገራቱ ፍትሀዊ የሆነ የውሀ አጠቃቀምና ጉዳት የሚያደርስ የውሀ አጠቃቀም እንከተላለን ብለው ተስማምተዋል፡፡ እነዚህ ራዕዮች በዓለም አቀፍ የውሀ ህግ ተቀባይነት አላቸው፡፡ የውሀ አጠቃቀሙ ዝርዝር ሲሰራ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባቱ አገሮች የያዙት አቋም ፍትሀዊ አጠቃቀም በሚለው አንቀጽ መሠረት ዝርዝሩ ይታያል የሚል ነው፡፡ ግብጽና ሱዳን ግን ከዚህ በፊት የተፈራረሙት ውሎች ሊታዩ ይገባል ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ የተካሄደው ድርድር ብዙ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ሚኒስትሮቹም ከዚህ በላይ ድርድር ቢካሄድ ፈቅ የሚል ነገር አይኖርም የሚል እምነት በማሳደራቸው ጉዳዩን ለአገራቱ መሪዎች አስተላልፈውታል፡፡ እስከ አሁን ድረስ መሪዎቹ አልተሰበሰቡም፡፡ የወቅቱ ሊቀመንበር ኡጋንዳ ነች ስለዚህ መሪዎቹ ኡጋንዳ ውስጥ ይገናኛሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ሪፖርተር፡- ጉዳዩ በመሪዎቹ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል ብለው ያስባሉ? አቶ ተስፋዬ፡- ሁሉንም አገሮች ስናይ እስከ አሁን የመጣንበትን የድርድር ሂደት ያደንቃሉ፡፡ ትብብሩን ሁሉም አገራት ይፈልጉታል፡፡ ምክንያቱም አገራቱ ከዚህ ውሀ በላይም ግንኙነት መፍጠር ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም አገራት ተመልሰው ወደ ፍጥጫ ለመሄድ ፍላጐት ያላቸው አይደሉም፡፡ ይህንን ያህል ዓመታት የተጓዙበትን ሥራና ወደፊት ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን ነገርም እንዲሁ በቀላሉ ያፈርሱታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለዚህ የመግባባቱ ሁኔታ ሊጠናከር ይችላል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ሪፖርተር፡- አገራቱ ስምምነት ላይ ከደረሱ ቀጣዩ እርምጃ ምንድነው? አቶ ተስፋዬ፡- የተፋሰሱ አገራት እየተደራደሩ ያሉት መዋቅሩ ላይ ነው፡፡ ይህ መዋቅር ህግ ሆኖ እንዲወጣ ነው የሚፈለገው፡፡ ከተስማሙ አገራቱ እንዲያፀድቁት ይጠበቃል፡፡ የትብብር ማዕቀፉ ሁለት አላማ ነው ይዞ የሚመጣው፡፡ በዚህ የህግ ማዕቀፍ ላይ በየሀገራቱ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበት ሕዝቡ እንዲያውቀው ተደርጐ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ፓርላማ ይሄዳል፡፡ የየሀገራቱ ፓርላማ ካፀደቁት የናይል ውሀ አጠቃቀም በሁሉም አገራት ተቀባይነት አግኝቶ ህጋዊ ማዕቀፍ ሆኖ ሥራ ላይ ይውላል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ የናይል ወንዝ ኮሚሽን ይቋቋማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ የናይል ወንዝ ኮሚሽን ህጐችን ያስፈጽማል፡፡ በማዕቀፉ ውስጥ የተጠቀሱ ነገሮች በሙሉ በዝርዝር ሲወጡ የኮሚሽኑ ሥራ ህጐችን ማስፈፀም ይሆናል፡፡ ሪፖርተር፡- ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ለማከናወን የሚረዳትን የውጭ እርዳታ እንዳታገኝ ግብጽ ተፅዕኖ ስትፈጥር መቆየቷ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ድርድሩ ከተጀመረ በኋላ በዚህ በኩል ለውጥ ታይቷል? አቶ ተስፋዬ፡- ለውጥ ታይቷል ብየ አስባለሁ፡፡ በዓለም ባንክ በኩል የመፍታታት ሁኔታ አለ፡፡ በሌሎቹም እንደዚሁ የተፋሰሱ ትብብር ከተመሰረተ በኋላ ለውጥ አለ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ድሮ የታችኞቹ አገራት ፈቃድ ካልተገኘ በስተቀር ግድቦች አይሰሩም የሚባል ነገር አለ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ከአፍሪካ ልማት፣ ከዓለም ባንክና ከሌሎች እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በሚገኙ ድጋፍ በተለይ በአባይ አካባቢ በርካታ ቁጥር ያላቸው ግድቦች ለመሥራት የሚያስችል ፕሮግራም ቀር”ል፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች በሙሉ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ ላያሳድሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ እነዚህ እየተሰሩ ያሉት ነገሮች አገራት በጀመሩት መቀራረብ የተነሳ ስለሆነ ለውጡ አለ፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ይሄዳል የሚለው የሚታይ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የታችኞቹ አገራት ሁልጊዜ በጐ አመለካከት ይኖራቸዋል፣ ይህንን ጥያቄያቸውንም ከጥያቄ ያነሱታል ማለት አይደለም፡፡ ግን ለውጥ አለ፡፡ አገራቱ ፕሮጀክት ቀርፀው መንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ በአበዳሪዎቹና በእርዳታ ሰጪዎቹ ላይ ለውጥ ያለ ይመስለኛል፡፡ ሪፖርተር፡- የተፋሰሱ አገራት መተባበርና መጠቃቀም አለባቸው የሚለው ነገር ሲነሳ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአገራቱ አቅም እንዴት ይገለፃል? አቶ ተስፋዬ፡- ሁሉም አገሮች እኩል አቅም የላቸውም፡፡ ይሁንና የውሀው ባለቤት ናቸው፡፡ እስከ አሁን ያለው ጥናት የሚያሳየው ኢትዮጵያ የውሀ ሀይል ለማመንጨት ምቹ መልክአምድራዊ አቀማመጥ አላት፡፡ ውሀውም አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ አገራት ውጭ ላሉ የአውሮፓ አገራት ጭምር ሀይል የማቅረብ አቅም እንዳላት ይነገራል፡፡ ለምሳሌ ከናይል ፕሮጀክቶች አንዱ የኢትዮ ሱዳን ፓወር ኢንተርኮኔክሽን ነው፡፡ ይህ ሥራው በጣም ተፋጥኖ የሄደ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያ ሀይል ታፈልቃለች፡፡ ሱዳን ሀይል ከእኛ ትወስዳለች፡፡ በሱዳን በኩልም ወደ ግብጽ ይሄዳል፡፡ ይህ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያሳይ ነው፡፡ የመስኖ ልማትን ስንወስድ እስከ አሁን ባለው ጥናት ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር ሱዳን በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት አላት፡፡ ሱዳን የምታመርተው የግብርና ምርት ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገሮች ሊተርፍ ይችላል፡፡ በጋራ እስከሰሩ ድረስ በጋራ የመጠቀም ሀኔታ ይሰፋል፡፡ በገበያም ይተሳሰራሉ በኢኮኖሚ ልማትም ይተሳሰራሉ፡፡ ጥቅሙም የጋራ ይሆናል፡፡ ግብጽን ብንወስድ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲመዘን የውሀውን አጠቀቀም የሚመለከት የተቋም አቅም አላት፡፡ በርካታ የውሀ ባለሙያዎች አሏት፡፡ ጠንከር ያሉ የውሀን ጉዳይ የሚመለከቱ ተቋሞች አሏት፡፡ ይህ አቅም ለሌሎች አገሮችም ሊደርስ ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- በተፋሰሱ አገራት ትብብር የኢትዮጵያ ሚና ምንድነው? አቶ ተስፋዬ፡- ኢትዮጵያ አንድ አገር ናት፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የውሀ መገኛ እንደመሆኗ መጠን እንደ አንድ አባል ብቻ የምትታይ ሳትሆን ለትብብሩ ቁልፍ ሚና ያላት አገር ናት፡፡ አገራቱ በትብብሩ ያላቸው ቦታ እኩል ነው፡፡ የውሀ ደህንነትን በሚመለከተው ሀሳብ ላይ በተደረገው ድርድር ውጤቱ 7ለ2 ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ መታወቅ ያለበትና ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ እኛ የመጪው ትውልድ ባለዕዳዎች ነን፡፡ የአሁኑ ትውልድ የሚገባውን ያህል አግኝቶ ለቀጣይ ትውልድ ይህን ሀብት፣ ይህን ውሀ ማቆየት አለበት፡፡ ዘላቂ ልማት ማለት ይህ ነው፡፡ የመጪው ትውልድ ባለዕዳ እንደመሆናችን መጠን ዛሬ የምንፈርመው ስምምነት የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ህልውና የሚጐዳ እንዳይሆን እንጠነቀቃለን፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጋ የምትንቀሳቀስ አገር ናት፡፡ እስከ አሁን የተደረገው ጥረትም ይህንን ነው የሚያሳየው፡፡ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በጥንቃቄ ስትሳተፍ ቆይታለች፡፡ ሪፖርተር፡- የውሀ ባለሙያዎችን በማፍለቅ ደረጃ ኢትዮጵያ እየሰራች ያለችው ምንድነው? አቶ ተስፋዬ፡- ከ1970ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በውሀ ጉዳይ ላይ በዚች አገር ጠቃሚ የሆነ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የአርባ ምንጭ ውሀ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ተቋሙ ብዙ የውሀ ባለሙያዎችን ያፈልቅ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ብዙ ኢትዮጵያውያን በውሀው ሴክተር የሚሰለጥኑት ህንድ አገር በመሄድ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ባለሙያዎች ለምን በአገር ውስጥ እንዲሰለጥኑ አይደረግም? የሚሉ ሰዎች ተገኝተው መንግሥትም አምኖበት የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ተቋቁሞ ብዙ ባለሙያዎችን አፍርቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በአገሪቱ ያሉት ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች የውሀ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ናቸው፡፡ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህዳር ዩኒቨርሲቲና አዳማ ዩኒቨርሲቲ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ መለስተኛ ባለሙያዎችን በማሰልጠን በኩልም ቢሆን በየክልሉ ት/ቤቶች አሉ፡፡ ውጭ አገርም እየሄዱ የሚሰለጥኑ አሉ፡፡ መንግሥት ከማንኛውም ጊዜ በላይ ለውሀው ልማት ትኩረት የሰጠ ስለሆነ በመስሪያ ቤት ደረጃ እንዲጠናከር ይፈልጋል፡፡ የውሀ መስሪያ ቤት በሚኒስቴር ደረጃ የተቋቋመውም በቅርቡ ነው፡፡ ይህ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ በክልሎች ደረጃም የውሀ ቢሮዎች አሉ፡፡ አሁን የተሰራውና በአዋጅ የወጣው መልካም ነገር የተፋሰስ መስሪያ ቤት ባለስልጣኖች መቋቋም ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የአባይ ተፋሰስ ባለስልጣን መስሪያ ቤትን ለማቋቋም አዋጅ ፀድቋል፡፡ ሥራው የሚጀምርበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ አባይ ስንል አማራን ኦሮሚያን ቤንሻንጉል ይመለከታል፡፡ ሶስት ክልሎች ይህንን ውሀ ይፈልጋሉ፡፡ በዚያ አካባቢ ምን መልማት እንደሚችል፣ ምን ፕሮጀክቶች እንዳሉ በማስተር ፕላን ደረጃ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡ እሱን ተግባራዊ ለማድረግ የእነዚህን ክልሎች ጥቅምና የተፋሰሱን ህልውና ባገናዘበ መልኩ ሥራውን ለመምራት የሚያስችል መሥሪያ ቤት ነው - የአባይ ተፋሰስ ባለስልጣን፡፡ በአባይ የተቋቋመው መሥራያ ቤት ስኬታማ ከሆነ እንደዚሁ ዓይነት መስሪያ ቤት በሌሎቹም ወንዞችና ክልሎች ላይ እናቋቁማለን የሚል ነው አላማው፡፡
አቶ ተስፋዬ፡- የናይል ሚድያ ኔትወርክ እንደአለመታደል ሆኖ በታሰበው መንገድ አልሄደም፡፡ የሚዲያ ኔትወርኩ አላማ በአገራት መካከል መተማመን መፍጠር ነው፡፡ መተዋወቅ እንዲኖርና የአባይ ተፋሰስ ትብብር አላማ በሕዝቡ እንዲሰርጽ ማድረግ ነው፡፡ ከሕዝቡ የሚነገረውን ነገር አስተያየት ለመሰብሰብ፣ የአባይ ተፋሰስ ትብብር የሚሰራቸው ነገሮችም በሕዝቡም በመንግሥትም እንዲታወቅ ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመ ማህበር ነበር፡፡ ሕዝቡ ያለውን ጥያቄ እንዲያነሳ የጋዜጠኞች ሚና ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብሎ ቢሮአችን ያምናል፡፡ ከ2005 ጀምሮ ይሄ ጥረት እየተደረገ ያለበት ነገር ሆኖ በተፋሰስ አገራት ደረጃ “ሪጅናል ናይል ሚዲያ ኔትወርክ” የሚባል የጋዜጠኞች ማህበር ተቋቁሟል፡፡ ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በየአገሪቱ ናይል ሚዲያ ኔትወርክ ናሽናል ቻፕተርስ የሚባል ማህበር ተቋቁሟል፡፡ አሁንም ከአገር አገር ይለያይ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን የሚፈለገውን ያህል እየሰሩ አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- ምንድነው ችግሩ? አቶ ተስፋዬ፡- አንዱ ችግር አቅም ይመስለኛል፡፡ በዚህ ሚዲያ ኔትወርክ አባል የሆኑ ጋዜጠኞች ለሚሰሩት ሥራ በጊዜው ድጋፍ አለማግኘት በሚጠበቀው መልኩ እንዳይንቀሳቀሱ ችግር የፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ የበለጠ ግን ጋዜጠኞቹ ለተፋሰሱ ያላቸው እውቀት ውስን መሆኑ ዋናው ችግር ነው፡፡ ስለ ተፋሰሱ አገራትና ስለአጠቃላይ ስለተፋሰሱ ሥራ ብዙ እውቀትና ብዙ መረጃ እንፈልጋለን የሚሉ ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ ጥያቄው ትክክል ነው፡፡ ይሁንና በተቻለ መጠን ይህንን ሁኔታ አገራዊ ጉዳይ አድርጐ ማየት እንደ ልዩ ተልዕኮ አድርጐ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከእያንዳንዱ ሚዲያ ኦርጋናይዜሽን ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ይህንን ጉዳይ ያውቃሉ? ምናልባት እነዚህ አባል የሆኑ ጋዜጠኞች አለቆቻቸው እየተሳተፉ ስላሉበት ኔትወርክ ብዙ የማያውቁ ከሆነ ተሳትፎአቸውን ይገድበው ይሆናል ብለን አስበን እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ለጋዜጦች ዋና አዘጋጆች፣ ለኤሌክትሮኒክ ሚዲያ የፕሮግራምና የዴስክ ኃላፊዎች ገለፃ ሰጥተን መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ነገር ግን በቂ የሆነ ግንዛቤ እንደሚፈልጉ ተግባብተናል፡፡ በተግባባነው መሠረት ሥራ ላይ ይውላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በላይ ግን ሥራው ትጋት ይጠይቃል፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር የእኛ አገር ጋዜጠኞች የግብጽ ጋዜጠኞችን ያህል አይሰሩም፡፡ የግብጽ ጋዜጠኞች በአባይ ዙሪያ ሰፊ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ስብሰባ ሊካሄድ ታስቦ ይቅርና በአንድ ነገር ላይ የወሬ ወሬ እንኳን ቢሰሙ ስለጉዳዩ ፈልፍለው አውጥተው ብዙ ነገር ይጽፋሉ፡፡ የእኛም ጋዜጠኞች እንደዚህ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ውሀ ለህልውናችን፣ ለልማታችን ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በአግባቡ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ በሚደረገው ሂደትም ተፅዕኖ ማሳደር እንዲችሉ እንፈልጋለን፡፡ የምንፈራረመው ውል ጥሩ ውል እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ድርድሩም ውጤት እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡ ስህተት እንዳንሰራ እንፈልጋለን የመጪው ትውልድ ጥቅምና ህልውና እንዳይጐዳ እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ የጋዜጠኞች ሚና ወሳኝ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የተከሰተውን ችግር ለማስተካከል በኩል ምን የታሰበ ነገር አለ? አቶ ተስፋዬ፡- እያሰብነው ያለ ነገር አለ፡፡ የካቲት ውስጥ ሪጅናል ስብሰባ ለማካሄድ ወስነናል፡፡ በነገራችን ላይ በአሁኑ ሰዓት የናይል ማዲያ ኔትወርክ ሊቀመንበር አቶ አማረ አረጋዊ ናቸው፡፡ በዚያ ስብሰባ የሚዲያ ኔትወርኩ ድክመትና ጥንካሬው ይታያል፡፡ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ይታያሉ፡፡ የተዳከሙበትን ሁኔታ ለመለወጥና ሁኔታውን ለማሻሻል ይሄ ስብሰባ ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ አሁን የበለጠ ጋዜጠኞች እንዲሳተፉ ሚኒስትሮች በወሰኑት መሠረት የአባይ ተፋሰስ አገራት “ናይል ዴይ”ን በየዓመቱ ያከብራሉ፡፡ ውሣኔው የተላለፈው አምና ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ ሲሆን ከሚሌኒየሙ ጋር በተያያዘ ፌብሩዋሪ 22 ኢትየጵያ ውስጥ እንዲከበር ተወስኗል፡፡ የ”ናይል ዴይ” ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ ሚዲያን የሚመለከትም ኮሚቴ አለ፡፡ ከበዓል በፊትና በኋላ በአባይ ተፋሰስና በአጠቃላይ በትብብሩ ዙሪያ ሕዝቡን ማሳወቅ የሚያስችል ሥራ እንሠራለን ብለን እናምናለን፡፡ የሚዲያ ኔትወርኩም አንዱ ሥራ ይሄ ይሆናል ብየ አምናለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ከተለያዩ የተፋሰሱ አገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች ውይይት ሲያደርጉ በባለሙያዎች ገለፃ ይደረግላቸዋል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ካይሮ በተካሄደው የናይል ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኞች ውይይት ላይ ማብራሪያ የሰጡት ባለሙያዎች ሁሉም የመጡት ከግብጽ ነበር፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሌሎች አገሮች ባለሙያዎች በአባይ ተፋሰስ ላይ ማብራሪያ ያልሰጡበት ምክንያት ምንድነው? አቶ ተስፋዬ፡- ስለዚህ ስብሰባ በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ስብሰባው በደንብ ያልታሰበበት አጀንዳም ያልነበረው፣ አላማው ምን እንደሆነ ያልታወቀ ስብሰባ ነበር፡፡ ስብሰባውን ያካሄደው የአባይ ተፋሰስ ቤዚን እኔ በምሠራበት ፕሮጀክት ውስጥ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ የሆነ ግብፃዊ ነው፡፡ አሁን ከሥራ ታግዷል፡፡ የተሠራው ሥራ አጀንዳ ተቀርፆበትና በደንብ ታስቦበት የተከናወነ ስላልነበር አሁን የተባለው ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለተካሄደው ስብሰባ ሪፖርት አልደረሰንም፡፡ ያን መድረክ ለምን እንደተጠቀሙበት አላውቅም፡፡ ስብሰባው የተካሄደው ለምሥራቅ ናይል ተብሎ ነው፡፡ ለምሥራቅ ናይል ተብሎ የሚከናወን ነገር ካለ ከምሥራቅ ናይል ቢሮ ጋር መተባበር ያስፈልግ ነበር፡፡ የምሥራቅ ናይል ቢሮ የሚገኘው እዚህ አዲስ አበባ ነው፡፡ እዚህ የግንኙነት መኮንኖች አሉ፤ እነሱ ማወቅ ነበረባቸው፡፡ እኛም መረጃው ሊደርሰን ይገባ ነበር፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ በስብሰባው ላይ ተዘጋጅተን መሄድ እንችል ነበር፡፡ በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ምንም ጥቅም እንዳላገኙበት፣ አጀንዳው ግልጽ እንዳልሆነ ነው የሰማነው፡፡ በባለሙያ ደረጃ ማብራሪያ የሚሰጡ ሰዎች የሚያስፈልጉ ከሆነ ከኢትዮጵያም፣ ከሱዳንም መጋበዝ ነበረበት፡፡ የግብጽ ባለሙያዎች ብቻ ገለፃ እንዲሰጡ የተደረገበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ ስብሰባው የተጠራው ጋዜጠኞች ውይይት እንዳያካሂዱ ከሆነ ራሳቸው ጋዜጠኞቹ አጀንዳ ቀርፀው ሊነጋገሩ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች የግብጽ ባለሙያዎች ተፈልገው የጋዜጠኞቹን ጭንቅላት ለመቀየር ተፈልጐ ከሆነ ይህ ስህተት ነው፡፡ የአባይ ተፋሰስ አገሮች ትብብር የመንግሥታት ነው፡፡ ስለዚህ በትብብሩ የሚንቀሳቀሱ በሙሉ በመንግሥታት ሥራ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ሊገባቸው ይገባል፡፡ አሁን የተባለው ነገር በካይሮው ስብሰባ ተፈፅሞ ከሆነ ትክክል አይደለም፤ ለወደፊቱም እንዲደገም አንፈልግም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |