Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow የአመፅ አባት የወለደው...
የአመፅ አባት የወለደው... Print E-mail
Sunday, 20 January 2008

የአመፅ አባት የወለደው የጥፋት ብዕር በወልደ ሥላሴ ዘብሔረ ካኑ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻዬ ታህሣሥ 20 ቀን 2000 ዓ.ም ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ "እኔ የምለው" በሚለው ገጽ ሥር ዘርዓ ቡሩክ ሰላማ የተባሉ ፀሐፊ "ፎቶ ማንጠልጠል የክብር መገለጫ ይሆናል?" በሚል መጠይቃዊ ርዕስ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የጎደለው ጽሑፍ ማቅረባቸው ይሆናል፡፡

የዘርዓ ቡሩክ ሰላማ ጽሁፍ የሀሳብ ተከታታይነት የሌለውና ድግግሞሽ የበዛበት ቢሆንም ባነሷቸው አንኳር ነጥቦች ላይ ተገቢውን መልስ ለመስጠት በቀጥታ ወደ ጽሑፋቸው ላምራ፡፡

"... የፓትርያሪካችን የአቡነ ጳውሎስ ታላላቅ ምስሎች በአዲስ አበባ አድባራት መስቀል ተጀምሯል፤ ይህ ከሥርዓታችን ውጭ ነው..." በማለት የጽሑፋቸውን ማጠንጠኛ ሀሳብ የሚጀምሩት ፀሐፊ፣ በዚህ የሀሳብ አቋማቸው ፀንተው እስከ መጨረሻው አይዘልቁም፡፡ ከተወሰኑ መስመሮች በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ትውፊት፣ የቆየና የተለመደ አሰራሩን በመጥቀስ፣ በመንፈሣዊ ምግባራቸው የተቀደሱና የተመሰከረላቸው የሃይማኖት አባቶችና ነገስታት ምስላቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደተሰቀለላቸውና እንደሚሰቀልላቸውም ያብራራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት እርስ በርሱ የሚጣረስ ሀሳብ ሲያዘንቡ ቆይተው ተቃውሟቸው ብዙም የሚያወላዳ ባለመሆኑ ይመስላል፤ የፓትርያሪኩ ምስል ከቅዱሳኑ ስዕል በመጠን ገዝፎ መሳሉ ተገቢ አይደለም ወደሚለው ድምዳሜ ይደርሳሉ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ የብፁዕነታቸውን ምስል በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመስቀል የሚያስችል የተቀደሰ መንፈሣዊ ምግባር አላቸው ወይ? ከሆነ ጥያቄያቸው ግልፅና ቀጥተኛው መልስ "አዎ፣ ያውም ከበቂ በላይ" የሚል ይሆናል፡፡ የቅዱስነታቸውን የተቀደሰ መንፈሳዊ ፍሬ በዝርዝር ማወቅ ከፈለጉም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በየደረጃው ተካቶ ያገኙታል፡፡ የብፁእነታቸው ምስል ለምን ገዝፎ ተሳለ? የሚለው በየትኛውም ማዕዘን ሲታይ በምንም መልኩ አሳማኝነት ያለው ጥያቄ አይደለም፡፡

የአንድ ምስል (ሥዕል፣ ፎቶግራፍ...) መተለቅና ማነስ የተሳዩን ማንነት፣ ግዝፈትና ትንሽዬነት ያን ያህል ትርጉም ባለው መልኩ የሚያመላክት አይደለም፡፡ ለምሳሌም በመጠን ረገድ ሲነፃፀር ሰማይ (ህዋ) ከምድር በእጅጉ ይተልቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ወረቀት፣ ሸራ፣ ወይም ዝርግ በሆነ ነገር ላይ ሲሳል የምድሩ (ያውም የአንድ አነስተኛ አካባቢ) ምስል ከግዙፍ ሰማይ መጠን ሁለትና ሶስት ጊዜ በላይ ገዝፎ የሚቀርብበት አጋጣሚው የበዛ ነው፡፡ ታዲያ! ትንሿ አካባቢ ከትልቁ ሰማይ በልጦ መሳሉ ተገቢ አይደለም ብሎ ማማረር ይቻላል!? አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ለአንድ ፎቶግራፍም ሆነ የሥዕል ምስል መተለቅና ማነስ ወሣኙ የሚሳልበት የመሳያ ቁሳቁስ መጠን እንጂ የተሳዩ "ማንነት" አይደለም፡፡ ከተሳሳትኩ የሥነ ጥበብ ምሁራን ሊያርሙኝ ይችላሉና ወደ ቀጣዩ የጽሑፍ ወቀሳ ልሸጋገር፡፡

የጽሑፉ አቅራቢ ..ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ በዘመናቸው በተጋድሏቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲታነፅ፣ ሀይማኖት እንዲስፋፋ አድርገዋልን?.. የሚል ጥያቄ ያቀረቡና ራሳቸው መልስ ሰጭ በመሆን "...አላደረጉም ማለት ይቻላል" ሲሉ ፍርድ ይሰጣሉ፡፡ አያይዘውም ቤተክርስቲያናት ቢታነፁም በምዕምናኑ ጉልበትና ገንዘብ እንጂ በብፁእነታቸው ተጋድሎ እንዳልሆነ ያወሣሉ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከአገልጋዮቿ፣ አገልጋዮቹንም ከምዕምናኑ ነጣጥሎ መመልከት ስህተት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትናንትም ሆነ ዛሬ ቤተክርስቲያናት የተገነቡትም ሆነ የሚገነቡት በሀይማኖቱ አባቶች ፈቃድና አመራር፣ በምዕምናኑም ገንዘብና ጉልበት ስለመሆኑ ፀሐፊው እስከ ዛሬ ካላወቁ ተነጋግሮ መግባባቱም የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡ የሆነው ቢሆንም በብፁእነታቸው ፓትርያሪክነት ዘመን ቤተክርስቲያናት በብዛት መገንባታቸውን፣ ወንጌል በስፋት መሠራጨቱንና ሀይማኖትም እንዲስፋፋ ከፍተኛ ተጋድሎ መደረጉን ለግራ ቀኙ ወገን መግለፅ ተገቢና አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ቅዱስነታቸው ከታላቁ የፓትርያሪክነት መንበር ላይ ከተቀመጡ ወዲህ በቅዱስነታቸው ያላሰለሰ ጥረት የዚህች ጥንታዊትና ታሪካዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የሐዋርያዊ አገልግሎቷ አድማስ እጅግ በጣም ሰፍቷል፡፡ በአፍሪካ አህጉር በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያና በጅቡቲ አብያተ ክርስቲያናት ታንፀዋል፤ መንበረ ጵጵስናዎች ተዘርግተው ጳጳሳትና መምህራኑ ወንጌል ተመድበዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችም ተከፍተው በተለያየ ምክንያት በዚያ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የየአህጉሩ ዜጎች የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርትና መንፈሣዊ አገልግሎቶች በስፋት መስጠት ከተጀመረ ውሎ አድሯል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ በአረብ ኤምሬትስና በአካባቢው፣ እንደዚሁም በቤይሩት (ሊባኖስ) መንበረ ጵጵስናዎች ተዘርግተው በተለያዩ ሥፍራዎች አብያተ ክርስቲያናት ተከፍተውና ትምህርት ቤቶችም ተቋቁመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ጥንታዊው የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርትም ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለውጭ ዜጎችም ጭምር በቋንቋቸው መስጠት መጀመሩ ቅን ህሊና ላለው ሁሉ ታላቅ የምሥራች ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ፣ በካናዳና በአውስትራሊያ በሚገኙ የተለያዩ ስቴቶችም በተመሣሣይ ሁኔታ አስፈላጊው ሁሉ ተሟልቶ ተገቢው አገልግሎት መስጠት ከተጀመረም ከራርሟል፡፡

በሀገር ውስጥም ቅዱስነታቸው ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በሚሰጡት ያላሰለሰ ትምህርትና በሚያደርጉት ሀዋርያዊ ጥረት የአብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ቀድሞ ከነበረው በእጥፍ ጨምሯል፡፡

በአዲስ አበባና በየአህጉረ ስብከቱ አያሌ አብያተ ክርስቲያናትና ካቴድራሎች ታንፀው በቅዱስነታቸው ቡራኬ ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሮ አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡ በዘመን ብዛትና በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ገዳማት እየተጠገኑና እየተደጎሙ ነው፡፡ አዳዲስ ገዳማትም ተገድመው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡ ተወርሶ የነበረው የቀድሞ የቅድስት ስላሴ መንፈሣዊ ኮሌጅ ተመልሶ አገልግሎት በመስጠት አያሌ የቤተክርስቲያን ደቀመዛሙርትን በዲግሪና በዲፕሉማ እያስመረቀ ለአገልግሎት እያሰማራ መሆኑንም መካድ ይቻላል!? እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህን እንደ አብነት ጠቀስኩ እንጅ በቅዱስነታቸው ጥረት የተካሄዱ አያሌ በጎ ክንውኖችን ከብዛታቸው የተነሳ በዚህ ጽሑፍ ማጠቃለል ያስቸግራል፡፡

ቅዱስነታቸው ሐምሌ 5 ቀን 1984 ዓ.ም አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ በካህናትና በምዕምናን ከፍተኛ የድምፅ ብልጫ ከተመረጡና በታላቁና በመጨረሻው የቤተ ክርስቲያን መንበር ላይ ከተቀመጡ ወዲህ በአሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ የተፈፀሙትን ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተግባራት ካለፈው የረዥም ዘመን የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪካዊ ጉዞ ጋር ሲነፃፀር እንደ ገቢረ ተዓምር የሚቆጠሩ ናቸው ቢባል ገለፃው የተጋነነ አይደለም፡፡ የተቃውሞ ፅሑፍ አቅራቢው ዘርዓ ብሩክ ሰላማ ግን እነዚህን በጊዜና ሥፍራ ተለይተው የሚታወቁ፣ በዓይን የሚታዩና በእጅ የሚዳሰሱ ተጨባጭ ክንውኖችን ጨርሶ ማውሳት አልፈለጉም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ምግባር እንኳን ተናግረውት ሲሰሙትም የሚያማቸው ነው የሚመስሉት፡፡

ወደ ሶስተኛው ነጥብ ስናመራ ደግሞ "ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሀይማኖቶች የሰላም የክብር ፕሬዚዳንት" መባላቸውም ፀሐፊውን በእጅጉ እንዳብከነከናቸው ከፁሁፋቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ የብፁእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዓለም አቀፋዊ ሰውነት፣ ክብርና ታላቅ ዝና እንዲሁ ከሜዳ እንደተገኘ ተቆጥሮ ከሆነ ትክክለኛ ግንዛቤ አይደለም፡፡ ይህ ታላቅ ክብርና ዝና ከብፁእነታቸው መንፈሣዊ ፍሬና ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ እድገቷ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን አምኖ መቀበል በራሱ ብልህነት ነበር፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም ስሌት ሆነ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያልዘሩትን ማጨድ አይቻልምና፡፡

የብፁእነታቸው ታላቅ ዝናና ማዕረግ የድካማቸው ውጤት ነው ከምንልባቸው አብይ ምክንያቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ለመግለፅ ያህልም፡-

- ብፁእነታቸው ከልጅነት እስከ እውቀት በድንግልና ህይወት የኖሩ፣ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ታንፀው ያደጉ፣ በነገረ መለኮት ትምህርት ከመንበረ ጸባኦት ቅዱስ ስላሴ መንፈሣዊ ኮሌጅ በከፍተኛ ማዕረግ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ፣ በቤተክርስቲያኒቱ ፈቃድ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ተልከው በተለያዩ ዝነኛ ዩኒቨርሲቲዎች እየተዘዋወሩ ለአሥራ ስድስት ዓመታት ተከታትለው ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ (ዶክተር ኦፍ ፊሎዞፊ) የደረሱ ናቸው፡፡

- ብፁእነታቸው በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ እውቀትና አገልግሎታቸው ተመርጠው በ1967 ዓ.ም በሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አንብሮተ እጅ ጵጵስና የተሾሙና ያላንዳች በደል ለሀይማኖታቸው ባላቸው የፀና አቋም ምክንያት በደርግ መንግሥት ለሰባት ዓመታት በፅኑ እስራት የታሰሩ፣ በወህኒ ቤት ቆይታቸውም የደርግን ፀረ ሀይማኖት አቋም ፊት ለፊት ተጋፍጠው ለእስረኛው ህብረተሰብ ወንጌልን በመስበክ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ ቆራጥ አባት ናቸው፡፡

- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው ከመመረጣቸው በፊትና ከተመረጡም በኋላ ባላቸው ከፍተኛ መንፈሳዊ እውቀት የቤተክርስቲያኗን የሀይማኖት ቀኖና በተለያዩ አያሌ አለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተገኝተው በማሳወቅ ታላቅ አለም አቀፍ ሥራ የሰሩ ለታላቅ ማዕረግና ሽልማት የበቁና የተከበሩ አባት ናቸው፡፡ በተለይም ከሰባት በላይ አገራዊና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መቻላቸው ለሀይማኖታዊ ተልዕኳቸው ታላቅ ስኬት አይነተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

በዚህ ጽሁፍ ካልተካተቱ አያሌ የተቀደሱ መንፈሣዊ ፍሬዎቻቸው አኳያ ሲመዘኑ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አለማችን ካፈራቻቸው ጥቂት እውቅና ዝነኛ የሃይማኖት ምሁራን ውስጥ ከመጀመሪያው ተርታ የሚገኙ የሃይማኖት አባት ናቸው፡፡ እንዲያውም የብፁእነታቸው ፈርጀ ብዙና የላቀ ክንውን በአስተውሎት ሲፈተሽ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምንጊዜውም በበለጠ የተሻለ መሪ ያገኘችበት ወቅት ነው፡፡ ታዲያ! በዚህ ሁሉ የተቀደሰ ምግባራቸው የብፁእነታቸው ምስል በቅጥር ግቢ ውስጥ መሰቀሉ ያንስባቸው እንደሆነ እንጂ አይበዛባቸውም፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሚሌኒየሙ ፓትርያሪክ ሊባሉ ይገባቸዋል ባይ ነኝ፡፡

የዘርዓ ብሩክ ሰላማ የተቃውሞ ጽሁፍ መነሻው ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ መልሱ ከሁለት ምክንያቶች የዘለለ አይሆንም፡፡ አንድም የግል ጥቅማቸው የተነካባቸው፣ አሊያም ቅን ህሊና የሌላቸውና በባዶ ጥላቻ የተመረዙ ፅንፈኞች የሚያናፍሱት አሉባልታ ይሆናል፡፡ በተለይም እግዚአብሄር በቀባው የሀይማኖት መሪ ላይ አፍን ማላቀቅ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የጎደለው ከመሆኑም ባሻገር ፈሪሃ እግዚአብሄርን ማጣት ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የዘርዓ ቡሩክ ሰላማ ጽሑፍ ሀይማኖታዊ ሥነ ምግባርን የሚሸረሽር፣ ምዕምናንን የማያንፅ፣ ፍቅርና ሰላምን መተሳሰብና መደጋገፍን የማይሰብክ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ አመፅን፣ ዘለፋን፣ ባዶ ጥላቻን የሚዘራ የጥፋት ብዕር ነው፡፡

በሦስተኛው ሚሌኒየም የመጀመሪያ ዓመት ላይ ሆነን ስለ ትናንት ስናስብ በእያንዳንዷ እለትና እንቅስቃሴ በግልም ሆነ በጋራ አጠራቅመን ያለፍናቸው የልማትም ሆነ የጥፋት መዋጮዎች ይታወሳሉ፡፡ አልምተን ከሆነ እንበረታታለን፣ አጥፍተን ከሆነም በኑሯችንና በህይወታችን ዋጋ መክፈል የግድ ነው፡፡ ምንም ይሁን ምንም ያለፈው አልፏል፤ ከትናንት በመማር ዛሬን በአግባቡ መጠቀም ያሻል፡፡

መኮራረፍ ያራርቃል፣ ዓመፅም ጥፋትን ይወልዳል፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን ብንደጋፍ ፀንተን እንቆማለን፣ ብንጣጣል ወይም ብንገፋፋ ግን ተለያይተን እንወድቃለን፡፡ በተለይም ሦስተኛው ሚሌኒየም በአእምሮ የበሰልንበትና ከህይወትም ሰፊ ልምድ ያካበትንበት በመሆኑ "መነጋገር"፣ "መደማመጥ"፣ "መተሳሰብ" እና "መቻቻል" ይኖርብናል፡፡ ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነት ያዋጣል፡፡  በፍቅር ብንጓዝ ጎባጣው ይቀናል፤ ደረቁም ይለመልማል፡፡

 
< Prev   Next >