| በግል ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ይፈፀማል |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
በታምሩ ጽጌ
በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የግል ተቋማት ውስጥ ስር የሰደደና መጠኑ የማይታወቅ ከፍተኛ ሙስና እንደሚፈፀም የሴንተር ፎር ዴቨሎፕመንት ኮንሰልቲንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ገለፁ፡፡ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ጌታቸው ደመቀ ይኸንን የገለፁት “ሙስናና የግል ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ” በሚል የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በጊዮን ሆቴል መስከረም 15 ቀን 2001 ዓ.ም ባዘጋጁት የግማሽ ቀን አውደ ጥናት ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ነው፡፡ ጽሑፍ አቅራቢው እንደገለፁት፣ ሙስና አብዛኛውን ጊዜ ከሕዝብ ወደ ነፃ ኢኮኖሚ፣ ከግል ወደ ሕዝብ በሚተላለፉ ነገሮች ላይና ከግል ወደ ግል በሚደረግ ማንኛውም የልማት ወይም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚፈፀም ተናግረዋል፡፡ “ዋናው የሙስና ማስፋፊያ መሣሪያ የሆነው ከፍተኛ የሆነ የሕግ ውስብስብነት በመኖሩ ነው” ያሉት ዶ/ር ጌታቸው የሕግ መብዛትና መወሳሰብ፣ ቀለል ብሎ አለመተርጐሙ፣ በተፈፀመ የሙስና ወንጀሎች ላይ በፍርድ ቤቶች በኩል ፈጣን ውሳኔ አለመሰጠቱ ሙስናን ከሚፈጥሩና ከሚያባዙ መንገዶች በዋነኛነት የሚጠቀሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲቋቋም የመንግሥት ልማት ድርጅቶችንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ብቻ ሊቆጣጠር መሆኑን የገለፁት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ሙስና እየተፈፀመበት ያለውና ህግ ወጥቶለት ቁጥጥር መደረግ ያለበት የግሉ ተቋም ጭምር መሆኑን አስምረውበታል፡፡ አንድ ሰው አንድን ጉዳይ ለማስፈፀም ወይም ለመፈፀም (በግሉ ተቋ..ም) ቢያንስ ቢያንስ 10 በመቶ ሳይሰጥ (እንደ ቢዝነሱ ይለያያል) እንደማይፈፀምለት የገለፁት ዶ/ር ጌታቸው፣ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ የመልካም አስተዳዳር ማጣት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት አለመኖር፣ ዝቅተኛ የፓለቲካ አመለካከትና ድህነት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አንድ በማደግ ላይ ያለ አገር ውስጥ ሙስና በጣም እንደሚስፋፋ፣ በተለይ ከግል ወደ ሕዝብ በሚከፈሉ የታክስ፣ የቫትና የመሳሰሉት ላይ፣ የቤት ስም ወይም ካርታ በማዘዋወር ስራ ላይ ሰነድ በመሠረዝና በመደለዝ ከፍተኛ የማጭበርበርና የሙስና ሥራ እንደሚሠራ ዶ/ር ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ “በተለይ የመሬት ፖሊሲ የለንም፡፡ መሬትን በተመለከተ በድርድር ነው የሚሸጠው፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ሙስና ቢፈፀም ምን ይገርማል?” ያሉት ዶ/ር ጌታቸው ከግል ወደ ግል በሚሰሩ ሥራዎች ወይም ተመሳሳይ ተቋማት መካከል ሙስና እንደሚፈፀም ተናግረዋል፡፡ አንድ የግል ድርጅት ከግል ባንክ ብድር ለመውሰድ ቢፈልግ፣ የብድር ክፍል ኃላፊው ብድሩን ለማፋጠን “ሁለት በመቶ ታስብልኛለህ” በማለት ከተበዳሪው ጋር እንዴት እንደሚደራደርና ሙስና እንደሚፈፀም በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ “ጉቦ አልከፍልም” የሚል ባለጉዳይ የሚፈልገውን ነገር ማስፈፀም እንደሚችል የገለፁት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ በ20ና በ30 ቀናት የሚፈፀም ጉዳይ (በሙስና ከሆነ) እስከ አንድ ዓመት እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ ለሙስና ዋናው ማስፋፊያ መንገዶች ፍርድ ቤቶችና የሕግ አወጣጥ ስርዓቱ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ጌታቸው፣ ፍርድ ቤቶች የተፋጠነ ውሳኔ ቢሰጡና አስገዳጅ ህግ ቢወጣ ሙስናን በእንጭጩ መግታት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ሙስና ሕብረተሰቡን የሚያቀጭጭ፣ በመንግሥት፣ በሕዝብና በግል ተቋማት ላይ እንደሚፈፀምና በተለያዩ አገራት የተለያየ ትርጉም ያለው መሆኑን፣ ነገር ግን “ኃላፊነትን ከህግ ውጭ ለግል ጥቅም ማዋል” የሚለው ሁሉንም የሚያስማማ ትርጉሙ መሆኑን የገለፁት ሌላው በአውደ ጥናቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ መድህን ኪሮስ ናቸው፡፡ አቶ መድህን መመረቂያ ጽሁፋቸውን በግል ተቋማት ላይ መስራታቸውን አስታውሰው “በተቋማቱ ውስጥ የሚፈፀመው ሙስናና የማጭበርበር ቴክኒክ በጣም የሚያስፈራ ነው” በማለት በተቋማቱ ውስጥ ህገወጥ ምዝበራ እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡ በሙስና ህጉ ላይ ጥናት ተደርጐ ህጉ በግል ተቋማት ላይ የሚፈፀሙ ሙስናዎች ላይ መሻሻል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |