| ለኦሊምፒክ ጀግኖች የማዕረግና ... |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
ባለፈው ሐሙስ ምሽት በጊዮን ሆቴል ሳባ አዳራሽ የማረሚያ ቤቶች ስፖርት ክለብ ያዘጋጀውን የማዕረግ፣ የሜዳሊያና ማበረታቻ ሽልማት የሰጡት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ማዕረጉ ሐብተማሪያም ሲሆኑ በቤጂንግ ኦሊምፒክ በ5 እና 10 ሺህ ሜትር የድርብ ድል ባለቤት የሆነችው ጥሩነሽ ዲባባ ዋና ሱፐር ኢንተደንትና 40 ግራም ወርቅ፣ በቤጅንግ ኦሊምፒክ 10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ስለሺ ስህን ደግሞ ሱፐር ኢንተደንትና 20 ግራም ወርቅ ተበርክቶለታል፡፡ የዓለምና የኦሊምፒክ ሻምፒዮና ጥሩነሽ ዲባባ እና ስለሺ ስህን በዕለቱ የለበሱት ሙሉ የማዕረግ ልብስ አትሌቶቹ በሩጫው ዘርፍ ከተጐናፀፉት ክብር በተጨማሪ ልዩ ግርማ ሞገስን እንዲላበሱ አድርጓቸዋል፡፡ ሁለቱም የኦሊምፒክ ጀግኖች ከማዕረጉ አሰጣጥ በፊትና በኋላ ለእንግዳው የሰጡት የነበረው ወታደራዊ ሰላምታ እንደሩጫው ሁሉ በወታደራዊ ሳይንስ የተካኑ ይመስሉ ነበር፡፡ በቤጅንግ ኦሊምፒክ ውጤት ባይቀናትም በ1 ሺህ 500 ሜትር በጠንካራ አትሌትነቷ የምትታወቀው ገለቴ ቡርቃ ከረዳት ኦፊሰርነት ማዕረግ ምክትል ኦፊሰርነት 10 ግራም ወርቅ፣ በቤጅንግ ኦሊምፒክ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪ ለነበረችው መቅደስ በቀለ የምክትል ሰርጀንት ማዕረግና 10 ግራም ወርቅ፣ የብሔራዊ ቡድን የ5 እና 10 ሺህ ሜትር ረዳት አሰልጣኝና የማረሚያ ቤቶች ክለብ ዋና አሰልጣኝ ሱፐር ኢንቴንዲንት ሁሴን ሽቦ ሁለት እርከን የደመወዝ ጭማሪና 15 ግራም ወርቅ፣ በቤጅንግ ኦሊምፒክ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል የዲፕሎማ ተሸላሚ ለሆነው ያዕቆብ ጃርሶ ደግሞ የአስር ሺህ ብር ሽልማት ሲያገኝ የክለቡ ወጌሻ ምክትል ሰርጀንት ጥበበ አለው የ10 ግራም ወርቅ ሽልማት ተበርክቷል፡፡ የስፖርት ክለቡ ያዘጋጀውን ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው አራት ኦሊምፒክ በመሳተፍ የበርካታ ሜዳሊያዎችና ክብር ባለቤት የሆነችው ዋና ሱፐር ኢንተደንት ደራርቱ ቱሉ፣ በሴቶች ማራቶን ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ ተሳታፊና የሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ሱፐር ኢንተደንት ፋጡማ ሮባ፣ ዋና ኦፊሰር ቁጥሬ ዱለቻ፣ ኦፊሰር ጌጤነሽ አራጌ፣ ምክትል ሰርጀንት መሪማ ሐሽም፡፡ ኦፊሰር ደጀኔ ብርሃኑ፣ ምክትል ኦፊሰር ታዬ ገመቹ፣ አትሌት ማሩ ዳባ፣ ዳንኤል ዘገየ፣ እልፍነሽ ዓለሙና ቱርቦ ቱሞ እንዲሁም በቦክስ ስፖርት ከማረሚያ ክለብ ተመርጠው ኦሊምፒክ ላይ በተሳተፉት ምክትል ሰርጀት ፀጋስላሴ አረጋዊና ሰለሞን ታደሰ ናቸው፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 28 September 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |