Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የሽካሽ ጐሣ አባላት የአስተዳደር እና...
የሽካሽ ጐሣ አባላት የአስተዳደር እና... E-mail
Sunday, 28 September 2008
የሽካሽ ጐሣ አባላት የአስተዳደር እና የረሃብ ችግር አለብን አሉ

በጋዜጣው ሪፖርተር

በሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከሽካሽ (ፊቅ ዑመር) ጐሣ የመጡ የአገር ሽማግሌዎች የአስተዳደርና የረሃብ ችግር እንዳለባቸው ገለፁ፡፡ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ለግብርና ሚኒስቴርና ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጉዳዩ ተጣርቶ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ደብዳቤ ፅፏል፡፡

የሱማሌ ክልል ነዋሪ የሆኑ የአገር ሽማግሌዎች የጐሣቸው ማለትም የሽካሽ ጐሣ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ መዋቅር በአካባቢያቸው እንደሌለ፣ ምርጫ መርጠው እንደማያውቁ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በአካባቢያቸው ተደርጐ እንደማያውቅ፣ በአሁኑ ወቅት በደረሰው ረሃብ አደጋ በቀን ከ3 እስከ 5 ሰዎች እንደሚሞቱ ይገልፃሉ፡፡ የአስተዳደር መዋቅር ካለመኖሩም በላይ ከኦጋዴን ጐሣ አባላት እንዲሁም የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ጥቃት ሠለባ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ወክለው እንደላኳቸው የሚናገሩት እነዚህ የአገር ሽማግሌዎች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለሶማሌ ክልል ኘሬዚዳንት፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ምላሽ የሚሰጣቸው አካል አለማግኘታቸውንና የጐሣቸው አባላትም ለከፍተኛ ስቃይ መጋለጣቸውን ይገልፃሉ፡፡

እነዚሁ የአገር ሽማግሌዎች አቤቱታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ይዘው ያመሩ ሲሆን ኮሚሽኑም ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና ለግብርና ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ክትትል እንዲደረግና ችግሩ ደርሶም ከሆነ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ለግብርና ሚኒስቴር መስከረም 9 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በፃፈው ደብዳቤው “ከሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከሽካሽ ጐሣ የመጡ የአገር ሽማግሌዎቹ ጳጉሜ 4 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. በጽሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ አካባቢዎች በድርቅ ክፉኛ የመመታቱ የተነሳ ከነዋሪው ሕዝብ በምግብ እጦትና በበሽታ በቀን ከ3 እስከ 5 ሰዎች እየሞቱባቸው መሆኑን ገልፀው ለአጐራባች ወረዳዎችና ቀበሌዎች የተፈቀደው የዕርዳታ እህልና መድሃኒት ቀኑ ሳይዛባ የሚላክ ሆኖ የራሶና አካባቢ ግን እንደሌሎቹ በችግር ላይ መሆኑ እየታወቀ ዕርዳታውን ማግኘት ባለመቻል ለችግር መዳረጋቸውን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና ለአደጋ መከላከል በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም አጥጋቢ ምላሽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ኮሚሽኑ በመኖር መብታቸው ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለሚመለከው አካል እንዲያሳውቅላቸው እየተፈፀመ ያለውን አድልዎም እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል” በማለት ገልጿል፡፡

ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በፃፈው ደብዳቤ አክሎ እንደገለፀው የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ችግር ተከስቶ፣ በተደጋጋሚ የሚመለከተው አካል አሳውቀው፣ የአካባቢው አጐራባች ሕዝቦች እየተረዱ እነሱ የዕድሉ ተጠቃሚ ሊሆኑ ባለመቻላቸው የተባለው ጉዳት ደርሶ ከሆነ አግባብነት ስለሌለው የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር ጉዳዩን በማጣራት አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ እንዲያሳውቃቸው ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠይቋል፡፡

የሽካሽ ጉሣ የአገር ሽማግሌዎች በአካባቢያቸው ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት እንደሌለ፣ የመንግሥት መዋቅርም እንደማያውቃቸው፣ በአጠቃላይ “የተረሱ ሕዝቦች” መሆናቸውን የጐሣቸው አባላት ብዛትም ከ25ዐ ሺህ በላይ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ሶማሌ ብሔራዊ ክልል ኘሬዚዳንት ጽህፈት ቤትና የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባዔ ያደረግናቸው ተደጋጋሚ ጥሪዎች ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
 
< Prev   Next >