Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow ክለቦችና ቅድመ ዝግጅታቸው
ክለቦችና ቅድመ ዝግጅታቸው E-mail
Sunday, 28 September 2008

ክለቦች ከመደበኛው ፕሪምየር ሊግ ውድድር በፊት የሚያደርጉትን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ከክለብ ክለብ የሚደረገው የተጨዋቾች ዝውውር በክረምቱ ተጠናቋል፡፡

 

በ2000 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት የክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር ከሳምንት በኋላ መስከረም 26 እና 27 ቀን 2001 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚከናወን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውድድርና ስነስርዓት ቢሮ የውድድር ፕሮግራሙን ይፋ አድርጓል፡፡ የጥሎ ማለፍ ውድድር እንዳበቃ ክለቦች ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሚያካሄዱት መደበኛ የፕሪምየር ሊግ ውድደር እንደሚጀመር መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማሕበር (ፊፋ) በኢትዮጵያ ላይ የእገዳ ውሳኔውን ከማስተላለፍ ቀደም ሲል፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መውደቅ በርካታ ምክንያቶች ሲቀርቡ ነበር፡፡ አንደኛው የስፖርት ቤተሰቡ ከአገር ውስጥ ውድድር ይልቅ ለአውሮፓ እግር ኳስ ትኩረት መስጠቱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይከተለው በነበረው ዝርክርክ አሰራር፣ እንዲሁም ክለቦቻችን በኢንተርናሽናል ውድድር ላይ የነበራቸው ደካማ ተሳትፎ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ችግሩን ለማስተካከል በሚል ነበር፣ ክለቦች በቀድሞ የፌዴሬሽኑ አመራር ላይ የተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙት፡፡ ይሁንና በወቅቱ "ለውጥ ፈላጊ የክለቦች ኅብረት" በሚል በተነሱት ክለቦችና በቀድሞ አመራር የተፈጠረው አለመግባባት መልኩንና ይዘቱን እየለወጠ በመምጣቱ የተነሳ፣ ለእግር ኳሱ ልማት የሚውለው ጊዜ በውዝግቡ መባከኑ ከጅምሩ አቅጣጫው የጠፋበት ስፖርቱ በሁሉም ረገድ በማይታመን ደረጃ ላይ ነው፡፡ እስካሁንም ይመለከተኛል የሚል አካል መፍትሄ ያለውን ፍንጭ አልሰጠም፡፡

የአገሪቱ እግር ኳስ ይህንን ከመሰለ ውስብስብ ችግር ሳይወጣ የለውጡ ግንባር ቀድሞ ተዋንያን ክለቦች፣ በ2001 ዓ.ም ለሚያደርጉት መደበኛ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የሚያደርጉት ቅድመ ዝግጅት በአሁኑ ሰዓት የስፖርት ቤተሰቡን እያወያየ ነው፡፡ እንደሚሰማው ከሆነ፣ ከአዲስ አበባ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ሁለቱም ለቅድመ ዝግጅቶቻቸው አዳማ እንደሚገኙ ሲነገር፣ የተቀሩት ጠዋትና ማታ በመመላለስ እየተዘጋጁ ናቸው ተብሏል፡፡

አገሪቱ ታግዳለች፡፡ ብሔራዊ ቡድኑም ሆነ ክለቦች በየትኛውም አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ አይሳተፉም፡፡ ይህ ባለበት በተጠናቀቀው ክረምት ሁሉም የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ቡድናቸውን ለማጠናከር እንደወትሮ ሁሉ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ተጨዋቾችንና አሰልጣኞችን አዘዋውረዋል፡፡ ለዝግጅቱም ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ናቸው፡፡ ለምን ብሎ የጠየቀ አካል ግን አሁንም አልታየም፤ አልተሰማም፡፡  

ክለቦች የአገሪቱን እግር ኳስ ለማሳደግ ከፍተኛ በጀት በጅተው እየተንቀሳቀሱ ስለመሆናቸውም፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ይደመጡ ነበር፡፡ ለታሪክም ሆነ ለስፖርት ቤተሰቡ በማይመች መልኩ እግር ኳሱ አደጋ ተደቅኖበት ባለበት በአሁኑ ሰዓት፣ ክለቦች ግለሰቦችን ለእግር ኳሱ ውድቀት ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ ዛሬ ለምን ዝምታን እንደመረጡ ግራ አጋቢ ሆኗል፡፡

በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከአህጉር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ቢታገድ፣ ከዓመታት በኋላ የተሻለ ነገር ሰርቶ ለመቅረብ እንደሚበጅ የሚስማሙ አሉ፡፡ ሐሳቡ ባልከፋ፡፡ ግን ክለቦች በአሁኑ ሰዓት የያዟቸው ተጨዋቾች ከሁለትና ሶስት ዓመት በኋላ ስንቶቹ ለዚህ ቅዱስ ዓላማ በስነልቦናውና አካል ብቃቱ ጎልብተው እንደሚያገኟቸው ሲታሰብ ግን ሐሳቡን ሙሉ ለሙሉ የሚያፋልሰው ይሆናል፡፡

አዲሱ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማሕበር (ፊፋ) እገዳና ከእገዳው ጎን ለጎን የሊጉ ውድድር ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሚጀምረው ፕሪምየር ሊግ ጋር እንዴት ተጣጥሞ መሄድ እንዳለበት ለሕዝቡ ማሳወቅና ማሳመን የሚጠበቅበት የመጀመሪያው ተግባሩ ሆኖ በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ የማያበራ በሚመስል መልኩ የተጋረጠው አለመግባባት፣ ከፕሪምየር ሊጉ ውድድር በፊት እልባት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

ከጥቂት አመታት ወዲህ የአዲስ አበባ ስታዲየም ከተመልካች ጋር ዳግመኛ ላይታረቅ በተለያየበት በአሁኑ ወቅት፣ የፊፋ እገዳ ከመተላለፉ በፊት የአፍሪካ ቡድኖችና ክለቦች ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ መጠነኛ ተመልካች የሚስተዋልበት የአዲስ አበባ ስታዲየም፣ እገዳው ሲፀናበት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ማሰብን አይጠይቅም፡፡ ስለዚህ አዲሱ የፌዴሬሽኑ አመራርም ሆነ የቀድሞው፣ እንዲሁም የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለቤት የሆነ መንግስትና የክለብ መሪዎች ጎራ ለይተው ከሚያደርጉት መናቆር ተላቀው፣ ለሕግ የበላይነት ተገዝተው፣ በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመታደግ፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት ብልህነት እንጂ ሽንፈት አለመሆኑን እንዲረዱት ያስፈልጋል፡፡
 
< Prev   Next >