Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow “የሚገርም ቢሮክራሲ አለ”
“የሚገርም ቢሮክራሲ አለ” Print E-mail
Sunday, 20 January 2008

አቶ ሙሉጌታ ፀደቀ
የ”አይስ ብሉ” እና “ሉሲ” ሬስቶራንቶች ባለቤት

በብሔራዊ ሙዚየም ግቢ ውስጥ፣ በስተቀኝ ባለው መግቢያ በር በኩል የ”ሉሲ ጋዜቦና ሬስቶራንት”ን መግቢያ ያገኙታል፡፡ ከበሩ ፊት ለፊት የቆመ “ዋልያ” ይቀበልዎታል፡፡ ሲታጠፉና ወደ ሬስቶራንቱ ሲጠጉ በመጀመሪያ የተጫነች አህያ፣ ከአጠገቧ ሞፈር፣ ከጎኗ ስንዴና ገብስ መሬቱ ላይ ለምልሞ ይታያል፡፡ የሬስቶራንቱ ውጪ ክፍል ግድግዳ የተሠራው በቀርከሃ ነው፡፡ ውስጡ ኮርኒሱ በእንጨት ጣሪያው በጎጆ ቤት የሳር ክፍክፍ የተሠራ ነው፡፡

የሬስቶራንቱ ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ፀደቀ እንደነገሩን ሬስቶራንቱ በተቻለ መጠን የኢትዮጵያውያንን ባህል እንዲያንጸባርቅ ለማድረግ የየብሔረሰቦቹን አልባሳት በሬስቶራንቱ ግድግዳዎችና ጣሪያዎች ከመስቀል ሌላ የገበሬውን ሁለንተናዊ ሕይወት የሚያሳይ ጎጆ በግቢው ተሠርቷል፡፡ ጎጆው የንብ ቀፎ እና ጎተራ እንዲሁም የከብቶች በረት (ከጀርባው) ያለው ሲሆን ለማንፀባረቅ የተፈለገውን የተሟላ ለማድረግ ከብቶች በቅርቡ እንደሚቀመጡ አቶ ሙሉጌታ ነግረውናል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ለረጅም ዓመታት በእንግሊዝ አገር የኖሩ ሲሆን አሁንም አገልግሎት እየሰጠ ያለና ከ15 ዓመታት በፊት በለንደን የተከፈተው “ላሊበላ ሬስቶራንት” ባለቤት ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ሬስቶራንት ከመክፈታቸው በፊት ደግሞ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ተቀጥረው ይሠሩ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ሬስቶራንት ሌላ ጋለሪም ከፍተው የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለፃ በለንደን የሚገኘው ሬስቶራንታቸው በአገሪቱ ከተከፈቱ ቀደምት የአፍሪካውያን ሬስቶራንቶች አንዱ ሲሆን በርካታ ደንበኞች ያሉትና በአገሪቱ ጋዜጦችም ብዙ የተፃፈለት ነው፡፡

አቶ ሙሉጌታ የመንግሥት አካላት በየአገራቱ እየዞሩ ስለተደረጉ የፖሊሲ ለውጦችና በአገር ውስጥ ተመልሰው እንዲሠሩ ለማበረታታት የሚደረገውን ጥረት በማስመልከት የሰጧቸውን መረጃ ይዘው ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡

ከዚያን ወቅት ጀምሮ እየተመላለሱ በለንደን ያለ የንግድ ሥራቸውንና በኢትዮጵያ የጀመሯቸውን ሥራዎች ያከናውናሉ፡፡ ለቃለመጠይቅ ቀጠሮ የተገናኘንበት ሉሲ ሬስቶራንት ብቻ ሳይሆን ቦሌ የሚገኘው “አይስ ብሉ” ሬስቶራንትና ካፌ ባለቤትም ናቸው፡፡

አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት ሬስቶራንቶቹን ከመክፈታቸው በፊት ኢትዮጵያ ሲመጡ የተገነዘቡት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አለመስፋፋታቸውን ነው፡፡ የኮንስትራክሽንና ሌላው ዘርፍ ያደገውን ያህል ይህ ዘርፍ አለማደጉ በተለይ ከውጪ አገራት ለሚመጡ ሰዎች መሰጠት ያለበት አገልግሎት እንዳይከናወን እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ በአገልግሎት ዘርፉ ያለውን አሠራር በተመለከተ መዋቅሩ ቢኖርም የሬስቶራንቶች አሠራርና የንፅህና ሁኔታ ምን መሆን አለበት የሚለውን የሚከታተል አካል አለመኖሩን አቶ ሙሉጌታ ይናገራሉ፡፡

ይህንን በተመለከተ ማድረግ የሚቻለው ኃላፊነቱን ወስዶ በጥሩ ሁኔታ በመሥራት ሰዎች ያንን በምሳሌነት አይተው እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ ለዚሁ ተግባር በአፍሪካ ጎዳና ባቋቋሙት የአውሮፓውያን ሬስቶራንት ጀምረው አሁንም በሉሲ ጋዜቦና ሬስቶራንት ደረጃውን የጠበቀ አሠራርን መከተላቸውን ያብራራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ሁለተኛውን ሬስቶራንት ለመክፈት ምክንያት የሆናቸው ብሔራዊ ሙዚየምን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶች፡-ንፁህ የመፀዳጃ ቤት፣ በግልፅ የሚታይ የምግብ ማብሰያ ቤት ወዘተ. ያለበት ቦታ እንዲያገኙ በማሰብ ነው፡፡ ይኸውም “ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የሚነገራቸው የንፅህና ችግር እንዳለ ነው፡፡ ሲመጡ ይህንን ቤት አይተው አድንቀው፣ አዎንታዊ ምስል ይዘው እንዲሄዱ በማሰብ ነው ይህንን ቦታ የጀመርኩት” ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የገበሬውን አነኗኗር የሚያሳይ ጎጆና የተሟላ ቁሳቁስ ያስቀመጡት 80 በመቶ የሚሆነውን ገበሬ ጎብኚዎቹ ገጠር ሄደው የማየት ዕድሉ ስለማይገጥማቸው ያንን የሚያንፀባርቅ ነገር እንዲያዩ ለማድረግ ነው፡፡ የሰለጠነው ዓለም በማያደርገው መልኩ ገበሬው አካባቢውን እንዴት እንደሚጠብቅ ለማሳየትም ጭምርና ምዕራባውያኑ ከኢትዮጵያ ገበሬ ይማሩ የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡

ባህላዊውን ነገር ለማሳየት ደግሞ በሬስቶራንቱና በጋዜቦው መቀመጫዎች ከጠፈርና ከገመድ እንዲሁም ከሸማ የተሠሩ ሲሆኑ ከተከፈተ ጀምሮ እያዩት ያለው ምላሽ በጎ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሥራውን ሲጀምሩ በተለይ በብሔራዊ ሙዚየም ችግር እንዳልገጠማቸው ያገኙት ትብብርም ጥሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

የኢንቨስትመንት ፈቃድና ሌላውን በተመለከተ ብዙውን ጊዜ ቢሮክራሲያዊ አሠራር የሰፈነበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ እርስዎ ያጋጠመዎት ምን ነበር? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሙሉጌታ ሲመልሱ “ትክክል ነው፡፡ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ሙዚየም የጀመርኩት ሥራ አለ፡፡ በጣም ቢሮክራሲ አለ፡፡ የሚገርም ዓይነት ቢሮክራሲ ነው ያለው፤ ቢሮክራሲ አለ ተብሎ ግን ሳይሠራ አይቀርም፡፡ መታገል ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያሉት ይህንኑ ነው” ብለዋል፡፡

“እኔ ከለንደን ስመጣ እዚያ ሬስቶራንትና ቢዝነስ ስላለኝ ሰዎቹ እንደ አሉታዊ ነገር ያዩታል፡፡ እዚህ ሁሉም ተሟልቶልህ ወደ ኢትዮጵያ ለምን ትመለሳለህ? ይሉኛል” የሚሉት አቶ ሙሉጌታ ምንም ያህል ትንሽ የሚባል እንኳ ቢሆን ማንም ሰው ለአገሩ ልማት አስተዋፅዖ ማበርከት አለበት በሚለው አምነው እንደመጡ ይገልፃሉ፡፡ “ኢትዮጵያ ደሃ ብትሆንም ከ45 ዓመታት በፊት እንግሊዝና ሌሎቹም ደሃ ነበሩ፡፡ ስለሠሩ እዚህ ደርሰዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ አገራችን ኢትዮጵያ በመሆኗ ሠርተን ካልለወጥናት ከድህነት አትወጣም፡፡ ምሳሌ ለመሆን ስለምፈልግም መጥታችሁ እዩ እላቸዋለሁ” ይላሉ አቶ ሙሉጌታ፡፡ ዲያስፖራውም ይህንን መመልከት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ አስተዋፅዖ ለማበርከት እና ከሕሊና እርካታ አንፃር እንጂ እዚህ ኢንቨስት የተደረገው ገንዘብ ውጪ ቢደረግ የተሻለ አትራፊ ሊሆን እንደሚችልም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ውጪ ላሉት አገር ውስጥ ስላለው ሁኔታ መረጃ በመስጠት ምን ያሀል ይሠራሉ ተብለው ሲጠየቁም “እዚያም እየሠራሁ ነው፡፡ እዚህ ስመጣ ባይሳካልኝ መጥፎ ምሳሌ መሆን ስላልፈለግኩ የተቻለኝን ያህል እየታገልኩ ነው፡፡ ቢሮክራሲ ቢኖርም የምታገለው ለዚሁ ነው፡፡ ከተሳካልኝ ደግሞ ጥሩ መልዕክት እንዲያገኙ እፈልጋለሁ፡፡ ብዙዎቹ እዚህ እየመጡ የምሠራውን እያዩ ነው ያ ጠቃሚ ነው” የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

በአሠራር ላይ ሊስተካከሉ ይገባሉ የሚሏቸውን ነጥቦች በተመለከተ “የቢሮክራሲው ነገር አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ ጀንበር የሚስተካከል አይደለም፡፡ መንግሥት መንገድ ለማስያዝ እየሞከረ ነው፡፡ የሁላችንንም ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡ የምለው ተስፋ መቁረጥ የለብንም” ብለዋል፡፡

በቤተልሔም ነጋሽ

 
< Prev   Next >