| አልአሙዲን በአርባ ምንጭና በቡራዩ አጥረው... |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
አልአሙዲን በአርባ ምንጭና በቡራዩ አጥረው የያዙዋቸው ቦታዎች ጥያቄ አስነሱ
በጋዜጣው ሪፖርተር ሼህ ሁሴን መሐመድ አልአሙዲ በአርባ ምንጭ ሰፊ መሬት ለቱሪዝም ሥራ አጥረው ቢይዙም እስካሁን ግንባታ አለመጀመራቸውን የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡ በሌላ በኩል ባለሀብቱ በቡራዩ 15.77 ሄክታር ቦታ ተረክበው ካጠሩት 12ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ታገሰ ጫፎ እንዳስታወቁት በአርባ ምንጭ ባለሀብቱ መሬት ከተረከቡ ስድስት ዓመት አልፏል፡፡ በስድስት ዓመት ውስጥ ቦታው በአጥር ከመከለሉ ውጪ ግንባታ አልተጀመረበትም፡፡ የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው ባለሙያዎች በሄሊኮፕተር ቦታውን ተመልክተው የዲዛይን ስራ በመስራት ላይ እንደሆኑ በተደጋጋሚ እንደተለጸላቸው የገለፁት አቶ ታገሰ “ለቱሪዝም ስራ የተከለለው ቦታ በሊዝ ውል መሰረት ጉዳዩ ይታያል” ብለዋል፡፡ “መሬት የአገሪቱ ዋንኛ ሀብት ነው፡፡ በጥንቃቄ ልንጠቀምበት ይገባል” ያሉት አቶ ታገሰ ባለሀብቱ በክልሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራ መስራታቸውን ገልፀው ታጥሮ የተያዘውን ቦታም ያለሙታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ማንኛውም ባለሀብት በእኩል ዓይን እንደሚታይ ያስታወቁት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ባለሀብቱ በሐዋሳ ከተማ የቺፑድ ማምረቻ ፋብሪካ ሰርተው ማጠናቀቃቸው፣ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የቡራዩ ማዘጋጃ ቤት ለሚድሮክ ኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት መገንቢያ በሚል በባለሀብቱ የታጠረው 15.77 ሄክታር ቦታ ታጥሮ ከአሥራ ሁለት ዓመት በላይ እንደቆየ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከማዘጋጃ ቤቱ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው የባለሀብቱ ወኪል ከወቅቱ ከቡራዩ ከንቲባ አቶ ቸርነት ገልሜቻ ጋር በመፈራረም ውል የገቡት በ1989 ዓ.ም ነበር፡፡ ቦታው ታጥሮ ያለግንባታ ለዓመታት ሲቀመጥ የከተማዋ ከንቲባ በተቀየረ ቁጥር አዳዲስ ውል ሲፈፀም ቆይቷል፡፡ አዲስ ከንቲባ በተሰየሙ ቁጥር አዳዲስ ውል የሚፈፀምበት ይኸው ቦታ ያለአንዳች ግንባታ ለዓመታት መቆየቱን ተከትሎ ማዘጋጃ ቤቱ ጥያቄ ማቅረቡን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የማዘጋጃ ቤቱ ሰራተኛ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ባለሀብቱ መሬቱን ሲረከቡ በተገባው ውል መሰረት ሥራ ባለመጀመራቸው መነጠቅ ሲገባቸው እስካሁን ዝም መባላቸው አግባብ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ሌሎች ልማታዊ ያለሆኑ ባለሀብቶች ተመሳሳይ ጥያቄ ሲቀርብላቸው “ባለሀብቶችን ትለያያላችሁ” ይሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የቡራዩ አዲሱ ከንቲባ አቶ ሞቱማ መቀሳ ጉደዩን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ግንባታው የተጓተተው በሲሚንቶና በብረት እጥረት ምክንያት መሆኑ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል፡፡ “ስራውን በውሉ መሠረት እንዲጨርሱ አሁንም ክትትል ይደረጋል” ያሉት ከንቲባው ማንኛውም ግንባታ ውል በተገባ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ መጀመር እንዳለበት የሚያስገድድ ውል መኖሩንም አክለው ገልፀዋል፡፡ በኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖች ሰፋፊ መሬት ወስደው አጥረው የያዙት ሼህ አልአሙዲ በተለይም ሐዋሳ መዳረሻ ጥቁር ውሃ አካባቢ በኤልፎራ ስም የያዙት ሰፊ ቦታ ለ7ኛ የኢሕአዴግ ጉባኤ ወደ ሐዋሳ የመጡ ጉባኤተኞች ቆመው ሲያዩት፣ አንዳንዶቹም ፎቶ ሲያነሱት የጋዜጣው ሪፖርተር በስፍራው በመገኘት ለመመልከት ችሏል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |