| ኩማ ትዕግሥት ጠየቁ |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
በአሰግድ ተፈራ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጊዜያዊነት የአዲስ አበባን ችግሮች በመፍታት ላይ ያተኮረ ስራ ብቻ እንዲሰራ የሚጠየቅ ከሆነ ተቋሙ ሊወጣው ከማይችል አዙሪት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ጠቁመው አስተዳደሩ ስር ነቀል ለውጥ ለማካሄድ የሚያደርገውን ጥረት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በትዕግሥት እንዲጠብቁ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ጠየቁ፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ይህንን የገለፁት በአዲስ አበባ በተለያዩ እርከኖች የተሟላ አገልግሎት ማግኘት አለመቻሉን ተከትሎ ከነዋሪዎች የሚነሳውን ቅሬታ አስመልክቶ ለተጠየቁት በሰጡት ምላሽ ነው፡፡ ከንቲባው በተለይ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት በአዲስ አበባ ተገልጋይን የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት ሰርነቀል ተቋማዊ ለውጥ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ተቋሙ መንቀሳቀስ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን ያስታወቁት አቶ ኩማ በየደረጃው ያለውን የአዲስ አበባን አስተዳደር “. . . ባለሙያዎች በከፍተኛ ሁኔታ የተመናመኑበት፣ በርካታ የተዝረከረኩ ስራዎች ያሉበት” ሲሉ ገልፀውታል፡፡ የአዲሱ አስተዳደር ተቀዳሚ ተግባር የተቋሙን መሰረታዊ ችግሮችና የአሰራር ጉድለቶች ማወቅ በመሆኑ አዲስ መሰረታዊ የአሰራር ማሻሻያ ስርዓት ለመዘርጋት ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ጥናቱም በቅርቡ ይጠናቀቃል፡፡ አቶ ኩማ እንደሚሉት ጥናቱ ችግሮችን መለየት ብቻ ሳይሆን መፍትሄም ስለሚያስቀምጥ ወደ ትግበራው ሽግግር እስኪደረግ ህዝቡ በትእግስት ሊጠብቅ ይገባል፡፡ “አዲስ አበባ በጥናት እስክትታደስ እንዴት እንጠብቃለን?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ከንቲባ ኩማ “ቢሮ ድረስ እየመጡ ለዚህ ነው የመረጥናችሁ? የሚሉ አሉ” በማለት ነው የሚመልሱት፡፡ እንደ ከንቲባው ገለፃ አቤቱታ አቅራቢዎቹ አልተሳሳቱም፡፡ ደጋግመው ግን የሚያስገነዝቡት “በአንድ በኩል መፍትሄ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስር ነቀል ለውጥ ካልተካሄደ ከአምስትና ስድስት ዓመት በኋላ ተቋሙ መስራት የማይችልበት ደረጃ ይደርሳል” በማለት ነው፡፡ የህዝቡ የአገልግሎት ጥያቄና የተቋሙ አገልግሎት የመስጠት አቅም ሊቀራረቡ ባለመቻላቸው ተወደደም ተጠላም መሠረታዊ ለውጥ ማካሄዱ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ከንቲባው በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ የችግሩ ግዝፈት ለአዲሱ አስተዳደር ፈታኝ መሆኑን ያልሸሸጉት አቶ ኩማ ጐን ለጐን ግን ፋታ የማይሰጡትን ችግሮች በመለየት አገልግሎት እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ተግባር ግን ተቋማዊ ለውጥ ስለማያመጣ የአስተዳደሩ ዋና ትኩረት የተጠናው ጥናት ተጠናቆ፣ ባለሙያዎች ሰልጥነው በአዲሱ የመሰረታዊ አሰራር ማሻሻያ መሰረት ወደተግባር የሚገባበትን ጊዜ ማፈጠኑ ላይ ነው፡፡ “ለዘላለም እየተቸገርን ከምንኖር ፋታ የማይሰጡትን ስራዎች በመስራት ለተቋማዊ ለውጥ ስንሰራ ህዝብን እናሳትፋለን” በማለት አቶ ኩማ ተናግረዋል፡፡ “በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ያለው ችግርና አዲስ አበባ ራስዋ የተተበተበችበትን ችግር ያጠናው ጥናት ለሕዝብ ቀርቦ ውይይት ይካሄድበታል” የሚሉት አቶ ኩማ ከዚያ በኋላ የከተማዋ የ5 ዓመት እቅድ ለህዝብ ቀርቦና ዳብሮ እንዲፀድቅ እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡ በአዲስ አበባ የተሟላ ተቋማዊ ስራ በሙሉ ኃይል የሚሰራበትን ጊዜ በትክክል መናገር ባይቻልም በቅርቡ የአስተዳደሩ የምክር ቤት ስብሰባ እንደሚያካሂድ፣ ቢያንስ እስከ ጥር ወር ድረስ ከቀድሞው የተሻለ የሚባል የአገልግሎት አሰጣጥ በየእርከኑ እንደሚኖር ከንቲባው ቃል ገብተዋል፡፡ የህዝቡ ጥያቄና ግፊት እንደማይጠቅም፣ ጥያቄው መነሳቱ ደግሞ አግባብ እንደሆነ የገለፁት አቶ ኩማ ጥናቱ ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም የአዲስ አበባን ችግር እውቆና መፍትሄ አስቀምጦ መስራት ግድ በመሆኑ “ነዋሪዎች ይታገሱ” በማለት ጠይቀዋል፡፡ “የመሬትና የቤት ጥያቄ ብቻ እያስተናገድን እንስራ ካልን አደጋ ውስጥ እንገባለን” ሲሉን ከንቲባው አስጠንቅቀዋል፡፡ በየትኛውም ዓይነትና ደረጃ ችግር ውስጥ ቢኮንም የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንደማይቋረጥ ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡ አያይዘውም ከሲሚንቶና ብረት መወደድ በቀር በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዙሪያ የአስተዳደሩ ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫ ዋንኛው የቤቶች ልማት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |