| አስቸኳይ ጉባዔ ይጠራልን |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
በ4/1/2001 በዚሁ ጋዜጣ በገጽ 1 እና 39 ላይ ያስነበባችሁን የኦሮሞ ባህል ማዕከል ለማስገንባት ጨረታ መውጣት ጉዳይ አቶ አሊዬ ዑመር የሰጡትን አጭር ማብራሪያ በማንበቤ የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ተገድጃለሁ፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት ባለፉት የኢትዮጵያ ገዢዎች ሥር ወድቆ የራሱን መብት ማክበርም ሆነ ማስከበር አለመቻሉ ያለፉት ታሪኮች ይመሰክራሉ፡፡ ዛሬ ደግሞ ከ1983 ጀምሮ ሕዝቦች ክልላቸውንና መብታቸውን አውቀው ማክበርና ማስከበር ተጀምሮ እየተሰራበት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት አሁን ከደረስንበት 21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ያለፉትን የአፄዎች አገዛዝና ተፅእኖዎቻቸውን በማዘን እያስታወስን ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በዲሞክራሲ ስርዓት እራሱን የሚያስተዳድር የኦሮሞ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመሀል ሀገሩ የሆነችውን ፊንፊኔ ላይ የራሱን ባህል ማዕከል ለመገንባት የሚያግደው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ባለፉት የገዢዎች ዘመናት የሌሎች ቤት ሲሰራ የነበረው የኦሮሞ ሕዝብ ዛሬ በመሀል አገሩ ፊንፊኔ ላይ የራሱን የባህል ማዕከል ማሰራት የማይችልበት አንዳችም ምክንያት አይታየኝም፡፡ በመሆኑ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተባባሪነትና አመራር ሰጪነት በአስቸኳይ የኦሮሞ ሕዝብ እንዲወያይበት በማክበር ስጠይቅ ይህ ቤት የመላ ኦሮሞ ሕዝብ የጋራ ቤት መሆኑን አውቀን እንድንንቀሳቀስ በዚህ ሕዝብ ስም አደራ እላለሁ፡፡ (ኩምሳ ቃበታ ገመቹ፣ በፊንፊኔና አካባቢዋ የኦሮሞ ባህልና ቋንቋ ዕድገት ማዕከላዊ ቦርድ ሊቀመንበር፣ ፊንፊኔ) የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ወይስ የሞባይል ቀፎ ተሸካሚ የሞባይል ስልክ መሥመር ለማግኘት ተሰልፈን የሌት ቁርና የቀን ሐሩር ተፈራርቆብናል፡፡ ተራችንን ለማስከበር ከምናውቃቸውና ከማናውቃቸው ሰልፈኞች ጋር ክፉና በጎ ተነጋግረናል፡፡ በግርግርና በግፊያ ሰልፉ ፈርሶ አቅም የሌለን አቅም ባላቸው ወረፋችንን ተነጥቀናል፡፡ ከዚያ ሁሉ ውጣ ውረድና እንግልት በኋላ ያገኘነው የሞባይል ሲም ካርድ (ስልክ) ግን አንድ ሳምንት ቢሠራ ሁለት ሳምንት ይጠፋል፡፡ የእኛ ሲሰራ የምንፈልገው ሰው መስመር ደግሞ በተራው ይጠፋል፡፡ ፈላጊና ተፈላጊ አንገናኝም፡፡ “አልጋው ሲገኝ ባሉ አይገኝ፤ ባሉ ሲገኝ አልጋው አይገኝ” የሚሉት ዓይነት፡፡ በሠፈር ድንገት አደጋ ወይም አስቸኳይ ጉዳይ ቢያጋጥም በሞባይል ስልክ ደውሎ ድረሱልኝ ከማለት በእግር መሄድ እጅግ ይፈጥናል፡፡ እጅግም ይመረጣል፡፡ የቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ይህን ችግር ለመፍታት የሚሰጠው ቀጠሮ ደግሞ ማለቂያ የለውም፡፡ በሐምሌ ይስተካከላል፡፡ በነሐሴ አትጠራጠሩ፡፡ በአዲሱ ዓመትማ የሞባይል ስልክ መሥመር አስገቡ እያለን መቀስቀስ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዳችሁን በር እያንኳኳን እንለምናችኋለን ይለናል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ሳንሆን የሞባይል ቀፎ ተሸካሚ ነን፡፡ (እያዩ ማዘን፣ ከደሴ) ቦታ ተረክበው በማያለሙት ላይ መንግሥት እርምጃ ይውሰድ “ሁዳ ሪል ስቴት የሲቲ ሴንተር የግንባታ ፈቃድ ጊዜ አልፏል” በሚል ርዕስ መስከረም 11 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም. በፊት ገፅ የዘገባችሁትን አነበብኩኝ፡፡ የዜናው ይዘት በአጭሩ ከሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ሁዳ መሃል ፒያሣ (ማዘጋጃ ቤት አጠገብ) ከ 1ዐ ዓመት በፊት ተረክቦ ያጠረውን ቦታ እስካሁን ማልማት እንዳልቻለ የሚያትት ነው፡፡ እንግዲህ ሼሁ በየክልሉ መሬት እየተረከቡ ያጠሯቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው፡፡ ግለሰቡ መንግሥት ልማታዊ ባለሀብቶች እያለ ከሚያቆለጳጵሳቸው አንዱ ቢሆኑም ካለሙት ይልቅ ያጠሩት ቦታ እየበዛ ነው፡፡ ቦታ ተረክበው በፍጥነት ወደ ልማት የማይገቡ ባለሀብቶች ላይ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ካለበት ከሼሁ ሊጀመር ይገባል፡፡ አለበለዚያ የእሳቸው አጥር ሳይነካ ሌሎች ላይ ጣት መቀሰሩ ፍትሀዊ አይሆንምና ቢታሰብበት፡፡ (እነዋቅጅራ፣ ከኦሮሚያ ክልል) ለአገልግሎት ሰጪ ሰራተኞችም ይታሰብላቸው በአሁኑ ጊዜ በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በአገራችን የተከሰተው የኑሮ ውድነት ለማቃለል በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስዷል፡፡ እየተወሰዱም ይገኛሉ፡፡ ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝቡ የቀረበና እየቀረበ ያለው የስንዴና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦትን በዋናነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ አቅርቦቱ ህዝቡን ከከፋ የኑሮ ሰቆቃ በእጅጉ የታደገ ነው ስለመሆኑም የማንም ቅንና አስተዋይ ህሊና አሌ አይለውም፡፡ ይሁን እና የስራውን ኃላፊነት የተሸከመው የእህል ንግድ ኮርፖሬሽን በአሰራሩ ላይ የሚታዩትን አንዳንድ ችግሮች ለማቃለልና ለማስወገድ ሊወስዳቸው የሚገቡ ጥቂት እርምጃዎች አሉ፡፡ በየሽያጭ ጣቢያው ያለውን የስራ እንቅስቃሴ መጠነኛ ክትትል አድርገን እንደተገነዘብነው 1. በዚህ ስራ የተሰለፉ አንዳንድ ሰራተኞች የመኖሪያ ቤታቸውንና የስራው ቦታው የተራራቀ በመሆኑ ለስራው ቅልጥፍና አመቺ አይደለም፡፡ 2. ሰርቪስ መኪና አልተመደበላቸውም 3. የእህል ሽያጭ በሚከናወንበት ወቅት በ”እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም” እና ተዛማጅ ሁኔታዎች ብዙ ውጣ ውረድና ግርግር ስለሚታይ በእህሉና ከእህል ሽያጭ በተገኘው ገንዘብ አያያዝ እንዲሁም አጠባበቅ በኩል ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ 4. ለእህል ግዢ የሚቀርበውን ህዝብ በመመዝገብ የሚረዱ የኮሚቴ አባላት ከስራው ጋር እምብዛም ትውውቅ የሌላቸው በመሆኑ አንዳንድ ችግሮች ሲከሰቱ ሸማቹንና አስተናጋጅ ሰራተኞቹን ማቀራረብና ማሳመን የሚችል ቀልጣፋ መፍትሄ መስጠት ይቸግራቸዋል፡፡ 5. በመንግሥት በተፈቀደው የሥራ ሰዓት እንደማንኛው ገንዘብ አንቀሳቃሽ መሥሪያ ቤት የሽያጭ ገንዘብ የሚቀበሉበት ሂሳቡን በወረቀት መተማመኛ አስፍረው የተረካቢ ሰራተኞችን መድረስ የሚጠብቁት ከዚህ እስከ እዚህ ድረስ ተብሎና በውል ተቆርጦ የተወሰነ ሰዓት የላቸውም፡፡ ይህ ግን የአስረካቢና ተረካቢ ሰራተኞችና ለመንግሥቱ ገንዘብ ደህንነት ሲባል ሊኖር የግድ ነው፡፡ የባንክ ቤቶችን አሰራርና የየእለቱን ሂሳብ አያያዝ በምሳሌነት መውሰድ ይቻላል /ይገባልም/ በየቀኑ ወደ ሽያጭ ጣቢያዎች እየሄዱ ገንዘብ የሚረከቡ ሰራተኞች መኖራቸው በጠንካራ ጎኑ የሚታይ ሲሆን በየጣቢያው የሚደርሱት በመንግሥት የተወሰነው የሥራ ሰዓት ካለፈና ከመሸ በኋላ በመሆኑ የመኖሪያ ቤታቸው ሩቅ የሆኑ ሰራተኞች በሂሳብ ተማምነው ገንዘቡን አስረክበው ቤታቸው ለመድረስ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥርባቸው ከመሆኑ ባሻገር በገንዘብና በተረካቢ ሰራተኞችም ደህንነት አስተማማኝ ዋስትና አይኖረውም፡፡ በመሆኑም መሥሪያ ቤቱ ሰራተኞቹ ለችግር ሳይጋለጡ የመንግሥት ገንዘብም ሳይዝረከረክ በአስተማማኝና በወቅቱ ተሰብስቦ ካዝና እንዲገባ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነት አለበት፡፡ (ፀሐይ አበራና መላኩ አመለወርቅ፣ ከሰሜን አዲስ አበባ) ማረሚያ በእሁድ መስከረም 11 ቀን 2ዐዐ1 እትማችን በመጀመሪያ ገፅ “የኢሕአዴግ የገንዘብ አጠቃቀም ለብክነት የተጋለጠ ነው” በሚል ርዕስ በወጣው ዜና የፓርቲው የኦዲት ኮሚሽን ሰብሳቢ የነበሩት አቶ አቡ ያደታ የሚለው አቶ አብዲሣ ያደታ በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ እየገለፅን ለተፈጠረው ስህተት ውድ አንባቢያንን ከፍ ያለ ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |