| ሚስ ሊቪኒ የጥምር መንግሥት... |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
ሚስ ሊቪኒ የጥምር መንግሥት ለማቋቋም አቅደዋል
ከድሉ በኋላ ከከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት ያካሂዱት ሚስ ሊቭኒ የጥምረት መንግሥት ለመመስረት እንደሚሞክሩ ካልሆነ ግን ጠቅላላ ምርጫ እንዲካሄድ እንደሚያደርጉና በምርጫውም እንደሚያሸንፉ መናገራቸው ተገልጿል፡፡ ለፓርቲው ሊቀመንበርነት የተወዳደሩት ተቀናቃኛቸው ሚስተር ሻወል ሞፉዝ ለተወሰነ ጊዜ እራሳቸውን ከፖለቲካው እንደሚያርቁ አስታውቀዋል፡፡ ሚስ ሊቭኒ ተቀናቃኛቸውን ያሸነፉት በ1.1 በመቶ እጅግ ጠባብ ውጤት ነው፡፡ የሚዲያ ዘገባዎች እንደሚሉት የሚስ ሊቬኒ የጥምር መንግሥት የመመስረት እቅድ በቀላሉ የሚሳካ አይመስልም፡፡ በተለይም የካዲማ ፓርቲ ተባባሪ የሆነው ሌበር ፓርቲ ጠቅላላ ምርጫ እንዲካሄድ መፈለጉ ጉዳዩን አጠራጣሪ አድርጐታል፡፡ አንዳንድ ተንታኞች እንደገመቱት በ431 ድምጽ የተሸነፉት ሚስተር ሞፋዝ ካዲማን ፓርቲን በመተው ሊኩድ ፓርቲ ሊቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ ሰውየው በደረሰባቸው ሽንፈት በጣም መበሳጨታቸው ታውቋል፡፡ "ሞፋዝ እዚህ እኛ ጋር ባለመገኘቱና ከፖለቲካው መድረክ ለተወሰነ ጊዜ እንደሚርቅ በመስማቴ አዝኛለሁ" ያሉት ሚስ ሊቭኒ ከሞፋዝ ጋር የመስራት ፍላጐት እንዳላቸው በግልጽ ተናግረዋል፡፡ የገዢው ካዲማ ፓርቲ መሪ መሆናቸው ባለፈው ሳምንት ሀሙስ በይፋ የተገለፀው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስ ሊቪኒ ራሳቸውን ከስልጣን ያገለሉትን የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርትን በመተካት የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ሊይዙ ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ግምትም ተሰጥቷቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1958 የተወለዱት ሚስ ሊቭኒ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሁለተኛዋ ሴት ናቸው፡፡ የመጀመሪያዋ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሚስ ጐልዳ ሜይር ኋላ ላይም ከ1969 እስከ 1974 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት እድሜያቸው 5ዐ የሞላው ሚስ ሊቪኒ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርት ከስልጣናቸው መልቀቅ አለባቸው በማለት ዘመቻ የጀመሩት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ እ.ኤ.አ በ2ዐዐ6 በተካሄደው የሊባኖስ ጦርነት የኦልመርትን አካሄድም አውግዘዋል፡፡ ዚፒ ሊቭኒ ለእስራኤል ፓርላማ ተወዳድረው ያሸነፉት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነው፡፡ የፓርላማ አባል ከሆኑ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የካቢኔ አባል መሆን ችለዋል፡፡ ከተዋጊና አክራሪ እስራኤላዊያን ቤተሰቦች የተወለዱት ሚስ ሊቪኒ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል መግባባት እንዲፈጠር የሚፈልጉ ለዘብተኛ የፖለቲካ ሰው መሆናቸው ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሚስ ሊቭኒ በፓርላማ ተወዳድረው ያሸነፉት የሊኩድ ፓርቲ አባል በመሆን ነበር፡፡ የእስራኤልና የፍልስጥኤም ግጭት በተለየ መልኩ እየተቀየረ ሲመጣ ግን የሊቪኒም አመለካከት እየተቀየረ መምጣት ጀመረ፡፡ ሚስ ሊቭኒ በሌበር ፓርቲው መሪ የተፈረመውን የኦስሎ ስምምነት ለረጅም ጊዜ ሲቃወሙ ነበር የኖሩት፡፡ ነገር ግን የ2ዐዐ1 የፍልስጤማውያን አመጽ እየተስፋፋ ሲመጣ በእስራኤላውያን ላይ የሚፈፀመው የቦምብ ጥቃት ሲጨምር ሚስ ሊቪኒ ከልጅነታቸው ጀምሮ ይዘውት የቆዩትን አቋም መገምገም ጀመሩ፡፡ ከዚያም የእስራኤልና የፍልስጤም ችግር የሚፈታው በድርድር ብቻ መሆኑን እንደሚያምኑ ገለፁ፡፡ ይህ የሊቭኒ አመለካከት ከጊዜ ወደጊዜ እየጐለበተ መጣ እንጂ አልተቀየረም፡፡ እ.ኤ.አ በ2ዐዐ5 የእስራኤልን ጦር ከጋዛ የማስወጣት ዕቅድ በመደገፍ አሪያል ሻሮንን ሲረዱ የቆዩት ይህች ሴት ኋላ ላይም ከእኝሁ ሰው ጋር በመሆን ሊኩድ ፓርቲን በመተው የካዲማ ፓርቲን አቋቁመዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2ዐዐ6 በተመሰረተው 31ኛ የእስራኤል መንግሥት ሚስ ሊቭኒ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ስልጣን ተረክበው ቃለ መሀላ ፈፅመዋል፡፡ ከሊቭኒ ጋር በመተባበር የእስራኤል ፍልስጤም የሰላም ሂደት በአዲስ መንፈስ እንዲጀመር እየሰሩ ያሉት ምዕራባውያን ዲኘሎማቶች ሚስ ሌቪኒን ለስላሳ ሴት አድርጐ በሚስሏቸው ሚዲያዎች ይስቃሉ፡፡ "ሴትዮዋ ለስላሳ አይደለችም፡፡ ጠንካራ ሴት ነች፡፡ የእስራአልና ፍልስጤም ስምምነት ለሰላም ዋና መሠረት መሆኑን ግን ታምናለች" ሚስ ሊቪኒ ባለፈው ወር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት የሰላም ስምምነት ይፈረማል የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከስልጣናቸው ከመልቀቃቸው በፊት የሰላም ስምምነት ይፈርማል ሲሉ ከነበሩት ኘሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ሀሳብ የተለየ ሆኗል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊቨኒ እንዳሰቡት የጥምር መንግሥት መመስረት ከቻሉና በምርጫ ካሸነፉ ከ3ዐ ዓመት በኋላ የመጀመሪያዋ የእስራኤል ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ፡፡ እ.ኤ.አ በማርች 2ዐዐ6 ከተካሄደው የፓርላማ ምርጫ በኋላ ሊቨኒ በእስራኤል ውስጥ ሁለተኛዋ ኃይለኛ የፖለቲካ ሰው ተደርገው ሲጠቀሱ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2ዐዐ7 የወጣው ታይም መጽሄት በአለም ላይ ከሚገኙ 1ዐዐ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች ውስጥ ሚስ ሊቭኒን አንዷ አድርጐ ጠቅሷቸዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |