Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የሶማሊያ “ትርፍ” እና “ኪሣራ”
የሶማሊያ “ትርፍ” እና “ኪሣራ” E-mail
Sunday, 28 September 2008
በጌታቸው ንጋቱ

የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ለ18 ዓመታት ያህል መንግስት አልባ ወደሆነችው ሶማሊያ ካመራ ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን ተቃርቧል፡፡ የሶማሊያ መረጋጋት እየራቀ፣ የሶማሊያ ዜጎችም መስማማት አቅቷቸው እንደአለፉት ዘመናት ሁሉ የአገሪቱ ሕዝቦች እየተሰደዱና ያለመረጋጋቱ ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦሯን መላኳን ምክንያታዊ በማድረግ ስታቀርብ ሌሎች ወገኖች ግን ኢትዮጵያ ሶማሊያን በኃይል ወርራ ይዛለች በማለት ይተቻሉ፡፡ የሶማሊያ አክራሪ ኃይሎች ሞቃዲሾን በተቆጣጠሩበትና ደካማው የአብዱላሂ ዩሱፍ የሽግግር መንግስት ወዳለበት የባይደዋ ከተማ ሲገሰግሱ የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን ወደ ሶማሊያ ለማዝመት ተገዶ ነበር፡፡ ምክንያቶቹም አክራሪዎቹ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት በማወጃቸውና ኢትዮጵያን የማጥቃት ዕቅድ ስላላቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመመከት፣ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ማለትም በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት ጭምር እውቅናና ድጋፍ የተሰጠውን የሶማሊያ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት መታደግ ነበር፡፡

የሼክ አዌይስ እስላማዊ ምክር ቤት የኢትዮጵያን ጦር መመከት ሳይችል የተበታተነ ሲሆን የኢትዮጵያ ጦር መውጣት ግን እንደ መግባቱ ቀላል አልሆነም፡፡ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ራሱን መከላከል የማይችል ደካማ መሆኑና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወደ ሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ የገባውን ቃል አለመተግበሩ የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያን ግዛት ለቆ እንዳይወጣ አድርገውታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን ወደ ግዛቱ ለመመለስ ይፈልጋል፤ ግን አልቻለም፡፡ የሶማሊያ ኃይሎች የኢትዮጵያን ጦር በምድራቸው ማየት እንደማይፈልጉ ይገልፃሉ፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ በመውጣቱ በመርህ ደረጃ ይስማማል፤ ግን ጊዜው ገና ነው ይላሉ፡፡ ከጦሩ መውጣት አለመውጣት ይልቅ ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦሯን በመላኳ ምን አገኘች? ምን አጣች? ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር አንፃር የተሰራው ሥራ አዋጭነቱ ምን ያህል ነው የሚለውን ከተለያዩ ወገኖች አስተያየት አንፃር መቃኘት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦሯን መላክና በዚያው ግዛት እስካሁን ለሁለት ዓመታት ያህል እንዲቆይ ማድረጓ ያስገኘላት ፖለቲካዊ ትርፍ ቢኖር በአፍሪካ ቀንድ ይህንን ለማድረግ የምትችል ብቸኛ ክልላዊ ኃይል (regional power) መሆኗን ለሌሎች የማሳየት ዕድል ነው፡፡ ኬንያና ጅቡቲ ይህንን ለማድረግ የማይቻላቸው አገራት እንደሆኑ የተረዳችው አሜሪካም ለኢትዮጵያ መንግሥት ያላት አመለካከት የተለየ መሆኑን የአገሪቱ ባለስልጣናት በተለያዩ አጋጣሚዎች ይገልፃል፡፡

ኢትዮጵያ የአካባቢው ኃይል መሆኗን ለማስመስከርም በሶማሊያ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች ማስማማት፣ አንድ ላይ ሆነው መንግስታቸውን እንዲመሰርቱ የማድረግ ሥራም አለበት፡፡ የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግስት ማቋቋም ፈታኝ ከመሆኑ አንፃር ግን አገሪቱ ከፍተኛ ጋሬጣ ተደቅኖባታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ሶማሊያ ያደረገው ዘመቻ ድጋፍም ተቃውሞም አስከትሎበታል፡፡ በፖለቲካ ትርፍነት አንፃር የሚጠቀሰው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመርህ ደረጃ የሰጠው ድጋፍ ነው፡፡ ጦርነቱን ኢትዮጵያ በአሜሪካ ትዕዛዝ እንደፈፀመችው ሲገለጽ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከአሜሪካ ሠባራ ሳንቲም እንዳላገኘና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለመመከት ሲል ጦሩ ወደ ሶማሊያ መላኩን ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚደግፉ ኃይሎች የመኖራቸውን ኃይል የአገሪቱን ገጽታ ጥላሸት የቀቡና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ኪሳራ ያደረሱ ተቋማትም ተቃውሞ ተሰምቷል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን ለቆ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ጦሩ ሰብዓዊ መብቶችን ጥሷል በማለትም ይከሳሉ፡፡ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የኢትዮጵያ ጦር ሰብዓዊ መብት እየጣሰና በሲቪል የሶማሊያ ዜጎች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች እየፈፀመ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝብ ግንኙነትም ቀድሞ ከማጥቃት ይልቅ የመንግስት ስም ከጠፋ በኋላ ለመመከት ስለሚሞክር ብዙም አዋጭነት ያለው ሥራ እንዳልሰራ ይገልፃል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን በመላክ የሽግግር መንግስቱን ለመደገፍና ለማጠናከር ቢሞክርም የሽግግር መንግስቱ አመራሮች ግን በየጊዜው በስልጣን ክፍፍል፣ በጎሳ እና በጥቅማ ጥቅም በመበጣበጥ የኢትዮጵያን ጥረት መና እያስቀሩትም ይገኛሉ፡፡ በጂቡቲ ከሶማሊያ ተቃዋሚዎች ጋር የሽግግር መንግስቱ ድርድር ቢጀምርም የሽግግር መንግስቱ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ተበጣብጠው ኢትዮጵያ ሁለቱን ለማስታረቅ ከአስር ቀናት በላይ ማደራደር ነበረባት፡፡ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር ሁለት ዓመት እየረዳት አሁንም ያለችበት ደረጃ ተስፋ የሚያሰቆርጥ መሆኑ የኢትዮጵያ መንግስትን ትርፍ አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ለችግራቸው ራሳቸው ሶማሊያውያን መውጫ ካላበጁ ማንም ሊረዳቸው እንደማይችልና በተለይ የፕሬዚዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብጥብጥ አሳፋሪ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ ሲያመራና የሽግግር መንግስቱ ወደ ሞቃዲሾ ሲመለስ የነበረው ሕሳቤ (assumption) የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰላም አስከባሪ ጦር ይልካል፣ ሶማሊያን መልሶ ለማቋቋምም ከፍተኛ ርብርብ ያደርጋል የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኡጋንዳ ከላከቻቸው ጥቂት ወታደሮች በስተቀር ኢትዮጵያ እንደገባሽበት ተወጪው ተብሎ የተተወች ነው የምትመስለው፡፡ የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያን ሰላም በመርህ ደረጃ ከመደገፍ አልፈው በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እና የተረጋጋ መንግስት እንዲቋቋም ያደረጉት ተጨባጭ ጥረት ደካማ ነው፡፡ ይህም የአካባቢው ኃይል መሆኗን በተለይ በሶማሊያ ላይ ላስመሰከረችው ኢትዮጵያ የፖለቲካ ክስረት ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር ሰብዓዊ መብት በሶማሊያ የኢትዮጵያ ጦር እየጣሰ ነው እያላት የምታገኘው የፖለቲካ ትርፍ የሚያወላዳ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ ያደረገው ዘመቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን የፀረ ሽብርተኝነት ትግል በከፍተኛ ደረጃ ያገዘ መሆኑን የአሜሪካ መንግስት በተደጋጋሚ ይገልፃል፡፡ ሶማሊያ የአልቃይዳን መሪዎች ጨምሮ የዓለም አቀፍ ሽብርተኞች መሸሸጊያ በመሆኗ የኢትዮጵያ መንግስት የአክራሪ ቡድኑን አከርካሪ በመምታቱ አሜሪካ ደስተኛ ነበረች፡፡ የኢትዮጵያን ጦር ዘመቻ በመደገፍም በአየር የተጠኑ የሽብርተኞች መደበቂያዎችን የአሜሪካ መንግስት ደብድቧል፡፡ በዚህም አገራቱ ተነጋግረውና ተስማምተው ጦርነቱን አብረው በእስላማዊ ምክር ቤቱ ጦር ላይ ማካሄዳቸው ይገለፃል፡፡

የእስላማዊ ቡድኑ ከመደራጀት ወደ መበታተን ተቀየረ እንጂ ሙሉ በሙሉ ሊደመሰስ አልቻለም፡፡ ለዚህም የሶማሊያ ሕዝብ ውስጥ ተሸሽገው ለመኖር አመቺ ሁኔታ ስለተፈጠረላቸው መሆኑ ይገለፃል፡፡ በሶማሊያ አሁንም የቦምብና የሞርታል ጥቃቶች የዕለት ተዕለት ወጎች ናቸው፡፡ አክራሪ ኃይሎቹ በኢትዮጵያ ጦር አልፎ ተርፎም በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪዎች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ ነው፡፡ ከሁሉም ወገኖች ሕይወት በየዕለቱ ያልፋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ጦር የሞቃዲሾንና የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥና ራሱንም ለመከላከል በሚል አንዲት እርምጃ ሲወስድ የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብና የሚዲያ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግሥት ሲቪል ሶማሊያውያንን እየገደለ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ጦር የተሰሩበትን ዜናዎች ከማስተባበልና የቀረቡትን ሪፖርቶች ከማጣጣል ያለፈ መሄድ አልቻለም፡፡ ”አንድ መስጊድ ውስጥ የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያውያን የመስጊድ አገልጋዮችን አንገታቸውን እየቀላ ገደላቸው” የሚል ሪፖርት በአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ቀረበ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት “ይህ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሥራ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት የወረደ ሞራል የኢትዮጵያ ጦር በታሪኩ ፈጽሞ አያውቅም” በሚል ማስተባበያ ቢሰጥም ቀደም ብሎ የወጣው የአምኒስቲ ሪፖርት የበለጠ ኃይል ነበረው፡፡ በመሆኑም የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዋና ዜናዎች የኢትዮጵያ ጦር አጠፋ፤ ሠላማዊ ዜጎች አረደ የተባለው ሆኖ የኢትዮጵያ ማስተባበያ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው ቀርቷል፡፡ ይህ አገሪቱ በሶማሊያ ጉዳይ እየደረሰባት ያለውን ኪሳራ የሚያሳይ ነው፡፡

ከኢኮኖሚ አንፃር ያለውን ክስረትና ጠቀሜታ ሲቃኝ ሁለት ዓይነት አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦሯን በመላኳ ተጨማሪ ወጪ እንዳላወጣችና ያወጣችው ወጪም ጦሩ ኢትዮጵያም ቢሆን የሚወጣለትንና የተመደበለትን በጀት እንጂ የተለየ ኪሳራ በኢኮኖሚው ላይ እንዳልደረሰና የመከላከያ በጀቱንም እንዳላዛባው ገልፀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሰጡት አስተያየት የሶማሊያ ጦርነትና በሶማሊያ መቆየት እጅግ አክሳሪ መሆኑንና አገሪቱም ለሶማሊያ ብዙ እየከፈለች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ያደረገችው ዘመቻ በአሜሪካ መንግስት ሙሉ ወጪው እንደተሸፈነ አሜሪካ ከጦርነቱም ወጪ በላይ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎች ማድረጓ በተለያዩ ወገኖች ሲገለጽ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከአሜሪካም ይሁን ከሌላ አገራት ለጦርነቱ ቤሳቤስቲን አለማግኘቱን ያስረዳል፡፡ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የኢኮኖሚ ኪሳራ ቢደርስ ተቀባይነት ይኖረዋል፤ ይሁን እንጂ የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ችላ ላላት ሶማሊያና ራሳቸው ሶማሊያውያን ደንታ ላጡላት ምድር የአንድ ጥይት ዋጋ ማውጣት እንዴት ምክንያታዊ ይሆናል? በማለት የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ይገልፃሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስታት ከሶማሊያ ወገን የሚሰነዘረውን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ተግባራት በተለያዩ ጊዜያቶች ሲመክቱና የአገሪቱንም ሉዓላዊነት ሲያስከብሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ማስከበር መቻሏ እንዳለ ሆኖ ዓለም ትኩረት በነፈጋት ምድር የሽግግር መንግስቱ እንዲጠናከርና በእግሩ እንዲቆም እየጣረች መሆኗን ትገልፃለች፡፡ ሶማሊያውያን ግን ይህንን የኢትዮጵያና ጥቂት የውጭ ድጋፎች እየረዱ አለመሆኑንና ብዙም ተስፋ የሚሰጡና የሚያበረታቱ ነገሮች ከሌሎች ወገኖች አለመታየታቸው የኢትዮጵያን መንግስት ልፋት በድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ምድር ብቻዋን ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች፡፡ ምን አተረፈች የሚለው ሲታይ አንደኛው አገሪቱ ሉዓላዊነቷን አስከበረች፤ የሚል ሲሆን ሌላው የጽድቅ ሥራ ማለትም የሽግግር መንግስቱን ረዳች፣ ለሶማሊያ ሠላም ብቻዋን እየታገለች ነው እና ሌሎችም ይገለፃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ ደካማ፣ የራሷ ሕዝቦች በቸነፈር እየተቆሉ ያሉባትና ሌሎችም ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እያስተናገደች ያለች አገር ሆና ሌላ የጎረቤት ራስምታት ታስታምማለች፡፡ ወደ ሶማሊያ የተደረገው ዘመቻና አሁንም እየተከፈለ ያለው መስዋዕትነት የብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር አንፃር ያለው ትርጉምም አጠያያቂ ሆኗል፡፡

አሜሪካ በኢራቅ ላይ ዘመቻ ከፍታ ጊዜያዊ ድል አግኝታለች፡፡ ያ ድል በኢራቅ ሠላም አላመጣም፡፡ የኢራቅ ዜጎች ይሞታሉ፤ የአሜሪካ ወታደሮች ይገደላሉ፤ የአሜሪካ ሕዝብ የኢራቁን ጦርነት ይወቅሳል፤ ልጆቻችን ወደ አገራቸው ይመለሱ እያለ ይጠይቃል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ጥቅሙን እያስከበረ መሆኑን ይገልፃል፤ ሣዳም ሁሴንን አሜሪካ በአለም ሕዝብ ፊት አሰቅላለች፡፡ ኢራቅ ያላት የነዳጅ ሃብት የአሜሪካን ፍላጎት የሳበ ከመሆኑም በላይ በኢኮኖሚ አንፃር ያወጣችውን ወጪ ከኢራቅ ልታገኘው በምትችለው ነዳጅ እንደመታካክሰው የሚገልፁም አሉ፡፡

በሶማሊያ ይህ ትርጉም የለውም፡፡ የሶማሊያ ሕዝቦች እርስ በርስ የሚጋጩት አጀብ የሚባልለት ሃብት ኖሯቸው አይደለም፡፡ ሃብትም የአለመግባባት መነሻ ሆኖ በሶማሊያ ተነስቶ አያውቅም፡፡ በጎሳ እኔ እበልጣለሁ፣ እኔ እበልጣለሁ ግብግብ አገሪቱም፤ ሕዝቡም ብዙ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ አልፎ ተርፎም ለጎረቤት አገራት የሥጋት ምንጭ እንዲሁም ቀውስ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጦር ሁለት ዓመታት ያህል በሶማሊያ ቆይቷል፤ ሶማሊያም ያው የ18 ዓመታቱ ሶማሊያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን እንዴት ማውጣት እንዳለበት እያሰላሰለ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ቢወጣ ሶማሊያ አሁን ካለችበት ወደባሰ አዘቅት ትገባለች፤ አሁን መውጣት የለበትም የሚሉ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ኃያላንም የተሻለ መፍትሄ ይዘው መቅረብ አልቻሉም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በፖለቲካ ካገኘው ትርፍና ኪሳራ፤ ኪሳራው እንደሚያመዝን የሚገልፁ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች መንግስት በፍጥነት ሶማሊያን ለቆ ይውጣ ይላሉ፡፡ የአገሪቱን ዲፕሎማሲ ክፉኛ የሚጎዱ ሪፖርቶችና ዘገባዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ይቀርባሉ፤ ለሠራዊቱ ከፍተኛ ወጪ እየተደረገ ይገኛል፤ ሶማሊያ ዛሬ ተስፋ አገኘች ሲባል ነገ ተመልሳ ወደ ጨለማ ትወርዳለች፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የረባ ተሳትፎ እያደረገ አይደለም፤ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ በተባለው ብዛትና ፍጥነት አልቀረበም፡፡ ኢትዮጵያ ታዲያ ሉዓላዊነቷን ካስጠበቀች በኋላ ለብቻዋ እስከመቼ የሶማሊያን ችግር ትገፋዋለች? አገሪቱስ ምን ተረፋት? የኢትዮጵያስ ጦር መቼ ከሶማሊያ ምድር ለቆ ይወጣል?  ምላሽ ይሻሉ፡፡         

 
< Prev   Next >