| ኢኮኖሚያችን “ሾክ አብዞርበር” የለውም! |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
የኢኮኖሚያችንን ሁኔታ በምንመረምርበት ወቅት እያደገ ነው? ወይስ እየወደቀ? የሚለውን ብቻ ሳይሆን፣ ችግር ሲያጋጥም ሊያግደረድረን የሚያስችል አቅም አለው ወይ የሚለውን ጭምር መሆን አለበት፡፡ መኪኖችና ሌሎች ማሽኖች ሲንገጫገጩ፣ ኮረኮንቻማ ቦታ ላይ ሲጓዙ፣ ከፍ ዝቅ ሲሉ፣ እንዳይሰበሩና እንዳይወላልቁ፣ እንዳይወድቁ "SHOCK ABSORBER" (ሾክ አብዞርበር) ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ከበዛ አደጋና ከኪሳራ ይድናሉ፡፡ ኢኮኖሚያችን ችግር ሲያጋጥመው፣ ሲንገጫገጭ፣ ከፍና ዝቅ ሲል ከስብራትና ከመወላለቅ የሚያግደው መከላከያ ያለ አይመስልም፡፡ ባጭሩ ኢኮኖሚያችን ..ሾክ አብዞርበር.. የለውም፡፡ ከአበባም፣ ከቡናም፣ ከቅመማ ቅመምም፣ ከቆዳና ሌጦም ከሌላ ሌላም ኤክስፖርት የምናገኘው የውጭ ምንዛሬ አለ፡፡ ነገር ሁሉ ደህና ሲሆንና ዓለም በተረጋጋ መንፈስ ሲጓዝ እንደምንም ካለን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታችንን እያቻቻልን እንጓዛለን፡፡ ግን የነዳጅ፣ የብረት፣ የሲሚንቶ ዋጋ በዓለም ደረጃ ጨመረ ሲባል ንግድ፣ እርሻና ኢንዱስትሪው ይንገጫገጫል፡፡ ሾክ አብዞርበር ስለሌለው ይሰበራል፡፡ ይላላል፣ ይወላልቃል፡፡ የውጭ ምንዛሬ አንሷል፤ ወይም ጠፍቷል፤ ተብሎ ኢምፖርት ይዳከማል፡፡ ኤል.ሲ መክፈት ችግር ይሆናል፡፡ ይህ የሚያሳየን የኤክስፖርት እንቅስቃሴያችን ከስብራት፣ ከመጉበጥና መወላለቅ የሚያድነው “ሾክ አብዞርበር” የሌለው መሆኑን ነው፡፡ የኤክስፖርት እንቅስቃሴያችን ችግር ውስጥ ገባ፤ ማለት የኢምፖርት ሥራችንም እንደዚሁ ችግር ውስጥ ገባ ማለት ነው፡፡ ተያይዘው ይዳከማሉ፣ ይሰበራሉ፡፡ ለችግር ጊዜ የሚሆን ሸክምና መገነጣጠልን የሚችል ድጋፍ ሰጪ አካል የላቸውምና፡፡ እርሻችንም ቢሆን፣ እንደዚሁ “ሾክ አብዞርበር” የለውም፡፡ ደህና ዝናብ ባለበት ወቅት ደህና እህል ይገኛል፡፡ ረሃብ አይኖርም፣ ሞት አይኖርም፤ መፈናቀል አይኖርም፡፡ የዝናብ እጥረት ወይም መጥፋት ሲያጋጥም ግን መላው የሰብል ሁኔታችን ውልቅልቁ ይወጣል፡፡ በየጎተራው ያለ ይከፈት፣ ይውጣ፣ ለገበያ ይዋል የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ እህል ይጠፋል፣ ዋጋ ይንራል፣ ረሃብ ይከሰታል፡፡ መፈናቀል ይታያል፡፡ ሞትም ያንዣብባል፡፡ ይህ የሚያሳየንም የእርሻ ኢኮኖሚያችንም “ሾክ አብዞርበር” የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ሰኞ ጠግበን ማክሰኞ የምንራብ ሆነናል፡፡ ከምግብ ጋር በተያያዘ ህይወታችን መከላከያ የለውም፤ ማለት ደግሞ ኑሯችንም ዋስትና እያጣ ነው ማለት ነው፡፡ ኢምፖርት፣ ኤክስፖርት የእርሻ ድጋፍና ዋስትና ካጣ ኢንዱስትሪውም እንደዚሁ “ሾክ አብዞርበር” የለውም ማለት ነው፡፡ በውጭ ምንዛሬ እጦት ጥሬ ዕቃና አስፈላጊ መለዋወጫ ያጣል፡፡ በነዳጅ ንረት የትራንስፖርት ዋጋው የማይቻል ይሆናል፡፡ ኢንዱስትሪውም ይንገዳገዳል፡፡ እያስተዋልነው ነው፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎቻን የመድሃኒት ፋብሪካዎቻችን ከህንድና ከቻይና የሚመጡ ርካሽ ምርቶችና በኮንትሮባንድ በሚገቡ ዕቃዎች ምክንያት ሲንገጫገጩና ሲዘጉ ሲሰበሩ በርካታዎቹ መዘጋታቸውን አይተነዋል፡፡ “ሾክ አብዞርበር” የላቸውም፡፡ ለኢኮኖሚያችን “ሾክ አብዞርበር” መግጠም ይቻላልን? ይህ ጥያቄ በቀላሉ ሲተረጎም አንዳንድ ችግሮች ሲያጋጥምም ኢኮኖሚያችን መቋቋም እንዲችል ማድረግ ይቻላልን? ነው፡፡ በርግጥ ሰሞኑን በግልጽ እያየነው እንዳለነው ጠንካራ ኢኮኖሚ አላቸው የሚባሉት አሜሪካና እንግሊዝም ኢኮኖሚያቸው ተንገዳግዷል፡፡ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተደረገለትም ሊወላልቅ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ችግርን እየተቋቋመ ረዥም ጊዜ መጥቷል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ እንዳይወድቅና እንዳይወላልቅ በመቶ ቢልዩን ዶላር የሚገመት ገንዘብ እየተደጎመ ነው፡፡ ይህ ማለት የአሜሪካና የእንግሊዝ ኢኮኖሚም “ሾክ አብዞርበር” ተገጥሞለታል ማለት ነው፡፡ በዘላቂነት የሚታይ ጠንካራ ኢኮኖሚ የሚባል ነገር የለም፡፡ “ሾክ አብዞርበር” የተገጠመላቸው ኢኮኖሚዎች ግን ተንገጫግጨውም አይሰበሩም፡፡ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚም “ሾክ አብዞርበር” ሊገጠምላት ይችላል፡፡ ኤክስፖርትን ማጠናከር ይቻላል፡፡ እርሻዎችንም ማጠናከር ይቻላል፡፡ እንዴት? ፖሊሲዎችን በማስተካከልና በማጠናከር፣ መዋቅሮችን በማስተካከል “ሾክ አብዞርበር” መግጠም ይቻላል፡፡ እውነት የእርሻ ምርትን ከዚህ በላይ ማጠናከር ለኢትዮጵያ አስቸጋሪና የማይቻል ነውን? ይቻላል፡፡ ማጠናከርና ማሻሻል ይቻላል፡፡ ህንድና ቻይና ከኢትዮጵያ የተሻለ የአየር ጠባይ ኖሯቸው አይደለም፤ በምግብ ከመቸገር ተላቀው ወደ ምግብ ኤክስፖርትነት የተቀየሩት፡፡ እንዲህ ሊሆኑ የቻሉት ፖሊሲያቸውን ስላስተካከሉ ነው፡፡ ለሰፋፊ ሜካናይዝድ እርሻዎች ቦታ ስለሰጡ፣ በዚህ ለሚሰማራ ባለሀብት ማበረታቻ ስላደረጉና ለዓለም ኢንቨስተሮች ትኩረት ስለሰጡ ነው፡፡ እኛም እንደዚሁ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይህን ስላላደረግን ነው ስንዴ ኤክስፖርት ማድረግ እየቻልን ስንዴ ኢምፖርት የምናደርገው፡፡ ከዚህ በላይም “ቀይ ካርድ” መጠበቅ የለብንም፡፡ ኤክስፖርታችን በእርሻ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ፣ አስተማማኝና ዘመናዊ የእርሻ ፖሊሲ፣ የኤክስፖርት አቅማችንን ያጠነክረዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አቅማችንን ያሳድገዋል፡፡ ኤክስፖርትም ኢምፓርትም ይጠናከራል፡፡ ኢንዱስትሪውም ይጠነክራል፡፡ ዋናው ቁም ነገር፣ ኢኮኖሚያችን “ሾክ አብዞርበር” እንደሚያስፈልገው ማመንና “ሾክ አብዞርበር” ለመግጠም ፖሊሲያችንና አሰራራችንን ማስተካከል የሚያስፈልግ መሆኑ ነው፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 28 September 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |