Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow እፍኝ ሰጥቶ በቁና መቀበል
እፍኝ ሰጥቶ በቁና መቀበል E-mail
Sunday, 28 September 2008
በአብርሃም ግሩም

በአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማው ሰሞን እኔና አንድ የልብ ወዳጄ አቅራቢያችን ከሚገኝ ካፍቴሪያ ታድመናል፡፡ ከሻይ ቡናችን ጋር የበዓሉን ወሬም ፉት እያልንለት እያነሳን እንጥላለን፡፡

ካለንበት ጥቂት ፈቅ ብሎ የተቀመጠ አንድ የክፍለ አገር ሰው ወሬያችን ስቦት ተቀላቀለ፡፡ “ይገርማል፡፡ አዲስ አበባ ሁሉም ነገር ወረት ነው፡፡ ዛሬ ካልሆነ ዛሬ ካልተደረገ ሞቼ እገኛለሁ ነው ነገሩ ሁሉ፡፡ እንግዳችን ከትዝብቱ መለስ አለና ጥያቄ አከታተለ፡፡ ለመሆኑ .ዶሮ ስንት ገባ?”

“ሰባ፣ ሰማንያ ይባላል፡፡ ማምሻውን ካልጨመረ” ብሎ ወዳጄ ይመልሳል፡፡ ጉድ ሳይሰማ . . . እንዲሉ ሰውዬአችን መብሰክሰኩን ጀመረ፡፡ “ፈርቼ እንጂ እንዲህ መሆኑን ባውቅማ ዶሮዎቼን በርካሽ አልጥላቸውም ነበር” በስንት ብሸጣቸው ነው ብለን በመገረም አላቆምንም እርሱም እንደዚያው፡፡

“ይገርማችኋል፡፡ በ2ዐ ብር ምን የመሳሰሉ ዶሮዎች በርከት አድርጌ ገዝቼ መጣሁ” በ5ዐ እና 6ዐ ብር ቸብችቤ ጨረስኳቸው፡፡ ይሞቱብኝና ጉዴ ይፈላል ብዬ እንጂ ዋጋ እንደሚጨምርማ አስቤው ነበር፡፡

ለአፍታ ዝምታ ሆነ፡፡ እንግዳው ቁጭቱን ማስወጫ ፍለጋ ይሁን አሊያም ጉዳይ ኖሮት እመር ብሎ ይወጣል፡፡

ለመሆኑ ነጋዴዎች ስንት ቢያገኙ ነው የሚጠረቁት? ለመሆኑ ሦስት አራት እጥፍ አትርፈውም ከተቆጩ የያዙት ንግድ ሳይሆን፣ ሰጥቶ መቀበል ሳይሆን መበዝበዝ ቆንጥሮ ሰጥቶ ማስተፋት ይመስልባቸዋል፡፡

እርግጥ ሁሉም አይደሉም፡፡ ተመጣጣኙን አትርፈው ለተጠቃሚውም አስበው የሚሰሩ በርካቶች አሉ፡፡”ነገ ተመልሶ ይመጣል፣ ደንበኛ ይሆነኛል የሚሉ በርካቶች እንዳሉ ሁሉ በአንድ ቀን ትርፍ የሰማይ ደጅ ለመክፈት በሚመስል አኳኋን የሚሰሩት ቀናዎቹን ውጠዋቸዋል፡፡

በነፃ ገበያ ሥም፣ “የት ይሄዳል፡፡ ያው ዞሮ ሲያጣ ይመጣታል” እየተባለ በሰበብ አስባቡ ሰማይ የነካ ዋጋ ይጠይቃል፡፡

በተለይ አገልግሎት መስጫ አካባቢ ስንመለከት ጉዳዩ የጐላ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ምስለ ሬስቶራንትና ምግብ ቤቶች በሜኑዋቸው ለተዘረዘረው የምግብ ዓይነት የሚጠይቁት ዋጋ እድሜ ለንረቱ ራስ ምታት ነው፡፡ ቢሆንም ዋጋ መጨመር እንጂ የአገልግሎቱን ጥራት ማን በጄ ብሎት?

የምግቡን ጥራትና አሠራር እንዳለ እናቆየው ተብሎ፣ ተነግሮ ጉንጭ አልፍቷል፡፡ ውጤቱ ባይታይም፡፡

የተመጋቢውን ዓይን የሚስቡና በቀላል ውጪ ሊሰሩ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች አሁን የጐንዮሽ እየታዩ ነው፡፡ የእጅ መታጠቢያዎችና የውሃ አቅርቦት፣ መፀዳጃ ቤቶችና የአስተናጋጆች ንፅህና አሁንም እንዳሉ ያሉባቸው በርካታ ሥፍራዎች እናያለን፡፡

ዋጋው ሌላ አገልግሎቱ ሌላ፡፡ ለአንድ ምግብ 2ዐ ብር እና ከዚያም በላይ እየተከፈለ ባለበት ሁኔታ አንዳንድ ቤቶች ውሃ ጠፍቷል በሚል ለመታጠበያ የሚያቀርቡትን ያየ “አልበዛም ወይ” ቢል አይፈረድባትም፡፡

ተክለሃይማኖት አካባቢ ከሚገኝ አንድ ምግብ ቤት የታዘብነው ይህ ጉዳይ ሌሎችም ጋር ስላለመኖሩ መናገር አይቻልም፡፡ የሁሉም ነው ባይባልም፡፡

ገበታ ከመቅረብዎ በፊት እጅዎን ይለቃለቃሉና ወደ መታጠቢያ ጐራ ይላሉ፡፡ ሌላ ሌላው መቼም አይነሳ፡፡ የውሃው ጉዳይ ጤና ቢሮ፣ ጤና ይስጥልኝ ያለበት ቤት ይመስላል፡፡

ውሃ በመጥፋቱ ከጀሪካን የሚቀርብልዎ ውሃ ዓይንዎ እያየ ከአስቀያሚ በርሜል ይጨለፍ ይሆናል፡፡ ሊታጠቡ ሲቀዱት መዓት ዓይነት ጉድ አብሮ ይፈላል፡፡

ደንግጠው “ምንድ ነው ይሄ ውሃ?” ያሉ እንደሆነ “ዘይት፣ ዘይት ነው” ፈርጠም ያለ ምላሽ ይሰጥዎታል፡፡ በተወደደ ዘይት እንደውሃ መታጠቢያ? የማይመስል ወሬ ይሆንብዎታል፡፡ ከበረቱ ተቆጥተው፣ ይሉኝታ ከያዞትም የምንተ እፍረትዎን ታጥበው ይሰየማሉ፡፡

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ በርካታ ሸማቹ ዋጋ እንዲከፍል እንጂ እንዲገለገል፣ ገንዘቡ እንጂ ጤናው እርካታው፣ ፍላጐቱ ሌሎቹም የሚይጠበቁበት ሁኔታ ይታያል፡፡

ሸማቾች ከምንግዜውም በላይ ትኩረት ሰጥተው ለሚጠየቁት ክፍያ ተገቢ ግልጋሎት ማግኘታቸውን፣ የሚገዙት ዕቃ ትክክለኛ ደረጃና ጥራት ማሟላቱን የሚያረጋግጡበት ጊዜ ላይ ነን፡፡

ለመኖር፣ በጤና ለመቆየት በተቻለ መጠን ጥራታቸውና ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠ ዕቃዎችን መግዛትና መጠቀም የዘመኑ ጥያቄ ሆኗል፡፡
 
< Prev   Next >