Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የገደለ ሲያለቅስ
የገደለ ሲያለቅስ E-mail
Sunday, 28 September 2008

ትርንጎ ሙዘይን

ባለፈው ሐሙስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የፖለቲካ ገጽ ያነበብሁት የአቶ በረከት ስምዖን ቃለመጠይቅ በተለይ በሚዲያዎች ላይ የተሰጠው መልስ ይህቺን ማስታወሻ እንድጽፍ አነሳሳኝ፡፡

 

በቃለ መጠይቁ ላይ ያለው ይዘት ቀድሞ ሲነገር ከቆየው የተለየ ይዘት ያለው ሆኖ አይደለም፡፡ ወይም ሚኒስትር የተናገረውን ለመተች ብዬና ከከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ለመገዳደር አስቤ አይደለም፡፡ ወይም የአቶ በረከትን ሃሳብ ማስለወጥ ቀርቶ ለማረሚያ ይገለገሉበታል የሚል ሃሳብም ኖሮኝ አይደለም፡፡ እኔ ቀርቶ ከእኔ በእውቀትም በሥልጣንም የሚበልጡት ሲወተውቱ ቢውሉም "ወይ ፍንክች የአባ ቤላዋ ልጅ" ዓይነት መሆናቸው ይሰማኛል፡፡

ለመፃፍ ያነሳሱኝ ሃላፊዎች በተለይም እንደ አቶ በረከት አይነት በከፍተኛ እርከን ላይ የሚገኙ ባለሥልጣኖች የሚናገሩት የሕዝቡ አኗኗር የሚመራበትን አቅጣጫ የሚያሳይ በመሆኑ ዝም ሊባል አይገባም ብዬ ስላመንሁ ነው፡፡

መነሻዬን ቢያንስ ሕዝቡ ይወቅ ነው፡፡ ሕዝብ ቢያውቅ ምን ያመጣል? ሊባልም ይችላል፡፡ ግን ሕዝብ ካወቀ ቢያንስ፣ ቀና ልቦና ያላቸውን ሊመልሳቸው ይችላል፡፡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ተቃውሞም ለመሰረታዊ ለውጥ ይረዳል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ሚኒስትር አቶ በረከት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተናገሩት የመንግሥትን፣ የፓርቲንና የግል ሚዲያን በተመለከተ ነው፡፡ የግሉ ሚዲያን ሲገልፁ ቆይተው "ሚዲያችን" ብለው መናገር ስለቀጠሉ በባለቤትነት የሚያዙባቸውን የመንግሥትና የፓርቲ ሚዲያውንም አስመልክተው እንደተናገሩ ስለገመትሁ አስተያየቴን አቅርቤያለሁ፡፡

በአዲስ ዘመን ቃለ መጠይቃቸው ሚዲያችን የሚሉት የዴሞክራሲ አቅምን ያላጎለበተ መሆኑን፣ ጠንካራ ሚዲያ ተፈጠረ ከሚባልበት ደረጃ ላይ አለመድረሱን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ንፅፅር በኬንያ ያለ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ከ250-300ሺ ኮፒ እንደሚሸጥ "የኛ" የሚሉት ግን ከ7"000 በላይ መሸጥ እንዳልቻለ ይገልፁና ለዚህ "እንቅፋቱ መንግሥት እንቅፋት ስለሆነ ነው ወይስ ሚዲያችን በራሱ ማደግ ስላልቻለ?" ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በመልሳቸው ድክመት የመንግሥት ሳይሆን፣ ሚዲያዎች ራሳቸውን ችለው ለመቆም ያለመቻል መሆን ለመጠቆም ፈልገዋል፡፡ "የተከፈተው እድል ሰፍቷል" ሲሉም የመንግሥትን አስተዋፅኦ ከፍ አድርገው "እድል መፍጠር ያለባችሁ እናንተ ናችሁ" ሲሉ አለ ለሚሉት የፕሬስ ድክመት የጋዜጠኞች ደካማነት መሆኑን ሊናገሩ ፈልገዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ያለፉትን 17 ዓመታት የኢሕአዴግ ሥልጣን ዘመን የመንግሥትና የፓርቲውን ሚዲያ ሲመሩት ከቆዩት ዋነኛው በመሆናቸው እንዲህ ያለውን ቃለመጠይቅ ለመስጠት ትክክለኛው ሰው ናቸው፡፡ ነገር ግን የሚመሩት ሚዲያ እንኳንስ ከኬንያዎቹ ጋር ሊወዳደር ቀርቶ መለስተኛ የሙያ ሥራ መሥራት የተሳነው የማ ጥፋት መሆኑን፣ የማ አመራር ስንኩልነት መሆኑን በግልፅ ለማሳየት አልፈለጉም፡፡

የመንግሥት ሚዲያዎች ከደርግ የፕሮፖጋንዳ አጣብቂኝ ተገላገሉ በተባለላቸው የመጀመሪያው የኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን፣ ቀስ በቀስ ሸምቀቋቸው እያጠበቀ ከጋዜጠኛነት ይልቅ ታማኝነት የሥራ መቅጠሪያ እያደረገ በመሄዱ ተነቃቅቶ የነበረው እርምጃው እየደከመ ሄደ፡፡

በሃገራችን ባለሥልጣኖች ዘንድ ፕሮፖጋንዳ ማለት የፈለጉትን ማስተላለፍ እንጂ ተጠቃሚው አድምጦና ተረድቶ፣ የአሰራር ለውጥ ያመጣበታል ወይ የሚለውን ጥያቄ አይጨነቁበትም፡፡ እንዲህም ስለሆነ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት ሚዲያዎች በአብዛኛው የጋዜጠኛነት ሥራ ሳይሆን የመልዕክት አስተላላፊነት ሥራ መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡

ጋዜጠኞች እውነትን እንዲያወጡ እና እንዲዘግቡ፣ የባለሥልጣኖች አረንጓዴ መብራት ካላዩ በራሳቸው ተነሳሽነት የምርምር ሥራ እንዲሰሩ አይፈቀድላቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከዚህ ዓይነቱ ውስጥ ለውስጥ እየተንፏቀቀ ሙያውን ሰቅስቆ ከያዘው አሰራር ያፈነገጡ ሲኖሩ "በካልቾ እንደሚጠለዙ" አቶ በረከት በማስታወቂያ ሚኒስትርነት ጭምር እንደመምራታቸው አበክረው የሚያውቁት ነው፡፡

አንድ ጊዜ የሄራልድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ለአንባቢ አስተያየት የሰጠው መልስ የሚጎሽማቸው በመሆኑ ሌላ ሰበብ ተፈልጎ ከሃላፊነቱ መባረሩ አይዘነጋም፡፡ የዚህን መነሻውንም መድረሻውንም ሚኒስትሩ አይረሱትም፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ይመደቡ የነበሩና አሁንም ድረስ ያሉት ሃላፊዎች ከሥራቸው ይልቅ የታመኑ አገልጋዮች መሆናቸው ባልከፋ፡፡ ነገር ግን ይኸ አስተሳሰብ እታች ድረስ ዘልቆ፣ ነባሩ ሙያተኛ "የእኛ ታማኝ ሊሆን አይችልም፤" በሚል ጦረኛ አመለካከት ባለሙያዎቹ እንዲገፉ መደረጉ ነው ክፋቱ፡፡ በምትካቸው ሰራተኛው "አንሚ" በሚላቸው ዓይነቶች አዳዲስ ተቀጣሪዎች በመተካት የቁጥር ምጣኔውን ማስተካከሉን ብቻ ቁም ነገር ያደርገዋል፡፡ ይኸ ሁሉ ግን ውጤት አላመጣም፡፡ የሚዲያው አገልግሎት እየተደፈቀ፣ ለራሱም ለኢሕአዴግ የማይጠቅመው ሆኖ ቀረ፡፡

በመንግሥት ሚዲያ የሚሰራ ባለሙያ እየተገፋ እንደነበር በሚያስቅና በዘቀጠ መልኩ የሚገልፅበት መንገድ በአንድ ወቅት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የሚፈቀድለት የቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ እንዲሆን ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን የሾሙዋቸው ሰዎች ለእንደዚያ አይነት ሥራ ምን ያህል የራቁ መሆናቸው ፊት ለፊት ሲጋፈጥባቸው በሌሎች ታማኞች እንዲተኩ አደረጉ  ለወጡዋቸው፡፡

ይኸን ስል በመንግሥት ሚዲያ አንዳችም ቁም ነገር አልተሰራም ማለቴ አይደለም፡፡ ከመዝናኛ ፕሮግራም ጀምሮ አንዳንድ በሰው ፊት የሚቀርቡ ፕሮግራሞች መኖራቸው አይካድም፡፡ ግን እንደነዚያ አይነት ባለሙያዎች የታማኝነት "ካርድ" ካልያዙ ተገፍትረው ስለሚወረወሩ እድሜያቸው አጭር ነው፡፡ ሁልጊዜ ባለሙያው በሥራው የመቆየት እምነቱ እንዲናወፅ የድርጅቱ አባሎች በሆኑ ዘመናዊ ስራተኞች እንዲጎሸም ይደረጋል፡፡ ኧረ ስንት ነገር አለ፡፡

አንዳንድ ባለሙያዎች የራሳቸውን ጥያቄ አዘጋጅተው ወግ ያለው ተግባር እንዳያሳዩ የድርጅቱ የፕሮፖጋንዳ ክፍል አይኑን እንደሚተክልባቸው የሚያውቅ ማን አለ? ሌላው ቀርቶ ለምሳሌ ያለፈውን ሐሙስ የአዲስ ዘመን ቃለመጠይቅ እናንበው፡፡ ከአንድ "ትልቅ ጋዜጣ" በሚጠበቁ ሙያውን የሚያውቅ ጋዜጠኛ የሚጠይቃቸው፣ የራሱ የሆነ ጥያቄዎች ናቸው፤ ለማለት ያስቸግራል፡፡ አቶ በረከት ለማስተላለፍ የፈለጉትን ይሁነኝ ተብሎ የተፃፈ ይመስላል፡፡ ጥያቄውም አንድ ጋዜጠኛ ብቻ የፕሬስን መስፋፋት የሚመኝ ሳይሆን ጥርሱን እንደነከሰ ባለሥልጣን፣ ለምን የግል ጋዜጦች አይከሰሱም፣ አይታገዱም፣ አይታሰሩም፣ የሚል አንድምታ የያዘ ነው፡፡ እነዚህ እነዚህ አይነት ጥያቄዎች፣ "የራስ ጥያቄ" ስለሚመስሉ ጋዜጣውን ያስተቻሉ፡፡ ፎቶግራፉን ተመልከቱት፡፡ እፊታቸው ያለው ማይክራፎን "ዋልታ" የሚል የባለቤትነት ማስረጃ ተጽፎበታል፡፡ ያ ማለት ቃለመጠይቅ የተደረገው በዋልታ የዜና ማዕከል ሆኖ አዲስ ዘመን በአስተላላፊነት አገልግሎት ብቻ ማለት ነው፡፡ ወይም ፎቶግራፍም ከፋይል "ቃለመጠይቁም" በፁሁፍ የተሰጠ ነው ወደሚል ግምት ይወስዳል፡፡ ግምት እየጠነከረ ሲሄድ እውነት ስለሚመስል የጋዜጣውን መታመን፣ የጋዜጠኛውንም በራስ መተማመን ይሸረሽራል፡፡ በዚህ አጣብቂኝ ያለ ሚዲያ፣ እንዴት በአግባቡ ማደግ የሚያስችለውን እድል ፍጠር ተብሎ ሊነገረው ይችላል?

በመንግሥት ሚዲያው የበዛ፣ የተቆለለ፣ ከዓመት ወደ ዓመት የተላለፈ ችግር አለ፡፡ የችግሩም መንስኤ ራሱ የመንግሥት መሆኑ በተደጋጋሚ ቢገለፅም መፍትሄ ሊፈልግላቸው ቀርቶ መፍትሄ እንዳይገኝ መንገዱን ሲዘጋ ቆይቷል፡፡

በአንድ ወቅት በአቶ በረከት ማስታወቂያ ሚኒስትርነት ጊዜ፣ በሁሉም የሚዲያ ዘርፎች በሰራተኛው የተመረጡ፣ ችግሮችን አጥንተው መፍትሄ የሚያፈላልጉ ኮሚቴዎች እንዲመረጡ ተደርጎ ነበር፡፡ ሃሳቡም የመጣው ከራሳቸው ነበር፡፡ አባላቱ ከሰራተኛው ጋር ተከታታይ ውይይት አድርገው የችግሩን መንስኤና መፍትሄ ሪፖርት አደረጉ፡፡ ሪፖርቱ ደግሞ በአብዛኛው የሚያነጣጥረው በሚዲያዎቹ አስተዳደር ላይ ሆነ፡፡  ሚዲያዎቹን በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩትና የእነዚያ ዋና ሥራ አስኪያጆች የቅርብ ሃላፊዎች አቶ በረከትና ወይዘሮ ነጻነት አስፋው ነበሩ፡፡ ስለዚህ ሪፖርቱ ታፈነ፡፡ እንዲያውም በሦስቱ (በፕሬስ፣ በቴሌቪዥንና በዜና አገልግሎት) ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት ጋዜጠኞች ከሥራቸው እንዲፈናቀሉ ጫና ስለበዛባቸው ሥራቸውን ለቀቁ፡፡ ሌሎችም የኮሚቴው አባላት ተመሳሳይ እድል ገጠማቸው፡፡     

በዚህ የደፈቃ አሰራር የሚኮረኮም የኢትዮጵያ ሚዲያ፣ እንዴት ብሎ እንደሚያንሰራራ መረዳት አይቻልም፡፡ በቅርቡ፣ ልምድና በውጭ አገር ሳይቀር ትምህርት የቀሰሙትን የስቱዲዮ ቴክኒሽያኖች አባሮ "በማግስቱ" በቅጥር ማስታወቂያ የሚያወጣ ሚዲያ ጤናማ አሰራር አለው ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡ ለምን እንዲህ እንደሆነ በግልፅ የሚያስረዳ የለም፡፡ በሹክሹክታ የሚነገረው ግን "የታማኞች የጥላቻ ሪፖርት" ነው፡፡ የኢሕአዴግ አሰራር "ለሚስጥራዊ ሪፖርቱ" ልቡን የከፈተ ነው፡፡  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ስለ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ወይም ስለ ጋዜጣዊ አጻጻፍ አንዳችም ሃሳብ የሌላቸውን ዋና ኃላፊ ማድረግ ቀጥሏል፡፡ ከዚህ ዓይነት አሰራር እውነት  የሚዲያ እድገት ይጠበቃል?

የመንግሥትም ሆነ የፓርቲ ሚዲያዎች እንዲያድጉ ከተፈለገ፣ ባለሙያዎች እንዲታደሙበት፣ ባለሙያዎች በስራቸው ላይ ጫና ሳይደረግባቸው እንዲሰሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲህ አይነት አሰራር ከሰፈነ ተጠቃሚው መንግሥት ጭምር ነው፡፡ የማይደመጥ፣ የማይታይና የማይነበብ ሚዲያ ታቅፎ መቆየት ለምንም ሲጠቅም አልታየም፡፡ በየዕለት "ውዳሴ ጥንካሬ ማነብነብ" ለአጠቃላዩ ውጤት እንደማይጠቅም ኢሕአዴግ በቅጡ የተረዳው ይመስለኛል፡፡

መንግሥት ሚዲያውን እስከ አንገቱ አስምጦ አላፈናፍን ባለበት ሁኔታ፣ ከኬንያ ጋዜጦች ጋር መወዳደር "ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ" የሚለውን ተረት ያስታውሳል፡፡ በመሰረቱ በኬንያ የእንግሊዝኛ ጋዜጣና በሄራልድ መካከል፣ የኮፒ ብዛት ልዩነት ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች አሉበት፡፡ እነዚህ እንዳሉ ሆነው አንደኛው፣ የኬንያዎቹ ጋዜጦች መንግስት የሚፈተፍትባቸው አለመሆናቸውን መርሳት አያስፈልግም፡፡ "በዚህ ተመለስ፣ በዚያ ተቀለስ" እያለ ጫፋቸው አይደርስም፡፡ ባለሙያ ሙያውን ያስባል እንጂ የመንግሥት ፊትን መጥቆርና መፍካት እያየ አይሰራም፡፡ ይህንን ለዓመታት አቆይተውታል፡፡ እየገሰገሱበትም ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከኬንያ ጋዜጦች የኮፒ ብዛታቸውን ብቻ ሳይሆን የተሻለ የሚዲያ አስተዳደር እንዳላቸው መርሳት የለበትም፡፡ እንኳንስ በፎቶ አመራረጥ፣ በማንኛውም የኤዲቶሪያ ሥራ ጥልቅ እንደማይሉ ተቀበለው አልተቀበለው ማወቅ አለበት፡፡

ስለዚህ የመንግስት ሚዲያ እንዲያድግ ከተፈለገ መንግሥት የፈጠረውና ያሳደገው ጥልቅ ብዬነት ባይጠፋ እንኳ መቀነስ አለበት፡፡ ሚዲያ የታማኝነት ዋጋ ተደርጎ የሚሾሙበት ሥራ ሳይሆን ሙያተኛነትን የሚጠይቅ፣ ሥራውም ፊት ለፊት የሚያሳጣ መሆኑን ግንዛቤ መውሰድ ለሿሚውም ለተሿሚውም ይጠቅማል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች እንዲያስተዳድሩት መደረግ አለበት፡፡

ስለ ግሉ ሚዲያ

በዚህ ዙሪያ መንግሥት ያለው አቋም ተደጋግሞ የተገለፀ በመሆኑ መደጋገም እንዳይሆን አስተያየቴን በጥቂቱ አደርጋለሁ፡፡ አቶ በረከት በግል ሚዲያው በኩል ችግሮች እንዳሉ የገለፁት ሊስተባበል የሚችል አይደለም፡፡ እውነት ነው፣ በግል ጋዜጣው ውስጥ ሥነ ምግባር የጎደለው፣ የጋዜጠኝነት ሙያን የሚያጎድፍ ተግባር የሚፈጽሙ የሉም፤ ተብሎ መከራከር አይቻልም፡፡ ሥራ ያጣ በቀላሉ በአንዳንድ ጋዜጦች የሚነግድበት መሆኑም ይታያል፡፡ ግን ሁሉንም የግል ሚዲያ በዚያ መንገድ መፈረጅ ሥር የሰደደ ጥላቻ የሚፈጥረው ስሜት ነው፡፡ ኢሕአዴግ በተለይም አንዳንድ ባለስልጣናት ሥር የሰደደ ቂምና ጥላቻ ሲያሳድሩ ዝም ማለት ባልተገባው ነበር፡፡

በግል ጋዜጦች የሚታየውን ጉድለት ለማረም "ስለታማ ሕግ" በማውጣት መፍትሔ መስጠት አይቻልም፡፡ በማዋከብና ከሕግ ውጭ በማስፈራራትም አይፈታም፡፡ ኢሕአዴግ እያደረገ ያለው ግን ይህንን ነው፡፡

አንዳንድ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ሰማይ ይሰቅሉና ሌላው ያልበሰለ፣ ሌላው ምንም የማያውቅ፣ አድርገው በመገመት ራሳቸውን ያታልላሉ፡፡ የችግሮቹ ምንጭ የነሱ "የአትናገሩን" ሹማዊ ባህርይ መሆኑን ይረሱትና የሌላው አለማወቅ መሆኑን በመስበክ ለማታለል ይሞክራሉ፡፡

አቶ በረከት አንዳንድ የግል ሚዲያዎች በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፕሬስ ጉባኤ ላይ እንዲገኙ መደረጉን ታላቅ ችሮታ አድርገው የቆጠሩት ይመስላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ለፕሬስ መልስ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ሚዲያዎቹም ሕገመንግስታዊ መብት እንዳላቸው ለምን ይረሱታል? ለጥቂቶቹ የተፈቀደውን ጋዜጣዊ መግለጫ እንደ ታላቅ የፕሬስ እመርታ አድርገው መቁጠራቸው ትክክል አይመስለኝም፡፡ እነዚህም ቢሆን የተለያየ አስተያየት ወይም ትችት ከፃፉ ሊከለከሉም ይችላሉ፡፡ ከኬንያ ያልተማሩት ይህንን ነው፡፡ በኬንያ የግል ጋዜጦች ባለስልጣኖችን ፕሬዚዳንቱን ጭምር በተናጠልም በጋራም ለማነጋገር እንደማይከለከሉ፣ ከኬንያ ጋዜጦች ኮፒ ብዛት እኩል ሊያውቁት ይገባቸዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡

በኬንያ ባለስልጣን በሙስና ሲዘፈቅ የሚያጋልጥ የግል ጋዜጣ በሌሎች የኬንያ ባለሥልጣኖች ጭምር ይበረታታል፡፡ የእኛ መንግሥት ግን እንዲህ አይነቱን ተግባር እንደ ግል ጥላቻ ከኋላው የተደበቀ ተልዕኮ ያለውና እንደ ድፍረት ይቆጥረዋል፡፡

መንግስት አሁንም የመግረፊያ አርጩሜ ለመቁረጥ የሚያስችለውን ሕግ በማጽደቁ የግል ጋዜጣውን የተበቀለ አድርጎ ቆጥሮት ይሆናል፡፡ ግን ብቀላው ለራሱም ጭምር መሆኑን ማሰብ አለበት፡፡ ችግሮቹንም የሚያባብሱ ናቸው፡፡ መቼም የእኛ መንግስት በፕሬስ ከኤርትራ እንደሚሻል ደጋግመን መናገር የተሟላ የፕሬስ ነፃነት አለ ማለት እንዳልሆነ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡

"በፕሬስ የመስራቱ መንገድ እየጠበበ" አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ በረከት በሕግ ስም፣ ማነቋቸውን አጥብቀው በአስተዳደራዊ ርምጃ ስም እያስፈራሩ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለዚህ አገር እድገት አንዳችም ፋይዳ የለውም፡፡ ኢሕአዴግንም ፣አመግል ብላ አቆሰለች፣ ይሆንበታል እንጂ ትርፍ አይገኝበትም፡፡ በእስካሁኑ የሚዲያ አጠቃቀም በሕዝቡና በዓለም አቀፍ መድረክ ያገኘነውን ውጤት በድብቅም ቢሆን እውነት እውነቱን ቢነጋገሩበት ጥሩ ነው፡፡ በግልጽ መነጋገር እንኳ ባይችሉ በዝግ ስብሰባቸው የተደረገውንና የተገኘውን ውጤት መነጋገር የተሻለ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ ይችላል፡፡

በአጠቃላይ የምለው ይህንኑ ነው፡፡ ፕሬስ እንዲያድግ መንግሥት የተጽዕኖ መዳፉን ያንሳ፡፡ ባለስልጣኖቻችን ቀሪውን እድሜያቸውን ለፕሬስ ማደግ ቢሰሩ ከእስከዛሬው የተሻለ ስም ያገኙበታል፡፡ በሰይፈኛ ሕግ ሳይሆን በሚያስተምር ሕግ የሚተዳደር ፕሬስ ለመፍጠር መጣር ያስፈልጋል፡፡
 
< Prev   Next >