Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow "መርህ የሌለው መሪ የሚገዛው ነገር የለውም"
"መርህ የሌለው መሪ የሚገዛው ነገር የለውም" E-mail
Sunday, 28 September 2008
አቶ ታገሰ ጫፎ

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት
አቶ ታገሰ ጫፎ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት አርባምንጭ ወረዳ ላንቴ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአምርባምንጭ ከተማሩ በኋላ በስነህይወት ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ትምህርት ህንድ አገር ተምረው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡


ከወረዳ ጀምሮ በየደረጃው በተለያዩ የአመራር ደረጃ ያገለገሉት አቶ ታገሰ በክልል ደረጃ የኢንቨስትመንትና የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ነው፡፡ የደኢህዴንና የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ታገሰ ባለትዳር፣ የሁለት ልጆች አባትና የ38 ዓመት ጎልማሳ ናቸው፡፡ አሰግድ ተፈራ በሐዋሳ አግኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የስነ ህይወት ተማሪ እንደመሆንዎ በቀጥታ ከሙያዎት ጋር ተያያዥነት ባለው የሥራ መስክ ቢመደቡ ክልልዎን ይበልጥ አይጠቅሙም?

አቶ ታገሰ፡-
ሁለት ዓይነት ሥራዎች አሉ፡፡ አንደኛው ሥራ መሪ ሆኖ የሚሰራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቴክኒሺያን ሆኖ መስራት ነው፡፡ እኔ የምሰራው ሥራ የመሪነት ሥራ ነው፡፡ መሪ ሆኖ መስራትና የቴክኒሽያን ሥራ መስራት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ቴክኒሺያን ቴክኒካል የሆነ ሥራ ይሰራል፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነቴ በርካታ ሥራዎችን የምሰራው በማስተባበር ነው፡፡ ማንም መሪ ሁሉም ዓይነት ሙያ ሊኖረው አይችልም፡፡ በመሪነት ደረጃ የሚሰራ ሥራ ግንኙነት በመፍጠር የተለያዩ ጉዳዮችን በማደራጀት በትክክል ማስተባበር መቻል ነው፡፡ ማስተባበር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሙያዎችን የማዋሃድ ሥራም ነው፡፡ ዋናው የመሪነት ሚና ግንኙነት መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ ለመሪነት ሥራ ዝግጁ የሆነ ሰው ጉዳዮችን በትክክል ተረድቶ ኃላፊነትን የመወጣት ብቃት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድ መሪ የሚለካው በአፈፃፀሙ ነው፡፡ አንድ መሪ ብቃቱ፣ የመሥራት ችሎታው፣ የማደራጀት እውቀቱ ባሳለፈው የሥራ ሂደት ተለክቶ ነው የሚሾመው፡፡ በተለያዩ የአመራር እርከኖች ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ እዚህ የደረስኩት እያንዳንዷን መዋቅር አልፌ ነው፡፡ ተፈትኜ ነው፡፡ ከስራው ልምድ በተጨማሪ በማንበብ ደረጃዬን አሻሽያለሁ፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ትምህርቶችን ተከታትያለሁ፡፡ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ እንጂ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ አስተዳደር ትምህርትም እየተከታተልኩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መሪ ለመሆን ዋናው የፖለቲካ እምነትና ፖለቲከኛ መሆን ብቻ ነው የሚል አቋም አልዎት?

አቶ ታገሰ፡-
ኢህአዴግን አልሰራም በማለት ተከራክሬያለሁ፡፡ ስፔሻላይዝድ ባደረኩት የሙያ ዘርፍ መስራት አለብኝ ብያለሁ፡፡ ከተለያዩ የውጪ አገር ዜጎች ጋር በሥራ በተገናኘሁበት ወቅት ተነጋግሬያለሁ፡፡ ሰው በሙያው ማገልገል እንዳለበት ላሳምናቸው ሞክሬያለሁ፡፡ ሰው የሚማረው በአግባቡ በስፋት ማሰብ የሚችልበትን የግንዛቤ ደረጃ እንዲጨብጥ ወይም እንዲደርስ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ጉዳይ በማንበብ፣ ጉዳዮችን በመረዳትና በሥራ ሂደት በመብሰል የአመራር ብቃትን በማሳደግ የሚመጣ ነው፡፡ እናም የውጪ አገር ዜጎቹ በአገራቸው ከሙያቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሳይኖራቸው በልምድ ከፍተኛ የአመራር ቦታ የሚይዙ እንዳሉ በመዘርዘር ሊያሳምኑኝ ሞክረዋል፡፡ እነሱ ባይሉም በዓለም ላይ ኢንጂነር ሆነው ታላቅ ፖለቲከኛ የሆኑ አሉ፡፡ ስፔሻላይዝ ካደረጉት ትምህርት ውጪ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተሳካላቸው በርካታ ናቸው፡፡ ወደ ጥያቄው ስመለስ እኔ ኢህአዴግን ስቀላቀል አምኜበት ለኅብረተሰቡ ይጠቅማል ያልኩትን ለመስራት ነው፡፡ በዋናነት ቅድሚያ የምሰጠው ግን መሪ ዲሲፒሊንድ የመሆኑ ጉዳይ ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዲሲፒሊን ሲሉ?

አቶ ታገሰ፡-
የመንግስትና የድርጅት የሥራ ዲሲፒሊን አለ፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ የራስ ዲሲፒሊን ያስፈልጋል፡፡ ለራሱ ዲሲፒሊንድ የሆነ ሰው ራሱን ይገዛል፡፡ በወጣትነት እድሜዬ ወደ አመራር በመጣሁበት ወቅት በርካታ የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የያዝኩት የድርጅት ኃላፊነት ገዝቶኛል፡፡ ይህንን የማደርገው ደግሞ ተቆጣጣሪ አለብኝ በማለት ሳይሆን የራሴ ዲሲፒሊን ስላለኝ ነው፡፡ በዓላማ ሲባል ከራስ ፍላጎት መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ አብረው የሚሰሩ ሁሉ እኩል ዲሲፒሊን ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ዓላማን ለማሳካት ግን ቀጥ ያለውን መንገድ ፊት ለፊት እያዩ መጓዝ ግድ ነው፡፡ የድርጅትና የሕዝብ ፍላጎትን ለማስጠበቅ፣ አገራችንን ለማሻሻልና ለመለወጥ በሚሰራ ሥራ ውስጥ የእኔ ድርሻ አለ፡፡ ሊኖርም ይገባል፡፡ ምድር ላይ የምንኖረው አጭር እድሜ ነው፡፡ ባለኝ አጭር እድሜ ትርጉም ያለው ሥራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ መጽሀፍ ላይ እገሌ ተወለደ፣ ሞተ፡፡ የሚል አጭርና ረዥም የአሟሟት ታሪክ ያላቸው አሉ፡፡ እኔም አንድ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ተወለደ፣ ሞተ ተብሎ ታሪኬ እንዲዘጋ አልፈልግም፡፡ በዓላማ ጽናት መስራት እንዳለብኝና ምን መስራት እንደሌለብኝ አሳውቆኛል፡፡ ምክንያቱም አእምሮዬ ሁሉ ያለው ዓላማዬ ላይ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በከተሞች የነበረውን ችግር አንዴት ይገልፁታል?

አቶ ታገሰ፡-
በኢትዮጵያ የከተማ ልማት ፖሊሲ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ፖሊሲው የወጣው በ1997 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያቶች የነበረን ትኩረት ሙሉ በሙሉ በገጠር ልማት ሥራችን ላይ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አግባብ ነው፡፡ አንድ ሥራ ሲሰራ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ አለ፡፡ እኛም በገጠር የተንቀሳቀስነው ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተሞች ላይ ትኩረት አለማድረጋችሁ እንደጎዳችሁ በተለያዩ መድረኮች እየተገለፀ ነው፡፡ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ፡-

አቶ ታገሰ፡-
መጀመሪያ የተመረጠው አካሄድ ትክክል ነበር፡፡ የገጠር ልማት ሥራ በከተማ ልማት ሥራ ካልታጀበ፣ ከገጠር የሚወጡ ምርቶችን የሚጠቀሙ ከተሞች ካልተፈጠሩ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ከተሞች ውስጥ መካከለኛ፣ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ተፈጥረው አርሶ አደሩን ምርት ገበያ የሚሆኑበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ከተማ ላይ ያለው ለገጠሩ ልማት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች የሚያቀርቡበት ትስስር መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የገጠሩን ልማት ሥራችን አንድ ደረጃ ላይ ካደረስን በኋላ በከተሞች ልማት ሥራ ትኩረት መስጠት አለብን፡፡ ከዚህ አንጻር የከተማና የገጠር ልማትን ትስስር በሚያጠናክር መልኩ የከተማ ልማት ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡ በክልላችን የከተሞች ሪፎርም የጀመርነው፣ ከተሞች የከተማ አስተዳደር እንዲኖራቸው የህግ ማዕከል ሥራ የጀመርነው በ1995 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱ ከህዝቡ ጋር ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡ ከህዝቡ ምን ይጠበቃል? መንግስትስ ምን ማድረግ ይገባዋል? በከተሞች ያሉት ችግሮች እንዴት ሊቀረፉ ይችላሉ? የሚሉት ጉዳዮች ተነስተው በሁሉም ከተሞች ህዝብ ለከተማ ልማት ሥራ ትኩረት አልሰጣችሁም ተብለናል፡፡ አስተያየቱን ተቀብለናል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ከተሞች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ያደረግነውና ግንቦት 20/1995 የከተማ አስተዳደሮች አቋቋምን፡፡ ከቀድሞ የወረዳ አስተዳደር ለይተን የከንቲባ መዋቅር ፈጠርን፡፡   

ሪፖርተር፡- የመዋቅር ለውጡ በከተሞች አካባቢ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ሆነ?

አቶ ታገሰ፡-
የመዋቅር ለውጡን ስንጀምር በከተሞች አካባቢ የነበሩት ዋንኛ ችግሮች ሥራ አጥነት፣ የመኖሪያ ቤት ችግርና የአካባቢ ልማት ሥራዎች አለመኖር ነበር፡፡ በዚህ መሰረት በከተሞች ያሉ ሥራ አጦችን በማደራጀት ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ፣ የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ለማቃለል የቤቶች ልማት ፕሮግራም ስላልተጀመረ ማዘጋጃ ቤቶች የመኖሪያ ቤት እንዲገነቡ ማስደረግ፣ ይህ የሆነው በአገር አቀፍ ደረጃ የቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ሳይጀመር ነበር፡፡ የተሻለ የመሬት አቅርቦት በመፍጠር ነዋሪዎች ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲገነቡ፣ በአካባቢ ልማት በውስጥ ለውስጥ መንገድ በሌሎች የልማት ሥራዎች የሕዝብ ተሳትፎን በማዳበር እንዲሰሩ ማድረግ ነበር፡፡ በመንገድ ግንባታ በተፈጠረው ከፍተኛ መነሳሳት በወላይታ ሶዶ፣ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ አርባምንጭ ኅብረተሰቡ የአስፓልት መንገድ በራሳቸው ወጪ እየገነቡ ነው፡፡ የክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው በሐዋሳ ከተማ የመሰረተ ልማት ችግር ለመቅረፍ ተወስኖ ባለፉት ሦስት ዓመታት ትልቅ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በሐዋሳም ታላቅ ለውጥ ሊታይ ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገልግሎት ማሻሻያ ጥናት ስታደርጉ በማህበራት ስም የተደራጁትን ጨምሮ በርካታ ችግሮች ቢገኙም፣ በተለይ መሬት አየር በአየር የቸበቸቡት ላይ ተመጣጣኝ ርምጃ አልወሰዳችሁም ይባላል፡፡ ለምን?

አቶ ታገሰ፡-
በሐዋሳ አልሚ ማኅበራት የቤት ጥያቄ አቅርበው ሲጣራ ንጹህ ሆነው የተገኙት ስምንት ብቻ ናቸው፡፡ ባል፣ ሚስት፣ ልጅ፣ ቦታ ያላቸው በተለያዩ ማህበራት ስም ይመዘገባሉ፡፡ ስናጣራ ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡ ያስተናገድናቸውም ስምንቱን ብቻ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የፀዳ ማህበር መስርተው ለሚመጡ ወደ ጎን ሳይሆን ወደ ላይ የጋራ መኖሪያ እንዲገነቡ እናበረታታለን፡፡ ርምጃን በተመለከተ ያለአግባብ ትርፍ መሬት የወሰዱትን ጨምሮ ጥብቅ ርምጃ እንዲወስድ በድርጅት ተወስኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ኃላፊዎችን ጨምሮ የተወሰደውን ርምጃ ቢያብራሩልኝ?

አቶ ታገሰ፡
- በክልሉ ከተሞች አመራርም ቢሆን ስልጣኑን ተጠቅሞ ያለአግባብ መሬት መውሰድ አይችልም፡፡ ይህንን ፈጽሞ የተገኘ አመራር ሙሉ በሙሉ ከድርጅት ይወገዳል፡፡ ይህ የወሰድነው ርምጃ ነው፡፡ ከአንድ በላይ መሬት የወሰዱ ተነጥቀዋል፡፡ ይህ የክልሉ መንግስት ውሳኔ ነው፡፡ በክልሉ ካሉ ማዘጋጃ ቤቶች በርካታ ሠራተኞች ተባረዋል፡፡ መጠነኛ ስህተት የሠሩት ከመሬት ጋር ግንኙነት በሌላቸው መስሪያ ቤቶች ተመድበዋል፡፡ በህግ መጠየቅ ያለባቸው በህግ እንዲጠየቁ፣ መታሰር ያለባቸው እንዲታሰሩ፣ ከጥበቃ ጀምሮ እስከ ከንቲባ ድረስ በጥብቅ የተሄደበት ጉዳይ ነው፡፡
 
ሪፖርተር፡- እርስዎ የመኖሪያ ቤት አላስገነቡም?

አቶ ታገሰ፡
- የለኝም፡፡ የምኖረው መንግስት በሰጠኝ ቤት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መሬትም የልዎትም?

አቶ ታገሰ፡-
አለኝ፡፡ ግን ቤት አልሰራሁበትም፡፡ የመንግስት ደመወዝተኛ በመሆኔ ከንፁህ ገቢዬ ላይ ቀንሼ በአንዴ መስራት አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በሐዋሳም ሆነ በሌሎች የክልሉ ከተሞች መሬት አጥረው የሚያስቀምጡ ባለሀብቶች ጉዳይ እንዴት እያስተናገዳችሁ ነው?

አቶ ታገሰ፡-
የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሆኜ በመስራቴ በከተማም ሆነ በገጠር ተመሳሳይ ችግር ያጋጥመናል፡፡ መሬት አስቀድመው በመያዝ አቆይተው ለሶስተኛ ወገን በማስተላለፍ ትርፋማ ለመሆን መሬት የሚወስዱ አሉ፡፡ ሌላው ችግር አቅዶ አለመነሳት ነው፡፡ ከእውቀት ማነስ ወደ ሥራ ገብተው መጨረስ የማይችሉ አሉ፡፡ በልምድ መስራት ነው የሚፈልጉት፡፡ በባለሙያ መታገዝን አይመርጡም፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ጀምረው ይወድቃሉ፡፡ በከተማ መሬት ሲሰጥ ህግ አለ፡፡ በገጠርም እንደዚሁ ተመሳሳይ ህግ አለ፡፡ ስለዚህ ህጉ በሚያስፈቅደው መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጊዜ ገደባቸው በዓመታት ያለፈባቸው የሉም?

አቶ ታገሰ፡
- ከእቅድ ችግር፣ ከባንክ ጋር እንዴት ግንኙነት መፍጠር እንደሚችሉ እንኳን የማያውቁ አሉ፡፡ አንዳንድ ባለሀብቶች የቀለም እውቀት ባይኖራቸውም ውስጣቸው አንድ ነገር ለማድረግ የሚነሳሱ አሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹን በትዕግስት እንጠብቃለን፡፡ ችግሮቻቸውን በመለየት ከቆሙበት ወይም ከወደቁበት እንዲነሱ እናደርጋለን፡፡ ይህ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ሙሉ በሙሉ በማይሰሩት ላይ ርምጃ እንወስዳለን፡፡ ርምጃ ሲወሰድ ጫጫታ አለ፡፡ የእኛም አመራር የሚፈራው ይህንን ጫጫታ ነው፡፡ ዋናው የአገራችን ሀብት መሬት ነው፡፡ ይህንን ብቸኛ ሀብት በአግባቡ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚወሰደው ርምጃ ከግለሰቦች ጋር ቅንጣት ታክል ግንኙነት የለውም፡፡ ጉዳዩ የአገር ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ አገርን የማልማት አገርን የማሳደግ ጉዳይ ነው፡፡ ግለሰብ በአገር ጉዳይ ላይ ምንም አይደለም፡፡ የሕዝብ ጉዳይ የሕዝብ በመሆኑ የምንወስደው ርምጃ ጥብቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሐዋሳ የመንገዶችና የሆቴሎች ጽዳት በእጅጉ ተሻሽሏል፡፡ ይህን ለውጥ እንዴት ማምጣት ቻላችሁ?

አቶ ታገሰ፡-
በንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ውስጥ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ማሻሻያ ሥራ ሂደት መሥራት ከጀመርን አስር ወራት ሆኖናል፡፡ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች፣ ባሮች፣ ፔንሲዮኖች እንዴት አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነና ምን ችግር እንዳለ አጥንተናል፡፡ ጥናቱ ከተጠና በኋላ ከመስተንግዶ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዴት መሰራት አለበት? የማብሰያ ቤት እንዴት መደራጀትና መሰራት አለበት? በሚል ደረጃ ወጥቶለታል፡፡ መፀዳጃ ቤቶችን ጨምሮ በጥናቱ ተካተተ፡፡ ባለንብረቶቹን ሰብስበን ጥናቱን አቀረብን፡፡ ጥናቱ ሲቀርብ መደናገጥ ተፈጠረ፡፡ መንግስት በስራቸው ጣልቃ የሚገባ መስሏቸው ስጋት ላይ ወደቁ፡፡ በውይይት ባለሀብቶቹ ስራቸውን በአግባቡ በመስራታቸው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመኑ፡፡ ንግድን ተገልጋይ እንደሚመራው ሙሉ በሙሉ ተረዱ፡፡ መንግስት መሰረተ ልማት ከማሟላት ሥራ እንደማያልፍ ተገነዘቡ ከአንድ ወር በኋላ ከቢሯችን ባለሙያ መድበን ገምግመን በድጋሚ በጠራነው ስብሰባ ሪፖርት ሲቀርብ ለውጡ በእያንዳንዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ተለይቶ በመቶኛ ተሰልቶ በአማካይ ከፍተኛ ውጤት ተገኘ፡፡ ህዝቡም በለውጡ ደስተኛ በመሆኑ ከተማዋን ይንከባከባል፡፡ መንገዶቹን በተመለከተ በቀን ሦስት ጊዜ የሚያፀዱ ሠራተኞች አሉ፡፡ ይህ እኔ የምለው ሳይሆን ሁሉም በአደባባይ የሚመለከተው ነው፡፡ ሐዋሳ የፀዳችው በዚህ መልክ ነው፡፡ በሐዋሳ ነዋሪዎች ዘንድ መንገድ እጽዋቾች የራሳችን ናቸው የሚል እምነት ተፈጥሯል፡፡ በሐዋሳ አንድ የታየው ትልቅ ነገር በልማት የኅብረተሰብ አመለካከት እንደሚለወጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተሞች ያላችሁ የተለየ እቅድ አለ?

አቶ ታገሰ፡-
ለአስፓልት ብቻ 140 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ወጪ አድርገናል፡፡ የሰራነው ከ26 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መንገድ ነው፡፡ ሆሳዕና፣ አርባምንጭና ሌሎች ከተሞች ተመሳሳይ እቅድ አለን፡፡ በአደጉ አገሮች እንደሚደረገው በከሰል ድንጋይ መንገዶች እንሰራለን፡፡ ለመጠገን ወጪው ቀላልና ረዥም አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ በሐዋሳ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጭቃ የሚባል ነገር እንዳይኖር ነው ያቀድነው፡፡ ከያዝነው የካፒታል በጀት በተጨማሪ ርዳታ ሰጪዎችም ተባባሪ ሆነዋል፡፡ በዚህ መሠረት በዲዛይን የሚሰራው የከሰል ድንጋይ መንገድ ለከተማው ሥራ አጦች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ በከተሞች 36ሺ የሚጠጉ የመኖሪያ ቤቶች ይሰራሉ፡፡ ሥራው የሚሰራው ሥራ አጥነትን ከመቅረፍ አንፃር ነው፡፡ ለምሳሌ በውስጥ ለውስጥ መንገድ ድንጋዩን በመጥረብና በማንጠፍ በርካታ ሥራ አጦች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ቢሮ ከሚሰሩት በላይ ይከፈላቸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ 40 ሚሊዮን ብር ለዚህ ሥራ ቢውል በከተማ ውስጥ ያሉ ሥራ አጦች ሲሳተፉ በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ አደረግን ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የከተማዋን እንቅስቃሴ ያነቃቃል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከሌላ ክልል የሚመጡ ባለሀብቶች በእኩል ታስተናግዳላችሁ?

አቶ ታገሰ፡-
በሚገባ የክልላችን ሕዝብ በኢንቨስትመንት ተጠቃሚ መሆኑን አምኗል፡፡ ለምሳሌ በሐዋሳ ሁሉም ነዋሪ አንድ ባለሀብት መጣ ሲባል ምን ይዞልን መጣ ይላል እንጂ ማን ነው? የት ተወለደ? ብሔሩ ምንድ ነው? የሚል ጥያቄ አያነሳም፡፡ ይህ የሆነው አሁን በከተማ ከሚታየው አስገራሚ ለውጥና እድገት የመጀመሪያ ተጠቃሚው ራሱ ነዋሪው እንደሆነ በማረጋገጡ ነው፡፡ ሌላ ባለሀብት እንዲመጣ ከመናፈቅ በቀር አንዱን አቅፎ ሌላውን የማግለል ነገር የለም፡፡ በመንግሥት ደረጃም የምንሰጠው አገልግሎት ያለአድልዎ ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በሐዋሳ ያለሙ ባለሐብቶች በአብዛኛው ታዋቂና የሌላ ክልል ተወላጆች የሆኑት፡፡
 
< Prev   Next >