| “ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የአጭር... |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
“ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የአጭር ጊዜ እርዳታ ሣይሆን ቋሚ ሥራ ነው”
በዳዊት ታዬ ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ ለ27 ዓመታት ሆላንድ ውስጥ ኖረዋል፡፡ ወደ ውጭ የወጡት እንደ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን በደርግ ጊዜ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ነው፡፡ ባለትዳርና የአንዲት ልጅ አባት የሆኑት ኢንጂነር ታደሰ ከስደት መልስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የቤት አውቶሞቢል መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመገንባት ችለዋል፡፡ በስደት በነበሩበት ጊዜ በፓወር ኤሌክትሮኒክስ ኢንጂነሪንግ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ሔሎት በሚባል ኩባንያ ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ሥራ ላይ ሰርተዋል፡፡ ከዚህ ሥራ ጎን ለጎንም ላዳ መኪኖችን ከሆላንድ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ይሸጡም ነበር፡፡ በዚህ ሥራ 500 የሚሆኑ ላዳዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመኪና መገጣጠሚያ ለመገንባት ያነሳሳቸውም በትርፍ ጊዜያቸው ይሰሩ የነበሩት ይኸው መኪና የመላክ ሥራ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ የሚልኩት መኪና ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱና የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ስላመኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝብ ማቅረብ ይኖርብኛል በማለት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ይገልፃሉ፡፡ ይህንን ሃሳብ ይዘው ማቋቋም ላሰቡት የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ የፋይንስ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የሆላንድ መንግስትን ይጠይቃሉ፡፡ በጥያቄያቸው መሠረትም አዎንታዊ መልስ አገኙ፡፡ በሆላንድ ውስጥ ከሚገኘው ቴሬንቶ የተባለ ኩባንያ ከእርሳቸው ጋር እኩል 50 በመቶ የባለቤት ድረሻ ኖሮት ኩባንያ እንዲያቋቁሙ ተደረገ፡፡ የኩባንያውንም ስም “ሆላንድ ካር” በማለት ሞጆ ከተማ ቦታ ተረክበው በኢትዮጵያ የመጀሪያ የሆነውን አውቶሞቢል መኪና መገጣጠሚያ ለመገንባት ችለዋል፡፡ ለዚህ ኩባንያ ከጠቅላላ የፕሮጀክት ወጪውም 60 በመቶውን የሆላንድ መንግሥት ሸፍኖ ኩባንያው ሥራ ጀምሯል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን “ዶክ” የተባለ የቤት አውቶሞቢል ለገበያ ማቅረብ የቻሉ ቢሆንም ዶክ እንደተፈለገው አትራፊ መሆን ባለመቻሉ ወዲያው ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ለማምረት በመወሰን ሊፋን ከሚባል የቻይና ኩባንያ ጋር በመሆን “አባይ” የሚል መጠሪያ የተሰጣት የቤት አውቶሞቢል ለገበያ ማቅረብ ቻሉ፡፡ አባይ ባለፈው አመት ለገበያ ስትቀርብ ኩባንያው አቅዶ የነበረው በአመት 250 አውቶሞቢሎችን ለማምረት ነበር፡፡ ሆኖም የመኪናዋ ይዞታና አጠቃላይ ገጽታ ተቀባይነት በማግኘቱና መኪናዋን ለመግዛት በርካታ ጥያቄዎች በመቅረባቸው ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራ እንዲሰሩ አስገድዷቸዋል፡፡ አባይ መመረት ከጀመረች ወዲህ 520 የሚሆኑ አውቶሞቢሎች ሸጠዋል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን አስረክበዋል፡፡ ሌሎቹን በወረፋ እያስተናገዱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ትልቅ ችግር የሆነባቸው የገበያውን ፍላጎት የሚመጥን ምርት ማምረት ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ ወደ ማስፋፊያ ስራ እንዲገቡ በማድረጉ የምርት መጠኑን ለማሳደግ የማስፋፊያ ግንባታውን አካሂደው ጨርሰዋል፡፡ በጥቅሉ ይህንን ሥራ ከጀመሩ ጊዜ ጀምሮ 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የማስፋፊያ ግንባታው በመጠናቀቁ በቀን አንድ መኪና ይገጣጠምበት የነበረውን ፋብሪካ ከሶስት እስከ አምስት መኪኖች ለመገጣጠም የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሡን ከኢንጂነር ታደሰ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችን በተለመለከተ ላቀረብንላቸው ጥያቄም “ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ሥራ አልተነካም ዲያስፖራው የሚሠራው ብዙ ሥራ አለ” ይላሉ፡፡ የተለያዩ ሥራዎች ለመስራት የውጭ ዜጎች እየገቡ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ታደሰ ይህ አካሄድ መለወጥ እንዳለበት ያምናሉ፡፡ “ዲያስፖራዎች ውጭ ቁጭ ብለን እኛ መስራት የምንችለውን ሥራ ሌሎች እንዲሰሩ እየፈቀድንላቸው ነው፡፡ ይህ አካሄድ መለወጥ አለበት” ይላሉ፡፡ “ዲያስፖራው ብዙ እገዛ አግኝቶ እዚህ ሊሰራበት የሚችል እድል አለው፡፡ ብዙ ያልተሰራባቸው መስኮች ላይ መስራት እውቀቱም ገንዘቡም ያላቸው ዲያስፖራዎች በዚህ እድል ሊጠቀሙ ይገባቸዋል፡፡ ቢያንስ ውጭ የሚሰራውን ሥራ እዚህ መጥቶ መሥራት ይቻላል፡፡ በተለይ በእርሻ ብዙ ያልተሰራ ሥራ አለና ለትንሹም ለትልቁም ሥራ የውጭ ሰዎች መፈለግ የለብንም፡፡” ያሉት ኢንጂነር ታደሰ እርሣቸው የጀመሩት ሥራ ውጤት ማስገኘቱንና ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ እድል ለመኖሩ ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆን ያመለክታሉ፡፡ ይህንን የእኛ ሥራ የተመለከቱ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት እያሠቡ ነው፡፡ የተገነዘቡና በቅርቡ አባይ መኪናን ሆላንድ ልከን ያዩ ብዙ ሰዎችም በሥራችን ተገርመውበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ መስራት ከተቻለ እንመለሳለን የሚሉ ዲያስፖራዎች እንዲፈጠሩም ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ እየሠሩ ያሉት ሥራ በዲያስፖራው ብቻ ሳይሆን ይህንን ኩባንያ ለማቋቋም እገዛ ያደረገላቸው የሆላንድ መንግስትም ሥራችንን ውጤታማ ብሎታል ይላሉ፡፡ ለዚህም አባባላቸው እንደምሳሌ ያቀረቡት በቅርቡ የሆላንድ መንግስት ባለፉት 10 ዓመታት የገንዘብ ድጋፍ ላደረገላቸው 4ሺህ ከሚደርሱ በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ኩባንያዎች ውስጥ እንደ ምሳሌ የቀረበውና ውጤታማ ከተባሉት አምስት ኩባንያዎች ውስጥ ሆላንድ ካር አንዱ ሆኖ መመረጥ መቻሉንም ነው፡፡ ይህ ለኩባንያው ትልቅ ነገር ነው፡፡ እኛም መስራት መቻላችንን ያሳየንበት በመሆኑ ሌላው ዲያስፖራ ከእኛ ሊማር ይችላል ባይ ናቸው፡፡ ይህንን ሥራ ለመጀመር ያን ያህል ችግር እንዳልገጠማቸው የሚገልፁት ኢንጂነር ታደሰ በመንግስት በኩል እገዛ አግኝተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ “እኛ የጀመርነው ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ነገር በመሆኑ ምንም አይነት ልምድ የለም ነበር፡፡ ያቀድነውን ሥራ በተግባር እየለወጥን ሥራችንን ከሰራን በኋላ ሁለት ሦስት ጊዜ ታክስ ተሻሽሎልናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ውጤታማ ሥራ ከተሠራ መንግስት የማይደግፍበት ምክንያት እንደሌለው ነው” ብለዋል፡፡ ማንኛውንም ሥራ ሲሰራ የራሱ ፈተና አለው፡፡ አጣብቂኝ አለው፤ ይህንን ተቋቁሞ መሥራት ከተቻለ ውጤቱ ያማረ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ውጤታማ መሆን የተቻለው ምንም አይነት ችግር ሳያጋጥም ቀርቶ አይደለም፡፡ እቅድን ዳር ለማድረስ መሰልቸት እንደሌለብን በማመናችን ጭምር ውጤቱ ጥሩ ሆኗል፡፡ ዲያስፖራው ይህችን አገር በመለወጡ ረገድ ያለው ሃብትና አቅም ከፍተኛ ነው፡፡ በትክክልም ልንጠቀምበት ከቻልን በአጭር ጊዜ ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ “ብዙዎቻችን ዲያስፖራዎች በየአቅማችን ብንሰራ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ድህነት መቅረፍ ይቻላል” የሚሉት ኢንጂነር ታደሰ ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት የአጭር ጊዜ እርዳታ ሳይሆን ቋሚ የሆነ ሥራ ነው፡፡ ይህንን ክፍት ለመዝጋት ደግሞ ዲያስፖራው ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ውጭ ያሉት ዲያስፖራዎች እዚያው ሆነው ኢንቨስት ቢያደርጉና በሥራቸው አስር ሰው የሚቀጥር ኩባንያ ቢያቋቁሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውጭ እርዳታ ራሳችንን ማላቀቅ እንችላለን፡፡ ኢንጂነር ታደሠ ከሆላንድ ካር ውስጥ ካላቸው ድርሻና ኩባንያውን በሥራ አስኪያጅነት ከመምራት ባሻገር ከእናታቸው ጋር በመሆን በሽርክና ያቋቋሙት ኦስናድ ካር የሚባል ኩባንያ አላቸው፡፡ ይህ ኩባንያ ሚኒባሶችና መለስተኛ የሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥም ሲሆን ለመገጣጠሚያ ፋብሪካው የሚሆን የግንባታ ቦታ ጠይቀው እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ እንደርሳቸው ገለፃ ቦታውን ካገኙ ወዲያውኑም ሥራ እንደሚጀምሩም አመልክተዋል፡፡ በሌሎች ኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ከሌሎች ዲያስፖራዎች ጋር በመሆን መስራት የሚፈልጉ ሲሆን የማስታወቂያና የህትመት ሥራዎችን የሚሠራ ኩባንያም እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 02 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |