Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Monday
Oct 13th
Home arrow Sections arrow የብላታ መርስዔ ኀዘን...
የብላታ መርስዔ ኀዘን... E-mail
Sunday, 20 January 2008

የብላታ መርስዔ ኀዘን መጻሕፍት በአንድ ጥራዝ ተታሙ

በሃያኛው ምእት ዓመት ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ ምሁራን መካከል ግንባር ቀደም የነበሩት ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የጻፏቸውና በረቂቅ ደረጃ የነበሩት የታሪክ ማስታወሻ መጻሕፍት ታትመው ለንባብ በቁ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ (አ.አ.ዩ ፕሬስ) አማካይነት "የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት 1896 - 1922" በሚል ርእስ የታተመው መጽሐፍ ባለፈው ኅሙስ ምሽት በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ራስ መኮንን አዳራሽ በተመረቀበት ጊዜ የአ.አ.ዩ ፕሬስ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ እንደተናገሩት፣ መጽሐፉ በተጠቀሰው ርእስ ተጠናቅሮ ከመቅረቡ በፊት ረቂቅ "የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ ካየሁትና ከሰማሁት"፣ "የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በአቤቶ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት፣ ካየሁትና ከሰማሁት" እና "የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት፣ ካየሁትና ከሰማሁት" በሚሉ አርእስት የቀረበ ነበር፡፡

የብላታ መርስዔ ረቂቅ ጥራዞች በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በአደራነት ተቀምጠው ለታሪክ መጻሕፍት ዝግጅት መነሻነትም ለታሪክ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች እንደመረጃ ምንጭ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ በውጭ አገር ሰዎች ከሚጻፈውና ከሚዘገበው ባሻገር አገራዊ የታሪክ ምንጮች በተለይም በዓመታት ቅደም ተከተል የተዘገቡ እምብዛም በማይገኙበት ጊዜ ክፍተቶችን በመሙላት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ገልፀዋል፡፡

በልጃቸው አቶ አመኃ መርስዔ ኅዘን የተዘጋጀውና 470 ገጾች፣ ስድሳ ገላጭ  ፎቶግራፎችና ሁለት ካርታዎችን ባካተተው "የሐያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ" መጽሐፍ ምረቃ ላይ ደጃዝማች ዶክተር ዘውዴ ገብረ ሥላሴ፣ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴና ዶክተር ፈቃደ አዘዘ በመጽሐፉ ይዘትና ጥራት፣ መጽሐፉ በሚኖረው አስተዋፅኦና ከመሰል የታሪክ መጻሕፍት የሚለይበትንና በደራሲው ሰብዕናና አስተዋፅኦ ዙርያ ያላቸውን አስተያት ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት በአማርኛ ሥነጽሑፍ ተሸላሚ በነበሩት በብላታ መርስዔ ኀዘን ህይወት ዙርያ የ30 ደቂቃ ዶክመንተሪ ፊልም ሲቀርብ የደራሲው ልዩ ልዩ ፎቶግራፎች፣ ልዩ ልዩ ሰነዶች በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ የሰጡትንም አስተያየት ያካተተ ነው፡፡ የአሁኑ መጽሐፍ ከመታተሙ በፊት ከአራት ዓመት በፊት "የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ ካየሁትና ከሰማሁት" በሚል ርዕስ እንዲሁም በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ በዛምራ አሳታሚ በመታተሙ በደራሲው ልጅ ክስ ተመስርቶ ፍርድ ቤት ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በተያያዘ ዜና የአ.አ.ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታሪክ መጻሕፍት ማሳተሙን በምረቃው ዕለት ተገል..ል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ መግለጫ በዩኒቨርሲቲው ፕሬስ የታተመው የታሪክ መጽሐፍ "ኢትዮጵያና ታላቋ ብሪታኒያ የዲፕሎማቲክ ታሪክ ከ1798 - 1966" በሚል ርዕስ በአምባሳደር ተፈራ ኃይለ ሥላሴ የተጻፈ ነው፡፡

"በእንግሊዝ ግዛት ጀምበር አትጠልቅም" እየተባለ ሲተረክላት የነበረችው ታላቋ ብሪታኒያ በዘመኑ ሥልጣኔ ኋላ ቀር ከሆነችው ሆኖም ግን፣ ነፃነቷንና የግዛት አንድነቷን ለመጠበቅ ጽኑ አቋም ከነበራት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት የጀመረችው በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ሁለተኛው መጽሐፍ ኦቶባዮግራፊ፣ (የሕይወቴ ታሪክ) የተሰኘ ሲሆን በፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም የተደረሰና ለሁለተኛ ጊዜ የታተመ መሆኑ ታውቋል፡፡

"የሕይወቴ ታሪክ" ደራሲው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት በ55 ዓመት ዕድሜያቸው ያጋጠማቸውን፣ ያዩትን እና የፈጸሙትን በዝርዝር የሚያመላክት፣ ስለ ትውልዳቸው፣ ስለዕድገታቸው ስለመስኮብ አገር ትምህርታቸው፣ በጣሊያን ወረራ ወቅት፣ በጅቡቲ፣ በኤደንና በማዳጋስካር የስደት ኑሮአቸውና ወደአገራቸው ተመልሰው የሰሯቸውን ሥራዎች ሁሉ ማጠቃለሉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ ዳይሬክተር አስረድተዋል፡፡ 

በሔኖክ ያሬድ

 
< Prev   Next >