| ለባህል ተኮር ቱሪዝም ስኬት |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
ባህል ከሌላው ባህል ጋር በሚኖረው መስተጋብር የማደግ የመለወጥና የመወራረስ ክስተት እንዲፈጠርበት በማፍጠን ረገድ ቱሪዝም ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ከእጅ ጥበባት (ከጥበባተ እጽ) አኳያ የባህላዊ ጥበብ ቅርስነቱ እንደተጠበቀ እንዲቆይ ለማድረግ ቱሪዝም በመሳሪያነትም ያገለግላል፡፡ በአቶ እንድሪያስ አገላለጽ ብዝሀ ባህል የሰው ልጆች ኅብረ ቀለማዊ ውበት ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡ ክብረ በዓሎች ከታሪክና ከእምነት ጋራ የተቆራኙ ትዕይንቶች የባህላዊው ሥርዓት አድማቂዎችና መገለጫዎች ናቸው፡፡ የባህል ድንቅ መገለጫዎች በቱሪስት መስህብነት መታወቃቸው የሀብቱ ምንጭ ለሆነው ሕዝብ ኩራትና የገቢ ምንጭ ማፍሪያነት የሚጠቅም መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ባህል ተኮር ቱሪዝም የባህልን ቁሳዊና ቁሳዊ ያልሆኑ ሀብቶች ለቱሪዝም መስህብነት ለማዋል የሚደረገውን ክንዋኔ የሚያመላክት መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ እንድሪያስ የባህል ተኮር ቱሪዝምን በማስፋፋት ረገድ ሀገራችን የተጓዘችበት አቅጣጫ ለማጣቀሻ የሚሆን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ባህል ተኮር ቱሪዝም ለቱሪስት መስህብነት በጥናት የሚገነቡ የፈጠራና የክሂሎት ማሳያ ሙዚየሞች፣ ጋለሪዎች፣ ትዕይንቶችና ቴአትሮችን በማጣመር አፍቃሬ ባህል ቱሪስቶችን ለመሳብና ለማስተናገድ የሚያዘጋጅ ነው፡፡ የባህል ፌስቲሻሎች፣ የባህል መንደሮች፣ የቅርስ መገኛ ጉዞና የመሳሰሉት በመልኩ ለሚከናወኑ የቱሪዝም መስፋፋት መሠረት ሆነው ያገለግላሉ፡፡ በባህል ሀብት የበለፀገችው ኢትዮጵያ መስህቦቿን በማዋሃድ ዓለም አቀፍ ትኩረት ልታገኝ እንደምትችል አጥኚው አጽንዖት ይሰጡበታል፡፡ ከተለያዩ ሀገሮች ልምድ መቅሰም አስፈላጊነቱን አያጠያይቅም፡፡ ለምሳሌ ከአውሮፓ የስኮትላንድ ተመክሮን ያነሳሉ፡፡ የሙዚቃ ፌስቲቫሎች፣ ብሔራዊ የመናፈሻና የአበባ ፌስቲቫል በተከታታይ በማዘጋጀት በመታወቋ የቱሪስቶችን ቀልብ ለመሳብ ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዘመነ አክሱም በተለይ ከ6ኛው ምእት ዓመት በአፄ ገብረ መስቀልና ቅዱስ ያሬድ ዘመን ጀምሮ በየዓመቱ ታከብረው የነበረውን "ተቀጸል ጽጌ" (አበባን ተቀዳጅ) ከክረምት ወደ መፀው የመሸጋገርን ምልክት የሚያሳየውን በዓል ወደ ፌስቲቫል ማሳደግ ሊተኮርበት የሚገባ ነው፡፡ ምዕራባዊውን ባህል እንደ ቫለንታይንስ ደይ የመሳሰሉትን ለማክበር እንደሚተጋው ሁሉ በውስጣችን የተደበቁትን ጠቃሚ እሴት ያላቸውን አከባበሮች ወደ ንዋይ የሚለወጡበትን መንገድ መፍጠር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቀዳሚ ተልዕኮ መሆን ይገባዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Sunday, 28 September 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |