Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የአርቲስት ሚስት ማለት ምንድነው
የአርቲስት ሚስት ማለት ምንድነው E-mail
Sunday, 28 September 2008

ImageImageበጋዜጣው ሪፖርተር

የአርቲስቶች ሥራና የትዳር ሕይወታቸው እየተጋጨ የፍቺና የጋብቻ ታሪክ ይበዛባቸዋል፡፡ ምሽትና ግብዣ ጊዜያቸውን ይወስደዋል፣ አድናቂያቸው ይበዛል፡፡ በነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የአርቲስት ሚስት ወይም ባል መሆን "ፈተናው" ብዙ እንደሆነ ይነገራል፡፡


የዕውቁና አንጋፋው አርቲስት ባለቤት የሆነችው ወይዘሮ ፅጌ ጌታነህ ግን ይኸንን መሰናክል እንዳለፈችው እሷም ባለቤቷም ይመሰክራሉ፡፡

ወይዘሮ ፅጌ ከአርቲስት ታምራት ሞላ ጋር ከ30 ዓመት በላይ በትዳር ቆይተዋል፡፡ በአዳማ ተወልዳ ያደገችው ወይዘሮ ፅጌ ከአርቲስቱ ጋር በትዳራቸው ፀንተው ለመቆየታቸው ምክንያቱን ጠይቀናታል፡፡

ለመሆኑ የአርቲስት ሚስት ማለት ምንድነው?  

ሪፖርተር፡- የት ነው የተዋወቃችሁት?

ወ/ሮ ፅጌ፡-
ይሄ የኔና የእሱ ጉዳይ መሰለኝ፡፡ ሰው ሁሉ ሲጠየቅ የምጠላው ጥያቄ  ይሄ ነው፡፡

ሪፖርተር - ለምንድነው ይኸን ጥያቄ መጠየቅ የማትፈልጊው?

ፅጌ፡-
እንዲህ አይነቱ ነገር የሁለቱ ጉዳይ ብቻ ስለሚመስለኝ ነው፡፡ ሬዲዮ ስሰማም እንዴት ተገናኛችሁ? ሲባል እሰማለሁ፡፡ ጋዜጠኛ ባልሆንም እንዲህ አይነት ጥያቄ ብተተውት ይሻላል፡፡ ሁሉም የየራሱ መንገድ አለው፡፡ አንዱ የሌላውን ቢሰማ ምን ይጠቅመዋል?

ሪፖርተር፡- መድረክ ላይ እንደተዋወቃችሁ የሰማነው እውነት ይሆን (ራስ ቲያትር በሚዘፍንበት ወቅት አበባ ከሸለመችው በኋላ ትውውቅ መጀመራቸውን ነበር)

ፅጌ፡-     
አዎ፡፡

ሪፖርተር፡- ከመተዋወቃችሁ በፊት የዜማው አድናቂ ነበርሽ?

ፅጌ፡-
አዎ ዘፈኑን ስለምወደው በቃሌ አዜመው ነበር፡፡ ከጓደኛዬ ጋር ተልኬ ዘፈኑን ስንዘፍን ዘግይተን የተገረፍኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ግን የምወዳቸው ዜማዎች፣ ዘፋኝ ታምራት መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ያንጊዜ የተገረፍሽበትንና የምትወጂውን የታምራትን ዘፈን ታስታውሻለሽ?

ፅጌ፡-
"የዘወትር ወርቅ ነሽና" "እነዚያን ቁም ነገር" የሚሉትን ዘፈኖች ነበር፡፡ እወዳቸው ነበር፡፡ የማን ዘፈን እንደሆኑ ግን አላውቅም ነበር፡፡ በኋላ ተገናኝተን ከሱ ጋር ሆኜ ነው ዘፈኑ የሱ መሆኑን ያወቅሁት፡፡ ይኸን ሳውቅ እናቴ የሱን ዘፈን ስዘፍን ከተላክሁበት ዘግይቼ ገርፋኝ ነበርና የተገረፍኩበት ዜማ የእሱ መሆኑን ጠብቄ ነገርኩዋት፡፡

ሪፖርተር፡- ምን አሉሽ?

ፅጌ፡
ለማያውቅ ሰው አይመስልም፡፡ ያንጊዜ የምታውቅህ ነው የሚመስለው፤ ብላ ለራሱ ነገረችው፡፡ (ሳቅ)

ሪፖርተር፡- መጀመሪያ መልኩን የት ነው ያየሽው?

ፅጌ፡-
በቴሌቪዥን፡፡

ሪፖርተር፡- አርቲስት አገባለሁ ብለሽ አስበሽ ነበር?

ፅጌ፡-
በፍፁም፡፡

ሪፖርተር፡- የጥበብ ሥራዎች ትከታተይ ነበር?

ፅጌ፡-
አንዳንድ ነገር እከታተል ነበር፡፡ ግን ብዙም አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወደ መንፈሳዊ መዝሙር ነበር የማደላው፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ ታምራት የሚዘፍነው እኮ መንፈሳዊ መዝሙር አልነበረም፡፡

ፅጌ፡-
ያንጊዜ የሱን ዘፈን ስወደው ትንሽ ነበርሁ፡፡ እንደ ልጅነቴ ሙዚቃ እወድ ስለነበር የሱንም ከዚያ አኳያ ነው የወደድሁት፡፡ ከሚገርምህ እኔ ብቻ ሳይሆን የአጎቴ ልጅ ሁሉ ይወደው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የታምራት ባህርይ ምን አይነት ነው?

ፅጌ፡-
ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥሩ ነው ማለት ምን ማለት ነው?

ፅጌ፡-
በቃ ጥሩ ሰው፡፡

ሪፖርተር፡- የማይቆጣ፣ ለሌላው የሚያስብ".

ፅጌ፡-
ቁጡ ማለት ምንድነው? በሌላ ሰው ቁጡ አይደለም፡፡ በራሱ ሰው ላይ ነው የሚቆጣው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንቺ ላይ አይቆጣም?

ፅጌ፡-
እኔማ የራሱ ነኝ፡፡ በሌሎች ላይ የማያስቆጣው እኔ ላይ ብልጭ ሲልበት ታያለህ፡፡ የራሱ ስለሆንኩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያን ጊዜ አንቺ ምን ትያለሽ?

ፅጌ፡-
ምንም አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- አንቺ ቁጡ አይደለሽም?

ፅጌ፡-
አይደለሁም፤ እኔ አልቆጣም፡፡ (ሳቅ)

ሪፖርተር፡- ሲቆጣ ምን ታደርጊያለሽ?

ፅጌ፡- 
እሰማዋለሁ፡፡ ዝም ብዬ እሰማዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለቤትሽ ኩራት፣ ከእኔ ወዲያ ላአሳር አይነት ባህርይ አለበት?

ፅጌ፡-
ጎንደሬ ነው ብለህ ነው? (ሳቅ"፡፡ ቅድም ብዬሃለሁ፣ኮ፡፡ ሚስት ለባሏ ምስክርነት አትጠራም፤ ግን እውነቱን ነው የምነግርህ፡፡ ለምንስ ብዬ እዋሻለሁ፡፡ ታምራት በጎንደር በጎጃም የሚባል ባህሪ የለውም፡፡ ታምራት ይኸ ሁሉ ባህርይ የለበትም፡፡ የእውነት ሰው ነው፡፡ አንድ ነገር ሲያወራህ "እስኪ ሙት በለኝ፤ እጄን ምታ" ይልሃል፣ ያምንሃል፡፡ ውሸት ሆኖ ካገኘው ግን ይጣላሃል፡፡ አንድ ጓደኛው እጁን መትቶ ውሸት ሆኖ አግኝቶት ሶስት አመት እንዳኮረፈው አውቃለሁ፡፡ የታምራት ጸባይ አንዳንዱ ለሌላው ላይገባ ይችላል፡፡ ግን ጥሩ የሚባል ባህርይ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ምንስ ቁጡ ባትሆኚ፣ በዝቶብሽ ወይም በተለያየ ምክንያት ተናደሽበት አታውቂም?

ፅጌ፡
- አልናደድም፡፡ የምንጣላው ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ ነው፡፡ እሱ መደበቅ አይችልም፡፡ አስመስሎ መናገር አይችልም፡፡ ፊት ለፊት ሲናገር ከሰው ያጣላዋል፡፡ "ለጠፍህና መጣህ?" እለዋለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ አልናደድበትም፡፡

ሪፖርተር፡- አርቲስቶች ሥራቸው ያስመሻል፣ ያሳድራል አድናቂ ነኝ ብላ አንገቱ ላይ የምትንጠለጠል ብዙ ናት".

ፅጌ፡-
ልትለው የምትፈልገው ገብቶኛል፡፡ የእኔ ሕይወት የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ሌሎች የሚያስቡትና እኔ የማስበው ጭራሽ አይገናኝም፡፡ እኔ ሁልጊዜ የሚያስጨንቀኝ እቤቱ በሰላም ይገባ ይሆን ወይ? ነው፡፡ በተለይ ሌሊት ሲሰራ መንገድ ላይ ምን ያጋጥመው ይሆን? እያልሁ ከማሰቤ የተነሳ ቁጭ ብዬ ነው የምጠብቀው፡፡ በረንዳ ላይ ስወጣ ስገባ አድራለሁ፡፡ የማስበው በደህና መምጣቱን ነው፡፡ ደክሞት መኪና ሲነዳ አደጋ ይደረሰበት ይሆን? እያልሁ ከማሰብ ውጭ ሌላ ሃሳብ የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራውን እንዲተው ተናግረሽ ወይም ፈልገሽ አታውቂም?

ፅጌ፡-
እፈልጋለሁ፡፡ እንዲያውም ነግሬዋለሁ፡፡ የምሽት ሥራውን እንዲተው የምፈልገው ግን አንተ ባሰብከው መንገድ አይደለም፡፡ ለደህንነቱ እየተጨነቅሁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተው ስትይው ምን አለሽ?

ፅጌ፡-
ምን ልትበይ ነው? አለኝ፡፡ (ሳቅ) እኛ እኮ ብር ላይ ነው ያለነው፡፡ ቤታችንን ብናከራየው ከዚህ በላይ አናገኝም? አልሁት፡፡

ሪፖርተር፡- 35 አመት የትዳር ዘመን አሳልፋችኋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የመጀመሪያዎቹን አምስት አመት እንኳ የሚያስቀና ነገር አልገጠመኝም  ነው የምትይው?

ፅጌ፡-
አምነዋለሁ፡፡ እጅግ አምነዋለሁ፡፡ አርቲስት የሰው ገንዘብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እገሊት ሸለመችው እገሊት እንዲህ አደረገችው ቢባል በሌላ አልተረጉመውም፡፡ በጭንቅላቴ ሌላ ነገር አንድም ቀን መጥቶ አያውቅም፡፡ እውነቴን ነው የምነግራችሁ፡፡ የቅናት መንፈስ የለብኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሴት ጋር አብረው ሆነው ብታይ ምን ትያለሽ?

ፅጌ፡-
የሥራ ጉዳይ አገናኝቷቸው ይሆናል እላለሁ፡፡ ወይም ይኸን የመሳሰለ ነገር እገምታለሁ እንጂ ወደ ቅናት ጎዳና አላመራም፡፡ ከአመንኩበት ነገር ወደኋላ መመለስ አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- መንፈሳዊነትሽ እየተጫነሽ ይሆን?

ፅጌ፡-
ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰው በመሐከላችሁ ገብቶ አያውቅም?

ፅጌ፡-
እንደሱ አይነት ነገር አለ፡፡ ግን እንደ አመጣጣቸው መልሻቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ታምራት አልኮል መጠጥ እንደማይቀምስ የታወቀ ነው፡፡ ግን ሌሎችን ይጋብዛል? ቸር ነው ወይስ ንፉግ?

ፅጌ፡-
ቸር ነው፡፡ እጁ ቀዳዳ ነው፡፡ እቤታችን ሁልጊዜ መጠጥ አለ፡፡ የሚገዛው እሱ ነው፡፡ ሰው ለመጋበዝ ብሎ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለማይጠጣ ቢያንስ ገንዘብ አይጠፋማ፡፡

ፅጌ፡-
እሱን ተወው፡፡ አይጠየቅም፡፡ ለራሱ ሳይሆን ለሰው የኖረ ሰው ነው፡፡ ደመወዝ ተቀብሎ ትንሽ ገንዘብ ይዞ የመጣበት ጊዜ አለ፡፡ ምነው ስለው እገሌ እገሌ ቸገረኝ ስላሉ ሰጠኋቸው አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን አልሽው?

ፅጌ፡-
ምን እለዋለሁ፡፡ ይኸ እኮ በጎ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ ጥሩ አደረግህ አልሁት፡፡


ሪፖርተር፡- ባለቤትህን እንዴት ነው የምትገልፃት?

ታምራት፡-
በትዳር የታደልሁ ሰው ነኝ፡፡ ባለቤቴ ቀና ናት፡፡ ትዳሩዋን ታከብራለች ለኔ ሁሉንም ነች፡፡ ስለእኔ የምትጨነቅልኝ ከአለባበሴ ጀምሮ በሁሉም ነገር እርሷ ናት፡፡ ትመክረኛለች፡፡ ጥሩ ሰው ናት፡፡

ሪፖርተር፡- ጥሩ ናት ስትል ምን ማለትህ ነው?

ታምራት፡-
ትዳሩዋን ታከብራለች፡፡ ወጣች ከቤተክርስቲያን ተመለሰች እቤቷ ነው፡፡ ለስላሳ ናት፡፡ እኔ ደግሞ ሚስት እንደዚያ ስትሆን ነው የምወደው ልታይ ልታይ የምትል ሴት አልወድም፡፡

ሪፖርተር፡- ይኸማ የወንድ ትምክህተኛነት አመለካከት አይሆንም?

ታምራት፡-
እንደሱ አይደለም፡፡ ሰው በተፈጥሮ የራሱ ምርጫ አለው፡፡ እኔ ሴቶች እንደ ሴት ሲሆኑ ነው የምወደው፡፡ የባህል ተጽዕኖ ሊሆንም ይችላል፡፡ የተፈጥሯዊ ስሜትም ሊሆንም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቃህን ታዳምጣለች?

ታምራት፡
- በፊትም ታዳምጥና ትወደው እንደነበር ነግራኛለች፡፡ አሁንም ታዳምጣለች፡፡ ካልጣማትም ፣ይኸን ለማሟያ ነው የሰራኸው፣ ትላለች፡፡ የመሰላትን ከመናገር ወደኋላ አትልም፡፡ ደህናውንም ታደንቃለች፡፡ ደግሞ ለሙዚቃ ንቁ ጆሮ አላት፡፡

ሪፖርተር፡- እሷን መነሻ አድርገህ ያዜምከው ዜማ አለ?

ታምራት፡-
እኔ እንጃ አስቤ ሳይሆን የሚገጣጠም ነገር ይኖር ይሆናል፡፡ ለምሳሌ "በምን ቃል ላስረዳሽ?" የሚለውን ዘፈን ብዙ ሰው ለሷ የዘፈነው፣ ነው ብሎ ይናገራል፡፡ እንዲያውም አንድ አክስቴ ለሚስትህ ብቻ ነው የምትዘፍነው፡፡ ለኛ አትዘፍንም ብላ ተቆጥታለች፡፡ ግን አስቤበት ባይሆንም አንዳንዱ ይገጣጠማል፡፡

ሪፖርተር፡- እቤትህ ቁጡ ነህ?

ታምራት፡-
ቁጡ ነኝ፡፡ ሚስቴ ደግሞ ቀዝቃዛ ናት፡፡

ሪፖርተር፡- ምን አይነት ነገር ያስቆጣሃል?

ታምራት፡-
ትንንሽ ነገር ሁሉ ያስቆጣኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቀን ሰራተኛችን በእርጥብ እጇ የነካቸውን ብርጭቆ ሰጠችኝ፡፡ ሳላስበው ተናድጄ ብርጭቆውን ወደ ባለቤቴ ወረወርኩት፡፡ የተቆጣሁት በሚስቴ ነው፡፡ ለምን አትቆጣጠራትም ብዬ ነው፡፡ ይኸ ትምክህት ሊባል ይችል እንደሁ አላውቅም፡፡ በኋላ እጅግ ፀፀተኝ፡፡ ግን በጊዜው ላልፈው አልቻልሁም፡፡

ሪፖርተር፡- ዝም አለችህ?

ታምራት፡-
ምንም አላለችኝም፡፡ ያ ደግሞ የበለጠ እንድፀፀት አደረገኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ስትፀፀት ይቅርታ ትጠይቃለህ?

ታምራት፡-
እንደሱማ በአበሻ አልተለመደም፡፡ (ሳቅ) ግን በአንዳንድ ድርጊቴ መፀፀቴ ይገባታል፡፡

ሪፖርተር፡- ይኸ ማለት እኮ በትዳርህ ደስተኛ የሆንከው ያንተ ፍላጎትና ባህርይ ብቻ ስለሚስተናገድ ነው፡፡

ታምራት፡-
ሊሆን ይችላል፡፡ ተመሳሳይ ባህርይ ካለንማ፣ እንደ እኔ ቁጡ ከሆነችማ፣ እስካሁንም አብረን ላንኖር እንችላለን፡፡ የሷ ቀዝቃዛነት ነው መቼም ዋናው የትዳራችን ውጤት፡፡

ሪፖርተር፡- መፀፀትህን በምንድነው የምትገልፀው?

ታምራት፡-
ምንም አላደርግም፤ ግን ይፀፅተኛል፡፡ መፀፀቴን ታውቃለች፡፡ 
Last Updated ( Sunday, 28 September 2008 )
 
< Prev   Next >