Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የ1918 ዓ.ም የመስቀል ደመራ ሰልፍ
የ1918 ዓ.ም የመስቀል ደመራ ሰልፍ E-mail
Sunday, 28 September 2008

የመስቀል ደመራ በያመቱ በወታደር ሰልፍ መከበሩ ምንም የተለመደ ቢሆን በዚህ ዓመት ግን ሰልፉ በፍልውሐ ሜዳ ላይ እጅግ ከፍ ብሎ ተከበረ፡፡ መስከረም 16 ቀን ቅዳሜ በ8 ሰዓት ተኩል ብፁዕ እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ወደ ደመራው ስፍራ መጡ፡፡ ቀጥሎም ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኰንን ታጅበው መጡና ወደ ተሰናዳው ድንኳን ገብተው በወምበር ላይ ሲቀመጡ ካህናቱ የበዓሉን ጸሎት ያደርሱ ጀመር፡፡


ከጸሎቱ በኋላ ብፁዕ እጨጌ ከካህናቱ ጋር ቀደሙ፡፡ ከዚያም ቀጥለው ልዑል አልጋ ወራሽ ከመኳንንቱ ጋር ደመራውን ሦስት ጊዜ ዞሩት፡፡ ልዑል አልጋ ወራሽ ወደ ድንኳን ተመልሰው ከተቀመጡ በኋላ የወታደሩ ሰልፍ በ9 ሰዓት ተሩብ ተጀመረ፡፡ በዚያ ሰሞን ለወታደር አለቆችና ለመንግሥት ሠራተኞች ሽልማት ሲሰጥ ሰንብቶ ነበረና ሁሉም በሽልማት ልብስ እያጌጠ መጥቶ በየቤተ ደንቡ ተሰለፉ፡፡

አብዛኛው ወታደር እንደ ቄየው ልማድ የሰልፍ ልብስ እየለበሰ በአንፋሮና በአቡቀዳዴ የተሰለፈ ሲሆን የአራዳ ዘበኞችና የክብር ዘበኞች ግን በዘመናዊ ሥርዓት በኮት ልብስ ተሰለፉ፡፡

የሰልፉም ተራ እንደሚከተለው ሆነ፤

የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሠራዊት በክፍል በክፍሉ ተሰልፎና አምሮ በመጀመሪያ አለፈ፡፡ ቀጥሎም የፈረስ ዘበኛ የሚባለው ጭፍራ በአለቃው በፊታውራሪ ደስታ ዳምጠው እግር ተሰልፎ አለፈ፡፡ እንዲሁ ደግሞ ጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ መስቀል ጭፍሮቻቸውንና የፖስታ ቤት ሠራተኞችን አሰልፈው አለፉ፡፡

ከዚያም በኋላ በዘመናዊው የሰልፍ ትምርት የሰለጠነው የመትረየስ ዘበኛ (በኋላ የክብር ዘበኛ) የተባለ ጭፍራ በአለቃው በግራዝማች ገብረ ዮሐንስ እግር ተሰልፎ አምሮ መጣ፣ የአርመን ልጆችም ሙዚቃ እየነፉ በሰልፉ ውስጥ ነበሩ፡፡

ከዚህ ቀጥሎ የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች በነጭ መለዮ ልብስ አጊጠውና አምረው፣ ትንንሽ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው መዝሙር እየዘመሩ ከአስተማሪዎቻቸው ጋር በሰልፍ አለፉ፡፡ ከተማሪዎቹ በኋላ ባለነጭ ሱሪ የሆነ አንጋች ዘበኛ ተሰልፎ መጣ፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ፊታውራሪ ወልደ አማኑኤልና ግራዝማች ከልክሌ የጭፍሮቻቸውን ሰልፍ አሳዩና በ10 ሰዓት የሰልፉ ፍፃሜ ሆኖ ልዑል አልጋ ወራሽ ወደ ግቢያቸው ተመለሱ፡፡

(መርስዔ ኅዘን ወልደ ቂርቆስ፣ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ 1999)

መስከረም

የመስከረም ታሪክ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ መስከረም ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳቱም የነጻነት፣ የፍቅርና የደስታ ወር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከረዥሙና አድካሚው የክረምት እርሻ ተላቆ እንዳሻው በልቶና ጠጥቶ ጊደር ፍለጋ እያገሳ የሚንጎማለለው ወይፈንና ከጭነት ሥራ ተላቆ እንዳሻው ሲራገጥ የሚውለው አለሌ አህያን ጨምሮ ለአብዛኛዎቹ የቤትና የዱር እንስሳት መስከረም "የጫጉላ" ጊዜያቸው ነው፡፡ ራሱን ከኃይለኛው የክረምት ጐርፍ ለመከላከል በየአለቱ ሥር ተደብቆ የከረመው ዓሣ በነጻነት መንፈስ በጠራ ውሃ መርመስመስ የሚጀምረው ከእንቁጣጣሽ ማግሥት ጀምሮ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር እባብ ከሁለት ወራት የክረምት እስር ተፈቶ ያረጀ ቆዳውን በአዲስ ለውጦ እንደ ልቡ መምዘግዘግ የሚጀምረው በመስከረም ወር ነው፡፡ በራሪዋ ጭልፊትም እንደዚሁ፡፡

ጃርት ሌሊት ሌሊት ተደብቆ ዱባ በመግመጥ፣ ጦጣ በቆሎ በመሸልቀቅ፣ ዝንጀሮ ስንዴና ባቄላን በመስረቅ፣ አምሮታቸውን ከመወጣት አልፈው ቁንጣን እስኪይዛቸው መመገብ የሚጀምሩት በመስከረም ነው፡፡ የንብ ነገርማ ምኑ ይነገራል? ሥራ ፈትዋ ቢራቢሮም ብትሆን ከኔ ወዲያ ቆንጆ ላሳር በሚል ስሜት አበባን ስታጅብ ውላ የሚመሽላት በመስከረም ነው፡፡

(ካህሣይ ገብረእግዚአብሔር፣ ኅብረብዕር፣ 1998)

በራ የመስቀል ደመራ

የአደይ ችቦ እየፋመ፣ እየጋመ
ኢዮሃ እያስገመገመ እየተመመ
የመስቀል ደመራ
በራ፡፡
በራ የአዲስ ዘመን ችቦ
በመስከረም ሰብል አብቦ
ከዋክብቱን ፈነጠቀ
ርችቱን አንጸባረቀ
ተኳለ አዲስ ደመቀ
መስኩን በቀለም አዝርእት፣ በጥበብ አጥለቀለቀ
ሸለቆው ተንቆጠቆጠ፣ ተራራው አሸበረቀ
ኢዮሃ ኢዮሃ አበባዬ" ምድር ሕይወት አፈለቀ፡፡
ነጋ፣ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ፣ ፀደይ አረብቦ
ሌሊቱ እንደጎሕ ቀደደ፣ ጨለማው እንደቀን ጠራ
እንደውቅያኖስ ዕፅዋት፣ እንደጠፈር ኮከብ ደራ
ምድር ሥጋጃ ለበሰ፣ የጌጥ አልባሳት ተቀባ
ሰማይ በእልልታ አስተጋባ
ኢዮሃ መስከረም ጠባ፡፡
ነጋ፣ የአዲስ ዘመን ችቦ፣ ምድር ሕይወት አፈለቀች
የምሥራች አዝርእቷን፣ አዲስ ቡቃያ ወለደች
የአደይ አበባን ለገሰች
ለአዲስ ዘመን አዲስ ብርሃን፣ አዲስ መስከረም ገበየች፡፡
ነጋ፣ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ፣ ፀደይ አረብቦ
በራ፣
የመስቀል ደመራ፡፡
(ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ እሳት ወይ አበባ፣ 1999)


መጠጥ በመጠኑ ይሁን

ከአርእስቱ መጠጥ በመጠኑ ይሁን ብየ የተነሳሁበት ምክንያቱ፤ ዘበልዐ በአቅሙ የሐድር በሰላም ያለውን ምክራዊ ቃል በመከተል ነው፡፡ ከልክ አሳልፎ ቢጠጡት እንኳን አልኮል በእሳት ነጥሮ የተሠራውና ልብን የሚያቀዘቅዝ፤ ጥምን የሚቆርጥ ውሀ እንኳ ከልክ አሳልፎ ቢጠጡት አንጀትን በጣጥሶ እንደሚገድል የተረጋገጠ ነው፡፡ ከህል የበለጠ የለም፤ እሱን እንኳ አብዝቶ ቢመገቡት በማስጨነቅ እንቅልፍ ነሥቶ እንደሚያሳድር የታወቀ ነው፡፡

ሰው ሆይ" ማንኛውም ነገርና መባልዕትም፤ መጠጦችም ቢሆኑ ከልክ አሳልፈው ከተመገቧቸው ለሰውነት ጸር እንደሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው፤ ከአራቱ ባሕርያት አዋጥቶ ስለፈጠረው፤ ወይም ወደ እሳትነቱ የሚያደላ ወይም ወደነፋስነቱ የሚያደላ እንደሆነ፤ ወደ ውሀም ያደላ የሆነ እንደሆነ፤ የሕይወቱ መጥፊያ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ ምግብም ቢሆን መጠጥ በልክ ከተመገቡትና መጠጥንም በልኩ መጥኖ ከጠጡት ለሰውነት ተስማሚ እንደሚሆን አይዘነጋም፡፡

ነገር ግን ከልክ አሳልፎ በመጠጣት ከተፈጥሮ ባሕርዩ አንዱን አጉድሎ እንደመንፈቅ ልጅ መሬት ለመሬት ሲጐተቱ መታየት ሰውን ማስቀየም ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም ማስቀየም እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ከልክ ከመጠን አልፎ በመስከርም ከተፈጥሮ ባሕርዩ እየተቀነሰ እንደሚጐድልበት የታወቀ ነው፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ በእሳት ተፈጥሮው ሙቀት ይሰማዋል፡፡ በውሀ ተፈጥሮነቱም ቅዝቃዜ ይሰማዋል፡፡ ደግሞ በነፋስ ተፈጥሮው እንደነፋሱ የሕይወት እስትንፋስ ይሰማዋል፡፡ በመሬትነቱም በሰውነቱ ወዝና እድፍ ይሰማዋል፡፡ ስለዚህ በእሳት ነጥሮ የተሠራውን የአልኮል መጠጥ ከልክ ከመጠን አሳልፎ በጠጡት ጊዜ የእሳትነትን ባሕርይ አግኖ የቀሩትን ባሕርያት አድክሞ፤ ሰውዬውን ወደጥፋት ዝንባሌ የሚያደርስ መሆኑን ማወቅ ያሻ ነበር፡፡

(ሥርጋዌ ካሣው፣ ሰንደቅ ዓላማችን ጋዜጣ፣ 1950)


ገራገር
ሰካራሙ የእሳት አደጋ ሠራተኞችን አታለለ


አንድ ሰካራም 999 በመደወል ቤቱ ላይ ቃጠሎ መድረሱን ለእሳት አደጋ ሠራተኞች በመናገር ሊፍት ለማግኘት ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ዜል ራጅሲክ የተባለው ይህ ሰካራም ሲጠጣ አድሮ፣ ጠዋት ከነበረበት 10 ማይሎች ርቀት ላይ የሚገኘው ቤቱ ቃጠሎ እንደደረሰ በማስመሰል ወደ ቤቱ እንዲወስዱት ሠራተኞቹን አታሏል፡፡

የእሳት አደጋ ሠራተኞች ከሰውየው ቤት ሲደርሱ የገጠማቸው ቃጠሎ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የሰካራሙ ሰውየ ቤተሰብ ለምን ከእንቅልፋችን ትቀሰቅሱናላችሁ በማለት አንገራግረዋል፡፡

የአካባቢው እሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ ቃል አቀባይ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት ሁኔታው የሚያስቆጣ ቢሆንም እሳት አጥፊ ሠራተኞቹ ሁኔታው አስቂኝ እንደሆነባቸውና ሰውየው በፈፀመው ጥፋት እንዲቀጣ አለማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡


ገንዘብ ለመቆጠብ ሚስቱን እንድትታሰር የመረጠ

አንድ ጀርመናዊ 180 ፓውንድ ከመክፈል ሚስቱን በእስር ቤት እንድትቆይ መረጠ፡፡ ይህ የሆነው ሚስቱ በስርቆት ወንጀል ተከሳ ለ15 ቀናት እንድታሰር ሲፈርድ ባሏ ፍርዷን በገንዘብ ተለውጦ መውጣት እንደምትችል ለባልየው በተነገረው ወቅት ነው፡፡

ባሏ እስር ቤቱ ድረስ በመምጣት 180 ፓውንዱን መቆጠብ እንደሚፈልግና በምትኩ 15 ቀናት እንድትታሰር ተናግሯል፡፡


የባለቤቱን ድመት ያባረረ ተቀጣ

ሳምሶናይቱ ላይ በሸናችበት ድመት ተበሳጭቶ ከቤት ውጪ እንድታድር ያደረገ ግለሰብ 400 ፓውንድ እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡

ሎራ ማርቼዚ የተባለችው የድመቷ ባለንብረት ባሏ በፈፀመው ድርጊት ወደ እንስሳ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ጉዳዩን በማቅረብ ለድመቷ ጠበቃ አቁማለች፡፡

ማርቼዚ ድመቷ በረሀብና በብርድ ስትንቀጠቀጥ ሌሊቱን ሙሉ ማሳለፏንና ወደ ቤት ለመግባት እየተንገዳገደች አገኘኋት በማለት ለማህበሩ ስሞታዋን አቅርባለች፡፡

ፍርድ ቤቱ የሴትዮዋን ስሞታ በማዳመጥ ባለቤቷ በድመቷ ላይ በፈፀመው ጥፋት 400 ፓውንድ ለባለቤቱ እንዲክስ ተወስኖበታል፡፡

ይህን የተፈረደላት ማርቼዚ ውሳኔውን በማስመልከት "በጠበቃዎች ለተደረገልኝ ሙሉ ትብብር እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ድመቴን እወዳታለሁ፣ እሷ ላይ በደረሰው ነገር እጅግ ደግሞ ተከፍቼ ነበር፡፡ የተከፈለኝ ካሳም ተገቢ ነው" ብላለች፡፡ የተሰጠው ፍርድ በጥንዶቹ ግንኙነት የፈጠረው ተፅዕኖ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡



በሌሴቶ ትልቅ የአልማዝ ግግር ተገኘ

የማእድን ተማራማሪዎች በሌሴቶ በትልቅነቱ የመጀመሪያ ሊሆን የሚችል የአልማዝ ግግር ድንጋይ አግኝቷል ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡

የተገኘው የአልማዝ ድንጋይ 478 ካራት ክብደት ያለው ሲሆን፣ እስከ አሁን የተገኙት የአልማዝ ድንጋዮች በትልቅነቱ 20ኛ ሊሆን እንደሚችል ጌም ዲያመንድ የተባለው የማዕድን ቁፋሮ ኩባንያ አሳውቋል፡፡

ኩባንያው አክሎ አንዳስታወቀው፣ እስከ አሁን ስያሜ ያልተሰጠው ይህ አልማዝ የተጣራ 150 ካራት ሊሰጥ የሚችል እንደሆነና በ10 ሚልዮኖች የሚቆጠር ዶላር ሊያወጣ የሚችል ነው፡፡

የካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ እንዳለው፣ የተደረገው የቅድመ ምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው በጥራቱና በቀለም መስህብነቱ ቀዳሚነት ሊይዝ እንደሚችል ነው፡፡

ቁፋሮውን ያካሄደው የሌሲንግ ማይን ኩባንያ ጌም ዲያመንድስ 70 በመቶ፣ የሌሴቶ መንግሥት ደግሞ 30 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ 
 
< Prev   Next >