Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 08th
Home arrow Sections arrow ዝክረ ጥምቀት - 2000
ዝክረ ጥምቀት - 2000 Print E-mail
Sunday, 20 January 2008
ትናንት በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የከተራ በዓል ነበር፡፡ በአገራቱ ባሉ ጥምቀተ ባሕሮች ታቦታቱ የወጡበትና አዳር ያደረጉበት ነው፡፡
ዛሬ ደግሞ የጥምቀት በዓል ይከበራል፡፡ ከቅዱስ ሚካኤል ታቦት በስተቀር ሁሉም ታቦታት ወደየአጥቢያቸው የሚመለሱበት ነው፡፡

ጥር 11 ቀን 33 ዓ.ም ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ አማካይነት በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ዕለት የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ ጥምቀት "ኤጲፋንያ" ተብሎም ይጠራል፡፡ "አስተርእዮ" ወይም መገለጥ ማለት ነው፡፡

አፀደ ተፈራ በጥናቷ እንደገለጸችው የጥምቀት ክብረ በዓል ከጥር 10 ጀምሮ እስከ ጥር 12 ድረስ ለሦስት ቀናት ይከበራል፡፡ ጥር ዋዜማ ሆኖ "ከተራ" ይባላል፡፡ የስያሜው መነሻም ለማግስቱ ለመጥመቂያ እንዲሆን ሰዎች በየክፍላቸው የሚገኙትን ወንዞች ውሃው እንዳይወርድ ይከትሩትና ባሕር ማድረገቸው ነው፡፡ ይህም ተከተረ ይባላል፡፡

በከተራ ዕለት ሌላም ተግባር ይከናወናል፡፡ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናት የሚገኙ ታቦታት ሁሉ ይወጣሉ፡፡ ወጥተውም በወንዝ ዳር (በሰው ሰራሽ የውኃ ግድብም ቢሆን)፣ በዳስ በድንኳን ያድራሉ፡፡ በከተራ ዕለት ታቦታት ከየመንበራቸው ወጥተው ወንዝ አጠገብ ወይም ድንኳን ውስጥ ማደራቸውም ተምሳሌታዊ ነው፡፡ በበዓለ ጥምቀት የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ ኢየሱስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው፡፡

መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስ በአንድ ድርሳናቸው ስለ በዓሉ አከባበር ሲገልጹ በዓሉ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት በሦስተኛው ምሽት ዓመት መከበር መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡

ስለ በዓሉ በየአብያተ ክርስቲያኑ የተለያየ ትውፊት አለ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ምዕምናኑ በቤተክርስቲያን ውስጥ ወይም በውጭ እንደ አየሩ ሁኔታ ተሰብስበው ካህኑ የኢየሱስን ጥምቀት የሚያመላክተውን ጥቅስ ከወንጌል አንብቦ በምእመናኑ ላይ ውሃ በመርጨት በዓሉ ይታሰባል፡፡ ሌሎች ደግሞ ወደ ወንዝ (ባሕር) ወርደው ሻማ አብርተው ሊሰጥም በማይችል ተንሳፋፊ በሆነ ዕቃ ላይ በመትከል በባሕሩ ይጥሉታል፡፡ ሻማው እስከሚያልቅ ድረስ ባሕሩ ላይ እየተንሳፈፈ በነፋስ ኃይል ይጓዛል፡፡ ይህም የሚያመለክተው ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ብርሃነ ትምህርቱን ማብራቱንና በሥጋ መገለጡን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለ ጥምቀት በዓል አከባበር የራሷ ትውፊት እንዳላት የሚገልጹት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ፣ በሥዕላዊ መልክ ከሚከበሩ በርካታ በዓላት መካከል አንዱ ጥምቀት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

የጥምቀት በዓል ባህላዊ ገጽታው ጎልቶ ይታያል፡፡ ኅብረተሰቡ ባለው አቅም ጽዱ ልብስ ለብሶና ደምቆ የሚታይበት ነው፡፡ እስከነ ምሳሌያዊ አነጋገሩ "ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ" ይባላል፡፡ በጥምቀት ባሕሩ ጉብሎችና ኮረዶች የሚፈላለጉበት ሎሚ የሚወራወሩበት ነው፡፡

ወጣቶች በአርሞኒክ በመታጀብ ደማቅና ፈጣን የዳንስ ትርዒት ሲያሳዩ አዋቂዎች እንደየ ትውልድ አካባቢያቸው ባህላዊ ጭፈራቸውን ያከናውኑታል፡፡

ታቦታት ሲወጡ ሴቶች "በሕይወት ግቢ በሕይወት ያገራችን ታቦት" በማለት ዘፈኑን ሲያደምቁት በሚገባበት ጊዜም "እንኳን በሰላም ገባሽ፤ የከርሞ ሰው በይን" በማለት ያመሰግናሉ፡፡

የሰቆጣ ከተማን የጥምቀት አከባበር የቃኘችው አፀደ እንዳብራራችው የእናቶች ዜማ በአብዛኛው በአቀንቃኝና በተቀባይ የሚዜም ነው፡፡ ከቡድኑ መካከል አንዲት እናት ወይም ወጣት ወደ መሐል በመግባት እንዲህ ታቀነቅናለች፡፡

"ይኸው ሎሌው ሲያምር ሎሌው ሲያምር፣
የወይብላ፣ የገብርኤል፣ የመድኂኑ ደብር" ስትል ተቀባዮቹም እያጨበጨቡና አካላቸውን ከዜማው ጋር እያንቀሳቀሱ ይህንኑ ይደግሙታል፡፡ አቀንቃኟ ዜማውን በመቀየር፣
"አፀድሽ ያብባል
እደሩ ዋሉ ይላል
አፀድሽ አባባይ
እደሩ ዋሉ ባይ" በማለት እየዘፈኑ የተወሰነ ርቀት ከተጓዙ በኋላ ሌላዋ አቀንቃኝ በ"ወፌ ይላላዬ" ዜማ መዝፈን ትጀምራለች፡፡ ተቀባዮች ይለጥቃሉ፡፡

"ወፌ ይላላ ወፌ ይላላዬ
ለጥምቀት ለልደት
ያልዘፈነች 
ሰቆጣ ስደዳት
ያህያ መናጆ"

በዚህ ጊዜ ሌሎች ሴቶችም የሚያጨበጭቡና አብረው የማይጫወቱ ከሆነ አቀንቃኟ እነሱን የሚነካ ቃል ግጥም በሌላ አዝማች በ"ሲያይሽ ዋለ" ዜማ ትገጥማለች፡፡
"ሲያይሽ ዋለ
ኦሆ
የሰው ቀሚስ
ተውሰሽ
የሰው አልቦ ተውሰሽ
የሰው ድሪ ተውሰሽ
ለማርያም ነወይ ኩራትሽ
ለእምዬ ነወይ ኩራትሽ
እኔሳ ወት ሂጅ ገረድሽ"

ካህናት ወረብ በሚወርቡበት ወቅት ታቦታቱም ጉዟቸውን ይገታሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ሴቶችም እንቅስቃሴያቸውን ገትተው በአንድ ቦታ ላይ ተሰባስበው ይዘፍናሉ፡፡ ከሚያዜሟቸው ዜማዎች ውስጥም አንዱ "እናናው ደማ ዓለም" የሚለው ነው፡፡

ቡድኑ ክብ ይሠራና ሁለት ሴቶች ነጠላቸውን አደግድገው በመታጠቅና ቦታ በመቀያየር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ማቀንቀን ትጀምራለች፡፡
ቃል ግጥሞችንም ትደረድራለች፡፡
 "እናናው ዳማ ዓለም
  ዳማ
ባምሳም በሰላሳ
ትገዛለች ላም
የመድኂኑ እናት
ወይብላ ማርያም"

የተቀባዮቹ ጭብጨባና አዘፋፈን ቅዝቀዝ ያለ ከሆነም አቀንቃኟ በዜማ የማነቃቂያ የስድብ ቃል ግጥም ትገጥማለች፡፡
"እጃችሁ ምንኛ
እሾህ ይውጋልኛ
አፋችሁ ምንኛ
ጉንፋን ይዝጋልኛ
የሰቆጣን ልጆች የቂጣ ደመኛ"

የካህናት ወረብ ሲጠናቀቅና ታቦታቱ ጉዞ ሲጀምሩም ሴቶችም ዜማቸውን በመቀየር የመንገድ ዜማ እያዜሙ ይጓዛሉ፡፡ ታቦቱ ከሚገባበት ቤተክርስቲያን ገብቶ ወደ መንበሩ የመግባቱ ምልክት የሆነው ደወል በሚደወልበት ወቅትም በሌላ ዜማ ይጫወታሉ፡፡

"በሕይወት ግባ በሕይወት
የአገራችን ታቦት" በማለት ዜማውን በመደጋገም እያዜሙ በእልልታ ያስተጋባሉ፡፡ ታቦቱ ከገባ በኋላም አቀንቃኟ እያወጣች ሌሎች እየተቀበሉ የሚከተለውን በመግጠም ይዘፍናሉ፡፡
              "ደህና እንገናኝ ላመት
              እንኳን ሰውና ወፍ አይሙት"
ሠናይ ጥምቀት!

በሔኖክ ያሬድ

 
< Prev   Next >