Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow እዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ደንበኛ...
እዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ደንበኛ... E-mail
Sunday, 28 September 2008

እዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ደንበኛ ንጉሥ አይደለም
በፍሥሐ ገብረ ኪዳን

የሪፖርተር ጋዜጣ ጋዜጠኞች በተለይም የዋና አዘጋጁ የአዲስ አበባ ላይ መያዝ ወደ ክልል ታስሮ መወሰድ እንዲሁም የቅድመ ክስና ያለክስ ፍርድ ቤት የማያስቀርብና የማይቆጣጠረውን "የእስራት ሳምንት በጎንደር" የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜናና መነጋጋሪያ ሆኖ ተከታትያለሁ፡፡ ጉዳዩን የተለየ የሚያደርገው ሰው በአጠቃላይ ጋዜጠኛም ቢሆን በተለይ እንዲህ ሲሆን የፕሬስ ነጻነት የግለሰብ የነጻነት መብት ይዞታ ለአደጋ ሲወድቅ "የመጀመሪያው" መሆኑ አይደለም፡፡ አሁን ከገበያ የጠፋው እሱም ከአገር የወጣው የጦማር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ክልል ተወስዶ መታሰሩ የአሜሪካ መንግሥት አቋም ርዕሰ አንቀጽ እስከመሆን ድረስ በእጅጉ የተዘገበና ከፍ ያለ ተቃውሞ ያስነሳ ጉዳይ ነበር፡፡

 

የሪፖርተርን ጉዳይ አዲስና ልዩ የሚያደርገው ተበደልኩ ባዩ የመንግሥትን የአገርን የወንጀል የፍትህ ሥርዓት መዘውር ማስነሳትና ማንቀሳቀስ የቻለው መንግሥት ወይም የመንግሥት የሥልጣን አካል ሳይሆን የግል ኩባንያ የግል የንግድ ድርጅት መሆኑ ነው፡፡ ጉዳዩንና ዝርዝሩን ከሪፖርተር ከራሱ አንብበናል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች (ከመንግሥት የአገር ውስጦች በስተቀር) ወቅታዊ ጉዳይ አድርገው በሰፊው ዘግበውታል፡፡ የኩባንያውን የራሱን ወገን ታሪክ ይህንን በስፋት ባስተናገደ አንድ ዌብ ሳይት አንብቤያለሁ ከአገር ውስጥ የመነጨ ድምጻቸውን አልሰማሁም እንጂ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ለቪኦኤ የአማርኛው ድምጽ የሰጡትን ምላሽም አድምጫለሁ፡፡ በኩባንያው በኩል ያለው እውነታ ምላሽና መከራከሪያ በአንጻራዊነት በሰፊው የተሸፈነው ከማንም በላይና ይበልጥ ኢትዮ ቻናል በተባለ ጋዜጣ ነው፡፡

ጋዜጣው በጳጉሜ 1 ቀን 2000 ዓ.ም እትሙ ኢንተርቪው ያደረጋቸው የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ስራ አስኪያጁ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ የሚፈረጁ ብዙ ነጥቦችን ባነሱበት በዚህ ቃለ ምልልስ ውስጥ ቅድሚያ ሰጥቸ ላንሳቸው የወደድኳቸው ጉዳዮችን ነው የዚህ ጽሁፍ መነሻ ያደረግሁት ከኢንተርቪው ይዘት እጀምራለሁ፡፡

ከጋዜጣው ጋር "አለመግባባት ውስጥ ልትገቡ የቻላችሁበት ምክንያት ምንድነው? አለመግባባቱስ መች ተጀመረ?" ብሎ ጠቀየ፡፡ ጥያቄው ራሱ በውስጡ የሚተናናቀው በውስጡ የሚታገለው የሆነ "የስጋ አውሬ" የዓላማ አድማና ሴራ ስለመኖሩ ለመጠርጠር፣ ከመጠርጠር በላይ ለማመን በቂ ምልክቶችና ምክንያቶች እዚያው የጳጉሜ 1 ቀን 2000 ዓ.ም "ኢትዮ ቻናል" ጋዜጣ እዚያው ቃለምልልሱ አምድ ውስጥ አሉ፡፡

የቢራ ፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥያቄዎቹን መመለስ የጀመሩት ከ"አለመግባባቱ" ምክንያት/ምክንያቶች አስቀድመው "አለመግባባት" መቼ ጀመረ? ከሚለው መነሳትን መርጠው ነው፡፡ ከዚያው መጀመር ይሻላል ብለው ነው፡፡ ግን ሁለቱም ወዲያው አንድ ላይ እየተደባለቁ ያስቸግሯቸዋል፡፡ የ"ታሪካዊ አለመግባበቱ"ን ታሪክና ምክንያት ወዲያውና በደፈናው፣ በአጭሩ ይቀጩና ወደ "አሁን በቅርቡ የተፈጠረውን"". በቀጥታ ይገባሉ፡፡ መልሱን ራሱን እንመልክተው፡፡ "ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር እንደ ፋብሪካ፣ እንደ ድርጅት አለመግባባት ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ሆኖታል፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ በተለያየ ጊዜ የፋብሪካውን ሥራ የሚያውኩና ችግር የሚፈጥሩ መረጃዎችን ሳያጣራ ፣ተብሏል፣ እያለ ሲያወጣ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከሪፖርተር ጋር ምንም ዓይነት የማስታወቂያ ግንኙነት አያደርግም" ይላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በቀጥታ "አሁን በቅርቡ ረወደሪ ተፈጠረው" አለመግባባት ይገባሉ፡፡ እዚያ ግንቦት እና ሐምሌ የሪፖርተር ሁለት ጋዜጦች ዝርዝር ውስጥ ገብተው ብዙ ይቆያሉ፡፡  

በዚህ መካከል ግን "ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር እንደ ፋብሪካ፣ እንደ ድርጅት አለመግባባት ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ሆኖታል" ተብሎ ኩባንያው "".እንደ ፋብሪካ እንደ ድርጅት" የኮርፖሬት ፖሊሲው አካልና እምነቱ አድርጎ የያዘውና ያነገበውን በምክንያትና ውጤት በሎጂክ ላይ መመሰረት የተሳነውን ተራ ክስና አሉባልታ አዝማች እያደረጉ ወጋቸውን አሳመርኩ መስሏቸው እዚያም እዚህም ጣል ጣል ማድረጋቸው አልቀረም፡፡
ለምሳሌ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ "ይህ የሚያሳየው ጋዜጣው በፋብሪካውና በማኔጅመንቱ ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ የማጥላላት ዘመቻ ለማድረግ ካለው ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ነው" ብለው ወደ "ታሪካዊው አለመግባባት" "ደም" ወደ ተቃባው የውጭ ግንኙነት ዘልለው የገቡት እያንዳንዱ የጋዜጣው በተለይም የመጨረሻው ዘገባ ላይ የተሰራው ጥፋት ምንጭ ያው የጋዜጣው ክፋት ነው ለማለት ነው፡፡ "የዳሽን ቢራ ፋብሪካ አመራር በሠራተኛ ማህበራት ተወቀሰ" የሚል ዘገባ ይዞ የወጣውና የሚያሳዝነው "የሚያሳዝነው ግን ዘገባውን መፃፍ ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያው ዘገባ ምክንያት "ጉዳዩ በሕግ በተያዘበት ሁኔታ ላይ መልስ አልሰጥም" እያልኩኝ ጋዜጣው ግን "የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በጉዳዩ ላይ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም በማለት ዘግቧል፡፡ ይህ የሚያሳየው ጋዜጣው በፋብሪካውና በማኔጅመንቱ ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ የማጥላላት ዘመቻ ለማድረግ ካለው ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ነው፡፡ ትክክለኛ ቢሆን ኖሮ ማለት የነበረበት ፣የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጣችሁ ተከሶ በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ መልስ አልሰጥም ብለዋል፣ ማለት ነበረበት" ያሉት በዚህ መካከል ነው፡፡

"እንደ ፋብሪካ እንደ ድርጅት"". ከጋዜጣው ጋር አለመግባባት ከተጀመረ በርካታ ዓመታት እንደሆነው "በዚህ የተነሳ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከሪፖርተር ጋር ምንም ዓይነት የማስታወቂያ ግንኙነት አያደርግም" ብለው ገና መጀመሪያና "ታሪካዊ" መግቢያቸው ላይ የገለጹት ሥራ አስኪያጅ ደሞ ሌላ ቦታ ላይ ብዙ ቆይተው እዚሁ ቃለምልልስ ውስጥ "ለምሳሌ የእኛ ድርጅት ምንም ዓይነት የማስታወቂያ ሥራ "ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር እንደማይሰራ ይታወቃል ይሄም ሊያስቆጣቸው ይችል ይሆናል፡፡ ይህንን የሚያውቅ ድርጅት ወይም ፕሬስ ነው፡፡ እኛን ሳይጠይቅ ያለመረጃ ስማችንን እያጠፋ ያለው"ም ብለዋል፡፡

"ይኸ ጉዳይ". ከሕግ አኳያ አያስኬድም". በዐቃቤ ሕግ የተያዘ ነገር ስለሆነ እኔ መልስ አልሰጥም"". ባሉት ጉዳይ ላይ ከዚያም በተጨማሪ ሌላ ጋዜጠኛ/ ዋናው አዘጋጅ ከአዲስ አበባ ተይዞ ታስሮ ወደ ጎንደር በተወሰደበት ጉዳይ ላይ ኢንተርቪው የሰጡት የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ "ጉዳዩ ግን ጋዜጠኛ እስከማሳሰር ይደርሳል ወይ? እንደ ፋብሪካ ሆናችሁ ስታዩት እንዲህ የመረረ ጉዳይ ነው?"". ተብለውም ተጠይቀው ነበር "እንደ ፋብሪካ ሆነን ስናየው" ብለው መልስ መስጠት የጀመሩት ሥራ አስኪያጁ "ይሄ በግልጽ ፋብሪካውን ከገበያ ለማስወጣት የፋብሪካውን ሥራ ለማወክ የተደረገ ነው እነዚህ የተባረሩ ሰራተኞች ፣ይህንን ፋብሪካ እናዘጋዋለን፣ እያሉ ሲፎክሩ ነበር፡፡ ይሄን ፉከራቸውን ነው በጋዜጣ ላይ ያወጡት፡፡ በእኔ ግምት ብዙ ጋዜጠኞችን ሳያነጋግሩ አይቀርም እሽ ብሏቸው ያወጣው ሪፖርተር ሊሆን ይችላል፡፡ (ሪፖርተር ጋዜጣ ብቻ ነው ማለት ነው) ብለዋል፡፡

የፋበሪካው ሥራ አስኪያጅ የበርካታ አመታት የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለውን የሚሉትን የቢራ ፋብሪካውንና የጋዜጣውን አለመግባባትና በቅራኔ የተወጠረ ግንኙነት ግን ብቻውን የድርጅቱ "ቻሌንጅ" አይደለም፡፡ የሠራተኛው ማህበር "ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ረከሰኔ 27ቀን 93 ዓ.ምሪ የወሰደው አቋም ከፋብሪካው ማኔጅመንት ሊሰራ እንደሚችል የሚያሳይ ነው" ብለውታል፡፡ ለፋብሪካው ማኔጅመንት ለ"ቀድሞው የፈረሰው የሰራተኛ ማህበር አለመግባባት መንስኤው ምንድነው ተብለው ሲጠየቁም "ለዚህ ትልቁን ሚና የተጫወቱት በእኛ አመለካከት "ኢሠማኮ እና የምግብና የመጠጥ". ሠራተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ብለዋል፡፡ የፌዴሬሽኑን የኮንፌዴሬሽኑን ቅኝት ሰራተኛ በአመጽ በሰልፍ ማኔጅመንትን የሚያወርድበትና የሚያወጣበት የሶሻሊስት ቅኝት ነው ሲሉም ወቅሰዋል፣ ከሰዋል፡፡

የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አምርረው የሚያዝኑበት በዚህ በፋብሪካቸው አማካኝነት የተጀመረው የ"ክስ" ሂደትና አካሄድ የመጨረሻውን ያሳየናል፣ ያሳየኛል የሚሉበት ሌላም "ጠላት" አለ፡፡ በእናንተና በሪፖርተር ጋዜጣ መካከል ያለው አለመግባባት ማቆሚያው ምንድነው ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ ይህንኑ የድርጅቱን "ኮርፖሬት ፖሊሲ" የሚያመለክት ነው፡፡ ጋዜጣው "አሁን የተከሰሰበት ክስ ውጤት ሲታወቅ መጨረሻውን ለማወቅ ይቻላል"". ብለው መልሳቸውን የጀመሩት ሥራ አስኪያጁ "ከዚህ ውጭ ረየጋዜጣውን ሥራ አስኪያጅሪ ስናየው የነጻ ፕሬስ ጥያቄ አድርጎ ሊወስደው አስቧል፡፡ ". የፕሬስ ነጻነት ገደብ የለውም እንዴ? እኔ በጣም ነው የማዝነው" በማለት ይቀጥላሉ፡፡ በጣም የማዝነው የሚሉትም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ "በተለይ ይሄ የፕሬስ ነጻነት የመጣው በከፍተኛ መስዋዕትነት ነው". ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡ ዛሬ ግን ይህ ነጻነት አለአግባብ እየዋለ ነው በግለሰብ ፐርሰናል ፍላጎት እየተመራ ነው፡፡ ለምሳሌ የእኛ ድርጅት ምንም አይነት የማስታወቂያ ሥራ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር እንደማይሰራ ይታወቃል ይህም ሊያስቆጣው ይችል ይሆናል"". በማለት ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ ሊሰጡ ከ"ቃለመሀላ" በመለስ ያረጋገጡትን ጉዳይ ዘንግተው ሌላ የምናልባት ጥርጣሬያቸውን እንደ ምሳሌ አድርገው ያስመዘግባሉ፡፡ "ይህንን የሚያውቅ ድርጅት ወይም ፕሬስ ነው እኛን ሳይጠይቅ ያለመረጃ ስማችንን እያጠፋ ያለው፡፡ እና ይሄ ብቻ አይደለም ሌሎችም ጋዜጦች ያንኑ የተሳሳተ ዘገባ ጽፈዋል፡፡ እስከመቸ ፕሬሱ እንደዚህ ይቀጥላል?". ሌሎችም ጋዜጦች ከአንድ ወገን ያገኙትን መረጃ ብቻ በመያዝ ተረባርበዋል፡፡ ችግሩ ምንድነው ብሎ የጠየቀን የፕሬስ አካል የለም፡፡ ይህ ችግር የሚያሳየው የሪፖርተርና የዳሽን ቢራ ውዝግብ የነጸው ፕሬስ የሥነ ምግባር ችግር እስካለ ድረስ የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ረየሪፖርተር ዋና አዘጋጅሪ ጉዳይ ቢያልቅ ነገ ሌላ ይመጣል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ጋዜጦች መብታቸውን እስከየት ድረስ መሆኑን አውቀው አስካልሰሩ ድረስ የሰውን ጆሮ የሚሰብ ወሬ ስለተገኘ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ በማቅረብ ሕብረተሰቡን ማደናገር አይገባቸውም፡፡ አሁን እየሆነ ያለው በዘመቻ መልክ የፋብሪካውን ስም ማጥፋት ነው" ይላሉ፡፡ ቋንቋው ጥቅሱ የሳቸው ነውና ስለሎጂኩ "ጥራት" ስለቋንቋው ሰዋሰው ይቅርታ፡፡

የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ በፖሊስ በ"ሕግ" ስለተያዘ መልስ አልሰጥበትም፡፡ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለሁም ባሉበት ጉዳይና አፍ ሰፊ መልስና ማብራሪያ ከሰጡበት ሌላ ጋዜጣ ካነበብኩት ውስጥ ሁለት ጉዳዮችን የሚመለከቱትን ከዚህ በላይ በሰፊው አቅርቤአለሁ፡፡ አንደኛው ጉዳይ የማስታወቂያ ነው፡፡ ሌላው የፕሬስ ነጻነት ጥያቄ ነው፡፡

የዳሽን ቢራ ፋብሪካ እና የሪፖርተር ጋዜጣ "አለመግባባት" በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የጫረው ስጋት አጀንዳ አድርጎ ያቀረበው ጉዳይ የፕሬስ ነጻነትን ብቻ የሚመለከት በፕሬስ ነጻነት ዙሪያ የተሰለፉ ሰዎችንና አካላትን ብቻ ያነጋገረ ብቻ አይደለም፡፡ "ፌዴራሊስቶች" የአሀዳዊት ኢትዮጵያን የትኛውንም ፍርድ ቤትና ፖሊስ ሥልጣን የሚወስነው ክስ የሚሰማበትን ቦታ የሚደነግገው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓትን ህግ እስከ አሁን አልተሻሻለም? ባይሻሻልስ? ብለው ጠይቀዋል፡፡ ሕንድ አገር በተካሄደውና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እጅግ በጣም ንቁና ትጉ ተሳታፊ ሆነው በተገኙበት ዓለማቀፋዊው የፌዴራሊዝም ስብሰባ ላይ የሚቀጥለው መደበኛ የዚህ ስብሰባ አስተናጋጅ አገር ኢትዮጵያ እንድትሆን መወሰኑን ሥራየ ብለው በአጀንዳቸው የመዘገቡት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሞያዎችና ጠበብቶች ጉዳዩን ሲሰሙ በእጅጉ ተገርመዋል፡፡ የሰራተኛ ማህበራት በዓለም ዙሪያ በአንድ ከ20 ሰራተኞች በላይ ባለው ድርጅት ውስጥ መቋቋም ስለሚችለው መሰረታዊ የሠራተኛ ማህበር "አንድ"ነትና "ብዙ"ነት በሰፊው አብራርተዋል፡፡ በዳሽን ቢራ ፋብሪካ አማካኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ አሰሪ ሥልጣን ለሠራተኛው ማህበር "እውቅና መስጠት ብቻ ነው" መባሉን ሲሰሙ እጅግ በጣም ስቀዋል፡፡ ጋዜጠኛውና የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ከአዲስ አበባ ጎንደር ተይዘው የተወሰዱት በዳሽን ቢራ ፋብሪካ መኪና ሾፌርና ውሎ አበል መሆኑን የሰሙ ይህንን "ከመሰረታዊው ጉዳይ ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም" እንዲሁም "ልክ እኔ የግሌን መኪና ልኬ እንዳስወሰደኩት ነው" የተዘገበው ብለው የተናገሩት የሥራ አስኪያጁን ምላሽ ያዳመጡ ከ"ብሩው ማስተሩ" የዋህነት ይልቅ የበርካታ የመሰረታዊ የመብት የነፃነት የአሰራር ጽንሰ ሀሳቦች እሴቶች ግንዛቤ ልክና መልክ በእጅጉ አሳስቧቸዋል፡፡ እኔ ራሴ ሲበዛ የተበሳጨሁበት ብቻየንም ያልሆንኩበት ጉዳይ አለ፡፡ ይህም በፕሬስ ነጻነት ብቻየንም ያልሆንኩበት ጉዳይ አለ፡፡ ይህም በፕሬስ ነጻነት በነጻነት መብት ላይ በግል አቤቱታ አቅራቢ መብት ዳር ድንበር በክልል ፍርድ ቤትና ፖሊስ ሥልጣን ላይ የተሰራውን ሥራ ያህል በሠራተኛ መብት የሥራ ሁኔታ የሰራተኛ ማህበር ላይ የተሰራውን ግፍን በደል ራሱ ሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ ብዙዎቹ የናቁትና ያገለሉት መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ብዙ የሚያነጋግሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱና ሌሎችም እዚህ ያልተጠቀሱት በርካታ ጉዳዮች ለብቻቸው ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚያወያዩ ናቸው፡፡ ከነዚህ መካከል የመረጥኩት ግን ከላይ እንደተገለጸው በማስታወቂያውና በፕሬስ ነጻነት ጉዳይ ላይ ነው፡፡

የአገራችን ያልተስተካከለና ያልታደሰ አበቃቀልና አካሄድ ሆኖ ነው እንጂ ይህም የአጠቃላይ የአገሪቷ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነጸብራቅ ሆኖ ነው እንጂ ማስታወቂያ ከዚህ "ጋዜጣ ጋር እንደማይሰራ ይታወቃል" የሚባል "ምንም አይነት የማስታወቂያ ግንኙነት አያደርግም" ተብሎ የሚማልበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ማስታወቂያ ለምሳሌ ለአንድ ፋብሪካ ያመረተው ምርት ሽያጭ አካል ነው፡፡ እጅግ በጣም ብዙ በጀት የሚመደብለት ወጪ ነው፡፡ በአገር ደረጃ የአገሪቷ ጠቅላላ ብሄራዊ ምርት (ጂ.ዲፒ) ውስጥ ይህን ያህል በመቶ ይወጣል እየተባለ መጠኑ የሚነገርለት የአገር ኢኮኖሚያዊ እድገትም የሚያመለክቱበት ነው፡፡ ከአንድ ፋብሪካ ወይም ኩባንያ ወይም ኢኮኖሚያዊ አሀድ አኳያ ታክስ ወይም ግብር ከሚከፈልበት ገቢ የማስታወቂያ ወጪ ተቀናሽ የሚሆነውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ይህን የመሰለ ታክስ ወይም ግብር የማይመለከተው በርካታ ወጪ የሚከሰከስበት የማስታወቂያ መድረክ ደግሞ የተለያየ ነው፡፡ ፌርማታ ጨምሮ በርካታ ዓይነት የቤት ውጪ (አውትዶር) መድረኮች አሉ፡፡ ሬዲዮ ቴሌቪዥን ሌላው ነው፡፡ ጋዜጣም አንደኛው ነው፡፡

ከዚህ አንጻር ማስታወቂያ ሰጭዎች ልክ እንደ አንባቢዎች የጋዜጣ ሸማቾች ደንበኞች (ኮንሲመርስ) ናቸው፡፡ አንባቢዎች የጋዜጣውን እትም ገዝተው ይዘቱን ያነባሉ፡፡ ገንዘብ የሚዲያውን "ሸቀጥ" ይገዛል፡፡ የሚዲያውን የይዘት አገልግሎት በማንበብ ለዚያ የተመደበ ጊዜ "ይባክናል"፡፡

አስተዋዋቂዎች (አድቨርታይዘርስ) እንደ አንባቢዎች የጋዜጣው ሸማቾች ናቸው የሚባለው ከዚያ በተለየ ምክንያትና ሁኔታ ነው፡፡ በተለምዶ አንድ አስተዋዋቂ ከኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የአየር ሰዓት ከህትመት ሚዲያ ደግሞ የጋዜጣ ገጽ ገዛ ይባላል፡፡ ይህ አባባል ግን ሲበዛ አሳሳች ነው፡፡ ከላይ ከላዩና በግልቡ ሲታይ አንድ አስተዋዋቂ (አድቨርታይዘር) ለማስታወቂያው የሚከፍለው ገንዘብ የሚተመነው በደቂቃዎች ብዛት በገጹ ስፋት ልክ ቢሆንም ከአንድ የቴሊቪዥን ጣቢያ 130 ሴኮንድ የአየር ሰዓት ከአንድ ጋዜጣ አንድ ገጽ የማስታወቂያ ቦታ ገዝቻለሁ ማለት ተመልካችን ወይም አንባቢን የእነሱንም ብዛት ከቁጥር ካላስገባ በስተቀር ይህ ትርጉም የሌለው እርምጃና ይልቁንም በጣም ደካማ የንግድ ሥራ ውሳኔ ነው፡፡ ስለዚህም አስተዋዋቂው (አድቨርታይዘሩ) "የሚገዛው" ተመልካችና አንባቢን ነው፡፡ አስተዋዋቂው የጋዜጣ ደንበኛ/ ሸማች የሚሆንበት ዋናው መልኩም ይኸው ነው፡፡

አንድ ኩባንያ የንግድ ሥራው፣ የሽያጩ ሥራ አካል አድርጎ በጋዜጣ ላይ የማስታወቂያ ወጪውን የሚከሰክሰው ከጋዜጣው ጋር "ለመተባበር" ከዚያ ጋዜጣ ጋር "ግንኙነት" ለመፍጠር ብሎ ሳይሆን ለራሱ ብሎ አንባቢው ውስጥ ለመግባት ሲል ስለመሆኑ ሌላ ምሳሌ ልጨምር፡፡ አንድ የቢራ ፋብሪካ ለምሳሌ የአገሪቱ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች በሙሉ በሚያነቡት የልጆች ጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ ላውጣ ቢል ይህ በእውቅት ላይ የተመሰረተ የጥሩ ማኔጅመንት ውሳኔ አይደለም፡፡ አይችልምም፡፡ የዚህ ምክንያት ተማሪዎቹ ከእድሜ አኳያ ቢራ የሚጠጡ የሸማች አቅም ያላቸው አይደሉምና፡፡ ከዚያም በላይ ክልክል ነው፡፡ ወንዶቹ ብቻ የሚያነቡት ጋዜጣ ላይ የጥፍር ቀለም ማስታወቂያ የአንባቢዎቹ ቁጥር በሚሊዮኖች ቢሆንም ይህም ያንኑ ያህል ከንቱ ውሳኔ ነው፡፡
ማስታወቂያ ሰጭ የጋዜጣ ደንበኞች ተገቢና በሳል የማኔጅመንት ፖሊሲ ላይ ተመስርተው የማስታወቂያው መድረክ ይመርጣሉ፡፡ የአንባቢዎች ብዛትና ባህርይ የጋዜጣው የስርጭት ስፋትና አድማስ መሰረታዊው ነው፡፡ ከዚያ ወጣ ባለ አሰራር እነዚህ ሁሉ ተሟልተው እዚህ ወይም እዚያ ገበያ አልመጣም አልወጣም ማለትም የምርጫ ጉዳይ ነው መብት ነው፡፡ በዚህ ላይ እቆጣለሁ ነገር አመጣለሁ የሚል ፕሬስ ካለ እሱ ከዚያኛው ኩባንያ በላይ ጅልና ቂል ነው፡፡

ከጅልነትና ከአላዋቂነት በላይ አልፎ ተርፎ "ምርጫው በአንድ የዴሞክራሲ ተቋም ላይ ያነጣጠረ ዩኒቨርሳል አደጋ የሚሆነው የምርጫው ምክንያት እንዴት ደንበኛ ንጉሥ አይደለም የሚል በዚህ ላይ ተመስርቶ የማስገደጃ የማስገበሪያ የማንበርከኪያ መሳሪያ ሲሆን ነው፡፡ ይህን ጊዜ ዘመናት ያስቆጠረው ዓለማቀፋዊ የነጻነት ተጋድሎ ከመንግሥታት እጅ ፈልቅቆ አውጥቶ ዋጋ ቢስ ያደረገውን በፈቃድ በግብር አምሳል የነበረውን ጉልበት ለግል "የራስ አምባዎች" መስጠት ይሆናል፡፡ የነጻ ፕሬስ የኮርፖሬት ፖሊሲ ሀሁ የማስታወቂያ "ደንበኛ ንጉሥ አይደለም" ነው እንደ ራስ ዳሽን ቢረዝም እንደ ዳሎል ቢያቃጥል እዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ደንበኛ በጭራሽ ንጉሥ አይደለም፡፡
 
ከዚህም የተነሳ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከዚህ ወይም ከዚያኛው ጋዜጣ ጋር የማስታወቂያ ሥራ አልሰራም የሚልበት ከዚህ ውጭ የሆነ ምክንያት መሰረት የሌለው ነው፡፡ ከሱ ጋር ማስታወቂያ አልሰራም የሚለው ጋዜጣ አንባቢዎች ብዛትና ባህርይ ከቢራ ፍጆታ አኳያ ትርጉም የሌለው ከሆነ ትክክል ነው መበቱ ብቻ ሳይሆን ተገቢ ምርጫ ነው፡፡

ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ የትኛውም ሚዲያ ጋዜጣን ጨምሮ እንደየትኛውም ኩባንያ ወይም እንደ ቢራ ፋብሪካው የቢዝነስ የንግድ ሥራ ገጽታ አለው፡፡ ይሸጣል ያስተዋውቃል፡፡ "የሚያስተዋውቀውና የሚሸጠው ጋዜጣውን ብቻ አይደለም፡፡ ሸማቾችም ጋዜጣውን ገዝተው ይዘቱን የሚያነቡት አንባቢዎች ብቻ አይደሉም፡፡ አንባቢዎቹ በኤዲተር ያሉ (በዜናው አምዶች ወዘተ) ጥራትና ብስለት ላይ የሚገነባ የስርጭቱም ብዛትና ስፋት በዚያው መሰረት ላይ የሚቆም ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ የአንድ ሚዲያ የፋይናንስ መሰረትና ምንጭ እንደ ሚዲያው ባህርይ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ የሪከርድ ኩባንያዎች (ካሴት ሲዲ አሳታሚዎች) ለፋይናንስ ምንጭ ሲዲውን ካሴቱን ገዝቶ የሚያየው የሚሰማው ሸማች ብቻ ነው፡፡ ማስታወቂያ የለበትም፡፡ ይህ አንደኛው ነው፡፡ ማስታወቂያዎች ብቻ የፋይናንሱ ምንጭ የሆኑም አሉ፡፡ ለቴሌቪዥንና ሬዲዮ አይከፍልም ወይም በጭራሽ የማይከፍልበት ቦታ አለ፡፡ ወጪያችንን የሚሸፍኑት አስተዋዋቂዎች ናቸው፡፡ ጋዜጦችና መጽሄቶች የፋይናንስ ምንጫቸው የሚያደርጉት ከአንባቢው እና ከአስተዋዋቂዎች ነው፡፡ የነዚህ ጋዜጦች ገቢ ግን በአዟሪዎች አማካኝነት በሚደረግ ሽያጭ ከደንበኞች በሚሰበሰብ ክፍያ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ማስታወቂያ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ነው ማስታወቂያ የሚወጣው ደግሞ የጋዜጣው አቋም "የመደብ ጀርባ" ተመርመሮ ሳይሆን የአንባቢውን ብዛት የስርጭቱን ስፋት ተከትሎና እሱኑ አሽትቶና መርጦ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የአንድ ጋዜጣ ሸማች አንባቢ ብቻ ሳይሆን አስተዋዋቂ የማስታወቂያ ሰጭ ጭምር ነው፡፡ ይበልጡኑም ማስታወቂያ ነው፡፡

እዚህ ላይ የሁለቱም ዓይነት ሸማቾች ጥያቄና ፍላጎት መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ አንደኛው ዓይነት ሸማችና ደንበኛ የአንባቢው መለኪያ በይዘቱ በኤዲተር ያለ በዜናው ጥራት ላይ የሚሽከረከር ነው፡፡ የሌላው የአስተዋዋቂው የምርጫ መለኪያ ደግሞ የገበያው መድራት መስፋትና መድመቅ ነው፡፡ የአንባቢው ብዛትና ባህርይ የስርጭቱ ስፋትና አድማስ ነው፡፡ ዋና ዋናዎቹና መሰረታውያኖኑ እነዚህ ናቸው፡፡

ከዚህ ውጭ አስተዋዋቂዎች ቢሉን የምንከፍለው፣ ወጪውን የምንሸፍነው፣ እኛ ስለሆንን በጋዜጣው ኤዲቶርያል ይዘትና በዜናው ምርጫና አቅጣጫ ላይ ተጽዕኖ የማድረግ "መብት" አለን ብለው የሚያንገራግሩ ለዚህም ከፍተኛ ጥራት የሚያደርጉ መኖራቸው እውነት ነው፡፡ በዓለም ደረጃም ብዙዎቹን ግራ ዘመም የሚባሉ ጋዜጦች ህልውና ያጠፋ ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በአገራችን ሁኔታ ከዚህም በበለጠና በከፋ በዘቀጠ ሁኔታ ይህ መርዘኛ አዝማሚያና የፕሬስ ነጻነት ፀር የሆነ አደጋ ከየአቅጣጨው መሞከሩ መቃጣቱ አልቀረም፡፡ አንዳንዶቹ ፕሬሶች የሽያጭ በተለይም የማስታወቂያ አቢይ ወይም ዋና ክፍላቸውን (ዲፓርትመንታቸውን) ከኤዲቶሪያሉ ጋር የማይተዋወቅና የማይገናኝ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ እንደዚያ ያለ ነገር እንጽፋለን እንጽፍላችኋለን ስለዚህ ማስታወቂያ ስጡን ወይም ማስታወቂያ ካልሰጣችሁን እንዲህ ብለን እንጽፋለን ብለው እንደራደር የሚሉ የሚያስፈራሩ ስለመኖራቸው መስማታችን አልቀረም፡፡

የዳሽን ቢራ ፋብሪካ አደባባይ ያወጣው ከዚህ በላይ መግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት "የኮርፖሬት አቋም" መታየት የሚገባው ከአንድ እውነተኛ ነጻ ፕሬስ የፖሊሲ አቋም አኳያ ነው፡፡ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ "ሪፖርተር ጋዜጣ በተለያየ ጊዜ የፋብሪካውን ሥራ የሚያውክና ችግር የሚፈጥሩ መረጃዎችን ሳያጣራ "ተብሏል" እያለ ሲያወጣ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከሪፖርተር ጋር ምንም አይነት የማስታወቂያ ግንኙነት አያደርግም" ሌላ ቦታ ደግሞ እንደ "ምሳሌ" አንስተው "የእኛ ድርጅት ምንም አይነት የማስታወቂያ ሥራ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር እንደማይሰራ ይታወቃል፡፡ ይህም ሊያስቆጣቸው ይችል ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የኋለኛው ተመሳሳይ አባባል ሪፖርተር የተቆጣው ማስታወቂያ ስለማይሰጠው ነው የሚል የሚመስል ሲሆን የመጀመሪያው ደግሞ አስቆጭው መጀመሪያ ሪፖርተር መሆኑን የሚናገር ይመስላል፡፡

እዚህ ላይ ተጋልጦ አደባባይ መውጣት የተገደደ አንድ ድንቁርና ግን አለ፡፡ ደንበኛ ሁሌም ንጉሥ ያልሆነበት ደንበኛ ሁሌም ትክክል ነው የማይባልበት ደንበኞችን ሁልጊዜምና መቼም ትክክል ነው የማይል አንድ ሥራ በዓለም ላይ ቢኖር ጋዜጠኛነት ነው፡፡ ማስታወቂያ የሚሰጠኝ "ደንበኛ"ዬ ላይ ዜና አልሰራም የምሰራው ዜናም "ደንበኛየን" ያስቆጣዋል፣ ደንበኛዬ ይቆጣኛል የሚል ጋዜጣ ነጻ ፕሬስነቱን እዚያው ላይ ያጣል ያበቃል፡፡ እንደዚያ ያለ ደንበኛው ሁሌም ትክክል ነው መስተንግዶ በነጻ ፕሬስ የሚጠብቅ አስተዋወቂም ያን ያህል ምናልባትም ከዚያ በላይ ነጋዴ ሳይሆን "ኪራይ ሰብሳቢ" ነው፡፡ 
 
< Prev   Next >