Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Tuesday
Dec 02nd
Home arrow Sections arrow የደኑ ሀብት ለግድቦች የውሀ ምንጭ ሆኗል
የደኑ ሀብት ለግድቦች የውሀ ምንጭ ሆኗል E-mail
Sunday, 28 September 2008

Imageበታደሰ ገ/ማርያም

በአዲስ አበባ ዙሪያ ኩታ ገጠም የሆኑና በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 19 ወረዳዎች ውስጥ ያለው የደን ሀብት ለገፈርሳ፣ ለለገዳዲና ለድሬ ግድቦች የውሀ ምንጭ በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አቶ ባቱ መስቀሉ ፊንፊኔ የደን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡


div align="justify">በእነዚሁ ወረዳዎች 12ዐ ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኘው ይኸው የደን ሀብት አዲስ አበባን ከከፍተኛ የጎርፍ አደጋ እንደታደገና ከጋራ እየታጠበ የሚመጣውን የአፈርን መሸርሸርና የግድቦችን በደለል የመሞላት መጠን መቀነሱን አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ሰበታና የሰንዳፋ ከተሞች ያልተበከለ አየር እንዲኖራቸው ማድረጉን፣ በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙና ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደሀ ሴቶች ቅጠላ ቅጠልና ጭራሮ በመልቀም ሕይወታችን እንዲመሩና ቤተሰቦቻቸውንም እንዲያስተዳድሩ ማድረጉንና ለዱር እንስሳትም በመጠለያነት ማገልገሉን ተናግረዋል፡፡

ልማቱን ዘለቄታዊ ጠቃሚነት እንዲኖረው ለማድረግ አስፈላጊው ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ፣ በዚህም የተነሳ ቀደም ባሉት ዓመታት በደኖቹ ውስጥ ኑሮአቸውን የመሠረቱት ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ የማዛወር ሥራ ለማከናወን እንደታቀደ፣ ለዚህም እውን መሆን ከደኑ መወጣት የሚችሉትንና የማይችሉትን የመለየት ሥራ በመከናወን ላይ እንዲሆን ከአቶ ባቱ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአፄ ዘርአያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የተቋቋመው የሰበታ ሱጳ (መናገሻ ሱጳ) ደን ልማት እስካሁን መብራት የሚያገኘው ከጄኔሬተር በሚመነጭ ኃይል መሆኑን፣ አሁን ግን ከሆለታ መስመር በመጥለፍ የ24 ሰዓት ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል በጀት የተያዘለት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚሁ ደን ልማት ውስጥ በሌላ ቦታ የሌሉ ሦስት ዓይነት የዱር እንስሳትና ብዛት ያላቸው አእዋፋት፣ ጥንታዊ ቤተ መንግሥትና ከ5ዐዐ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ዝግባ፣ ቀረሮ . . . እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በዚሁ የደን ልማት ውስጥ ለቱሪስት መስህብ የሚውል ሎጅ ለማሰራት ከአንድ የውጭ ባለሀብት ጋር ስምምነት መደረጉን፣ በስምምነቱም መሠረት ባለሀብቱ ኘሮጀክት ኘሮፖዛል አዘጋጅቶ ማቅረቡንና በኘሮፖዛሉ ላይም አስተያየት ታክሎበት የተመለሰለት መሆኑና በቅርብ ጊዜም ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ መጠበቁን አስታውቀዋል፡፡

"የሰበታ ሱጳ ደን ልማት በአፍሪካ የመጀመሪያው የደን ልማት ሥራ የተካሄደበት ሥፍራ ነው"  ያሉት አቶ ባቱ ይህም ሊታወቅ የቻለው የደን ልማቱ በአፄ ዘርዕያቆብ ዘመነ መንግሥት መቋቋሙንና በዚህም ወቅት ከአንኮበር ልዩ ልዩ ዓይነት የዛፍ ዘሮች እየተለቀሙ መጥተው ችግኝ ይፈላበት እንደነበር መረጃዎች መጠቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በጣሊያን ወረራ ወቅት በዚሁ የደን ልማት ለመጀመሪያ ጊዜ የእንጨት መሰንጠቂያ ፋብሪካ መቋቋሙን፣ አዲስ አበባና ቢሾፍቱ የሚገኙት ቤተመንግሥቶች በዚሁ ፋብሪካ ተሰንጥቀው በወጡ እንጨቶች መሠራታቸውን አመልክተዋል፡፡

ፊንፊኔ የደን ድርጅት በአዲስ አበባ የሚገኘውን ኢካፍኮ ፋብሪካን በ47 ሚሊዮን 150 ሺህ ብር ጨረታ አሸንፎ ከኘራይቬታይዜሽንና ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ መግዛቱን ሥራ አስኪያጁ ገልፀው ከዚህም ገንዘብ ውስጥ 3ዐ በመቶ ያህሉን ከፍሎ ቀሪውን ለመክፈል የንብረት ቆጠራ በመካሄድ ላይ መሆኑንና ቆጠራውም እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስ ተጠናቅቆና ቀሪው ክፍያ ተፈጽሞ ርክክብ የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

"የፋብሪካው" ሠራተኞች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?" ተብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሥራ አስኪያጁ ሲመልሱ "ፋብሪካው በአሁኑ ጊዜ ያቀፋቸውን 327 ቋሚ ሠራተኞችንና ማኔጅመንቱን እንደያዘ  ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ ይደረጋል፡፡ ድርጅቱ ደግሞ ጥሬ ሀብት በማቅረብና ምርቱ ገበያ እንዲያገኝ ለማድረግ የሚረዱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ተገቢውን ድጋፍ ያበረክታል" ብለዋል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን የፋብሪካውን አወቃቀር አፍርሶ ከድርጅቱ ጋር የመቀላቀል እቅድም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው አቶ ባቱ ጠቁመው ፋብሪካው ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮም ቢሆን የሚያስፈልገውን ጥሬ ሀብት መቶ በመቶ እየገዛ ሲጠቀም የቆየው ከድርጅቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ድርጅቱ ፋብሪካውን በመግዛቱ ሠራተኛው ከመበተን እንደዳነ፣ ጥሬ እቃም ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ከድርጅቱና በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ሌሎች መሰል የደን ልማት ድርጅቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያገኝ የማድረግ አጋጣማዎች እንደፈጠረላትም ተናግረዋል፡፡
Last Updated ( Sunday, 28 September 2008 )
 
< Prev   Next >