| ደንብ ማስከበር አወቃቀር የአደረጃጀትና... |
|
| Sunday, 28 September 2008 | |
|
ደንብ ማስከበር አወቃቀር የአደረጃጀትና የአሠራር ችግሮች አሉበት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙት እነዚሁ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዳመለከቱት በከተማ ተዘውትረው ከሚታዩ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች መካከል የሺሻና የጫት በቶች፣ የጎዳና ንግድ፣ የቆሻሻ አወጋገድና በአጠቃላይ የንጽህና አጠባበቅ የመሳሰሉ ይገኙባቸዋል፡፡ "ከእነዚህም መካከል ሺሻና ጫት ቤቶች የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነውን ወጣቱን ትውልድ ክፉኛ እየተፈታተኑትና ዓላማውንም እንዲያስተጓጉል እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ በእነዚህም ንግዶች ላይ የሚካሄደው ቁጥጥርና ክትትል ልል በመሆኑ የተነሳ በትምህርት ተቋማት ዙሪያ እንደ አሸን ፈልተዋል" ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ተማሪዎች በልዩ ልዩ ምክንያት ከክፍል እየወጡ ጫት በመቃምና ሺሻ በመሳብ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ይህም ሁኔታ በፈተና ውጤቶቻቸው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ የመንገድ ላይ ጎዳናም ለከተማው ፅዳት መጓደል መንስዔ ከመሆኑም ሌላ ግብር እየከፈለ የሚንቀሳቀሰውን ሕጋዊ ነጋዴ ክፉኛ እንደተፈታተነው አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተው የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሁኔታዎችን የማስተካከል ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 11/12 የሚገኙ አቶ ጌታቸው አበበ "ሕገ ወጥ እንቅስቃሴን የመግታት ኃላፊነት በአንድ መንግሥታዊ ተቋም ላይ ብቻ መጣል የለበትም፡፡ ሕብረተሰቡ በዚህ በኩል የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡" ብለዋል፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 16/17 18 ነዋሪ የሆነችው ወይዘሪት አዜብ ታዬ "ሕገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመግታት በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ ወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም እወን መሆን የቤተሰብ እገዛና ትብብር ያስፈልጋል" በማለት ገልፃለች፡፡ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው የደንብ ማስከበር ዓላማውን ለማሳካት በሚያስችል ደረጃ (ስታተስ) አለመቋቋሙ አንደኛውና ዋናው ችግር ሲሆን ከተደራጀበት ከ1995 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መዋቅሩ ተመልሶ አለመታየቱን ገልፀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የአደረጃጀትና የአሠራር ችግሮች እንደተንሰራፋበት፣ ይህም በመሆኑ ለአንድ ክፍለ ከተማ የተፈቀደ የጤና ተቆጣጣሪ የሰው ኃይል ብዛት ከሦስት ሰዎች በላይ እንደማይበልጥ፣ በአሁኑ ወቅት ይህም ተሟልቶ የማይገኙባቸው ክፍለ ከተሞች እንዳሉ በዚህ ዓይነቱ አነስተኛ የሰው ኃይል የቁጥጥር ሥራውን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስቸግር አስረድተዋል፡፡ "ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ለመከላከል ሙሉ ጊዜን ሰውቶ መሥራት ግድ ይላል" ያሉት አቶ ሲሳይ የደንብ ማስከበር መዋቅር የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ በመሆኑ በሲቪል፣ ሰርቪሱ ሕግ እንደሚተዳደር፣ ከዚህም ተነስቶ የሚሠራበት የሥራ ሰዓት እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የተገደበለትን ሰዓት በመጠቀም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴው በስፋት ጎልቶ የሚታየው ደግሞ ከሥራ ሰዓት ውጭ መሆኑን፣ በእነዚህም ሰዓታት ደንብ አስከባሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድዳቸው ሕግ የሌለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አልፎ አልፎ በመስማማትና በመግባባት መንፈስ የተኬደባቸው ሂደቶች መኖራቸውንና ነገር ግን ሁል ጊዜ በዚህ መልኩ ማሰራት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሲሳይ እንዳብራሩት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ደንብ አስከባሪዎች ከሥራ ሰዓት ውጪ ሊሠሩ የሚችሉበት ስልት ሊኖር ይገባል፡፡ ለዚህም እውን መሆን ሁለት አማራጮች ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ መልስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ አንደኛው በትርፍ ሰዓት ክፍያ መጠቀም ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በፈረቃ የአሠራር ሥርዓት መጠቀም ነው፡፡ በፈረቃ ለመሥራት ግን የሰው ኃይል ብዛቱ ከፍ ማለት ይኖርበታል፡፡ የጎዳና ላይ ንግድን ለመግታት እስካሁን የወጡ ደንቦችና መመሪያዎች በቂ አለመሆናቸውን ይህም በቁጥጥሩ ሥራ ላይ ክፍተት መፍጠሩን አቶ ሲሳይ ጠቁመው እንደአማራጭ ከቀረበው መፍትሄ ባሻገርም የአዲስ አበባ አስተዳደር የጀመረው መሠረታዊ የአሠራር ለውጥ ኘሮግራም ተግባራዊ ሲሆን የደንብ ማስከበርን ችገር ሊፈታ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ በየደረጃው የቀረቡት አማራጮች እና ጥናቶች ተጠናቅቀው በሥራ ላይ እስከሚውሉ ድረስ የተከሰቱትን ችግሮች ለመቅረፍ ከተማ አቀፍ የሆነ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ላይ የሚሠራ የደንብ ማስከበር ግብረ ኃይል መቋቋሙን ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመው ግብረ ኃይሉም ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስ፣ ከአቃቤ ሕግ፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ የተውጣጡ ባለሙያዎችን ማቀፉን አስታውቀዋል፡፡ "ይህ ግብር ኃይል እስከ ቀበሌ ድረስ የተዋቀረ ሲሆን ብቻውን ግን ምንም ዓይነት መፍትሔ ያመጣል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በሕብረተሰቡ ሲታገዝ መሆኑን በመረዳት ሕብረተሰቡ የሚሳተፍበት ሥርዓት ቢመጠናት ላይ ነው" ሲሉ ገልፀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |