| "ቄራዎች ድርጅት የሚጥለው አጥንትና... |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
"ቄራዎች ድርጅት የሚጥለው አጥንትና የሚለቀው ፍሳሽ ሽታ ለበሽታ እየዳረገን ነው"የካራ አካባቢ ነዋሪዎች "ስለተጣለው አጥንትም ይሁን ስለተለቀቀው ፍሳሽ እኔን አይመለከተኝም" ቄራዎች ድርጅት በታምሩ ጽጌ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 28 ቀበሌ 03 በተለምዶ ካራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ያለው የአዲስ አበባ ካራዎች ድርጅት፣ ከብቶችን ካረደ በኋላ የሚጥለው አጥንትና የሚለቀው ፍሳሽ ሽታ ለተለያየ በሽታ እየዳረጋቸው መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ ስለተጣለው አጥንትም ሆነ ስለሚደፋው ፍሳሽ እንደማይመለከተው ድርጅቱ ተናግሯል፡፡ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለረጅም ዓመታት ዙሪያውን አጥሮ በይዞታነት በያዘው ቅጥር ግቢ ውስጥ ከብቶችን አርዶ ሲያበቃ አጥንትና ፍሳሽ በአካባቢው ስለሚጥል ሽታው በአካባቢ ሊያስደርስ እንደማይችል ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ በአካባቢው የተቆለለው አጥንት በዝናብ ሲደበደብ ቆይቶ ፀሐይ ሲሞቀው የሚወጣው እንፋሎት ለጉንፋን፣ ለአስምና ለተለያየ የጉሮሮና የውስጥ ደዌ ታማሚ እንዳደረጋቸው ተናግረው፣ በተለይ ሕፃናት ሲወለዱ ወላጆች አካባቢውን በመልቀቅ ወደሌላ አካባቢ በመሄድ ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩ ገልፀዋል፡፡ "የተናገርነው የተጋነነ እንዳይመስል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቅርብ እርቀት ሆኖ እየደረሰብን ያለውን ችግር ሊመለከት ይችላል" የሚሉት ነዋሪዎቹ የአጥንቱ፣ የቁርጥራጭ ስጋ ብስባሽ ሽታ ሳያንሳቸው፣ የሚለቀቀው ፍሳሽ መድረሻ እንዳሳጣቸው ተናግረዋል፡፡ በአብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ የሥጋ ቦታ እንደሆነ በሚነገረው ካራ አካባቢ ዳገታማ ቦታ ላይ የተሰራው የከብት ማረጃ (ቄራ) ፍሳሽ ሲለቀቅ በቀጥታ ወደ መኖሪያ ሰፈር እንደሚገባ የገለፁት ነዋሪዎቹ፣ ችግራቸውን የሚመለከተው አካል ተመልክቶ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል፡፡ ስለተጣለውም አጥንት ይሁን ሰለተለቀቀው ፍሳሽ እንደማይመለከተው፣ በተባለው ቦታ እርድ እንደማያከናውንና የተባለው ሁሉ ሀሰት መሆኑን የገለፁት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳምጤ አበበ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ዳምጤ ገለፃ፣ በካራ አካባቢ ታጠረ የተባለው ቦታ፣ እንስሳትን የሚያርዱበት ሳይሆን፣ ከተለያዩ ቦታ ተነድተው የሚመጡ እንስሳትን (ወደ ቄራ የሚመጡትን) በመኪና ጭኖ ለማምጣት የሚጠቀሙበት የማቆያ ቦታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንስሳቱ ወደ መኪና ላይ ሲጫኑ እንዳይደነብሩና ችግር እንዳይፈጥሩ በታጠረው ግቢ ውስጥ በማስገባት ጭነው እንደሚወስዱ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ በአካባቢው የሚኖሩ ህገወጦች ሠራተኞቻቸውን እየተተናኮሉ በማስቸገራቸው ላለፉት በርካታ ዓመታት ማቆማቸውን ገልፀዋል፡፡ በከተማው ውስጥ እንስሳትን ለማጓጓዝ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ በትራንስፖርት ለማጓጓዝ በማሰብ ማንንም ሳይጠይቁና ሳያስፈቅዱ ቦታውን በማጠር ይጠቀሙበት እንደነበር የገለፁት አቶ ዳምጤ፣ እንደይዞታ እንደማይቆጠር ቦታው በህጋዊ ደረጃ እንዳልተሰጣቸውና የህብረተሰቡም ሮሮ እንደማይመለከታቸው ተናግረው ምናልባት "ህገወጥ አራጆች" ካሉ "እነሱን" መጠየቅ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 02 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |