| አሹራ - 2000 |
|
|
| Sunday, 20 January 2008 | |
|
የአሹራ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ባለፈው ዓርብ ጥር 9 ቀን 2000 ዓ.ም ተከብሯል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ፣ ከዐውደ ሺሕ ጋር ተያይዞ በመጀመሪያው መስጊድና በትግራይ ውቅሮ አካባቢ በሚገኘው ነጃሺ በብሔራዊ ደረጃ ለመከበር ችሏል፡፡ አሹራ በዓመተ ሒጅራ አቆጣጠር የመጀመሪያው የሙሀረም ወር በገባ በአሥረኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካርያ እንደሚገልጹት የበዓሉ አመጣጥ ከእስልምና በፊት የነበረና አይሁዳውያን (እስራኤላውያን) ያከብሩት ነበር፡፡ አሹራ ከ10 ቁጥር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የእስልምና ወር ሙሐረምን ይዞ በዐሥረኛው ቀን የሚከበር ነው፡፡ አሸራ ከሚለው ሥርወ ቃል የመጣ ነው አሹራ፡፡ አመጣጡ እንደሚባለው አይሁዶቹ በአሹራ ቀን /በዓለ ስርየት/ ይጸልያሉ፣ ይጾማሉ፡፡ መነሻው ከሃይማኖትና ከታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከነቢያት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የነርሱን ተአምራትን የሚያስታውስ ነው፡፡ የአብርሃም ከእሳት መዳን፣ የኖኅ ከጥፋት ውሃ መዳን፣ የሙሴ ባሕርን ማቋረጥ ታሪኩን ለማስታወስና ጥሩ መንገድን ለመከተል ይጾማሉ፡፡ ሌላው የቀኑ መነሻ ከነቢዩ በኋላ በአሊ ሰይድ ጊዜ በነበረው የፖለቲካ ችግር በጦርነት ምክንያት በአሹራ ቀን የአሊ ልጅ ሁሴን የተሰዋበት ቀን በመሆኑ፣ ሺአቶች ዕለቱን በሐዘን ያስቡታል፡፡ እንደ አቶ አሕመድ ማብራሪያ አሹራ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በእምነቱ ተከታዮች ይከበራል፣ ይዘከራል ማስታወሻነቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ሐረር ውስጥ የተለየ ድርጊት ይፈጸምበታል፡፡ በአሹራ ቀን ሦስት ድርጊቶች ይፈጸሙበታል፡፡ አንደኛው ኅብረተሰቡ በሙሉ ገንፎ ይበላል፡፡ የሚበላበት ምክንያትም የነቢዩ ኖኅን ታሪክ በማስታወስ ነው፡፡ ከጥፋት ውኃ በኋላ መሬት ላይ አርፈው ከመርከብ ሲወርዱ የነበራቸውን እህል አሰባስበው ገንፎ አገንፍተው የተቋደሱበት ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ይህ የገንፎ ባህል ቱርክ ውስጥም ይከበራል፡፡ ሁሉም ሰው በዕለቱ ጠግቦ ማደር አለበት ካልጠገበ ዓመቱን ሙሉ ይራባል ተብሎ ይገመታል፡፡ ሁለተኛውና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጅብ ገንፎ ይበላል መነሻ ታሪክ አለው፡፡ የተፈጥሮ ሚዛን ይዛባና ረሀብ ይገባል፡፡ በዘመነ ግራኝ አሕመድ በተከሰተ ረሀብ ምክንያት ጅብ ይተናኮላል፡፡ አንድ ሰው በሕልሙ ጅብን ገንፎ ማብላት መፍትሔ መሆኑን ያልማል፡፡ ሰዎችን አሳምኖ ለጅብ ገንፎ ያቀርብለታል፡፡ በጅብ ገንፎ አበላል ሥርዓት የዓመቱን ሁኔታ አቅጣጫዎች ሊያዩለት ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ጥሩ የሚባለው ዓመት ጅቦቹ በልተው ሲያስተርፉ ነው ይላሉ፡፡ የአሹራ በዓል ማብሰር የሚጀመረው የቁርአን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከየቤታቸውና ጎረቤታቸው ቅል መሰብሰብ በሚጀምሩበት ዋናው በዓል ከሚከበርበት ቀን አንድ ሳምንት በፊት ነው፡፡ የሰበሰቡትን ቅል በየትምህርት ቤታቸው ያከማቻሉ፡፡ ለበዓሉ አንድ ቀን ሲቀረውም የከተማው ሕዝብ በተከታታይ የወሩን ዘጠነኛና አስረኛ ቀናት ይጾማሉ፡፡ በአስረኛው ቀን ከአስር ሰዓት በኋላ የቅል ሰበራው በየትምህርት ቤቱ ይጀመራል፡፡ ከቅል ሰበራው ጋር ተያይዞ የሚዘምሩት አለ፡፡ የጭፈራ ዜማውን ጠንካራ ዱላ በማንገብ የሚከተለውን ያዜማሉ፡፡ በማለት ደማቅ እንቅስቃሴ የበዛበት ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡ ቅሉም ሲወረወርላቸው ተሽቀዳድሞ ለመስበር ሁሉም ይጥራሉ፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ የግጥሙን ይዘት እንደሚከተለው ያብራራሉ፡፡ በዝማሬው የቀኑን ሁኔታ ይገልፃሉ፣ መጥፎ ነገር ያወግዛሉ፡፡ አዲሱ ዓመት የደግና የሰላም እንዲሆን ይመኛሉ፡፡ በማጣቀሻ መልክ የከርበላውን ጦርነት በመጥቀስ የነቢዩ መሐመድ የልጅ ልጆችን ሐሰንና ሁሴንን ያስታውሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ይከበራል፡፡ በዓሉ ከአረፋ በዓል በኋላ የሚከበር በመሆኑ መልካም ምኞትን ያሳያል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ (በትግራይ በወሎና በጎንደር) አሕመድ ነጋሽ (ነጃሺ) የነቢዩ መሐመድ ቤተሰቦችን ተቀብለው ከማስተናገዳቸው፣ ከአደጋ ከመከላከላቸውና ታላቅ መሪ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ይከበራል፡፡ በተለይም እንደዛሬው የአውሮፕላን አገልግሎት ባልነበረበት ዘመን የሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከሐጅ ሲመለሱ ነጃሺ መስጊድ ተገናኝተው ጸሎት ያደርሱ እንደነበር የገለጹት አቶ አሕመድ በአሁኑ ጊዜም ልማዱ ቀጥሎ ወደ ሐጂ ያልሄዱ የወሎ፣ የትግራይ አልፎ አልፎ ይሁን እንጂ የጎንደር የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደዚያው በመሔድ የአሹራን በዓል እንደሚያከብሩ ካነጋገሯቸው የአካባቢው ተወላጅ ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ አሕመድ ዘካርያ እምነት የአሹራን በዓል በዩኔስኮ የረቂቅ ባህላዊ መዝገብ (ኢንታንጅብል ሔሪቴጅ) ውስጥ እንዲመዘገብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ የነቢያትን ታሪክ መዘከሪያ በመሆኑ ዓለምአቀፍ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባው ሲሆን ትልልቆቹ ሦስት ሃይማኖቶች (አይሁድ፣ ክርስትናና እስልምና) የሚያከብሯቸውን ነቢያት ማስታወስ ነው፡፡ የጅብ ገንፎ ሥርዓት ከተፈጥሮ ክስተት ጋር ያለንን ዝምድና የምናጠናበት ሁኔታ መሆኑ፣ ከቅል ሰበራው ጋር ያለው ክንውንም ከረቂቅ ቃላዊ ቅርስ አኳያ ማስመዝገቡ ሊተኮርበት የሚገባ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ቅል ሰበራ ከመጠጥ ጎጂነት አኳያ የሚታሰብ መሆኑ የመጠጥ መያዣው ቅል መሰበሩ የመጠጥን አስከፊነት የሚያመላክት ነው፡፡ መጠጥ ኅብረተሰብን ከሚጎዱ ሱሶች አንዱና ለተለያየ የጤና መታወክና ለሞት የሚዳርግ መሆኑን ብዙ ጥናቶች እንደሚያስረዱ ያወሱት አቶ አሕመድ በተባበሩት መንግሥታት ሲጃራን ያለማጨስ ቀን፣ የውሃ ቀን፣ በረሃነትን የመከላከል ቀን፣ የፖሊዮ ማስወገጃ ቀን ወዘተ እንደሚባለው ከሐረር አሹራ ልምድ በመነሳት የመጠጥን ጉዳት የማውገዣ ቀን በአሹራ ቀን ቢከበር መልካም እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ በሔኖክ ያሬድ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |