| በየወረዳው የተመለመሉ ሠራተኞች... |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
|
በየወረዳው የተመለመሉ ሠራተኞች የዩኒቨርስቲ መምህራን ሆኑ
በኃይሌ ሙሉ በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የክልል ወረዳዎች በመንግሥት ሠራተኝነት ሲያገለግሉ የነበሩ የዲግሪ ምሩቃን የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሆነው ተመደቡ፡፡ ከክልልና ከትምህርት ሚኒስቴር ካገኘናቸው ምንጮች ለመረዳት እንደቻልነው ትምህርት ሚኒስቴር ውጤታቸው ከ2.75 በላይ የሆነ የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ተመርጠው እንዲላኩለት ጠይቆ ለክልሎች በፃፈው ደብዳቤ መሠረት ክልሎች በየወረዳው የሚገኙ የመጀመሪያ የዲግሪ ምሩቅ የመንግሥት ሠራተኞችን መርጠው ልከዋል፡፡ በክልሎች የተመረጡት የመንግሥት ሠራተኞችም በቀጥታ በመምህርነት እንዲያገለግሉ በየዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል፡፡ ምንጮቻችን እንደገለጹት ከየወረዳው የተመለመሉት የመንግሥት ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ ለትምህርት ሚኒስቴር በተላከበት ወቅት በወረዳው ያከናወኑትን ሥራ የሚገልጽ ማስረጃ አብሮ ተያይዟል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ከ1500 የማያንሱ የዩነቨርሲቲ ምሩቃንን በረዳት መምህርነት የመደበ ሲሆን በየወረዳው የተመለመሉት ደግሞ ተጨማሪዎች ናቸው፡፡ ከየወረዳው ተመልምለው በየዩኒቨርሲቲው የተመደቡት የሐረማያ፣ የጅማ እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ መምህራን እንደገለጹልን በዘንድሮው ዓመት የሚያስተምሩት ኮርስ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዩነቨርሲቲው የሚያስተምሩት በርካታ መምህራን የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ብቻ መሆኑ በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረ ይገልፃል፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጸው እርሱ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በነበረበት ወቅት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የነበረ አንድ ጓደኛው ከተመረቀ በኋላ መምህሩ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከፍተኛ ውጤት ከማስመዝገቡ ውጭ ከእሱ ብዙም የማይበልጠው ይህ ጓደኛው መምህር መሆኑን መቀበል እንዳስቸገረውና ትምህርቱንም መከታተል ባለመቻሉ ውጤቱ እንደተበላሸበት ይሄው ተማሪ ያብራራል፡፡ የጐንደር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የቢዝነስ ማኔጅመንት ተማሪ በበኩሉ በዋና መምህርነት የሚያገለግሉ በርካታ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን በጐንደር ዩኒቨርሲቲ እንደሚገኙ ጠቁሞ መምህራኑ በሙያው የጠለቀ ሙያ ሊኖራቸው ይቅርና እንግሊዝኛ ቋንቋ በደንብ መናገር የማይችሉ በመሆኑ በመማር ማስተማር ሂደቱ ትልቅ ችግር መፍጠሩን ተናግሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ባለው የመምህራን ምደባ በተመለከተ ያነጋገርናቸው ፕሮፌሰር በየነ ቀደም ሲል በነበረው ስርዓት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂ ተማሪዎች ረዳት ምሩቅ ተብለው የሚቀጠሩበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸው አሁንም ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን የሚቀጥረው ተመሳሳይ አርዕስት ሰጥቶ ከሆነ ብዙም እንደማያስገርም ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር እንደገለጹት ችግሩ የሚመጣው በረዳት መምህራኑ የሚከናወነው ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ እርሳቸው ባለፉበትና ሲሰሩበት በነበረው የትምህርት ስርዓት የረዳት ምሩቃን ተግባር ከፍተኛ መምህራንን ማገዝ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር በየነ ምሩቃን በላብራቶሪ ውስጥ ተማሪውን በማሰራት፣ ፈተና በማረምና የትምህርት ድጋፍ (ቱቶሪያል) በመስጠት ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል እንዲያገለግሉ ከተደረገ በኋላ ተጨማሪ የትምህርት እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ረዳት ምሩቃን ኮርስ ይዘው እንዲያስተምሩ የሚደረጉት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ በተለያየ ምክንያት የድህረ ምረቃ ሳያገኙ የቆዩ ወደ ምርምር ገብተው ብዙ ልምድ ያካበቱ የምርምር ውጤቶችን ያሳተሙ ረዳት ምሩቃን በአካዳሚክ ኮሚሽን ውሳኔ ወደ ሌክቸረርነት እንዲያድጉ ይደረግ ነበር፡፡ አሁን ባለው የትምህርት ስርዓት ግን የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ረዳት ምሩቃን ለዲግሪ ተመራቂዎች የሚያስተምሩበት ሁኔታ መፈጠሩን የገለጹት ፕሮፌሰሩ ይህ አሰራር ህብረተሰቡን እንደካንሰር የሚያጠቃ፣ ብቃት የሚያሳጣ ትልቅ አደጋ በመሆኑ ፓርቲያቸው ግድፈቶችን አጉልቶ በማሳየት እርምት እንዲደረግባቸው እና ሁኔታው ስርዓት እንዲይዝ የሚታገል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ "ከሁሉም በላይ ወሳኙ የሰው ሀይል ነው፡፡ የሰው ሀይል ሳይኖር ምንም ግንብ ቢገነባ፣ ኮምፒዩተር ቢደረደር የሰውን ሀይል ሊተካ አይችልም (በመምህራን ምደባ ዙሪያ) ኃላፊነት መጓደልን አይቻለሁ" ብለዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጡ "ኢሕአዴግ ከጥራት ይልቅ በስታስቲክስ ላይ አጥብቆ የሚሰራ ይመስላል" ብለዋል፡፡ አረፍተ ነገርን አስተካክለው መፃፍ የማይችሉ ተማሪዎችን የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ማድረግ ለአገርም የማይጠቅም መሆኑን አስተያየት ተሰጥቶበት እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር መረራ መንግሥት ግን ከባለሙያዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ባለመቀበል የዩነቨርሲቲ ተማሪዎችን በሶስት ዓመት ሲያስመርቅ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በየዩኒቨርሲቲው የሚመደቡ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቅ መምህራንም ከዚህ ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም "ብዙ ነገሮች ስታስቲክስን መሰረት ያደረጉ ነገር ግን በጥናት ያልተመሰረቱ ናቸው" ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የትምህርት ሚኒስቴር የውጭና የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል ግን በየዩኒቨርሲቲው የተመደቡት ረዳት ምሩቅ መምህራን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቁመው እነዚህ መምህራን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ስልጠና እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ስልጠና ከመውሰዳቸው በፊት ግን ረዳት መምህር ሆነው እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ደሳለኝ ይህንን ይበሉ እንጂ ቀደም ባሉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ረዳት ምሩቃኑ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ትምህርት ሳይሰጣቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም ተጨባጭ ማስረጃ እንዳለን በመግለጽ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡፡ "ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ኮርስ እንዲሰጡ በዋና መምህርነት የተመደቡ ጥቂት መምህራን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነሱም ቢሆኑ በስነ ማስተማር ዘዴ የሁለት ወር ስልጠና ተሰጥቷቸዋል" ብለዋል፡፡ በትምህርት አማካኝነት ሚኒስቴር በየዩኒቨርሲቲው የተመደቡት ረዳት ምሩቃን የተመረጡት በውጤታቸው ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲዎቹ ባወጧቸው የተለያዩ መመዘኛዎች ጭምር መሆኑን አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡ ይህ መመዘኛ ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |