| እንዲጣራ የታዘዘው የፌዴራል ዋና... |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
እንዲጣራ የታዘዘው የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት ማክሰኞ ይቀርባልበፍሬው አበበ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መንግሥት ከመበደሪያ ጣሪያ በላይ ብድር ወስዷል በሚል በሰኔ ወር ያቀረበውን ሪፖርት ትክክለኛነት እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ሪፖርቱን የፊታችን ማክሰኞ ለፓርላማው ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች አመለከቱ፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሰኔ 17 ቀን 2000 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት መንግስት ሊሸጥ የሚችለው የግምጃ ቤት ሰነድ ባለፉት ሶስት ተከታታይ የበጀት ዓመታት ውስጥ ከተሰበሰበው አማካይ የመንግሥት መደበኛ ገቢ ከ25 በመቶ፣ የቀጥታ ብድር ደግሞ ከ15 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት መደንገጉን ጠቅሷል፡፡ በዚሁ መሠረት በ1995፣ በ1996 እና በ1997 በጀት ዓመታት በድምሩ 3 ቢሊዮን 295 ሚሊዮን 400ሺህ ብር መንግሥት በአዋጅ ከተፈቀደለት በላይ ተበድሯል ሲል ለፓርላማው ገልጿል፡፡ አያይዞም በ1998 ዓ.ም የበጀት ዓመት ላይ የአገር ውስጥ ብድር ለመበደር የፀደቀው በጀት 4 ቢሊዮን 207 ሚሊዮን ቢሆንም በበጀት ዓመቱ ከግምጃ ቤት ሰነድና ከቀጥታ ብድር ብቻ 7 ቢሊዮን 442 ሚሊዮን ተበድሮ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው መንግሥት የአገር ውስጥ ብድር፣ የገንዘብና የባንክ አዋጅንም ሆነ የበጀት አዋጁን ሳይከተል የተፈፀመ ነው ሲል ሪፖርት አድርጓል፡፡ ይህ ሪፖርት ለምክር ቤቱ ከቀረበ በኋላ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ሶፊያን አሕመድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሥዩም መስፍን፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በቀጥታ ሪፖርቱን በመንቀፍ መንግሥት ሕግና መመሪያን በጣሰ መልኩ የተበደረው ገንዘብ እንደሌለ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰኔ 27 ቀን 2000 ፓርላማው የ2001 በጀት ባፀደቀበት ስብሰባ ላይ ተገኝተው የዋና ኦዲተር ሪፖርት "ተራ የሒሳብ ሰራተኛ የማይሰራውና ሊሰራው የማይገባ ስህተት ነው" በሚል ተቃውሟቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ኢህአዴግ ሰኔ 30 ቀን 2000 ዓ.ም ለፓርላማው ባቀረበው ሞሽን መነሻነት ምክር ቤቱ ይህንኑ በመንግሥት ባለስልጣናት "ተዛብቷል" በሚል የተፈረጀ ሪፖርት ተጣርቶ እንዲቀርብ በዶክተር ወልዳይ አምሃ የሚመራ አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴ ሰይሟል፡፡ ኮሚቴው የሪፖርቱን ትክክለኛነት አጣርቶ ፓርላማው በመስከረም ወር ሥራ ከመጀመሩ በፊት ለአፈጉባኤው እንዲያቀርብና ፓርላማው እንደተከፈተም ሪፖርቱ በይፋ እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተሰጥቶት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በኢፌዲሪ ሕገመንግስት መሰረት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ ማለትም መስከረም 26 ቀን 2001 ዓ.ም በኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ንግግር በይፋ እንደሚከፈት ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በማግስቱ ማክሰኞ ዕለት ፓርላማው በሚጀምረው መደበኛ ስብሰባ በምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረት የመጀመሪያ አጀንዳው የአጣሪ ኮሚቴውን ሪፖርት ማዳመጥና ተወያይቶ ማጽደቅ እንደሚሆን ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ ጠቁመዋል፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 02 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |