| ሕብር ውበት ነው! |
|
| Wednesday, 01 October 2008 | |
ውብ አገር፣ ውብ ሕዝብ እያልን አገራችንንና ሕዝባችንን የምናደንቅበት ምክንያት እጅግ ብዙ ነው፡፡ አንድ የምንኮራበትና የምንደነቅበት ምክንያት ግን በአገራችን የሚታየው ሕብር ነው፡፡ የሃይማኖት ሕብር፣ የብሔር ብሔረሰቦች ሕብር፡፡ ውብ ሕብር፡፡በዚህ የመስከረም ወር ብቻ ያለው የአገራችን ሁኔታ እንደ ሰማንያ ብሄር ብሔረሰቦች በጋራ አዲስ ዓመት አከበርን፡፡ ሃይማኖት ሳይለየን፣ ብሔር ሳይለየን፣ ጐሳ ሳይለየን በጋራ አዲስ ዓመት አከበርን፡፡ አዲስ ዓመት በጋራ ስናከብር ግማሹ ሕዝብ ደግሞ በክርስቲያን ሃይማኖት ተከታይነቱ ቅዱስ ዮሐንስ የሚል ተደራቢ በዓል ይዞ አከበረው፡፡ የእስልምና እምነት ተከታይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ድጋፍና አድናቆትን ከመቸር በስተቀር እንቅፋት አልሆነም፡፡ መስቀል ብለን ስናከብርም እንደዚሁ ግጭት ሳይኖር፣ እንቅፋት ሳይኖር፣ አብሮ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይም ያከብራል፤ ይደግፋል፡፡ የረመዳን ፆም አልፎ ኢድ ስናከብርም የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ እንቅፋት ሳይፈጥር በጋራና በደስታ ኢድ ሙባረክ እያለ መልካሙን ይመኛል፡፡ ያከብራል፡፡ በእያንዳንዱ ብሔር ሙስሊም ክርስቲያንም አለ፡፡ በእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰቦች ሙስሊምና ክርስቲያንም አለ፡፡ ሁሉም በጋራ ይኖራል፡፡ ሁሉም ሃይማኖትና ወጉን ያከብራል፡፡ በጋራ ይኖራል፡፡ ሕብር ውበት ነው፡፡ በአገራችን ያለው የሃይማኖትና የብሔር ብሔረሰብ ሕብር የምናደንቅበት ልዩ ምክንያት አለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ክርስቲያንና ሙስሊም አብሮ መኖር የማይችል ይመስል ሲጋጭ እና ደም ሲፋሰስ ይታያል፡፡ በክርስቲያን ውስጥም እንደዚሁ፤ በእስልምና ውስጥም እንደዚሁ በትናንሽ ክፍፍሎች ምክንያት ሲጋጭ፣ ህይወትም ሲጠፋ ይታያል፡፡ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ ሱኒ፣ ሺአ እየተባለ የዚህ ዘር፣ የዚያ ዘር እየተባለም ይጋደላል፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ ግን አንዳንድ አሉታዊ የውጭ ሙከራዎች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ መኖር ይችላል፤ ብሎ ብቻ ሳይሆን ሕብር ውበት ነው፤ ብሎ እያጣጣመውና እያደነቀው ይኖራል፡፡ በመርካቶ አካባቢ ቤተክርስቲያንና መስጊድ አንድ የጋራ አገር አላቸው፡፡ ሙስሊሙ ሲሰግድ፣ በቤተክርስቲያን ያለው ስርዓት አድርጐ ሙስሊሙ እንዳይረበሽ ይተባበራል፡፡ ክርስቲያኑ ሲፀልይ ታቦት ሲገባና ሲወጣም ሙስሊሙ ይተባበራል፡፡ ጐን ለጐን ይኖራሉ ብቻ ሳይሆን በአንድ ግቢ ይገኛሉ፤ ማለት እስከሚቻል ድረስ አብረው ይገኛሉ፤ ይተባበራሉ፡፡ ያምራል፤ ይደነቃል፤ ያስመሰግናል፤ ሕብር እውነትም ውበት ነው ያሰኛል፡፡ በቅርቡም በአርሲ አካባቢ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሚበዙበት መንደር ክርስቲያኖች ሲሞቱ የቀብር ቦታ ስለሚርቅ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ገበሬዎች ከመሬታቸው ቆርሰው ቤተክርስቲያን እንዲሰራ ተባብረው አመቺ የቀብር ቦታ ለክርስቲያኖች ፈጥረዋል፡፡ የምን ግጭት፡፡ እጅግ ውብና ግሩም መተባበር እንጂ፡፡ "ሕብር ውበት ነው" ስንልም ይህ መብታችን ነው፡፡ ይህ የአገር ታሪክና ማህበራዊ ኑሮ ልንጠብቀውና ልናጠናክረው ይገባል፡፡ ሌላው እንዲማርበትም ያስፈልጋል፡፡ በሃይማኖትና የብሔር ልዩነት የግጭት፣ የህይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ከኢትዮጵያ ተማሩ ልንል ይገባል፡፡ ሕብር የግጭትና የጥላቻ ሳይሆን ውበት መሆኑን እያሳየ ያለ ሕዝብ ነውና፡፡ ይህን መሰረታዊ ሃቅ የማያዩ ግለሰቦች የሉም፤ ማለት አይደለም፡፡ በየድራፍት ቤቱና በየካፌው ይህን የሚፃረር ወሬና ግጭት የለም ማለታችን አይደለም፡፡ ግን የምንገልፀው ተግባሩም ስለ ሕዝብ ነው፡፡ ግለሰቦች ያሉትን ይበሉ፡፡ በሕዝብ ዘንድ ግን እምነቱና ሕብር ውበት ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ሕብር ውበት የመሆን ጉዳይ ወደ ኢኮኖሚ ጥቅም ልንቀይረው ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ቱሪዝም እንዲስፋፋ የመንግሥት አንድ መንገድ ሕብር ውበት መሆኑን በማሳየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጥንታዊት ክርስቲያን አገር መሆንዋን ብቻ ሳይሆን ጥንታዊት የእስላም አገር መሆኗን በቁርዓን የተመሰከረላት መሆንዋን ማሳየትና በዚህም የቱሪስት መስህብ ልናደርጋት ይገባል፡፡ ከቱሪዝም በተጨማሪም ለኢንቨስተሮች መስሪያ መሆንዋን እናሳይ፡፡ በአካባቢያችንና በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉት የእስልምና ሃይማኖትና የክርስትና ሃይማኖት ሚሊኒየሮች ኑና ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አድርጉ፣ የማታወቁትና አዲስ ሃይማኖትና ባህል አያጋጥማችሁም፤ ኢትዮጵያ ለክርስቲያኑም ለሙስሊሙም እኩል አገርና እንግዳ ተቀባይ ናት፤ እንበላቸው፡፡ ኢትዮጵያን በዚህ ረገድ የኢንቨስትመንት ማዕከል ማድረግ ይቻላል፡፡ ሕብር ውበት ነው፤ ውበት መሆን የለበትም፤ የሚሉ ሊኖሩና ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ልንከላከል ይገባል፡፡ የሕዝብ እምነት ምንጊዜም አሸናፊ ሆኖ መቀጠል አለበት፡፡ ሕብር ውበት እንጂ ጠላትነት አይደለም ብለን ተግተን እንቀሳቀስ፡፡ ነገር ግን ዋናው ቁም ነገር፣ ይህን አዎንታዊ ገፅታ ወጥ ወደሆነ ኢኮኖሚያዊ ልማት መቀየር ነውና፣ ይህም ሕብር ውበት ነው፣ ውበት ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት መስሪያ ነውና እንስራበት፡፡ |
|
| Last Updated ( Thursday, 02 October 2008 ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |